- Advertisement -

ወይ አራት ኪሎ?

እነሆ መንገድ! ከመገናኛ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። እልፍ አዕላፍ ተረቶች በህላዌ መንደር ዛሬም እየተኖሩ ይተረካሉ። እዚህ የተሳፈርንባት ታክሲ ውስጥ መካከለኛው የጥንዶች ረድፍ ላይ አባት የልጁን የፈተና ወረቀት ዘርግቶ ‘ኤክሶቹን’ ይቆጥራል። ልጅ አብዛኞቻችን የዕድሜ ልክ ደመወዛችን ቢደመር የማይሸምተው፣ ከፍሬው ቀድመን ያወቅነውን አፕል ስልክ የመጨረሻ ምርት ይዞ ‘ከረሜላ ማፍረስ’ ይጫወታል። ‹‹እንዴት ይኼን ትሳሳታለህ?›› አባት በድንገት ወደ ልጁ ተቆጥቶ ዞረ። ልጅ ቀናም አላለ። ‹‹የቱን?›› ከረሜላ በከረሜላ እያፏጨ፣ በለስ ከቀናው ቦምብ እያፈነዳ የቸኮሌት ‘ቦነስ’ ይለቅማል። ‹‹እስኪ አሁን ከረሜላ መሀል ቦምብ እያፈነዱ አድገው ነው ለሰው የሚመለሱት?›› ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ደርባባ ወይዘሮ ትጠይቀኛለች። ‹‹ይኼ ‘ካንዲ ክራሽ’ የሚሉት ጌም የስንቱን ትዳር በተነው መሰለህ። ታውቃለህ የጋሼ (ማን ነበር ስማቸው?) ልጅ ከባሏ ያፋታት እኮ ይኼ ‘ጌም’ ነው፤›› መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ጓደኛማቾች ያወጋሉ።

‹‹አንተን እኮ ነው የማናግረው! ይኼን እንዴት ‘ኤክስ’ ልትሆን ቻልክ?›› አባት ብስጭቱ ጨምሯል። እግዜር ባርኮለት ምንም እንኳ በሁለተኛው ዙር ቢሆንም ልጁም ደነገጠለት። ‹‹መቼ ያሳፍራል የእሱ ስጦታ ከሆነ?›› ብሎ ያጉተመተመውን ተሳፋሪ ልለየው አልቻልኩም። ‹‹እኔ ልክ ነኝ፣ አስተማሪው ነው የተሳሳተው፤›› ልጅ  በኩራት አባቱን ያስረዳዋል። ‹‹ጥያቄው ‘ገፀ ባህሪያት ቀርፀን ታሪክ ስንጽፍ ስንት ዓይነት የግጭት ዓይነቶችን መጠቀም እንችላለን?’ ነው የሚለው። መልሱ ‘ሰው ከሰው ጋር፣ ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋርና ሰው ከመኪና ጋር’ ነው። አስተማሪው ግን ‘ሰው ከመኪና ጋር’ አልክ ብሎ ‘ኤክስ’ ሰጠኝ፤›› ብሎ እንዳበቃ፣ ‹‹ተባረክ! ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ ማለት አንተ ነህ። ስንቱ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋ እንዳይሆኑ ሲሆን፣ ስንቱ የትዳር አጋሩን በድንገት እያጣ፣ ያለ እናት ወይም ያለ አባት ልጁን እያሳደገና ቤተሰብ እየተበተነ እያየ ይኼን ‘ኤክስ’ ካደረገህ መገምገም አለበት፤›› ብላ ወይዘሮዋ ደነፋች። ይኼ ዘመን ስንቱን ያሳየናል? ስንቱን ያሰማናል?

