Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የመስተንግዶ አገልግሎት ባለው መልኩ ከቀጠለ ሆቴል መገንባቱ ዋጋ የለውም››

አቶ ዜናዊ መስፍን፣ የሆቴል ባለቤቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት

አቶ ዜናዊ መስፍን የሆቴል ባለቤቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ወደ መስተንግዶ (ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ) የተቀላቀሉት በአጋጣሚ ነበር፡፡ በባህር ማዶ የተከታተሉትን ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ አውስትራሊያ በሚገኘው ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ተቀጠሩ፡፡ በሆቴሉ ቆይታቸው በኦዲተርነትና በዋና ኃላፊነት መሥራት ችለዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሲሆን፣ እንደመጡ የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሆቴሎችን የማማከርና የአስተዳደር ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የሚያገለግሉበት ማኅበሩ ከቀናት በፊት የሥራ ዓውደ ርዕይ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ስለፕሮግራሙ አጠቃላይ ሁኔታ፣ በሆቴል ዘርፍ ስለሚታዩ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውን በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን አቶ ዜናዊን አነጋግራቸዋለች፡፡ 

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ የተመሠረተው መቼ ነበር?

አቶ ዜናዊ፡- ማኅበሩ የተመሠረተው በ1988 ዓ.ም. ነበር የተደራጀው በ13 አባላት ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው የሆቴል ዕድገት ብዙም አልነበረም፡፡ ስለዚህም ማኅበሩ ብዙ የሚሠራቸው ሥራዎች ስላልነበሩ እንቅስቃሴውም በዚያ መጠን ደካማ የሚባል ነበር፡፡ ተጠናክሮና በአዲስ መልክ ራሱን አዋቅሮ መሥራት የጀመረው ከአምስት ዓመታት በፊት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የአባላት ቁጥር ወደ 115 ከፍ ማለት ችሏል፡፡ ከባለ አንድ ኮከብ ሆቴሎች ጀምሮ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሁሉ የኛ አባል ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ  ከቀናት በፊት  የሥራ ዓውደ ርዕይ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በፕሮግራሙ የነበረው አጠቃላይ ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ዜናዊ፡- ዜሮ የሥራ ልምድ ያላቸው የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ሥራ ፈላጊዎች የት መሄድ እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ እነዚህን ሥራ ፈላጊዎች ከቀጣሪዎች ለማገናኘት ሲባል ነው ይህ የሥራ ዓውደ ርዕይ የተዘጋጀው፡፡ በሆቴልና ቱሪዝም የተመረቁ ሥራ ፈላጊዎች ወደ ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው እንዲገቡ ከማድረግ ባለፈ ለሥራው የሚመጥኑ ቀልጣፋ ሰዎችን መርጦ ለመውሰድም ምቹ አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ እኔ ለትምህርት ውጭ አገር ስሄድ ላጠና ያሰብኩት የኢንጂነሪንግ ትምህርት ነበር፡፡ ነገር ግን አንዲት አስተማሪ ያለኝን ቅልጥፍናና  ተግባቢ ባህሪ ተመልክታ ወደ ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ እንድገባ ገፋፋችኝ፡፡ በወቅቱ ወደ ሆቴልና ቱሪዝም የሚገቡት ከፍተኛ ነጥብ ያላቸው ብቻ ነበር፡፡ ዓውደ ርዕዩ እንዲህ ለሙያው የተመቹ ነገር ግን በሌላ የሥራ መስክ የተሰማሩን ወደ ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው የማስገባት ዓላማም ነበረው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከስደት ለተመለሱ ሥራ አጥ ወገኖች ሥራ መፍጠርም ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አጠናቀው የተቀመጡ ወጣቶች ሌላ አልባሌ ነገር ላይ ከሚወድቁ እንዴት አድርገን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ልናሰማራቸው እንችላለን? የሚለውንም ነገር ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ከ30 እስከ 35 የሚሆኑ የውጭና የአገር ውስጥ ድርጅቶችም ተገኝተዋል፡፡ በአገር ውስጥ የሚገኙ 95 ሆቴሎች ተሳትፈውበታል፡፡ አንዳንዶቹ ሆቴሎች እስከ 200 የሚደርሱ አመልካቾችን አግኝተዋል፡፡ በአንዴ እስከ 20 ሰዎችን ወዲያው የቀጠሩም ነበሩ፡፡ ዓውደ ርዕዩ የፈጠረው ነገር ቀጣሪ ከተቀጣሪው ጋር ፊት ለፊት እንዲገናኙ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ያለውን ትልቅ የኮሙዩኒኬሽን ችግር የሚቀርፍ ነው፡፡ ምክንያቱም ቀጣሪ የሥራ ፈላጊውን ማመልከቻ በመመልከት ፈንታ ቀጥታ እሱን ፊት ለፊት እንዲያገኘው ያስችለዋል፡፡ ቀጣሪው የሥራ ፊላጊውን ማንነት፣ ቅልጥፍናና የኮሙዩኒኬሽን ክህሎት ተመልክቶ እዚያው ይወስናል፡፡ ልምድ እንኳ ባይኖረው ይሄ ለሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው ጥሩ ነው፡፡ ቀልጣፋና ተግባቢ ነው ብሎ ገምግሞ ይወስደዋል፡፡ የሥራ ዓውደ ርዕይ በሌላው ዓለም በጣም የተለመደ ነው፡፡ እኔም የተመረኩት በዚሁ ሙያ ነው፡፡ ይህ የመጀመርያው ፕሮግራም ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በየጊዜው እናዘጋጃለን፡፡ በሌሎች የሥራ መስኮችም ሊለመድ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- የራስዎን ሆቴል የመክፈት ዓላማ አለዎት?

