Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊዓለም አቀፉ ጉባኤና የኢትዮጵያ ተሞክሮ

  ዓለም አቀፉ ጉባኤና የኢትዮጵያ ተሞክሮ

  ቀን:

  ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ በጤናው ዘርፍ የሰው ሀብት ልማት ላይ በሚኒስትሮች ደረጃ ለሁለት ቀናት የሚወያየውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ታስተናግዳለች፡፡ የዚህ ዓይነቱ ጉባኤ ዋና ዓላማ አፍሪካ ከሌሎች አገሮች ልታገኝ ስለምትችለው ዕርዳታ ሳይሆን ያላትን ሀብት እንዴት አሟጥጣ መጠቀም ትችላለች በሚለው ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ የሰው ሀብት ልማት ለማብቃት ከጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች አንፃር ያከናወነቻቸውን ተግባራትና የተመዘገበውን ውጤት በተመለከተ የልምድ ልውውጥ ይደረጋል፡፡

  ዶክተር ወንድምአገኝ እምቢአለ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንደገለጹት፣ የተሞክሮና የልምድ ልውውጡ የሚካሄደው በሁለት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው የተከናወኑትን ተግባራት ለጉባኤተኞቹ አቅርቦ ማወያየት ሲሆን፣ ሁለተኛው አካሄድ ደግሞ በአካባቢው ያሉት የጤና ማዕከላትን፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሥራዎችንና ሞዴል ቤተሰቦችን ማስጎብኘት ነው፡፡

  ሞዴል ቤተሰቦችን የመጎብኘት ጠቀሜታ በጤናው ኤክስቴንሽን የተያዙ ወይም የታቀፉ 16 ፓኬጆችን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ምን ዓይነት ለውጦች እንዳመጡ ለመረዳት እንዲያስችል ነው፡፡

  ኢትዮጵያ ካለፉት አሠርታት  በፊት በጤናው የሰው ሀብት ልማትን ለማዳበር የሚረዳ ፕሮጀክት የቀረፀችው አንድ ሐኪም ለ40,000 ሰዎች፣ አንድ አዋላጅ ነርስ ለ57,000 ሰዎች በነበረበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በአጭር ጊዜ በቂ ሐኪም አምርቶ ማኅበረሰቡን ማዳረስ እንዳልተቻለ ነበር ዶክተር ወንድምአገኝ የተናገሩት፡፡

  ይህንን ችግር ለመቅረፍ በርካታ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን፣ ከዕርምጃዎቹም መካከል አንደኛው የጤና ሥራዎችን ላሉት የጤና ባለሙያዎች ማካፈል (ታስክ ሼሪንግ) ወይም መቀያየር (ታክስ ሺፍቲንግ) የመሳሰሉት አካሄዶች ይገኙበታል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የጤና ባለሙያዎችን ለአጭር ጊዜ አሠልጥኖ የሙያ ብቃታቸው እየታየ ወደ ማኅበረሰቡ እንዲደርሱ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች አስፈላጊነታቸው እየታየ እንዲመጣ አድርጓል፡፡

  ‹‹መከላከልን መርህ አድርጋ ለምትጓዝ አገራችን ትልቁ ችግር የእናቶችና ሕፃናት ሞት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለሕፃናት ክትባት፣ ለእናቶች የቤተሰብ ምጣኔና ጽዳት አጠባበቅ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ከተሠራ አብዛኞቹ የጤና ችግሮችን መግታት ይችላል፡፡ ይህም ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ይህም ቢሆን በእናቶችና ሕፃናት ሞት ላይ ትልቁ ችግር የነበረው ብቃት ያለው የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ባለሙያ አለመኖር ነበር፡፡ ይህንን ለማሟላት ደግሞ ሐኪሞችን ለስድስትና ለሰባት ዓመታት ያህል ትምህርት ቤት አስገብቶ፤ ከዛም ለስፔሻላይዜሽን አራት ዓመት አስተምሮ ለማድረስ ረዥም ጊዜ ይፈጥራል፡፡ ለዚህ ችግር የተወሰደው እልባት የጤና ሥራዎችን ባሉት ባለሙያዎች ማካፈል ወይም ማቀያየር የሚለውን አካሄድ በመከተል ነው፡፡

  ይህ ዓይነቱ አካሄድ በመቀጠል ላይ እንዳለ የጤና መኰንኖችን ለሦስት ዓመት አስተምሮ አብዛኛውን ጊዜ እናቶች አገልግሎት የሚፈልጉበትን የማዋለድና ድንገተኛ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንዲሠሩ ማድረግ ተቻለ፡፡ እነዚህም ሥራዎች በምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች የታየውን ውጤት አስጨብጧል፡፡

  የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ሙያተኞቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ከጤና ኤክስቴንሽንና ከመሠረተ ጤና ክብካቤ (ፕራይመሪ ሔልዝ ኬር) አንፃር የተሠሩና የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦችን ከማሳካት አኳያ የደረሰችበትን ተሞክሮ እንዲቀስሙ ተደርጓል፡፡ በዚህ መለኩ በቂ ልምድ ቀስመው ከተመለሱት መካከል የናሚቢያ ሙያተኞች ይገኙበታል፡፡ በዚህም የነሳ እነዚህ ሙያተኞች የቀሰሙትን ልምድ በአገራቸው እንዴት እንደተገበሩት ለጉባኤተኞቹ ያብራራሉ፡፡

  ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት ሥነ ሕዝብ ድርጅት ጋር በመተባበር ከሐምሌ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚያካሂደው በዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የአፍሪካ የጤናና የገንዘብ ሚኒስትሮች እንደሚሳተፉ፣ በጉባኤው ኢትዮጵያ ከምታቀርበው ተሞክሮና ልምድ ባሻገር የዓለም ጤና ድርጅት የሰው ሀብት ልማትንና አስተዳደርን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀው ስትራቴጂ ቀርቦ ከአፍሪካ አንፃር ምን መምሰል እንዳለበት ውይይት ይደረግበታል፡፡ በሰው ሀብት ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚሰጠውን ጠቀሜታ አስመልክቶ የተዘጋጁ ጥናቶችም ይቀርባሉ፡፡

  ሚስተር የስቱን ያሁ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር ኢትዮጵያ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ባከናወነችውና ባስመዘገበችው ውጤት የተነሳ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብና የአፍሪካ አገሮችን ትኩረት ለመሳብ እንደቻለች ተናግረዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...