[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር ከቤት ወደ ቢሮ እየወሰዳቸው ነው]
- ደህና አደሩ ክቡር ሚኒስትር?
- ሰላም አደርክ?
- ሥራ እንዴት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው ጠየቅኸኝ?
- ያው አገሪቷ ውጥረት ውስጥ ስለሆነች ሥራ ይበዛብዎታል ብዬ ነው፡፡
- እሱማ ሕዝብ ትልቅ ኃላፊነት ነው የጣለብን፡፡
- ግን የተጣለባችሁን ኃላፊነት እየተወጣችሁ ነው ወይ?
- ይኸው ቀን አንል ሌሊት ወጥረን እየሠራን ነው፡፡
- ታዲያ ቀን ከሌት እየሠራችሁ ነው አገሪቷ እንደዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ የገባችው?
- ምን ነካህ ከፍተኛ የሕዝብ ኃላፊነት እኮ ነው የተሸከምነው?
- እኔ ግን ሕዝቡ እናንተን የተሸከማችሁ ነው የሚመስለኝ፡፡
- ምን አልክ አንተ?
- ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ መጮህ ከጀመረ ሰነባበተ እኮ?
- ሕዝቡ ለምን ይጮሃል?
- እናንተ ናችኋ የምታስጮሁት፡፡
- እኛ ምን አድርገን ነው የምናስጮኸው?
- በመልካም አስተዳደር ችግሩ ቢሉ በፍትሕ ችግሩ ኧረ ምኑ ቅጡ?
- እሺ የእኛ አክቲቪስት?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ አክቲቪስት ሆኜ ሳልሆን እውነታውን ነው የነገርኩዎት፡፡
- የምን እውነታ ነው?
- ይኸው ሕዝቡን ማዳመጥ ትታችሁ ራሳችሁን ማዳመጥ ከጀመራችሁ ሰነባበታችሁ፡፡
- ምንድነው የሚያወራው ይኼ?
- አሁንማ ይባስ ብላችሁ ሕዝቡን ከፋፍላችሁ ኢትዮጵያዊነትን እያጠፋችሁት ነው፡፡
- እንዴት ነው ኢትዮጵያዊነት የጠፋው?
- ይኸው እንደ አገር አንድ የሚያደርጉንን በዓላት ማክበር ትተን ትልቅ ትኩረት የሚሰጣቸው የፓርቲ በዓላት ናቸው፡፡
- ምን ችግር አለው?
- ለነገሩ በትምህርቱ ብዙ ባልገፋበትም ከፋፍለህ ግዛ የሚል ታክቲክ መኖሩ ትዝ ይለኛል፡፡
- አልገባኝም?
- ያው እናንተ በሥልጣን ለመቆየት ሕዝቡን መከፋፈል አለባችኋ፡፡
- ለምን የማታውቀን ነገር ትዘባርቃለህ?
- ክቡር ሚኒስትር የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የምሥረታ በዓል ነው ወይስ እንደ ዓደዋ ያለ አገራዊ በዓል በድምቀት መከበር ያለበት?
- በነገራችን ላይ የአንተ ሥራ እኔን ከቦታ ቦታ ማዘዋወር መስሎኝ ነበር፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- አየህ አሁን ግን ሁሉም የፖለቲካ ተንታኝ፣ ሁሉም ያለ እኔ አዋቂ የለም ባይ እየሆነ ነው፡፡
- እኔ የፖለቲካ ተንታኝም ወይም አዋቂ ሆኜ ሳይሆን እንደ ዜጋ የሚሰማኝን ነው የነገርኩዎት፡፡
- ስማ በማያገባህ ነገር ብዙ ባትገባ ጥሩ ነው፡፡
- እንዴት አያገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- አንተ አርፈህ ሥራህን ሥራ፡፡
- እናንተም አርፋችሁ ሥራችሁን ሥሩ፡፡
- እንዴት ነው የተናናቅነው?
- እውነት ሲነገረዎት ለምን ይበሳጫሉ ክቡር ሚኒስትር?
- ስማ እዚህ ቦታ ላይ የተቀመጥኩት የማንን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሆነ ታውቃለህ?
- የሕዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ ነዋ፡፡
- ማን ነው ያለው?
- ለነገሩ የማንን ጥቅም እንደሚያስጠብቁ ይታወቃል፡፡
- የማንን ጥቅም ነው የማስጠብቀው?
- የራስዎትን!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ተቃዋሚ ከውጭ ደወለላቸው]
- ክቡር ሚኒስትር እንዴት ነዎት?
- ምን ፈልገህ ደወልክ?
- አሁን ወሳኝ ነጥብ ላይ ደርሰናል፡፡
- እንዴት ማለት?
- ይኸው እኛም እየተዘጋጀን ነው፡፡
- ምን ለማድረግ?
- አገሪቷ እኮ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ናት ያለችው፡፡
- ምን ይጠበስ?
- ይህችን አገር እንደ አገር ለማስቀጠል የእኛ ሚና ወሳኝ ነው፡፡
- አትቀልድ እባክህ?
- ክቡር ሚኒስትር ይኸው ከሩብ ምዕተ ዓመታት በላይ ቀልዳችሁ እዚህ ደርሳችኋል፡፡
- ወኔህን አደንቅልሃለሁ፡፡
- ይህ የወኔ ጉዳይ ሳይሆን የአገር ጉዳይ ነው፡፡
- ለማንኛውም ምኞት አይከለከልም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ለዚህች አገር ተስፋዋ እኛ ነን፡፡
- አታስቀኝ እባክህ?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ይኸው ከዛሬ ነገ ትኬት ለመቁረጥ ተዘጋጅቼ ነው ያለሁት፡፡
- ምን ለመሆን ነው የምትመጣው?
- የአገሪቷን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት የእኛ ሚና ወሳኝ ነው፡፡
- ማን ናችሁ እናንተ?
- በውጭ ያለን ተቃዋሚዎች ነን፡፡
- ዶሮ ብታልም ጥሬዋን አሉ፡፡
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እናንተ ከመቼ ጀምሮ ነው ስለኢትዮጵያ የሚቆረቁራችሁ?
- ለዚህች አገር ከእኛ በላይ የታገለ አለ እንዴ?
- እሱን እንኳን ተወው፡፡
- እንዴት ማለት?
- አሁን ያው ትራምፕ ራሱ አልመች እንዳላችሁ እናውቃለን፡፡
- በእርግጥ እሱ ለማንም አይመችም፡፡ ግን ይኼ ከእሱ ጋር ምንም አይገናኝም፡፡
- ወይስ የታክሲ ገበያው ተቀዛቀዘ?
- ክቡር ሚኒስትር ለአገሪቷ በጣም እናስፈልጋለን ስልዎት?
- የእኔ ምክር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
- ምንድነው?
- አርፈህ ኡበርህን አጧጡፍ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኛ ከእናንተ በላይ ስለአገሪቷ እናስባለን፡፡
- ለዚያ ነው አሜሪካ ታክሲ የምትነዳው?
- አሁን ክፉ መነጋገር አያስፈልግም፡፡
- ታዲያ አንተ ራስህ ለምን ክፉ ታናግረኛለህ?
- እኔ የደወልኩት አንድ ነገር ለመጠየቅ ነው፡፡
- ምን ልትጠይቀኝ?
- ቀኑ ተቆርጧል ወይ ለማለት ነዋ?
- የምኑ ቀን?
- የድርድር ነዋ፡፡
- ማን ከማን ጋር ነው የሚደራደረው?
- እኛ ከእናንተ ጋር ነዋ፡፡
- ሰውዬ በጣም ኮሜዲያን ሆነሃል፡፡
- ይኼ ቀልድ አይደለም እኮ አልኩዎት፡፡
- ስማ እኛ እዚህ ካሉት ጋር እንደራደራለን፡፡
- እኛስ?
- እናንተም እዚያው ተደራደሩ፡፡
- ከማን ጋር?
- እርስ በርሳችሁ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከልጃቸው ጋር እያወሩ ነው]
- አንድ ጥያቄ አለኝ ዳዲ፡፡
- የምን ጥያቄ?
- ምን እያደረጋችሁ ነው?
- ምን ማለት ነው?
- ትንሽ እንኳን ኃላፊነት አይሰማችሁም?
- ምንድነው የምታወራው?
- ሕዝቡን አጣልታችሁ አጣልታችሁ በኋላ ላይ ግፍ አይሆንባችሁም?
- የምን ግፍ ነው?
- ይኸው ሕዝቡ በብሔር፣ በጎጥ፣ በመንደር ተከፋፍሎ እየተባላ ነው፡፡
- እ. . .
- ወጣቱም እኮ ከእናንተ ጋር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው እያያችሁ ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ወጣቱ የሚፈልገው ሌላ፣ እናንተ የምታቀርቡለት ሌላ፡፡
- እሺ የእኛ ፖለቲከኛ፡፡
- ፖለቲከኛ ሆኜ ሳይሆን እውነቱን ነው የነገርኩህ ዳዲ፡፡
- አንተን ደግሞ ማን ነው የላከብኝ?
- ዳዲ ሕዝቡ ለሚጠይቀው ጥያቄ ትክክለኛውን ምላሽ ስጡ፡፡
- አሁን አንተ ምኑን አውቀኸው ነው?
- እንዴ ይኸው ሕዝቡ አስተካክሉ እያለ እየጠየቃችሁ እኮ ነው?
- ምንድነው የምናስተካክለው?
- ሕዝብን በጉልበት መግዛት አይቻልም፡፡
- ምን?
- አሁን የእኛን ቤት ጥበቃ በፍቅር ነው እንጂ ማስተዳደር ያለብን በጉልበት ማሠራት አንችልም፡፡
- ታዲያ እኛ መቼ በጉልበት አሠራነው?
- አየህ ሕዝቡን አሁን በጉልበት ማስተዳደር አይቻልም፡፡
- ወይ ጣጣ?
- እንደነገርከኝ ድሮ እናንተ በወጣትነት ጊዜያችሁ የራሳችሁ ጥያቄ ነበራችሁ፡፡
- እሱ እኮ ነው ለዚህ ያበቃን፡፡
- አየህ ልህ እንደዚያ የአሁኑ ወጣቶችም የራሳቸው ጥያቄ አላቸው፡፡
- ወጣትነት እኮ ከባድ ነው፡፡
- አይ ዳዲ የአሁኑ ወጣቶችም የራሳችን ጥያቄ አለን፡፡
- ጥያቄያችሁ ምንድነው?
- ጥያቄያችንማ ከብሔርና ከጎጥ ወጥተን ታላቋን ኢትዮጵያ መገንባት ነው፡፡
- እ. . .
- ለዚህም ስትራቴጂ ነድፈን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡
- ምን ዓይነት ስትራቴጂ?
- ፓርቲ ልናቋቁም ነው፡፡
- ምን የሚባል ፓርቲ?
- መአዴግ፡፡
- ምንድነው መአዴግ?
- መላው የአራዳ ዴሞክራሲያዊ ግንባር!
[ክቡር ሚኒስትር ከሌላ ሚኒስትር ጋር በቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዙሪያ እያወሩ ነው]
- ዛሬ ለምን እንደፈለኩግህ ታውቃለህ?
- ለምንድን ነበር የፈለጉኝ?
- የእኛ ፓርቲ የሚያቀርበውን ዕጩ እንድትመርጥልን ነው፡፡
- እሱን ባደርግ እኔ ምን እጠቀማለሁ?
- አየህ ከእንዲህ ዓይነቱ ነጋዴ ጋር ነው ማውራት የሚያስደስተኝ፡፡
- ሰጥቶ መቀበል እኮ ጥርሳችንን የነቀልንበት ነው፡፡
- ለነገሩ አንተ ከባለሥልጣንነት ባሻገር በንግድ ሥራ ነው የምትታወቀው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እንደዚያ ባይሆንማ ይኼን ሁሉ ሀብት ባላፈራሁ፡፡
- አሁን ከአንተ የአንተን ድምፅ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ወዳጆችህን ድምፅ እንፈልጋለን፡፡
- ስለ እሱ አያስቡ፣ ዋናው ለእኛ ምን አለው የሚለው ነው፡፡
- ምንድነው የምትፈልገው?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ከተገኘ ውጭ ጉዳይ፣ አይ ከተባለ የንግድ፣ አይ ከተባለም የፋይናንስና ኢኮኖሚክ ትብብሩን ባገኘው ደስ ይለኛል፡፡
- ለምን?
- እኔ ያው የቢዝነስ ሰው ስለሆንኩ ከኢንቨስተሮችና ከገንዘብ አካባቢ መራቅ አልፈልግም፡፡
- እነዚህን ብቻ ነው የምትፈልገው?
- በተጨማሪም አንድ ሦስት የሚሆኑ የልማት ድርጅቶች ቦርድ ውስጥ መግባት እፈልጋለሁ፡፡
- አሁን እዚህ መነጋገር ያለብን ነገር አለ፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ለአንድ ድምፅ የጠየቅከው ነገር ብዙ ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ውጭ ጉዳይ አራት ድምፅ ይፈልጋል፣ ስለዚህ ሦስት ተጨማሪ ሰዎች ያስፈልጉሃል፡፡
- እሺ፡፡
- ንግድ በሁለት ድምፅ ይሆናል፡፡
- ፋይናንስና ኢኮኖሚክ ትብብሩስ?
- እሱ ደግሞ ሦስት ድምፅ ይፈልጋል፡፡
- ለልማት ድርጅት ቦርድ አባልነትስ?
- እሱን ለአንድ ድርጅት በአንድ ድምፅ መደራደር እንችላለን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በዚህ ከተስማማን ሁሉን ነገር ለእኔ ይተውት፡፡
- ሰዎች አሉኝ እያልክ ነው?
- በአንድ የስልክ ጥሪ መጨረስ እችላለሁ ስልዎት?
- እርግጠኛ ነህ?
- የእኔን ብቃት አያውቁትም ማለት ነው?
- የእኛን ዕጩ ማስምረጥ ትችላለህ?
- ክቡር ሚኒስትር ብቻ የምጠይቀው ሁሉ ይፈጸምልኝ፡፡
- ይኼን ካስፈጸምክ ከሚኒስትርነቱ ባሻገር የአምስት ድርጅቶች ቦርድ አባል ትሆናለህ፡፡
- እንዲህ ካደረጉልኝማ ዕጩውን አይደለም ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ለሌላም ላስመርጥ እችላለሁ፡፡
- ለሌላ ለማን?
- ለእንግሊዝ!