ጉዟችን ከተጀመረ ጥቂት ደቂቃዎች አምልጠዋል። ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመ ጎልማሳ ያዙኝ ልቁኝ እያለ ነው። ‹‹ውይ! ኧረ አገር ስጡኝ ተው?! የት ሄጄ ልፈንዳ በመድኃኔዓለም?›› ይወራጫል። ‹‹ኧረ ቀስ! በተረጋጋ ቀጣና ውስጥ ምንድነው እንደዚህ ማተራመስ?›› ወይዘሮዋ ናት። ‹‹ምንድነው የሚለው? የት አለና ነው እንቆቅልሹ አገር ስጡኝ የሚለን?›› ይኼን የምትለው ከኋላዬ ከተደረደሩት መካከል አንዷ የቀይ ዳማ ናት። ‹‹አይ! እንቆቅልሹንስ ተይው። እንዲያውስ ለእንቆቅልሾቻችን የሚበቃ አገር አለ እንዴ?›› ሥጋ ባዳው አጉል ሰብቶበት፣ በከፊል ደመናማ የአየር ፀባይ ላብ የሚያጠምቀው ህያው ገፀ ባህሪ ከጎኗ ያሽሟጥጣል። ‹‹ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ’ ተብሏል። ምን እንቆቅልሾቻችን ቢበዙ በመልካም አስተዳደር ችግር ተጠቃለው ዕውቅና ተሰጥቷቸው ተቀምጠናል። ከዚህ በላይ ምን ይምጣ?›› ሲል ጋቢና መሀል ላይ የተቀመጠ ወጣት ዞሮ ታክሲያችን በምትሃት ወደ ክብ ጠረጴዛነት የተቀየረች መሰለች።

‹‹ዓይኔ ነው ጆሮዬ?›› ትላለች ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠችው ደግሞ ተደናግራ። ‹‹ምን የሆነው?›› ጎልማሳው መወራጨቱን ቀነስ አድርጎ ሲጠይቃት፣ ‹‹በአንዴ እንቆቅልሹን በፖለቲካ ፈትቶ ያሳየኝ ወይ ያሰማኝ ነዋ?›› ስትለው ቀልደኛው ጎልማሳ፣ ‹‹የለም! የለም! የአላዲንና የፋኖሱ ነገር ነው። ሳናስበው ዴሞክራት፣ ስናስበው ደግሞ አውቶክራትና ታይራንት የሚያደርገን  የአላዲንና የፋኖሱ ጂኒ ነው፤›› ይላታል። ›› ‘ዳዲ’ ጂኒ ምንድነው?›› ሲል ደግሞ ብላቴናው በከረሜላ ጥርሶቹን መጨረስ በሚገባው ዕድሜ ጌሙ ላይ እንዳፈጠጠ፣ ዓይኑን ከስልኩ ባትሪ እኩል እያዳከመ ይጠይቃል። ወጋ ወጋ ጠቅ ጠቁ ጂኒ፣ ጂኒ ቁልቋል ወሬ ቢመስልም ሰውን ግን ያስተነፍሰዋል። ታክሲ ሳንባን የመተካት አቅም እንዳለው ሳይንስ ደርሶበት ይሆን?

ሾፌራችን እንደ ሰደድ እሳት ጨዋታ ተጀምሮ ሲቀጣጠል፣ ‹‹ታክሲ ውስጥ በህቡዕ መደራጃት ሳይጀመር…›› እያለ ለወያላው የሬዲዮኑን ድምፅ ጨመር ያደርገዋል። አንጀት የሆነ የስፖርት ትንታኔ እናዳምጣለን። ‹‹ክርስቲያኖ ሮናልዶና ሊዮኔል ሜሲ እንደ አሜሪካና ሩሲያ ተፋጠዋል፤›› ይላል ጋዜጠኛው። ‹‹አሜሪካና ሩሲያ ተፋጠዋል እንዴ? ለመሆኑ እነሱም እንደኛ የሚያፋጥጥ ጉድ ያውቃቸዋል እንዴ?›› ትላለች ከኋላችን ቆንጂት። ወይዘሮዋ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ኧረ ዝም በይው። ይኼ ይኼ አንቺን አይመለከትም። የኮስሞቲክስና የፀጉር መሥሪያ ዋጋ የሚያሳስባችሁ አልበቃ ብሎ ጭራሽ የሩሲያና የአሜሪካ ፍጥጫ ይጨመርባችሁ?›› ስትላት ተሳፋሪዎች ተደናገጡ። ወዲያው ግን፣ ‹‹በተመሳሳይ ፆታ መሀል የተነሳን ‘ክሪቲሲዝም’ የሚዳኝ ሕግ እስኪወጣ ምን ማድረግ ይቻላል?›› ብሎ ጋቢና የተቀመጠው ወጣት ቀልባችንን ወደ ሜሲና ሮናልዶ ፍጥጫ መለሰው። አፍታም አልቆየ ሜሲ ይበልጣል ሮናልዶ ክርክሩ ጦፈ።

‹‹ደግሞ ሜሲ ጀግና ይባላል? በስንት ተጋዳይ ሰማዕታት ላብና ደም እኮ ነው እዚህ የደረሰው፤›› ሲል አንዱ ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ስለኳስ ተጫዋቹ ሜሲ ነው የሚያወራው ወይስ ሜሲ የሚባል ታጋይ ነበረ?›› ይላል ሌላው። ‹‹ሮናልዶንማ የሚያክለው የለም አይገርማችሁም? (ኧረ ማንም አልተገረመም ወንድም) ምናልባት ራሱ ስለራሱ ችሎታ አዳንቆ ሜሲን እበልጠዋለሁ ማለቱ ቢያስተቸውም…፤›› ብሎ ሌላው ንግግሩን ሳይጨርስ ደግሞ ከወዲያ ጋቢና ያለው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹እኔ እኮ ሐበሻ ብቻ ይመስለኝ ነበር በእኔ እበልጥ በእኔ እሻል የሚዳማው። የእኔ አስተዳደር፣ የአገር ግንባታ፣ የኢኮኖሚ ልማት፣ ወዘተ ካለፈው ከሚመጣው ይለያል የሚል ሐበሻ ብቻ ይመስለኝ ነበር። ለካ ፈረንጅም ራሱን ያንቆለጳጵሳል?›› ብሎ ባለታኬታውን ዘውድ ከሚጭነው ጋር ያመሳስላል። በተረፈ ልፋ ያለው ‘የሜዳን ለባለሜዳው! የዙፋንን ለባለዙፋኑ!’ ቢባል ጆሮ ዳባ ልበስ ባይ ሆኖ ይኼው እጅግ በጣም ብዙ በርካታ ዓመታትን የእንፉቅቅ እያዘገመ ነው፡፡

- Advertisement -

ቀዘዝ ያለው ወያላችን ነገረ ሥራው ሁሉ ዝግ ያለ ነው። ‹‹አቤት አንተ! እንኳንም ‘ቪዛ’ ሰጪ አልሆንክ፤›› ትለዋለች እዚህ ከጀርባዬ። ‹‹እውነትም! ቆይ አንተን እንደ ምንም ብዬ በዘመድም ቢሆን ገቢዎች ማስቀጠር አለብኝ፤›› ስትል ደግሞ ከጎልማሳው አጠገብ ያለችው ትቀልዳለች። ‹‹እንዴ በዘመድ መቅረት አለበት አልተባለም እንዴ?›› መሀል ላይ የተሰየመው ወላጅ ልሳኑ ተከፈተ። ‹‹ቢባልም አይተገበርም፣ ቢተገበርም አይዘልቅም በሚል ለምን አንይዘውም?›› ልጅት ፈገግታዋ ከፊቷ ላይ ሳይከስም ጨዋታውን አደራችው። ‹‹ለምን እንይዘዋለን እንዳንቺ ዓይነቷን ነው እንጂ ማስያዝ፤›› ሰውዬው የምሩን ጭሯል። ልጅት ቀልድ ያለችው መምረሩ ሲገባት ፊቷን አዙራ ድምጿን አጠፋች። ወዲያው ከጎኔ የተሰየመችው ወይዘሮ ባረጋጋው ብላ ነው መሰል፣ ‹‹እንደሷ ያለውን ከማስያዝ አንደኛውን አገሪቷን ማስያዝ አይቀልም ብለህ ነው? ሃሃሃ . . . ቂቂቂ . . .›› የውሸት ሳቅ ናት።

