Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

በቻይና በተለይ ቅዳሜ ሐምሌ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተከሰተው ከፍተኛ ሙቅት ለማምለጥ

ትኩስ ፅሁፎች

በቻይና ሺዋን ግዛት በተዘጋጀ ሰው ሠራሽ የመዋኛ ስፍራ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ባንዴ ገብተው ይታያሉ፡፡ በቻይና በተለይ ቅዳሜ ሐምሌ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተከሰተው ከፍተኛ ሙቅት ለማምለጥ ሲሉ የገቡት ከ8,000 በላይ እንደነበሩ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

*****

የጊዜ ጠበቃ

የንጋት ሰመመን – የሰማይ ጎረቤት፣

የአምላክ ምስክር – የምድር እመቤት፣

ከምዕራብ ድንበር – ከምሥራቅ ስትርቂ

በንዳዱ ቀልጠሽ – ስቀሽ ስትስቂ

በኦሪት ቃል ኪዳን – ስትንተከተኪ

ላ’ንዲት ሴኮንድ እንኳ ሳይደፍርሽ ተተኪ

እልፍ ዘመናቶች አይተሻል ሲከንፉ

አብበው በፀዳል – ዝለው እስኪጠፉ

ታሪክ ሲተካካ ከነጠፈጠፉ፡፡

ግርምት ነሽ ፍፁም! ዝንታ’ለም የነቃ

ይኸው አሁን እንኳ ‹‹አንድ›› አለ ደቂቃ!

እስኪ አስቢው ፀሐይ፣ ሲመሽ ወይ ሲነጋ

ዕድሜ፣ ዘመን አልፎ-ታሪክ ቢዘነጋ

የሰማይ ቅርስ ሆነሽ- የዘላለም ሃውልት

ጊዜ ሲበደርሽ፣ ዘመን ሲመፀወት፣

ጨለማ በግዝት – ተኝቷል ላይነቃ

በወገግታሽ ድርበብ – በዘመን ፈረቃ

የለም ነፍስ ስጋ – ተሽሯል ደቂቃ

ምድርን ሹም አድርገሽ – የዕድሜ ጠበቃ

ጨለማ እስኪወጣት – ብርሃን አውልቃ፡፡

ካሳሁን ወ/ዮሐንስ ‹‹ማርገጃ›› (2006)

*****

‹‹ትርጉም በስለሺ›› ሌላኛው መዘዝ

ማምሻውን ከአንዱ ወዳጄ እና ከሁለት ፈረንጅ የሥራ ባልደረቦቹ ጋር ነበርኩ፡፡ ፈረንጆቹ በኢትዮጵያ ውስጥ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በተመለከተ ጥናት ላይ ናቸው፡፡ የወዳጄ ዋነኛው ስራ ‹‹ሴትና ህፃናትን የሚያንቋሽሹ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እና አባባሎችን›› መዘርዘርና ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሞ መስጠት ነው፡፡

‹‹እስካሁን ምን ምንን መዘገብክ?›› ብዬ ጠየቅኩት፡፡

ላፕቶፑን ከፈተና ከአርባ በላይ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን ከነ ትርጉማቸው ያስቀመጠበትን ሰንጠረዥ አሳየኝ፡፡
‹‹ሴት በዛ ጎመን ጠነዛ››
‹‹ሴት ወደ ማጀት ወንድ ወደ ችሎት››
‹‹ልጅ ያቦካው ለእራት አይቀርብም››

ማንበቤን ስቀጥል፤ ‹‹ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›› የሚል አገኘሁ፡፡ የእንግሊዝኛ ትርጉሙ ላይ እንዲህ ይላል፤ ‹‹Children Should be killed for keeping promise>>

ክፉኛ ተደናግጬ ‹‹ይህ ምን ይሉት ትርጉም ነው?›› ብዬ ጠየቅኩት፡፡

‹‹ሃሳቡን ነው የተረጎምኩት- ቃል በቃል መተርጎም ይከብዳል ታውቂያለሽ›› አለኝ፡፡

‹‹ሃሳቡንስ መች ተረጎምከው!…ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ልጆች ይገደሉ ማለት ነው እንዴ…?!››
ይሄን ጊዜ ሞቅ ያለ ውይይት በአማርኛ መጀመራችን ያሳሰባቸው የሚመስሉት ፈረንጆች ምን እንደምናወራ ጠየቁን፡፡

ነገርናቸው፡፡

‹‹ችግሩ ምንድነው?›› አለችኝ ሴቷ

‹‹ሲጀምር ትርጉሙ በአሰቃቂ ሁኔታ ተዛብቷል፡፡ ይሄ አባባል እንደ ጎጂ አባባል ታይቶ እዚህ መግባት የለበትም…ቃል በቃል…በትክክል ቢተረጎምም እንኳን መንፈሱ ጎጂ ስላልሆነ እዚህ መግባት የለበትም››

‹‹እንዴት?›› ሌላኛው ፈረንጅ ጠየቀኝ

‹‹‹‹ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›› ማለት የኛ ሀገር ሰው ለቃሉ ያለውን ጥልቅ ታማኝነትና ክብር ሊገልፅበት የሚጠቀምበት አባባል እንጂ እዚህ እንደተፃፈው ልጆች ቃልኪዳን ለመጠበቅ ይገደላሉ ማለት አይደለም…በኔ አስተያየት እንደውም ለልጆቹ ያለውን ፍቅር ነው ሚያሳየው…እንደ መሃላ ነው…በምትወደው ነገር ካልማልክ ቃልህ ይታመናል አንተ?›› አልኩት::

‹‹የኔ አይታመንም›› አለች የመጀመሪያዋ
‹‹ሰው እንዲያምንሽ በምን ትምያለሸ?›› ጠየቅኩ፡፡
‹‹እኔ በውድ ጫማዎቼ ነው የምምለው ግን ነጥብሽን አግኝቼዋለሁ.›› አለችኝ እየሳቀች፡፡

ነገሩ እጅግ ከንክኖኝ ፤ ይህችን አባባል ከዘርዝሩ ለማስወጣት ብዙ ተከራክሬ ከተለያየን በኋላ ከአመታት በፊት በተደረገ ‹‹የድህነትና ደህንነት ሁኔታ›› ጥናት ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጥሮ ስለነበር አስቂኝም አሳዛኝም ነገር አስቤ ሳቅኩ፡፡

በጥናቱ የተሳተፉ አንዲት የገጠር ሴት በአንድ ኢትዮጵያዊና ብዙ ፈረንጆቸ ታጅበው መልስ ይሰጣሉ፡፡

‹‹አግብተዋል?›› አለ ጠያቂው
‹‹ትዳር ነበረን አሁን ግን…ተፋተናል›› ሴቲቱ ስቅቅ ብለው መለሱ፡፡
‹‹ለምን ተፋታችሁ?››
ሴቲቱ ፈጠን ብለው ‹‹ኣሃ! እህል ውሃችን አለቀአ!›› ብለው ሲመልሱ፣
ፈረንጆቹ ለመዝገባቸው የሴትየዋን የመጨረሻ መልስ ትርጉም ይጠይቃሉ፡፡ ኢትዮጵያዊው ጠያቂም ደቂቃ ሳይፈጅ፤ ‹‹no food and water>> ብሎ መለሰ አሉ፡፡

ይሄኔ ያኔ በተመዘገበች ይህች መልስ ‹‹በጥናት እንደተረጋገጠው አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ባልና ሚስቶች የሚፋቱት በምግብና ውሃ እጥረት ምክንያት ነው›› ተብሎ ስንት ቦታ ተፅፎልናል!

ችግርና ችጋር ሳንሸጥ ዶላር መሰብሰብ የማንችል የሚመስለን ሞገደኛ ተርጓሚዎች ስንቱን የሚነካ ስንት መዘዝ አምጥተን ይሆን!?

  • ሕይወት እምሻው በገጽዋ እንደጻፈችው

*****

ብልጭታና መብረቅ

የነጎድጓዳማ ዝናብ መንፈስ በጉ ስለጠፋበት ፍለጋ በወጣ ጊዜ እጅግ በጣም እየዘነበ በጉን በፍለጋ ላይ ሳለ የነጎድጓዱ መንፈስ ከአንዲት እንሽላሊት ዘንድ ይደርስና የጠፋበትን በግ አይታ እንደሆነ ጠየቃት፡፡

እርሷም “አይ! አላየሁትም፡፡ በዝናቡ ምክንያት በጣም በርዶኝ ስለነበረ ፀሃይ እየሞኩ ነበር፡፡” ብላ መለሰችለት፡፡

እርሱም “ታዲያ ምን ትመክሪኛለሽ? የጠፋብኝንስ በግ እንዴት ላገኘው እችላለሁ? ማንስ ይሆን የሰረቀው?” ብሎ ጠየቃት፡፡ እንሽላሊቷም “ግንደ ቆርቁር ጋ ሄደህ እርሷ የምታውቀውን ትነግርሃለች፡፡” አለችው፡፡

ነጎድጓዱም ወደ ግንደ ቆርቁር ሄዶ “በጌ ጠፍቶብኛልና አይተሽዋል?” ብሎ ጠየቃት፡፡

ግንደ ቆርቁሯም “እኔ የተለመደ ሥራዬን እየሠራሁ፣ እየቆረቆርኩ ነበርና በግህን አላየሁትም፡፡” አለችው፡፡

እርሱም “እናስ ታዲያ የጠፋብኝን በግ እንዴት ላገኘው እችላለሁ?” አላት።

እርሷም “እስኪ ወደ እስስት ዘንድ ሂድ ። ሌሎች እንስሳትን ባየ ጊዜ የሚደበቀው አንዳች ክፉ ነገር ቢሠራ ነው። በፀፀት ምክንያት፡፡” አለችው፡፡

ነጎድጓዱም “በርግጥ የተደበቀበት ምክንያት ገብቶኛል፤በጌን ሠርቆት ወይም መርዞት መሆን አለበት፡፡” ብሎ አሰበ፡፡

ይህንንም ካለ በኋላ ወደ እስስት ዘንድ በማምራት እስስቱ ዘንድ እንደደረሰ “በል ና ውጣ ፣አንተ እስስት!” ብሎ ቢጣራም እስስቱ ከአንድ ዛፍ ስር ተደበቀ፡፡

ነጎድጓዱም እስስቱን ፍለጋ ከዛፉ ጀርባ ቢዞርም እስስቱ ግን ጫካው ውስጥ ገብቶ ተደበቀ፡፡

ሆኖም በመጨረሻ ነጎድጓዱም እስስቱን አግኝቶ “በጌን የሰረቅኸው አንተ ነሃ! በልተኸው ወይም መርዘኸው ይሆናል፡፡” ብሎ ነጎድጓዱ እስስቱን ሰነጣጠቀው፡፡

አስከዛሬም ድረስ ነጎድጓዳማ መብረቅ በመጣ ጊዜ በሽማሌዎች ዘንድ “ወደ ውጪ ወጥታችሁ ዛፍ ስር አትቁሙ፤ ምክንያቱም መብረቁ በጉን የሰረቀበትን እስስት እየፈለገ ነው፡፡” የሚል ብሂል አለ፡፡

የዚህም ተረት መልዕክት ክፉ ነገሮችን ሰርተው እንደሚደበቁ ሰዎች አትሁኑ የሚል ነው፡፡

  • በአዬሻ ቱሽክሎ የተተረከ የማሊ ብሔረሰብ ተረት

*****

አወዛጋቢው የግብፅ ቅርፅ

ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ1300 ዓመታት በፊት ከባሏ ጋር ግብፅን የመራችው ንግሥት ነፈርቲቲ እጅግ ውብ እንደነበረች ይነገርላታል፡፡ ከግብፅ ፈርኦኖች የአንዱ ባለቤት የሆነችው ነፈርቲቲ፣ የቁንጅናዋ ዝና ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬም ግብፃውያንን የሚያኩራራ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የነፈርቲቲን ገፅታ የሚያሳይ ቅርጽም በግብፅ ይገኛል፡፡ በቅርቡ  በግብፅ ሳማሉት ከተማ የቆመው አዲስ የንግሥቲቷ ቅርፅ ግን በበርካታ ግብፃውያን ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ ቅርፁ የንግሥቲቷን ውበት አያሳይም በማለት የአገሪቱን ባለሥልጣኖች እንዲሁም የሥነ ጥበብ ኃላፊዎች ያብጠለጠሉም አልታጡም፡፡

ቅርፁ የንግሥቲቱ ውበት እንዳጎደፈ የተናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ አንዳንዶች ‹‹ቅርፁ ነፈርቲቲን የሚያዋርድ ነው›› ብለዋል፡፡ ብዙ ግብፃውያን  ቀራፂውንም ወቅሰዋል፡፡ ‹‹ያለፈውን ዘመን ያሁኑኑንም ገፅታ ያጎደፈ›› በማለት ቁጣቸውን የገለጹም አሉ፡፡ ከከተማዋ አደባባይ ቅርፁ እንደሚነሳ የሚያመላክቱ መረጃዎች እየተደመጡም ነው፡፡ የንግሥቲቷ ስም ትርጓሜው ‹‹ቆንጆ ሴት መጥታለች›› ማለት ነው፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች