Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምሜክሲኳዊው አደገኛ የዕፅ አዘዋዋሪ ከእስር ቤት አመለጠ

ሜክሲኳዊው አደገኛ የዕፅ አዘዋዋሪ ከእስር ቤት አመለጠ

ቀን:

በሜክሲኮ ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ወንጀሎች፣ ከሜክሲኮ አልፈው አሜሪካን የሚፈትኑበት ደረጃ ከደረሱ ዓመታት ቀቆጥረዋል፡፡  አደንዛዥ ዕፅ ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ እንደ ቀለብ መግባት ከጀመረም እንዲሁ፡፡

 አሜሪካም ሆነች ሜክሲኮ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመግታት በየፊናቸውና በጋራ እየሠሩ ቢሆንም፣ የለፉትን ያህል መቀልበስ አልቻሉም፡፡ የዕፅ ዝውውር መረቡም የራሱን ግዛት አስፋፍቷል፡፡ በንግዱ ብዙ ወንጀለኞች እጃቸው ያለበት ቢሆንም፣ የሲናሎአ መረብን ያህል ሁለቱን አገሮች የፈተነ የለም፡፡

 የሲናሎአ ግንባር ቀደም መሪ ደግሞ በሜክሲኮ ዕፅ በማዘዋወር የተዋጣለት ነው፡፡ ከሜክሲኮም አልፎ አሜሪካ ድረስ የዕፅ ንግድ መረብ በመዘርጋት ይታወቃል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ ቤተሰቦቹም የንግድ ሰንሰለቱ አካል ናቸው፡፡ ሀብታቸው የበዛ ወንጀላቸው የከፋ እንደሆነም ይነገራል፡፡

- Advertisement -

 የንግድ አድማሳቸውን ከሜክሲኮ አሜሪካ ለማድረስ የውስጥ ለውስጥ ዋሻ የዘረጉ፣ ከደኅንነት አካላት ቁጥጥር ውጭ የሆኑም ናቸው፡፡ ጠንካራ የገንዘብ አቅምና ጉልበት ያላቸውም ናቸው፡፡ ከንግዱ ባህሪ አንፃርም ይገድላሉ፣ ይገደላሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በሜክሲኮና በአሜሪካ ሲናሎአ የተባለውን የዕፅ ንግዱን ሰንሰለት የሚመራውን ጆአኩዊን ኤልካፖ ጉዝማን ጨምሮ አብዛኞቹ በወንጀል የሚፈለጉ ናቸው፡፡ ሆኖም የንግድ  ሰንሰለቱ መሪ የሆነው የ60 ዓመቱ ጉዝማን፣ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ በትውልድ አገሩ ሜክሲኮ የደኅንነት አካላት ብቻ ሳይሆን፣ አሜሪካውያንም በእጃቸው ለማስገባት ሲጓጉለት የነበረ፣ በዕፅ ንግድ የበለፀገና አድማሱን ያሰፋ ወንጀለኛ ነው፡፡

እ.ኤ.ኤ. በ2001 ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግበታል በተባለውና በሜክሲኮ ከሚገኘው እስር ቤት ያመለጠው ጉዝማን፣ ከ13 ዓመታት በኋላ ነበር ዳግም ተይዞ ወደ እስር ቤት የገባው፡፡ 13 ዓመቱን በመሉ ተሰውሮ የሲናሎአን መረብን ሲመራ የነበረው ጉዝማን፣ በሜክሲኮ ባህር ዳርቻ በሚገኝ ሪዞርት የተያዘው እ.ኤ.አ. በ2014 ነበር፡፡ ዳግም በቁጥጥር ሥር ከዋለበት ጊዜ አንስቶም በምዕራብ ሜክሲኮ ከሚገኘውና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ቁጥጥር ከሚደረግበት እስር ቤት አሳልፏል፡፡ ይህ ጊዜ ግን ለጉዝማንና ለግብረ አበሮቹ ከእስር ቤት የሚያመልጥበትን መንገድ የሚያጠኑበት ነበር፡፡

ከማንኛውም ቤተሰቡ ግንኙነት ያልነበረው ጉዝማን፣ ከእስር ቤት ሆኖ የዕፅ ንግዱን ይመራ እንደበር አሁን የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከእስር ቤት ሆኖ የዕፅ ንግዱን መምራቱ ግን አሁን ትልቁ አጀንዳ አይደለም፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥበቃ ከሚደረግበት ጥብቅ እስር ቤት ማምለጡ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

ከማደሪያ ክፍሉ ሲወጣ ጀምሮ ምልክት የሚሰጥ ቴክኖሎጂ በእስር ቤቱ ቢገጠምም፣ ጉዝማንን ከማምለጥ አላገደውም፡፡ ጉዝማን ሻወር ለመውሰድ ከገባበትና በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥበቃ ከማይደረግበት ክፍል ገብቶ ነው በዚያው የተሰወረው፡፡   በኋላ የወጡ መረጃዎች በመሰላል ተጠቅሞ ከሻወር ቤት በመውጣት ውስጥ ለውስጥ በተቆፈረና 50 በ 50 ሴንቲ ሜትር መግቢያ ባለው ዋሻ በመጠቀም፣ አንድ ማይል ወይም 1.5 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዞ እንዳመለጠ አሳይተዋል፡፡ ዋሻውም ውስጡ መብራት እንዲሁም ቬንትሌሽን ያለው ሲሆን የሞተር ቢስክሌትም ተገኝቷል፡፡

አሜሪካ በዕፅ ማዘዋወርና ግድያ በማቀነባበር ወንጀል ከሜክሲኮ ተላልፎ እንዲሰጣት ስትወተውት የከረመች ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ ጊዜ ጉዳዩ ሜክሲኮ ፍርድ ቤት ቀርቦ ውድቅ ተደርጓል፡፡ የሜክሲኮ ባለሥልጣናትም ጉዝማን ዳግም ከእስር አያመልጥም በማለት አሳውቀው ነበር፡፡ ሆኖም ጉዝማን ምናልባትም ዳግም በቁጥጥር ሥር ለማድረግ በሚያስቸግር ሁኔታ ከሜክሲኮ የደኅንነት አካላት እጅ አፈትልኳል፡፡ ለዚህም  በእስር ቤት ቆይታው በነበረበት ወቅት ከውጭ የነበሩ የንግድ አጋሮቹ የማምለጫውን መንገድ ሲያመቻቹ ከርመዋል ተብሏል፡፡

አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው፣ የአሜሪካ የደኅንነት አካላት ጉዝማንን ከእስር ቤት ለማስመለጥ መረብ እየተዘረጋ መሆኑን ደርሰውበት ነበር፡፡ ከ16 ወራት በፊትም ከእስር ቤቱ ሊያስመልጡ የሚችሉ ብዙ ዕቅዶች መነደፋቸውን አሳውቀዋል፡፡

የአሜሪካ ድራግ ኢንፎርስመንት አድሚንስትሬሽን፣ ጉዝማን  ዳግም ከታሰረበት እ.ኤ.አ. ከ2014 ጥር ጀምሮ ቤተሰቦቹና በዕፅ ንግድ ውስጥ ያሉት ነጋዴዎች ለማስመለጥ ጠንካራ መረብ ሲዘረጉ ከርመዋል፣ ይህንንም አሜሪካ ታውቅ ነበር ይላል፡፡

የሜክሲኮ ባለሥልጣናት ግን ከአሜሪካ የደረሰን የማስጠንቀቂያ ደወል አልነበረም ሲሉ አሜሪካን ኮንነዋል፡፡ አሶሼትድ ፕሬስ የአሜሪካ መርማሪ ቡድንን ጠቅሶ፣ የሜክሲኮ ባለሥልጣናት መረጃው ነበራቸው ብሏል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1990ዎቹ ጀምሮ የተስፋፋውና ለመቆጣጠር አዳጋች የሆነው ጠንካራው የሲናሎአ የአደንዛዥ ዕፅ ሰንሰለት በሜክሲኮ ድንበር አድርጎ አሜሪካ የሚደርስ የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ ዘመናዊ ዋሻ በመሥራት ይታወቃል፡፡ የዚህ መሪ የሆነው ጉዝማን፣ እ.ኤ.አ. በ1993 እስር ቤት ቢገባም በ2001 ነበር ከእስር ቤት ያመለጠው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ጥር ላይ ዳግም በቁጥጥር ሥር ቢውልም፣ ውስጥ ለውስጥ ዘመናዊ ተደርጎ በተሠራው አዲስ ዋሻ ማምለጥ ችሏል፡፡ ዋሻው የተሰሠራው ከሜክሲኮ ባለሥልጣናት ዕውቅና ውጪ ነበር፡፡ የአገሪቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ‹‹የዋሻው አሠራር ዘመናዊነት ሲታይ ጉዝማን እስር ቤት እንደገባ የተጀመረ ለመሆኑ ያመላክታል፤›› ብለዋል፡፡

ጉዝማን ከእስር ቤት ካመለጠ ጀምሮ በሜክሲኮ በሚገኙ የመንገድ መቆጣጠሪያዎች፣ የድንበር አካባቢዎች እንዲሁም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች አካባቢ አሰሳ ቢደረግም ማግኘት አልተቻለም፡፡ ዱካው የገባበትም ጠፍቷል፡፡ የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጆሽ ኧርነስት፣ የአሜሪካ መንግሥት ሜክሲኮ ጉዝማንን ለመያዝ ለምታደርገው ጥረት ሙሉ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ጉዝማን በአሜሪካም የሚፈለግ ከባድ ወንጀለኛ ነው ብለዋል፡፡

ጠበቃውን ወይም የእስር ቤቱን ኃላፊዎች በገንዘብ በመያዝና መረጃ በማለዋወጥ የማምለጫ መንገዱን አመቻችቷል ተብሎ የሚጠረጠረው ጉዝማን፣ የዕፅ ንግዱ ሰንሰለት በእርሱ መታሰር አልተቀጨም ነበር፡፡ ልጁና የእሱ ቀኝ እጅ በሆኑ ሰዎች እየተመራ ነበር፡፡ ይህ የዕፅ ንግድ መረብ ሳይረግብ ዳግም ዋናው መሪ ከእስር አምልጧል፡፡ ይህንን ተከትሎ የሜክሲኮ መንግሥት ጉዝማን ያለበትን ለጠቆመ 3.8 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ የሜክሲኮ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርም፣ የእስር ቤቱን ዳይሬክተርና ሌሎች ሠራተኞች ከኃላፊነት ማንሳታቸውንና ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጉዝማን ያለበትን የሚጠቁም ፈጽሞ ማግኘት እንደማይቻል ግን ይገመታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በገንዘብና በወንጀል የተጠላለፈውን የጉዝማን ሲናሎአ መረብ ማጋለጥ ለሞት ስለሚዳርግ ነው፡፡

ከአሜሪካ በሜክሲኮ ድንበር እንደ ቅዥት ብቅ ብሎ የሚሰወረውን ጉዝማንና የንግድ መረብ ማግኘት ቀላል አይሆንም፡፡ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት ኮኬይን፣ ማሪዋና  እና ሔሮይን ወደ አሜሪካና ሌሎች አገሮች በሕገወጥ መንገድ በማስገባት በዓለም ግዛቱን ዘርግቷል፡፡ ይህ ግለሰብ በሜክሲኮ የደኅንነት አካላት እ.ኤ.አ. በ2014 በቁጥጥር ሥር ሲውል፣ አሜሪካ ተላልፎ ይሰጠኝ ብላ ነበር፡፡ ሆኖም አልተሳካም፡፡ አሁን ደግሞ አሜሪካ ‹‹የፈራሁት ያስጠነቀቅኩት ደረሰ፣ ተላልፎ ተሰጥቶኝ ቢሆን ኖሮ አያመልጥም ነበር፤›› ስትል ተናግራለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...