Wednesday, November 30, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊድህነት የቀጠፋቸው

  ድህነት የቀጠፋቸው

  ቀን:

  ከወራት በፊት ጉርድ ሾላ አካባቢ ነው፡፡ አንዲት በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ እናት ከአንድ ጥግ ሆና ታቃስታለች፡፡ የደረሰች ነፍሰ ጡር ብትሆንም ምጥ ይዟት እየተሰቃየች መሆኑን የጠረጠረ አልነበረም፡፡ ከአፍታ ቆይታ በኋላ ግን ስቃይዋ እየበረታ መጥቶ የድረሱልኝ ጥሪ ማሰማት ጀመረች፡፡ በአቅራቢያዋ የነበሩ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች ግን አብረዋት ከማልቀስ በቀር የፈጠሩላት ነገር አልነበረም፡፡ መንገደኛውም ከንፈር ከመምጠጥ ባለፈ ምንም አልረዳትም ነበር፡፡

  ድንገት ከፍተኛ ጩኸት አሰምታ ወደ ኋላዋ ወደቀች፡፡ ልጇንም በዛው ቅፅበት ተገላገለች፡፡ ነገር ግን ልጇ በደቂቃዎች ዕድሜ ሕይወቱ አለፈ፡፡ ራሷን ስታ በወደቀችበት ብዙ ደም ይፈሳት ጀመረ፡፡ ሁኔታውን ከሩቅ ያዩ መንገደኞችም በፍጥነት ደርሰው አፋፍሰው ወሰዷት፡፡

  በሞትና በሕይወት መካከል የምትገኝ እናት በዚያው ሕይወቷ አልፎ ይሆን ወይስ ታድገዋት እንደሆነ መረጃው የለንም፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ ባለ አጋጣሚ ጥቂት የማይባሉ እናቶችና ሕፃናት ሕይወታቸው ያልፋል፡፡ በድህነት ምክንያት የሕክምና አገልግሎት ባለማግኘት፣ ከፅዳት ጉድለት በሚፈጠሩ በሽታዎችና በመሳሰሉት ሕፃናትና እናቶች ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ አጋጣሚው በከተሞች አካባቢ በተለይም በተጨናነቁ መንደሮች ውስጥ እንደሚበዛ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

  ረቡዕ ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ሴፍ ዘቺልድረን ‹‹ኧርባን ዲሳድቫንቴጅ››  በሚል በኢሊሊ ሆቴል ባዘጋጀው መድረክ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ እናቶችና ሕፃናት በችግር ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉ ተገልጿል፡፡ በወቅቱ የተለያዩ ጥናቶች ለውይይት ቀርበዋል፡፡ በጥናቱ መሠረትም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ሕፃናት በንፅህና ጉድለት፣ በሕክምና እጦትና በሌሎችም ምክንያት የአምስት ዓመት የልደት በዓላቸውን ሳያከብሩ ለኅልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡

  በርእሰ ጉዳዩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶ/ር ሚሊዮን ሺበሺ በሴቭ ዘችልድረን ኢትዮጵያ የጤናና ኒውትሪሽን ቴክኒካል ቲም ሊደር ናቸው፡፡ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ መሠረትም በአዲስ አበባ የሚገኙ ሕፃናት በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የመሞት ዕድላቸው ደህና ኑሮ ከሚኖሩ ሕፃናት በሁለት እጥፍ ይጨምራል፡፡

  ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑት ሕፃናት በተጨናነቀ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፣ በንፃሕና ጉድለት፣ የጤና ግልጋሎት ባለማግኘትና በቤተሰብ የግንዛቤ እጥረት ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለፃ፣ ቁጥሩ ከ15 ዓመታት በፊት አራት እጥፍ ነበር፡፡ ነገር ግን በተደረጉ ርብርቦች በግማሽ ለመቀነስ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ የጨቅላ ሕፃናትን ሞት በበቂ መቀነስ አልተቻለም፡፡ ማንኛውም ሕፃን መሞት የለበትም በሚል መሠራት እንደሚገባውና ልዩነቱ መጥበብ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

  ችግሩ የተፈጠረው በከተሞች ላይ በቂ ትኩረት ባለመደረጉ መሆኑን የሚገልጹት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በእናቶች ጤና ዳይሬክቶሬት የእናቶች ጤና ኬዝ ቲም አስተባባሪ ዶ/ር ኢክራም መሐመድ ናቸው፡፡

  ብዙ ትኩረት ያላገኙ እናቶችና ሕፃናት እየሞቱ ይገኛሉ፡፡ ይህም በቂ ትኩረት ካለማድረግ አንፃር የተከሰተ ነው፡፡ ከተሞች ዕድገት ላይ ሲሠራ ቢቆይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ አካባቢዎች በበቂ አልተካተቱም፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም የከተሞች ዕድገት፣ የሕክምና ተደራሽነትና ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

  የእናቶችንና የሕፃናትን ሞት በመቀነስ ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለፃ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እናቶችና ሕፃናትን ሕይወት ለመታደግ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የሕፃናቱ ሞትም በብዛት ከአቅም ጋር የተያያዘ በመሆኑ የእናቶችን አቅም የመገንባት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም 375,000 ሴቶችን ያቀፈ የሴቶች የልማት ቡድን ተቋቁሟል፡፡ እኚህ ሴቶች ልዩ ልዩ ሥራዎችን በመሥራት ኑሯቸውን ይደግፋሉ፡፡

  የአዲስ አበባ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ሙሉ ለሙሉ ትኩረቱን ያደረገው በከተማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰቡ አካል ላይ ነው፡፡ ፕሮግራሙ የጎዳና ተዳዳሪዎችንም ያካትታል፡፡ ‹‹ሠራተኞቹ ቤት ለቤት ሄደው ምክክር ያደርጋሉ፡፡ በዚህም እንደ ከተማ ትልቅ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ነገር ግን አሁንም ሕፃናትና እናቶች እየሞቱ ይገኛሉ፡፡ ይህን ለመቀየርም የጀመርናቸውን ሥራዎች አጠናክረን መቀጠል ይጠበቅብናል›› ብለዋል፡፡

  በአዲስ አበባ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሕፃናት ደህና ኑሮ ከሚኖሩ ሕፃናት ሞት በሁለት እጥፍ ቢጨምርም ይህ ቁጥር በብዙዎቹ ከሠሀራ በታች በሚገኙ አገሮች እንደሚጨምር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...