አቶ ዜናዊ፡- መጀመርያ የማሠልጠኛ ማዕከል ነው መክፈት የምፈልገው፡፡ ሆቴል ማንም ሰው ሊከፍት ይችላል፡፡ አሁን ያለው አንገብጋቢ ችግር አገልግሎት ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ያለው የአገልግሎት ሁኔታ የሞተ ነው ማለት ይችላል፡፡ አስተናጋጁ አቤት ምን ልታዘዝ ይላል ከዚያ የታዘውን ያቀርባል፡፡ ይኼ የሞተ መስተንግዶ ነው፡፡ ነፍስ ያለው መስተንግዶ ቅልጥፍና የታከለበት፣ ደንበኛን መንከባከብ የሚችል፣ 400 ብር ብቻ ሊያጠፋ የመጣን ሰው 1,000 ብር የሚያስጨርስ ነው፡፡ በአጠቃላይ ይኼ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ማለት ይቻላል፡፡ እንደ ሎዛን ያሉ ትልልቅ የሥልጠና ማዕከላት በኢትዮጵያ የሉም፡፡ በማኅበሩ በኩል መሰል የሥልጠና ማዕከላት እንዲከፈቱ ጥረት ይደረጋል፡፡ በግሌም የማሠልጠኛ ማዕከል የመክፈት ፍላጎት አለኝ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሆቴሎች እየተከፈቱ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸውም ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው፡፡ ያለው የመስተንግዶ ሁኔታ እንዲህ ሆኖ ከቀጠለ ሆቴል መገንባቱ ዋጋ የለውም፡፡ ቅድሚያ ለማሠልጠኛ ተቋማት ሊሰጥ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ያለው የሆቴል አገልግሎት በጣም ውድ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ሪፖርቶችም ይህንኑ እውነታ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ለዚህ ዋና ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ዜናዊ፡- ይህንን ከነፃ ገበያ አንፃር ስንመለከተው የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን የሚያስከትለው ችግር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያሉ የሆቴሎች ቁጥር ውስን ነው፡፡ በፍላጎት በኩል ደግሞ ብዙ ደንበኞች አሉ፡፡ ብዙ ሆቴሎች ወደ አገሪቱ ቢመጡ የዋጋው ነገርም ይቀንሳል፡፡ ሎጆችና ሆቴሎች በብዛት ቢከፈቱም እንዲሁ ዋጋውን መቆጣጠር ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ነገር ግን ሆቴሎች ሁሌም ሥራ ይኖራቸዋል ማለት በሚያስደፍር መጠን አይደለም ፍላጎቱ ያለው፡፡ በአንዳንድ ወቅቶች የሆቴሎች አልጋና አዳራሽ ሥራ ፈቶ እንደሚውል ይታወቃል፡፡ ይህም ያለው የዋጋ ውድነት ከፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ባለፈ ሌላ ክፍተት እንዳለ አመላካች ነው፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

አቶ ዜናዊ፡- ያልሽው ነገር ትክክል ነው፡፡ እያንዳንዱ ሆቴል ደንበኛን ለመሳብ ዋጋውን በየጊዜው ማሻሻል አለበት፡፡ ነገር ግን ትልቅ የአስተዳደር ችግር በመኖሩ ይህ አልተለመደም፡፡ ለምሳሌ ዱባይ ያሉ ሆቴሎች ጠዋትና ማታ ላይ ያላቸው ዋጋ አንድ አይደለም፡፡ የጠዋቱ ዋጋ 140 ዶላር ከሆነ ማታ እንግዳን ለመሳብ ወደ 80 ዶላር ዝቅ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ በኛ አገር ግን ይህ አልተለመደም፡፡ እኔ የማማክራቸው አምስት ሆቴሎች ግን ዋጋቸውን በዚህ መልኩ እንዲያሻሽሉ አድርጌያለሁ፡፡ እንደ ማኅበርም በዚህ ጉዳይ ለውጥ እንዲመጣ ምክርና ሥልጠና እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሆቴሎችን ደረጃ ኮከብ በማውጣት የመወሰን ሁኔታ ያለፈበት አሠራር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ስንት ኮከብ ነው ሳይሆን የትኛው ብራንድ ነው? የሚባለው የሚሉ አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

አቶ ዜናዊ፡- መጀመርያ ላይ የነበሩ ሆሎች ሲገነቡ የኮከብ ደረጃን መሠረት አድርገው አልነበረም፡፡ ሲሠሩም ጥሩ ዲዛይንና ጥሩ ጥራት ኖሯቸው በባለሙያ አይሠሩም ነበር፡፡ በብዛት የሚሳተፉትም ብቁ በሆኑ ባለሙያዎች አይደለም፡፡ ይህም ብዙ ሆቴሎች እንዲጎዱ ሆኗል፡፡ ወደ ኮከብ ደረጃ ለማምጣት ማፍረስና መገንባት ያለባቸው ነገሮች ይበዛሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የኮከብ ደረጃ አሰጣጥ ላይ እንደ ማኅበር ተሳትፎ አድርገናል፡፡ የኮከብ ደረጃ ለማውጣት የተቀመጡ መሥፈርቶች ከአገሪቱ አንፃር እንዲታዩ ሞክረናል፡፡ እኛም ቴክኒካል ኮሚቴ ተሳትፎ አድርገናል፡፡ ሆቴሎቹ የሚለኩበት 12 ምድቦች አሉ፡፡ ምድቦቹ መሠረታዊና ልዩ ደረጃዎች በሚል ለሁለት ይከፈላል፡፡ ነገር ግን ሆቴሎች ወደ ኮከብ ደረጃ አሰጣጥ ሥርዓቱ ከመግባታቸው በፊት የሚወስዱ የመግቢያ ፈተና አለ፡፡ ፈተናው ሆቴሎች እንደ ሴፍቲ ኤንድ ሴኪዩሪቲ (ደኅንነትና ፀጥታ) ያሉ መሠረታዊ ነገሮች ማሟላታቸውን የሚፈተሽበት ነው፡፡ አንድ ሆቴል የእሳት አደጋ ጊዜ መውጫ በሮች፣ የተለያዩ የእሳት ማጥፊያዎች ያሉ መሠረታዊ ነገሮች ከሌላው በኮከብ ደረጃ አሰጣጥ ሥርዓቱም መካተት አይችልም፡፡ ሌላው በምግብ ላይ ያለውን ጤናማ አሠራር፣ የማብሰያ ክፍሎች ፅዳትና በተገቢ መንገድ መዋቅሩ ይታያል፡፡ በጤና በኩል በተለይም የሠራተኞችን የጤና ምርመራ ይደረግላቸዋል ወይ? ከዚያ ሲያልፍም እነዚህ ሰዎች ወደ ሥራው የገቡት የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ወስደው ነው? አይደለም? የሚለው ጭምር ይታያል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው የሆቴሉ መሠረታዊ ደረጃና ልዩ ደረጃ የሚወጣው፡፡ መሠረታዊ ደረጃው ማለት የሆቴሉ ገጽታ፣ ፓርኪንግ አለው ወይ? ጋርደን አለው ወይ? የኤሌክትሪክና የመብራት አጠቃቀሙ፣ ኃይል ቁጠባ ላይ ያለው አቋምና የመሳሰሉት በዚህ ሥር ይካተታሉ፡፡ መፀዳጃ፣ መመገቢያና መሰብሰቢያ ክፍሎችም ይታያሉ፡፡ መኝታ ቤቶችና በየመኝታ ቤቱ ያሉ አልጋዎች ስፋት፣ ጥራትና ፅዳት ሁሉ ይፈተሻል፡፡ እንደ መዋኛ ገንዳ፣ የስፖርት ማዕከል የመሳሰሉ ተጨማሪ አገልግሎቶች ማቅረቡም የሚገመገምበት መሥፈርት ነው፡፡ አንድ እንግዳ ወደ ሆቴሉ ሲገባ ከጥበቃ ጀምሮ እስከ እንግዳ መቀበያው ድረስ ያለው አጠቃላይ መስተንግዶና አገልግሎት ምን ይመስላል? የሚለውም እንደ አንድ መሥፈርት ነው፡፡ የውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል ቁጠባም አንድ ሕግ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ እየታዩ ሁለት ኮከብ፣ ሦስት ኮከብ እየተባለ ይሰጣቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የሚያነሱት ነገር እንዳለ ሆኖ ለሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ማውጣት                                  ያለፈበት ነገር እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት በስፋት የሚሠራበትም ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸውን ሆቴሎች ማምጣት ነው ይባላል በዚህ ላይ ምን አስተያየት ይሰጣሉ?

አቶ ዜናዊ፡- ይኼ የአረዳድ ችግር ነው እንጂ የኮከብ ደረጃ አልቀረም፡፡ ብራንዶች ራሳቸው ኮከብ አላቸው፡፡ የትም ዓለም ብትሄጂ ባለአራት ኮከብና ባለ አምስት ኮከብ ተብሎ ነው የምታርፊው፡፡ ለምሳሌ በኒዮርክ ለሆቴሎች አምስት ኮከብ፣ አራት ኮከብ እያሉ ደረጃ ያወጡላቸዋል፡፡ በተለያዩ አገሮች ያለው የኮከብ ደረጃ ማውጣት አልቀረም፡፡ ብራንድ ሆቴሎችም የራሳቸው የኮከብ ደረጃ አላቸው፡፡ ለምሳሌ አራት ኮከብ ያላቸው ብራንድ ሆቴሎች አሉ፡፡ ራማዳ ሆቴል የትም ቢከፈት ባለአራት ኮከብ ሆኖ ነው፡፡ የኮከብ አሰጣጡ ግን እንደየአገሩ የቱሪዝም ተቋም ይወሰናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ያለው የሆቴልና ሌሎች የመስተንግዶ አገልግሎቶች ተደራሽነት እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ አብዛኞቹ ሆቴሎች የከተሙት በአዲስ አበባ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህም በቱሪስት ፍሰቱ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ምን እንደሆነና ክፍተቱን ለመሙላት እንደ ማኅበርስ ምን እያደረጋችሁ እንደሆነ ቢያብራሩልን?

አቶ ዜናዊ፡- የተነሳው ነገር ልክ ነው፡፡ የኛ ሐሳብ መጀመርያ በአዲስ አበባ ጀምሮ ከዚያ በኋላ በየክልል ከተሞቹ ለመሄድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና የአርኪዮሎጂ ቅርስ ያላት አገር ነች፡፡ ቅርሶቹ በየክልል ከተሞች ተሰባጥረው የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህን መስህቦች ለመጎብኘት የሚሄዱ ጎብኚዎች የሚስተናገዱበት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች የሉም፡፡ ቢኖሩም ከፍተኛ የአገልግሎት ችግር አለባቸው፡፡ የማሠልጠኛ ተቋም የመክፈት ዋና ዓላማም ይህንን ችግር መቅረፍ ነው፡፡ ማሠልጠኛው ቢከፈት  በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ ያሉ የአሠራርና የአስተዳደር ሥራዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማው የሚገኙ ትልልቅና ስመ ጥር ሆቴሎች በአገር ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎችን ወደ ጎን ብለው የውጭ አገር ዜጎችን ሲቀጥሩ ይታያል፡፡ ይህ በአገር ውስጥ ብቁ ባለሙያ በለመኖሩ የተፈጠረ ነው?

አቶ ዜናዊ፡- ከአራት ዓመታት በፊት ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ማናጀር ሆኜ በምሠራበት ወቅት ሆቴሉ ወርልድ ሌግዥሪ አዋርድ አሸንፎ ነበር፡፡ በውድድሩ 13,000 ሆቴሎች ተሳትፈው 1,042 ሆቴሎች ተመረጡ፡፡ ከአፍሪካ አሥር ሆቴሎች ሲመረጡ አንደኛ የነበረው ኢንተርኮንትኔንታል ነበር፡፡ የተመረጠው ሆቴል በነጮች የሚመራ አልነበረም፡፡ በኛ በኢትዮጵያውን የሚተዳደረው ነው ብልጫ አግኝቶ ሽልማት የተሰጠው፡፡ እኛ አገር በነጮች የመመካት ነገር አለ፡፡ እኔም በወቅቱ በዚያ ፕሮግራም ላይ የተገኘው ውጤት ለነጮች በሚሰጠው ቦታ ሳይሆን በሥራ መሆኑን ተናግሬያለሁ፡፡ ያለውን በነጮች የመመካት ነገርም ለመቀየር እየታገልን ነው፡፡ እዚህ አገር ብቁ ባለሙያ እያለ ከፍተኛ ደመወዝ ተከፍሏቸው የሚሠሩ ነጮችን መቅጠር ግን በጣም ተለምዷል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...