‹‹ወያላ! በልማ ‘የሚሳቀው አርተፊሻል’ የሚለውን ዘፈን ጋብዘን፤›› መጨረሻ ላይ ካሉት ጓደኛማቾች አንደኛው ‘ሙድ’ ይይዛል። ወይዘሮዋ ግን ያሰበችው ተሳክቷል። ‹‹ልክ ነሽ። እንክርዳዱና ገለባውን ማሳውን ሞልቶት፣ እሱን ከመለየት ፍሬውን ለቅሞ ሲያበቁ ማሳውን ባለበት ማቃጠል ይቀላል፤›› ብሎ ሰውዬው ተንፈስ አለ። ‹‹እንዴት ነው ነገሩ ጎበዝ? ‘እናት አባት ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣ አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል?’ ብለን መስሎኝ ያደግነው? አዝመራው ጎተራ ሳይኖረው ተመርጦ ቢታጨድ ምን ይረባል?›› ብሎ ጎልማሳው ገባበት። ‹‹ምን እናድርግ ጠፍቶን መሰለህ እሱ?›› ሲለው ሰውዬው ጎልማሳው ይመልሳል ብለን ስንጠብቅ የስልኩ መልዕከት በጩኸት አቋርጦት ገባ። ‹‹የፈለገው ቢሆን ፍላጎቶች ዕውን ይሆናታል እንጂ ወደኋላ ብሎ ነገር አይታሰብም፤›› እያለ ተሳፋሪው ሞባይሉን አውጥቶ ማፍጠጥ ጀመረ። የሞት ሽረት ማለት ይኼም አይደል?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ሾፌራችን እስኪያወርደን ከመቸኮሉ የተነሳ መንገዱ ሲዘጋጋበት እግረኛው መንገድ ላይ ተጠምዝዞ ወጥቶ ‘ቼ’ ይላል። ‹‹አይይ! ምናለበት አሁን መንገድህን ይዘህ ብትሄድ? ሰው አላልቅ አላችሁ አይደል? በዚህ እናንተ አላችሁ፣ ጉንፋንም በአቅሙ የ13 ወራት ደዌ ሆኖ ሥራ አላሠራ ብሏል አሉ። ‘በሞቴ አፈር ስሆን’ ቀርቶ ‘በኩላሊቴ ይዤሃለሁ’ ማለት እስክንጀምር ይኼው ኩላሊት ማሳጠቢያ አጥቶ ሰው ረገፈ። ልብስ ማጠቢያ ሳሙና መግዛትም አልሆነልን እንኳን ኩላሊት ልናሳጥብ፤›› ወይዘሮዋ ትለዋለች። ‹‹ምን ይደረግ? የዚህ ዓለም ነገር ይኼው ነው። አንዱ ሲመጣ አንዱ ይሄዳል። ዓለም ሐዘን ሲለመድ እንባ እንደሚደርቅ አውቃ በሽታውን፣ መጥፊያ መክሰሚያውን ትለዋውጠዋለች፤›› ጎልማሳው ነው ከንፈር እየመጠጠ የሚያስተክዘን። ድንገት ዘወር ስንል ‘ለሽምቅ ውጊያ ማስታጠቅ ጀምረናል’ የሚል ማስታወቂያ የተጻፈባት ያዘመመች ቤት አየንና ዓይናችንን ማመን ቢያቅተን ወያላው ‹‹ተረጋጉ! ምግብ ቤት  ነው፤›› ብሎ አፋችንን አስከፈተው።

