Friday, July 12, 2024

ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር መቀበያ ዋዜማ ላይ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች አዳዲስ ሊቃ መናብርትን በመምረጥ ስብሰባቸውን አጠናቀዋል፡፡ ሰሞኑን የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ምትክ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን በመምረጥ ሊቀመንበር አድርጓል፡፡ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡

ከኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ቀደም ብሎ ለረዥም ቀናት ስብሰባ በማድረግ አዳዲስ አመራሮችንና የውሳኔ ሐሳቦችን ያስተላለፈው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እንደነበር ይታወሳል፡፡ ፓርቲው ከወራት በፊት ለ35 ቀናት አድርጎት በነበረው ስብሰባ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልን (ዶ/ር) ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡ አይዘነጋም፡፡

ከኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል አንዱ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ሲሆን፣ ፓርቲው ባለፈው ሳምንት በአስቸኳይ ባደረገው ስብሰባ ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ አዲሱን ሊቀመንበር ከመምረጡ በፊት ለአሥር ቀናት አድርጎት በነበረው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ፣ በአገሪቱ ባልተለመደ ሁኔታ አገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገር ካሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ውሳኔ ማሳለፉን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ በክልሉ ብሎም በአገሪቱ እየከሰተ ያለውን ችግር ለመፍታትም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረትም የክልሉ መንግሥት ከ30 ሺሕ በላይ እስረኞችን እንደለቀቀ ሲናገር ተደምጧል፡፡

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሌላኛው የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅት ሲሆን፣ ለአንድ ወር በቆየው የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከዚህ በፊት የነበሩት የፓርቲው ሊቀመንበር በኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ መወሰኑ አይዘነጋም፡፡

ሌላኛው የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅት የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ሲያደርገው የነበረውን ስብሰባ ሰኞ የካቲት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ማጠናቀቁን፣ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ አቶ ሽፈራው አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በአገሪቱ ያጋጠመውን ችግር አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በራሳቸው ፈቃድ ከሥልጣን ለመነሳት መወሰናቸውን አድንቀው፣ የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚት ስብሰባ በዋናነት በክልሉና በአገሪቱ በተከሰተው ቀውስ ትኩረት ሰጥቶ መምከሩን አስረድተዋል፡፡ ‹‹በክልላችን ብሎም በአገራችን የተከሰተው ቀውስ ምክንያቱ ምንድነው? መፍትሔውስ? ብለን በጥልቀት ምናልባትም ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ገምግመን አቅጣጫዎችን አስቀምጠናል፤›› ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ለ24 ቀናት ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው የአቋም መግለጫ ላይ እንደጠቀሰው፣ አገሪቱ ያለችበትን አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔት በዝርዝር ገምግሟል፡፡ ‹‹ግምገማችን እንደተለመደው ችግሮቹን በመዘርዘር ብቻ ሳይሆን፣ የእያንዳንዱን ችግር ፈጣሪና ባለቤት በመለየት ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂነትና ኃላፊነት በመውሰድ መንፈስ የተካሄደ መሆኑ በእርግጥም ልዩና ታሪካዊ ያደርገዋል፤›› ሲል መግለጫው ጠቁሟል፡፡ የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም የደኢሕዴን ሊቀመንበር ሆነው ለአሥራ ሰባት ዓመታት እንዳገለገሉ ያስታወሱት አቶ ሽፈራው፣ አዲስ የፓርቲው ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መምረጡን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የደኢሕዴን ሊቀመንበር፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አዲስ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና በሌሎች በተጓደሉ የምክር ቤት አባላት አዳዲስ ግለሰቦችን እንደመረጠ ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ በተጓደሉ የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ማካሄዱንም አስታውሰዋል፡፡ በዚህ መሠረትም አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው መመረጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ላለፉት አሥራ ሰባት ዓመታት የደኢሕዴን ሊቀመንበር ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኃላፊነታቸው ለመነሳት ለደኢሕዴንና ለኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ማግኘቱን ለአገሪቱ ሕዝብ በይፋ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መንገድ ከሥልጣን መልቀቅ ባልተለመደባት ኢትዮጵያ ጉዳዩ አሁንም ድረስ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን ለመነሳት የወሰኑት በአገሪቱ በተከሰተው ችግር የመፍትሔ አካል ለመሆን በማሳሰብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ተተኪ ሆነው ስለሚሾሙት የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንነትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፓርላማ የመፅደቅ ጉዳይም መነጋገሪያ እንደሆኑ ቀጥለዋል፡፡

ምንም እንኳ ኢሕአዴግ አዲስ የፖሊሲ ለውጥ እስካላደረገ ድረስ ለውጥ ይመጣል ብለው እንደማያስቡ የሚናገሩ ግለሰቦች ቢኖሩም፣ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሆኑ? የየትኛው ፓርቲ ሊቀመንበር ይሆኑ? በአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖችን ያሳትፋሉ? ወይስ አያሳትፉም? በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ የታሰሩ ቀሪ ግለሰቦችን ሙሉ በሙሉ ይፈታሉ? ወይስ ምን ዓይነት ዕርምጃ ይወስዳሉ? በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያንን በምን መንገድ ለአገሪቱ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ያደርጋሉ? በአገሪቱ በአራቱም አቅጣጫዎች ለሚነሱ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣሉ? ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎች አሁንም ድረስ መነጋገሪያ ጉዳዮች ከሆኑ ውለው አድረዋል፡፡

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአንድ ወር ያህል ያካሄደውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባለ አምስት ነጥብ የውሳኔ ሐሳቦችን አውጥቷል፡፡ በፓርቲው መግለጫ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ላይ የአካልና የንብረት ጉዳት እንዳይደርስ በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡

ብአዴን አቶ ደመቀ መኮንን የፓርቲው ሊቀመንበር፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ አቶ ደመቀ መኮንን የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ማገልገል ከጀመሩ ስድስተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል፡፡

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ይይዛሉ ተብለው ከሚጠበቁት ግለሰቦች መካከል አቶ ደመቀ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ደመቀ የተወለዱት በቀድሞው አጠራር በጎጃም ክፍለ ሀገር ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ እንደተማሩ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ በዚሁ ወረዳም ለሁለት ዓመታት በአስተማሪነት ሠርተዋል፡፡

የአስተማሪነት ሥራቸውን ካቆሙ በኋላ በአማራ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር፣ በአማራ ክልል የፀጥታና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የአቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊና የትምህርት ሚኒስትር ሆነው እንዳገለገሉ የሕይወት ማኅደራቸው ያስረዳል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የብአዴን ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡

የአገሪቱ የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ሥልጣን ይይዛሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው መካከል አንዱ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ናቸው፡፡ አቶ ሽፈራው ሰኞ የካቲት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. የደኢሕዴን ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ በቅርቡ በሚካሄደው የኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ የፓርቲው ሊቀመንበር እንዲሆኑ ሊመረጡ ይችላሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው መካከል አንዱ ናቸው፡፡

አቶ ሽፈራው የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደርና የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብለው ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ግለሰቦች መካከል ሌላኛው ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አንዱ ሲሆኑ፣ የኦሕዴድ ሊቀመንበርነትን ከያዙ ገና ሳምንታቸው ነው፡፡ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ድንገተኛ ስብሰባ አቶ ለማ መገርሳን የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር እንዲሆኑ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ይህን ውሳኔ በተመለከተ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርና የኦሕዴድ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ‹‹ሕዝባችን በፌዴራል መንግሥት ተገቢውን የኃላፊነት ድርሻ ማግኘት አለብን ብሎ ሲጠይቅ ጥያቄው የሞራል ጥያቄ ነው፡፡ ድርጅቱም በዚህ ጥያቄ ተገቢነት ያምናል፡፡ በፌዴራል ደረጃ የሚቀመጠው አመራር በኦሮሞ ሕዝብ የተለየ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያመጣል ብለን አናስብም፡፡ አንድ ሰው ከመካከላችን በመውጣት አገሪቱን መምራት ይችላል፡፡ የአገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነትና በፍትሐዊነት ይመራል፡፡ የታገልነውም ለዚህ ነው፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ወክሎ እንደ መቀመጡ መጠንም የኢትዮጵያን ሕዝብ ክብርና ጥቅም በማስጠበቅ እኩልነት በአገሪቱ እንዲሰፍንና ፍትሐዊነት እንዲረጋገጥ መሠራት አለበት፤›› ብለዋል፡፡፡

አቶ ለማ በፌዴራል ያለውን በማየት የክልሉን ጉዳይ ችላ የሚባል ከሆነ ውድቀት እንደሚያስከትል ተናግረዋል፡፡ ‹‹አንድ ሰው አይደለም ሃያ ሰው በፌዴራል ደረጃ ወንበር ቢያገኝ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ መልስ አግኝቷል ማለት አይደለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዶ/ር ዓብይ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆኖ እንዲሠራ፣ እኔ ደግሞ ምክትል ሆኜ እንድሠራ ወስነናል፡፡ ይህን ስናደርግ ለሕዝባችን ግልጽ ሊሆን የሚገባው ምንም ነገር ተፈጥሮ አይደለም፡፡ ነገር ግን የሕዝባችንን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ የተጠቀምንበት ሥልት እንጂ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የአቶ ለማ መግለጫ የሚያመለክተው ዶ/ር ዓብይ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ፓርቲው በዕጩነት ከማቅረቡም በላይ፣ በሌሎች ብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮች ዘንድ ይሁንታ ያገኘ እንደሆነ የሚያመላክት ጉዳይ ነው በማለት የሚናገሩ አሉ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያምን ይተኳቸዋል ተብለው ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸውና በተለያዩ ሚዲያዎች እየተወራላቸው ከሚገኙት መካከል ዶ/ር ዓብይ ትልቁን ሥፍራ ይዘዋል፡፡

ዶ/ር ዓብይ ቀጣዩ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ምኞታቸው እንደሆነ የተለያዩ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ተንተኞች ሲናገሩም ተደምጧል፡፡ በምክንያትነት ከሚያቀርቧቸው ጉዳዮች መካከልም የኦሮሚያ ክልል ለሃያ ሰባት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ ሥልጣን ተሰጥቶት ስለማያውቅና በአቶ ለማ የተጀመረውን አበረታች እንቅስቃሴ ወደ ፌዴራሉ በማምጣት በአገሪቱ ዕርቅ ሊያወርድና መግባባት ሊፈጥር ይችላሉ ብለው ይከራከራሉ፡፡

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ኢሕአዴግ የፖሊሲ ለውጦችን እስካላደረገ ድረስ አሁን ያለው የአገሪቱ ችግር ይቀረፋል ብለው አያምኑም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መልቀቂያም በውስጥ ባሉ ችግሮች ግፊት የመጣ እንጂ፣ አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓቱን ለመለወጥ ካለ ፍላጎት አይደለም ይላሉ፡፡

ዶ/ር ጫኔ የአገሪቱን ሀብት እኩል ከመጠቀምና ወደ ልማት ከማምጣት አንፃር ችግር እንዳለና ይህም ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ጥገኝነት የፈጠረው አባዜ እንደሆነ፣ ይህ ችግር ካልተፈታ መሪ በመለዋወጥ ብቻ ለውጥ ይመጣል ብለው እንደማይገምቱ አስረድተዋል፡፡

አገሪቱ በችግር ውስጥ ባለችበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመልቀቂያ ጥያቄ ማቅረብ የለባቸውም ነበር ብለው የሚከራከሩ ቢኖሩም፣ በቅርቡ ግን ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ይሾማል፡፡ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ለሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ ከመደረጉ በፊት፣ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት የፓርቲውን ሊቀመንበር ይመርጣል፡፡ ከዚያ በፊት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውይይት ይቀድማል ተብሏል፡፡

የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ማን ይሆናል? የሚለው ጥያቄ አሁንም በስፋት መነጋገሪያ ሲሆን፣ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው የሚመረጡት ግለሰብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ መቼ እንደሆነ እስካሁን በግልጽ ባይታወቅም፣ አዲሱ የደኢሕዴን ሊቀመንበርና የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የስብሰባው ቀን እንዳልተቆረጠ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አገሪቱ ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሾም በዋዜማ ላይ እንዳለች ቢታወቅም፣ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀውና በመላ አገሪቱ ለስድስት ወራት የቆየው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሌላ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አገሪቱ አሁን ችግር ውስጥ እንዳለች ቢታወቅም፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ብቻ ያጋጠሙ ችግሮችን መፍታት እንደማይቻል ሲነገር ይሰማል፡፡ ዶ/ር ጫኔ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ አገሪቱን ለስድስት ወራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንድትመራ ማድረግና ሌላ የመፍትሔ ሐሳቦችን አለመፈለግ ይታይ የነበረውን የዴሞክራሲ ጭላንጭል ያጠፋዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀ በ15 ቀናት ውስጥ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቅ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማፅደቅ የፊታችን ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የፓርላማ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርተዋል፡፡

ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በመላ አገሪቱ ለስድስት ወራት ተጥሎ የሚቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፓርላማው ተወይቶ እንደሚያፀድቀው ይጠበቃል፡፡ በተመሳሳይ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚታወቀው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውይይቱን ሲያጠናቅቅ፣ ብሔራዊ ኮሚቴው በመሰብሰብ የግንባሩን ሊቀመንበር ከመረጠ በኋላ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -