ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ የክብር ዶክትሬት አግኝቷል፡፡ የስመ ጥሩ ሮሃ ባንድ መሥራቾች አንዱ የሆነው ዳዊት፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ጉልህ ስፍራ ከሚሰጣቸው ሙዚቀኞች ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት የሚመራው ሙዚቀኛው፣ በተለይ ሮሃ ባንድ ውስጥ ሙዚቃ አቀናባሪ በነበረበት ወቅት ከ200 በላይ አልበሞች ላይ አሻራውን አሳርፏል፡፡ ከሙዚቀኛው ጋር ሮሃ ባንድን ከመሠረቱ ሙዚቀኞች መሀከል ጆቫኒ ሪኮና ሰላም ሥዩም ይጠቀሳሉ፡፡ ባንዱ ካጀባቸው ሙዚቀኞች ሙሉቀን መለሰ፣ መሐሙድ አህመድ፣ ሐመልማል አባተና ኩኩ ሰብስቤ ጥቂቱ ናቸው፡፡ የሮሃ ባንድ አባላት በ1986 ዓ.ም. የተበታተኑ ሲሆን፣ በቅርቡ ከአባላቱ ጥቂቱ ተሰባስበው ከዝነኛው ዳምፃዊ መሐሙድ አህመድ ጋር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ መጣመራቸው ይታወሳል፡፡ ዳዊትን ጨምሮ እነዚሁ የሮሀ ባንድ አባላት የድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩን አልበም በማዘጋጀት ላይም ይገኛሉ፡፡