‹‹እና ስም አልቆባቸው ነው ‘ለሽምቅ ውጊያ ማስታጠቅ ጀምረናል’ የሚሉት?›› ሲለው ጋቢና የተሰየመው፣ ‹‹በዚህ ጊዜ ከዚህ የበለጠ ድንቅ ስያሜ ምን አለ? ሽምቅ ውጊያ የተባለው ኑሮ ነው፣ የሚዘጋጀው ትጥቅ ደግሞ ምግብ መሆኑ ነው። ሁለት ጥብስ ፍርፍር ለአራት አጥቅተህ፣ ጥግብ ብለህ . . . ሻይ፣ ቡና ውኃ ጠጥተህ 45 ብር ከከፈልክ ምን ትፈልጋለህ?›› ሲል ሰውየው ተሳፋሪዎች በጠቅላላ ‹‹ወራጅ!›› ብለው ከመቀመጫቸው ተነሱ። ጎልማሳው ብቻ ከመቀመጫው ንቅንቅ ሳይል፣ ‹‹ቅድም ምን ስትሉ ነበርና ነው አሁን እንዲህ የሚያደርጋችሁ?›› ብሎ ተቆጣ። ‹‹ቅድም የዓለም ሴራዋ፣ በሽታዋ፣ ስቃይዋ፣ ጦርነቷ፣ ስደቷ፣ ፍትሕ አልባነቷ፣ ወዘተ ምን ያላላችሁት ነበር? አሁን ደግሞ ዓለም አታላይ ሆዬ ‘ይውጋሽ ብላ በይማርሽ’ ሥልቷ ምግብ በነፃ በእጅ አዙር ስታቀርብ ትሻማላችሁ? የወጋ ቢረሳ የተወጋም ይረሳ?›› ብሎን አረፈው። ‹‹ቆይ ግን›› በመንገዱ ቂም ይዘን፣ ባለፉት ሥርዓቶች ቂም ይዘን፣ በፍትሕና በዴሞክራሲ ዕጦት፣ በሐሳብ አፈናው ሳቢያ ካሁኖቹ ጋር ሳይቀር ተኮራርፈን፣ ይኼ ሁሉ አልበቃን ብሎ ደግሞ በዓለም ላይ ቂምና ኩርፊያ? ጉድ ሲንተከተክ እንዲህ ነው ይኼውላችሁ፤›› ብላ ያች ወይዘሮ የጉዞውን ማጠናቀቂያ ትችት ስታቀርብ ተግተልትለን ወረድን፡፡ አራት ኪሎ ደርሰን ግራና ቀኙን ስናማትር፣ ‹‹ወይ አራት ኪሎ? ኃጢያት ተሠርቶ ሕልም ተፈርቶ እንዴት ይኮናል?›› ሲል ሌላው ደግሞ፣ ‹‹‘መብራት እስኪመጣ ቆሜ ስጠብቅሽ፣ አራዳው መጣና በሻማ ወሰደሽ’ ያለው ማን ነበር?›› እያለ ለአራት ኪሎ ተቀኘ፡፡ ወይ አራት ኪሎ? መልካም ጉዞ!

- Advertisement -

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን

ከ ተመሳሳይ አምዶች

አሳረኛው ኑሮ!

የዛሬው ጉዞ ከቦሌ ወደ ፒያሳ ይሆን ዘንድ ግድ ሆኗል፡፡ ለምን? በኑሮ  ምክንያት፡፡ የታክሲ መሠለፊያው ወሬ የነዳጅ ጭማሪውን ተከትሎ ስለሚመጣው ተጨማሪ ታሪፍ ነው፡፡ ‹‹የእኛ ኑሮ...

ሻካራው ነፍሳችን!

በገና በዓል ማግሥት ጉዞ ከአራት ኪሎ ወደ ቦሌ አራብሳ፡፡ ተማሪው፣ ሠራተኛው፣ ወዲያ ወዲህ የሚለው ሳይቀር አካባቢውን ሞልቶታል። ብዙኃኑ ሕዝብ የሠልፍ አጥር ሠርቶ ታክሲ ይጠብቃል።...

ለጊዜውም ቢሆን!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ኮተቤ። ትናንት ካቆምንበት ልንቀጥል ለአፍታ በዓውደ ዓመት ድባብ ውስጥ ሆነን ልንጓዝ ተዘጋጅተናል። በዚህ ምድር የሚለዋወጠው ቀን ብቻ ይመስላል። መሽቶ ይነጋል፣ ነግቶ...

ኩርፊያ!

ጉዞ ከቦሌ ወደ ሜክሲኮ፡፡ ጎዳናና ሕይወት መመሳሰላቸው ገዝፎብን በቆምኩበት ድንገት የመጣው ታክሲ ሲቆም ተራ ጠብቀን ገባን፡፡ ‹‹የሞላ በበራሪ…›› እያለ ወያላው ሲጮህ አብሮ የበረሩና ያልተኖሩ...

ይነገረን እንጂ!

ከኮተቤ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ‹‹እስቲ ጠጋ ጠጋ ብለን ብንቀመጥ ምን ይመስላችኋል?›› እያለ ወያላችን ያግባባናል። አንዲት ቆንጆ ጠይም አባባሉ አልዋጥላት ብሎ፣ ‹‹ትንሽ ቆይተህ...

አላፊና ጠፊ!

እነሆ መንገድ ከሜክሲኮ ወደ ሳሪስ፡፡ ሦስት አሠርት ዕድሜ ያስቆጠረ አሮጌ ሚኒባስ ተሳፍረን ጉዟችን ተጀምሯል። መሀል ወንበር ላይ የተሰየሙ አዛውንት እንደ መቆዘም እያሉ፣ ‹‹እኛም ታክሲዎቻችንም...

አዳዲስ ጽሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ቀኑን ሙሉ ከዋሉበት የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ተመልሰው ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው]

የምን ስብሰባ ላይ ዋልኩ ነበር ያልከኝ? የሥራ አስፈጻሚ። የምን ሥራ አስፈጻሚ? የገዥው ሥራ አስፈጻሚ። ምን ገጥሟችሁ ነው የተሰበሰባችሁት? ለመረጠን ሕዝብ ቃል የገባናቸውን ተግባራት አፈጻጸም የምንገመግምበት የተለመደ ስብሰባ ነው። የገባችሁት ቃል...

ሕወሓትን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተው መመርያ

በሁለት አንጃ ተከፍሎ የእርስ በርስ የቃላት ጦርነት ውስጥ የገባው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ልዩነቱን ትቶ ወደቀድሞው አንድነቱ በመመለስ የሚጠበቅበትን ጠቅላላ ጉባዔ የማድረግ አልያም...

ባንኮች እየፈጸሙት ያለው አቅርቦትንና ፍላጎትን ያላገናዘበ የውጭ ምንዛሪ ግዥ

የውጭ ምንዛሪ ግብይት በገበያ ዋጋ እንዲገበይ የወጣው ሕግ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከሰባት ወራት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ሕጉ ተግባራዊ በተደረገበት የመጀመርያው ቀን የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ...

አሳረኛው ኑሮ!

የዛሬው ጉዞ ከቦሌ ወደ ፒያሳ ይሆን ዘንድ ግድ ሆኗል፡፡ ለምን? በኑሮ  ምክንያት፡፡ የታክሲ መሠለፊያው ወሬ የነዳጅ ጭማሪውን ተከትሎ ስለሚመጣው ተጨማሪ ታሪፍ ነው፡፡ ‹‹የእኛ ኑሮ...

የግለሰቦች ለመብታቸው ኃላፊነት አለመውሰድ ለአገር ያለው አደጋ

በያሬድ ኃይለመስቀል አንድ የማከብረው ኢኮኖሚስት አንድ መጽሐፍ እንዳነብ መራኝና ማንበብ ጀመርኩኝ። ይህንን መጽሐፍ ሳነበው ከዋናው ሐሳብ ወጣ ብሎ ስለ “የነፃ ተጓዦች ሀተታ” (The Free Rider...

‹‹የብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ማጠናከር ያስፈልጋል›› አቶ ፍፁም አብርሃ፣ የአሚጎስ ብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ

አሚጎስ የብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበር ከተመሠረተ አሥራ ሁለት ዓመታት ሆኖታል፡፡ በእነዚህ ዓመታት 8,500 አባላትን ማፍራት ችሏል፡፡ አሚጎስ ስለተመሠረተበት ዓላማ፣ እያከናወናቸው ስለሚገኙ ተግባራት፣ የብድርና...
[the_ad id="124766"]

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን