‹‹ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ባይደረስ ኖሮ በመካከለኛው ምሥራቅ ለበርካታ ጦርነቶች መቀስቀስ ትልቅ አጋጣሚ ይፈጠር ነበር››
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ምዕራባውያን አገሮች ከኢራን ጋር ማክሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በኑክሌር መርሐ ግብሯ ላይ ከስምምነት ከደረሱ በኋላ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ፡፡ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እንደሚሉት፣ በስምምነቱ መሠረት ኢራን 98 በመቶ የሚሆኑትን በዩራኒየም የበለፀጉ መሣሪያዎች ታወድማለች፡፡ ይህ መጠን አሥር የኑክሌር አረሮችን ለመሥራት ያስችላል፡፡ ‹‹ይህ ስምምነት ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ለመፈብረክ የሚያስችላትን ሁሉንም መንገድ ዘጋግቶባታል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ በኦስትሪያ ቪየና የተደረሰው ስምምነት በመተማመን ላይ ሳይሆን፣ በማረጋገጫ ላይ የተመሠረተና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የተደገፈ ነው ሲሉ ኦባማ አስታውቀዋል፡፡ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ ስምምነቱን ታሪካዊ ሲሉት፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ግን መጥፎ ስህተት ብለውታል፡፡ ኢራን በዚህ ስምምነት ምክንያት ማዕቀብ ተነስቶላት በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚያወጡ የንግድ ግንኙነቶችን ከምዕራባውያን ጋር እንድታደርግ ያስችላታል ተብሏል፡፡ በምሥሉ ላይ ባራክ ኦቦማ መግለጫ ሲሰጡ ይታያሉ፡፡