Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከፍተኛ እንግልት የደረሰበት የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ይገባል

ከፍተኛ እንግልት የደረሰበት የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ይገባል

ቀን:

ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ለዓለም ወጣቶች እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ባለፈው እሑድ ካሜሩን ያውንዴ ላይ ከካሜሩን አቻው ጋር ተጫውቶ 0 ለ0 የተለያየው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡደን ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡ ቡድኑ በበረራ እጦት ምክንያት ለከፍተኛ እንግልት ተዳርጎ መቆየቱ የፌዴሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ከስፍራው በላኩት ዘገባ አረጋግጠዋል፡፡

ባለፈው ዓርብ ሰኔ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከአዲስ በአበባ ተነስቶ የካሜሩን ሁለተኛ ከተማ በሆነች ዱዋላ የደረሰው ዕደሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን፣ እሑድ ሰኔ 5 ቀን ያውንዴ ላይ ከካሜሩን አቻው ጋር ለሚጠብቀው የዓለም ዋንጫ ማጠሪያ ከዱዋላ ያውንዴ የ30 ደቂቃ የአውሮፕላን በረራ ማድረግ ነበረበት፡፡ ይህ የጉዞ ሒደት በአስተናጋጁ የካሜሩን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚከናወን መሆኑም ይታወቃል፡፡

ሁለቱ አገሮች እሑድ በኢትዮጵያ የጊዜ ቀመር 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን አድርገው 0 ለ0 በሆነ ውጤት ከተለያዩ በኋላ ወደ ሚቀጥለው ማጣሪያ የሚያልፈውን ቡድን ለመለየት ከሁለት ሳምንት በኋላ አዲስ አበባ ላይ በሚኖራቸው የመልስ ጨዋታ እንደሚወሰን የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) መርሐ ግብር ያስረዳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በጨዋታው ማግስት ሰኞ ወደ ዱዋላ በመጣበት አኳኋን መመለስ የነበረበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን፣ የካሜሩን አየር መንገድ በፕሮግራሙ መሠረት ሊያስተናግደው ባለመቻሉ ምክንያት ለከፍተኛ እንግልት መዳረጉ የፌዴሬሽን ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊና የቡድኑ አካላት በካሜሩን ለሚመለከታቸው አካላት ቢያስታውቁም ችግሩ እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ ሆኖ እንዳላገኙት በኢሜል አድራሻቸው ባሰራጩት ተደጋጋሚ መልዕክት አስታውቀዋል፡፡ እንደ ሕዝብ ግንኙነቱ ከሆነ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን በመጣበት አኳኋን ማስተናገድ የካሜሩን እግር ኳስ ፌዴሬሽንና መንግሥት ቢሆኑም፣ ኃላፊነታቸውን እንዳልተወጡ አስረድተዋል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ቡድኑ በያውንዴ አየር መንገድ ከዘጠኝ ሰዓት እንግልት በኋላ ወደ ያውንዴ ከተማ መመለሱን አስረድተዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የፌዴሬሽኑን ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ለማግኘት ያደረግነው ተደጋግሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡ ሆኖም ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ጋር ሪፖርተር ባደረገው የስልክ ቃለ ምልልስ፣ ለኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን መጉላላትና እንግልት ተጠያቂዎቹ የካሜሩን እግር ኳስ ፌዴሬሽንና አየር መንገዱ ናቸው፡፡

ምክንያቱን አስመልክቶ አቶ ጁነዲን እንዳስረዱት፣ ብሔራዊ ቡድኑ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በረራውን ያደረገው የካሜሮን ሁለተኛ ከተማ ወደ ሆነችው ዱዋላ ነው፡፡ ጨዋታው የተደረገው ደግሞ ከዱዋላ በአውሮፕላን የ30 ደቂቃ በረራ ተደርጎ ዋና ከተማዋ ያውንዴ ላይ ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑ በደረሰው ፕሮግራም መሠረት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተደረገ ማግሥት የካሜሩን አየር መንገድ ቡድናችንን በመጣበት አኳኋን ወደ ዱዋላ ከተማ መልሶ በስፍራው ለሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማድረስ ሲገባው አለማድረጉንና መጉላላቱ የተፈጠረውም በዚህ መሀል በተፈጠረው ክፍተት መሆኑን የጠቆሙት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ችግሩን ለመፍታት ዱዋላ ከሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅርንጫፍ ኃላፊ ከሆኑት አቶ ተስፋዬ ጋር ተደጋጋሚና እልህ አስጨራሽ የስልክ ጥሪ አድርጎ በመጨረሻም የካሜሩን አየር መንገድ ትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 7 ቀን ቡድኑን ከያውንዴ ዱዋላ ከተማ መልሶ እንዲያደርስ ከስምምነት መደረሱን ተናግረዋል፡፡

ማረጋገጫው ምንድን ነው? ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ አቶ ጁነዲን እንደመለሱት፣ ‹‹እርግጥ ነው ያውንዴ የሚገኘው የካሜሩን አየር መንገድ ትናንት ጠዋት (ማክሰኞ) ቡድኑን ወደ ዱዋላ ከተማ ለመመለስ ለኢትዮጵያ የቡድን አባላት ቦርዲንግ ፓስ ከሰጠ በኋላ መልሶ ያዘገየበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ሆኖም በድጋሚ ከተደረገው የስልክ ጥሪና መግባባት በኋላ ማክሰኞ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ምሽት ሁለት ሰዓት ቡድኑ ከያውንዴ ተነስቶ ዱዋላ እንደሚገባ የአገሪቱ አየር መንገድ ኃላፊዎች ማረጋገጫ ሰጥተውኛል፡፡ ይህንኑ ዱዋላ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅርንጫፍ ኃላፊና የኢትዮጵያ የቡድን አባላትም አረጋግጠውልኛል፤›› ብለዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡን ረቡዕ ምሽት አዲስ አበባ ይገባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጭምር አቶ ጁነዲን ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...