Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምከቻይና ታላላቅ መሪዎች ጎራ የተቀላቀሉት ዢ ጂንፒንግ

ከቻይና ታላላቅ መሪዎች ጎራ የተቀላቀሉት ዢ ጂንፒንግ

ቀን:

የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ብዙም ዝና ያልነበራቸው፣ ቢበዛ ሁለት የምርጫ ዘመናትን በመንበረ ሥልጣናቸው ላይ ከመቆየት የዘለለ ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ብዙም አልተጠበቁም ነበር፡፡

ሆኖም በሥልጣን ዘመናቸው ያሳዩት አመራርና በአሜሪካ ማፈግፈግ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ቻይናን ወደ ዓለም አቀፍ መሪነት የማምጣት ጥረታቸው፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ በሚመሩት የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ አገሪቱ እየሄደችበት ያለውን መንገድ አመላካች ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2012 የፓርቲያቸው ሊቀመንበር በመሆን የቻይናን መንበረ ሥልጣን ከሁ ጂንታኦ የተረከቡት ጂንፒንግ፣ በፓርቲያቸው ከማኦ ዜዶንግ በመቀጠል የፓርቲው ጠንካራ መሪ ለመሆን ችለዋል፡፡

ከቻይና ታላላቅ መሪዎች ጎራ የተቀላቀሉት ዢ ጂንፒንግ

 

እ.ኤ.አ. በ1921 የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ከተመሠረተ ጀምሮ የግል አስተሳሰባቸውን በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ በሕግነት ሊያካትቱ የቻሉ ሰዎች ማኦና ዴንግ ሺዎፒንግ ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ ይኼንን በሕይወት እያሉ ማየት የቻሉት ማኦ ብቻ ነበሩ፡፡ ይሁንና ዢ ጂንፒንግ በሕይወት እያሉ በማግኘት ከማኦ ዜዶንግ ጋር በፓርቲው ታሪክ እምብዛም የማይገኘውን ክብር ለማግኘት ታድለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2017 በቤጂንግ ለአንድ ሳምንት ያህል በተደረገው የፓርቲው 19ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ጂንፒንግ የዓለማችን ሁለተኛው ትልቁ ኢኮኖሚ ያላትን ቻይና ወደ ‹‹አዲስ ዘመን›› ለማሸጋገር ቃል ገብተው ነበር፡፡ ለሦስት ሰዓታት ከ23 ደቂቃ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹በዚህች የጋራ በሆነች ዓለም ላይ በጋራ እየኖርንና የጋራ ዕጣ ፈንታን እየተጋራን የትኛውም አገር ወደ ራሱ ደሴት ሊያፈገፍግ አይችልም፤›› ሲሉ፣ አሜሪካ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ለመውጣት ማሳወቋን ወርፈዋል፡፡

ስለዚህም ቻይና ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ መምጣቷን ሲያውጁ፣ ‹‹በኩራት ከዓለም ጋር ቆመን የምንመራ ኃይል እንሆናለን፤›› ያሉ ሲሆን፣ ይኼንንም ለማሳካት አንዱ አማራጭ በየትኛውም ውጊያ ተፋልሞ ድል ማድረግ የሚችል የጦር ኃይል መገንባት እንደሆነ አስረግጠው ነበር፡፡

ጂንፒንግ በዚህ ለምዕራቡ ዓለም ዴሞክራሲ ያላቸውን ጥላቻ በግልጽ ያንፀባረቁ ሲሆን፣ ቻይና ከየትኛውም አገር የፖለቲካ ሥርዓትን እንደማትቀዳ አስረግጠው ሲናገሩ የአገራቸውን ፖለቲካ ሥርዓት ማስጠበቅ ግባቸው እንደሆነ አስታውቀው ነበር፡፡

ከቻይና ታላላቅ መሪዎች ጎራ የተቀላቀሉት ዢ ጂንፒንግ

 

በሩቅ ምሥራቅ በተለይም በሆንግ ኮንግ ያለውን በአንድ መንግሥት ሥር ያሉ አገሮችን የተለያየ አስተዳደርና በታይዋን የሚታየውን የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለው፣ ‹‹የቻይናን መሬት አንዲት ኢንች እንኳን ለመክፈል የሚፈልግ ማንም ቢኖር የማንታገሰው ይሆናል፤›› በማለት በሁለቱ ግዛቶች ላይ የሚነሱ የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄዎች አጣጥለው ነበር፡፡

የቻይና ኢኮኖሚ ጠንካራ ሆኖ ይቀጥላል ያሉት መሪው፣ ‹‹የሕዝቡን ያማረ አካባቢ ፍላጎት ለማሟላት›› ፓርቲው እንደሚሠራ፣ ደስታ ከተጨባጭ ንብረቶች የበለጠ እንደሆነና ፓርቲው የከባቢ አየር የመርዛማነት መጠንን ለመቀነስ እንደሚሠራም ተናግረው ነበር፡፡

ይህ የሦስት ሰዓታት ከግማሽ ንግግራቸው ነው እንግዲህ ጂንፒንግ ከማኦ ዜዶንግ እኩል ክብር አሰጣቸው የተባለለት የመመሥረቻ መተዳደርያ ደንብ ውስጥ የተካተተውና የ‹‹ጂንፒንግ አስተሳሰብ›› (Jinping Thought) ተብሎ የተመዘገበው፡፡

ከቻይና ታላላቅ መሪዎች ጎራ የተቀላቀሉት ዢ ጂንፒንግ

 

‹‹ፓርቲያችንን ጤና ከሚያውክ ማንኛውም ቫይረስ ራሳችንን ማፅዳት አለብን፡፡ እንደ ድንጋይ በፅናት መቆምና ድል በማድረግም መኖር አለብን፤›› ሲሉ የጉባዔው አባላት ፈንጥዘዋል፡፡ ‹‹ዛሬ ከ 1.3 ቢሊዮን በላይ ቻይናውያን በሞገስና በክብር እንኖራለን፡፡ ምድራችን  በአስደማሚ ድምቀት ታበራለች፡፡ የቻይና ሥልጣኔያችን በማይሞት ብርሃንና ነፀብራቅ ያበራል፤›› ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የ64 ዓመቱ ጂንፒንግ እስካሻቸው ጊዜ ድረስ በሥልጣን ላይ ይቆዩ ዘንድ የሚያስችላቸውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በፓርቲው ምክረ ሐሳብ ቀርቦ መፅደቁ፣ በፓርቲያቸው ውስጥ ያገኙትን እምነትና ተቀባይነት በእጅጉ የሚያስረግጥ ነው፡፡

ኮሙዩኒስት ፓርቲው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ያደረገበት፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንቶች እያንዳንዳቸው አምስት ዓመታት ለሆኑ ሁለት የሥልጣን ዘመናት እንዲቆዩ ያስገድድ የነበረውን ድንጋጌ ነው፡፡ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን እ.ኤ.አ. በ2022 ያጠናቅቁ ለነበሩት ጂንፒንግ ሲባል ነው ያሻሻለው፡፡ ይህ ማሻሻያ ጂንፒንግን ብቻ ሳይሆን ምክትላቸውን ሊ ዩዋንቻዎንም ተመሳሳይ ሥልጣን የሚሰጣቸው ነው፡፡

ማኦ ዜዶንግ አገራዊ አንድነትን በመጠበቅና በማጠናከር፣ ሺዎፒንግ ደግሞ ነፃ ገበያን በማስፋፋት ሲታወቁ፣ ጂንፒንግ የቻይናን ኢኮኖሚ ከግቡ ማድረስና የአገሪቱን የወታደራዊ ኃያልነት በማረጋገጥ አሻራቸውን ማኖራቸው ይነገራል፡፡ ይህም ‹‹አዲሱ የቻይና የዢ ጂንፒንግ አስተሳሰብ ዘመን መጀመርያ›› የሚል ስያሜን ሊያገኝ ችሏል፡፡

ለፋይናንሻል ታይምስ የጻፉት የቀድሞ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድ፣ ‹‹ከአምስት ዓመታት በፊት ከዴንግ ሺዎፒንግ ቀጥሎ ኃይለኛው መሪ ይሆናሉ ብዬ ነበር፣ ግን ተሳስቼ ነበር፡፡ ከማኦ ዜዶንግ ቀጥሎ አሁን ኃይለኛው የቻይና መሪ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና ሰባት ሰዎች ያሉበት ዋና አስፈጻሚው አካል ውስጥ ሊተካቸው የሚችል ብቃት ያለውን ሰው በቅርብ ያለማድረጋቸው፣ ጂንፒንግ አምባገነን የመሆን ዕቅድ አላቸው የሚሉ አስተሳሰቦች እንዲመጡ አድርጓል፡፡

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የቻይና ማዕከል ኃላፊዋ ሱሳን ሺርክ፣ ጂንፒንግ ከእሳቸው በፊት ከነበሩት መሪዎች በተለየ መንገድ እየመሩ እንዳሉና ሰዎች በሙስና ላይ በሚያደርጉት ዘመቻ በእጅጉ እንደሚፈሯቸው ገልጸው፣ ወደ አምባገነንነት እያመሩ ነው ለማለት ግን የማዕከላዊ አስፈጻሚዎች ማንነት ሳይለይ መናገር ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ግልጽ የሆነ ተተኪ ከእነዚህ ውስጥ ከሌለ ግን አለቀ፡፡ ጂንፒንግ ወደ አምባገነንነት እያመሩ ነው፤›› ይላሉ ተመራማሪዋ፡፡ ‹‹ያኔ አምባገነን እላቸዋለሁ፣ እስከዚያ ግን እየጠበቅኩ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከቻይና ታላላቅ መሪዎች ጎራ የተቀላቀሉት ዢ ጂንፒንግ

 

እ.ኤ.አ. በ1953 በቤጂንግ የተወለዱት ዢ ጂንፒንግ የቻይና አብዮት ታጋይና የቻይና ኮሙዩኒስት መሥራች የነበሩት የዢ ዦንግሱን ልጅ ሲሆኑ፣ ከፍተኛ ማዕረግና ክብር ባላቸው ሰዎች ተከብበው በማደጋቸው ‹‹እንደ ልዑል ናቸው›› እያሉ የሚጠሩዋቸው አሉ፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. በ1962 በተደረገው የባህል አብዮት አባታቸው ታስረው ንብረታቸው ሲወረስ፣ የ15 ዓመቱ ጂንፒንግ ወደ ገጠር ተልከው እንደገና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና የጉልበት ሥራም ጭምር እየሠሩ እንዲያድጉ የግድ ሆነ፡፡

ፓርቲውን ከመጥላት ይልቅ ወደ ፓርቲው ለመቅረብ ጥረት ቢያደርጉም፣ በአባታቸው ምክንያት ሲዘለፉ ቆይተው እ.ኤ.አ. በ1976 በፓርቲው ተቀባይነት አባል ከሆኑ በኋላ የፓርቲው ቁንጮ ላይ ለመውጣት ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደከፈሉ ይነገራል፡፡ በሻንጋይና በሔቤይ የፓርቲው ጸሐፊ በመሆን ያገለገሉት ጂንፒንግ፣ እ.ኤ.አ. በ2012 የፓርቲው ሊቀመንበርና የቻይና ፕሬዚዳንት ለመሆንም በቁ፡፡

በሲንጉሃ ዩኒቨርሲቲ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ የሆኑት ጂንፒንግ፣ ከድምፃዊቷ ባለቤታቸው ፔንግ ሊዩዋን አንዲት ሴት ልጅ ወልደዋል፡፡ ልጃቸው ሺ ሚንግዜ ሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የተማረች ሲሆን፣ ብዙም ስለርሷ የሚታወቅ መረጃ የለም፡፡ ጂንፒንግ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቅቀው ለሚያስጠጉት ተተኪ ያስተላልፉ ይሆን የሚለው ጥያቄ አሁን የብዙዎች ሆኗል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...