Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርቅንጅትና ቁጥጥር የሌላቸው አሠራሮች ሊቀጥሉ አይገባም!

ቅንጅትና ቁጥጥር የሌላቸው አሠራሮች ሊቀጥሉ አይገባም!

ቀን:

በደነቀ ፀጋዬ አባይሬ

የአገራችንን ልማታዊ እንቅስቃሴ እንደ አንድ ዜጋ ሆኜ ስመለከትው በየትኛውም ዓይነት ፖሊሲ ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ነገር የለኝም፡፡ በፖሊሲ አፈጻጸም ላይ ግን ትንሽ የማይባል ቅሬታ ሊኖረኝ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚለውን ጉዳይ ብንመለከት በዚህ ፖሊሲ ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞ የለኝም፡፡ ይልቁንም ድጋፍና አዎንታዊ አመለካከት አለኝ፡፡ ምክንያቱም አገርና ሕዝብ ሊለወጥ ካስፈለገ የግድ «ሥራና ሠራተኛ» የሚባሉት በአግባቡ መገናኘት ስላለባቸው ማለት ነው፡፡  የሥራ ዕድል ፈጠራው ጥቅም ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ለዜጎች ህልውና በእጅጉ አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡ የሰው ልጅ «ዳቦ» የሚባለው ጉዳይ በእጅጉ ያስፈልገዋል፡፡ ከዳቦም በዘለለ ተጨማሪ የሆኑ ግብዓቶችም እንደሚያስፈልጉት በእጅጉ የታመነ ነው፡፡ እነዚህን ግብዓቶች ለማሟላት ደግሞ «ሥራ» የሚባለው የግድ ሊፈጠር ይገባል ማለት ነው፡፡ በዚህ ነባራዊ ዕውነታ ላይ ሁሉም ወገን እንደኔው ሆኖ ያለምንም ልዩነት ይስማማል ብዬ እገምታለሁ፡፡ «የሥራ ዕድል ፈጠራ» የሚባለው በእጅጉ ሊበረታታ ይገባል፡፡ ግን ይህ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ በርካታ ተግዳሮቶችም አብረውት ብቅ ብቅ ሲሉ ማየት በእጅጉ የተለመደ ነው፡፡ በሁለት ጎኑ ማለት ነው፡፡

የመጀመሪያው ጎኑ በራሱ የሥራ ዕድሉን በፈጠረው ወገን በኩል ማለት ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሥራ ዕድሉ በተፈጠረለት ወገን በኩል ማለት ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ዘርዘር አድርጎ ማየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ላይ ያለውን የሥራ ዕድል ፈጠራ ብቻ በአግባቡ እንመልከት፡፡ በግንባታው ጥራትና በግንባታው ፍጥነት ዙሪያ ላይ ያለውን ችግር ብንመለከት ለሚፈጠሩት ችግሮች ተጠያቂው መንግሥት ሳይሆን፣ የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ወገን ነው በማለት መግለጽ ይቻላል፡፡ ይህን ነባራዊ ችግር ተቆጣጥሮ በአግባቡ ማስተካከልና ማስቀጠል፣ እንዲሁም ሌሎች አስተዳደራዊ ችግሮችን በመፍታቱ ዙሪያ ያሉትን ተግባራት በማከናወኑ ላይ ያለው ተግዳሮት ደግሞ በመንግሥትና በመንግሥት ሥራ አስፈጻሚዎች (በከተማ አስተዳደር) በኩል ሊገለጽ የሚችል ችግር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ለማንሳት የምፈልገው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህ ዓይነቱ ችግር በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ላይ ተደጋግሞ የሚታይ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህ ችግር በአግባቡ ሊታረም ያለመቻሉን ለማሳየትና መፍትሔ እንዲበጅለትም ለማሳሰብ ነው፡፡

መንግሥት በርካታ አገራዊ ፕሮጀክቶችን ሲቀይስ ይስተዋላል፡፡ ለማስፈጸም ደግሞ መጠነ ሰፊ የሆነ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ይታያል፡፡ በእነዚህ በርካታ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ደግሞ ተደጋጋሚ የሆኑ ተግዳሮቶች ሲያጋጥሙ ማየት በእጅጉ የተለመደ ነው፡፡ ከአቅም በላይ ሊሆኑ የማይችሉ ግን ደግሞ የአገርን ኢኮኖሚ ያለበቂ ምክንያት የሚያባክኑ ችግሮች አሉ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ መንግሥት በዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉት በተደጋጋሚ ጊዜ የተለያዩ ምክንያቶችንና መልሶችን ሲሰጥበት ቆይቷል፡፡ መንግሥት ለነዚህ ተግዳሮቶች ችግር ፈቺ የሆነ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ይህንን ነባራዊ ዕውነታ ተጨባጭ በሆነ ምሳሌ ላይ ተመሥርቶ ማሳየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከሦስትና ከአራት ዓመታት በፊት የባቡር መስመር ዝርጋታ ከመጀመሩ በፊት ከመስቀል አደባባይ ወደ ቃሊቲ ወይም ወደ ሳሪስ አቅጣጫ በሚወስደው አስፋልት መንገድ መሀል ለመሀል ላይ ክፍት የሆነ ሥፍራ ይገኝ ነበር፡፡ (ዛሬ የባቡር ሐዲድ የተዘረጋበት ቦታ ማለት ነው) ይህ ሥፍራ የወደፊት ማስፋፊያ ሊሆን እንደሚችል ነጋሪ ሰው አያስፈልግም ነበር፡፡ ልክ ወደ አያት አቅጣጫ በሚወስደው አስፋልት መንገድ መሀል ለመሀል ላይ እንዳለው ክፍት ሥፍራ ማለት ነው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ክፍት የነበረው ሥፍራ (ወደ ሳሪስ የሚወስደው ማለቴ ነው) በወቅቱ አስፋልት መንገድ ነበር፡፡ አስፋልት ከሆነ በኋላ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ የባቡር ፕሮጀክቱ ሥራ ሊጀመር ነው ተባለና ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ሲቀርቡ ነበር፡፡ በርካታ መልሶችም ተሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ ዓይነቱ ችግር አይፈጠርምም ተብሎ ይገመት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ ሲደጋገም በግልጽ ይታያል፡፡ ይህ አንድ ነባራዊ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእግረኛውን መንገድ ጉዳይ ልብ ብለን እንመልከት፡፡ ይህም ጉዳይ በእጅጉ የከፋ ነው በማለት መግለጽ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል የቅርቡን ጊዜ ተወት ላድርገውና ራቅ ያለውን በዘመነ ከንቲባ አርከበ ዕቁባይ ጊዜ ያስተዋልኩትን ጭብጥ ነገር እንደ መነሻ አድርጌ ላንሳው፡፡ በዚህ ወቅት በአንድ የመንገድ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ መንገዱ “የወሎ ሠፈር” የሚባለው ነው፡፡ (ከጎተራ ተነስቶ ቦሌ ዋናው መንገድ ላይ የሚገጥመው ማለት ነው)

ይህ መንገድ በተከበሩ ከንቲባ አርከበ ዕቁባይ በዕለተ ቅዳሜ በደመቀ ሥነ ሥርዓት እንደተመረቀ ትዝ ይለኛል፡፡ በምረቃው ዕለት በመንገዱ ግራና ቀኝ ጠርዝ ላይ ተሠርቶ የነበረውን የእግረኛ መንገድ በቀይና በብጫ ሸክላ አጊጦ ይታይ ነበር፡፡ ይህንን የሸክላ ንጣፍ በአግባቡ የተመለከተ ቢኖር ከአካባቢው ነዋሪዎች በበለጠ ይደሰታል ማለት ይቻላል፡፡ ለከተማው አዲስ ውበትና የተለየ ገጽታም ፈጥሮ ነበር፡፡ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ታድመው የነበሩ በሙሉ በእጅጉ የተደሰቱበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ልክ በ15ኛው ቀን በዕለተ ቅዳሜ ጓደኛዬን የዚህን የከተማ ውበትና ገጽታ ላሳየው ፈልጌ ወደ ሥፍራው እንሂድ ብዬ ጋብዤው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሥፍራው ላይ ስንደርስ ያ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ዕለት አበባ መስሎ ደምቆ ይታይ የነበረው ቀይና ብጫ ሸክላ (የእግረኛ መንገድ) ያልጠበቅኩት ነገር ሆኖ አጋጠመኝ፡፡ ያ! ውበት ፈሶበት በዓይኔ በብረቱ የተመለከትኩት የከተማችን የእግረኛ መንገድ በሁለቱም አቅጣጫ እጅግ በጣም በሚያስደነግጥ ሁኔታ ምንግልግሉ ወጥቶ ታየ፡፡ በእጅጉ ደነገጥኩ፡፡ የምናገረውን  አጣሁ፡፡ ቀጠል አደረግኩና ይህ ለምን እንዲህ ሆነ አልኩና አንዱን እዚያው አካባቢ በሥራ ላይ የነበረን ሰው ለመጠየቅ ሞከርኩ፡፡ «. . . ሳይሠራ ቀርቶ እሱን ለማስተካከል ነው፤» በማለት መለሰልኝ፡፡ በእጅጉ አዘንኩ፡፡ «ቅንጅት» በሚባለው ጉዳይ በጣም አዘንኩ፡፡ ግን ደግሞ ለወደፊት ትልቅ ትምህርት ሰጥቶ ያልፋል በሚለው ለመፅናናት ሞከርኩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ትምህርት ሳይወሰድበት ቀረ፡፡ ለረጅም ጊዜያት የከተማችን ችግር እንደሆነም ሊቀጥል ቻለ፡፡ አሁንም እንዳለ ቀጥሏል፡፡

አሁን በዚህ በባለፈው ወራት ይኸው ነባር ችግር ከመስቀል አደባባይ እስከ ጎተራ ባለው ቀይና ብጫ ሸክላ የእግረኛ መንገድ ላይ በተመሳሳይ ቀጥሎ ታይቷል፡፡ ችግሩ በዚህ ላይ ብቻ አላቆመም፡፡ በሌላውም በሌላውም ጉዳይ ላይ ይታያል፡፡ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ነዋሪው ሕዝብ በከፍተኛ ተሳትፎ ገንዘብ አዋጥቶ የተሠራው የኮብልስቶን መንገድም ዕጣ ፈንታው እየደረሰው ነው፡፡ ችግሩ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ይህ ነባራዊ ችግር አብዛኛውን ነዋሪ በእጅጉ ግራ እያጋባ ነው፡፡ እያንዳንዱ ነዋሪ በኮብልስቶኑ መንገድ መሠራት በእጅጉ ሲደሰት ነበር፡፡ የኮብልስቶኑ መንገድ አንድ ዓመት ሳይሞላው ደግሞ ሌላ አዲስ ዕቅድ መጣ ተብሎ መሀል ለመሀል በአንድ ሜትር ከሃምሳ ሴንቲ ሜትር ጥልቀት መቆፈር ተጀምሯል፡፡ የኮብልስቶኑ መንገድ በሙሉ አፈር በአፈር እየሆነ ነው፡፡ ስለጉዳዩ ቢጠየቅ የትኛውም ወገን ሊያስረዳ አይችልም፡፡ ወረዳው የሚያውቀው የለም፡፡ የልማት ኮሚቴው የሚያውቀው የለም፡፡ ነዋሪው የሚያውቀው የለም፡፡ ችግሩ ግን በነዋሪው ላይ ጎልቶ እያታየ ነው፡፡ ችግሩ መቆፈሩ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የየአካባቢው ነዋሪ ስለጉዳዩ አስቀድሞ እንዲረዳውና እንዲያውቀው ያለመደረጉ ጉዳይም በዋናነት ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ ይህ አለመደረጉ ትልቅ ስህተት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ወቅት የሚባለው ነገር ጨርሶ ግምት ውስጥ አለመግባቱ ነው፡፡ ወቅቱ ክረምት መሆኑ ግምት ውስጥ አልገባም፡፡ አፈርና ክረምት በምንም ዓይነት ሁኔታ ሊጣጣሙ አይችሉም፡፡ አፈሩ ተጠርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ አከባቢው በሙሉ ጭቃ በጭቃ ሊሆን የግድ ነው፡፡ መንገድ ተሠርቷል፣ አካባቢያችን ለምቷል በተባለበት ሁኔታ ነዋሪው ኅብረተሰብ ተመልሶ ጭቃ በጭቃ የሚሆንበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ ይህ በአግባቡ ያልታየ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ ዋነኛው ችግር ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም እየተሠራ ያለው ሥራ «በአግባቡ ተጠንቷል ወይ?» የሚለው ነው፡፡ ኮብልስቶኑ ከመነጠፉ በፊት ለምን አልተሠራም? ለሚለውም ተገቢ ጥያቄ ትክክለኛ የሆነ ምላሽ አልተገኘም፡፡ ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ አሁንም በአግባቡ ሊታይ የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ አለ፡፡ አሁን እየተቆፈረና እየተቀበረ ያለው የፕላስቲክ ቱቦ (ፒቪሲ) ቀበራ በቀጣዩ ጊዜ በተለይ ለልማት ተነሺ ሊሆኑ በሚችሉ አካባቢዎች ላይ እንዴት ታስቧል? የሚለው ዋነኛ ጥያቄ ነው፡፡ ይህ አሁንም በአግባቡ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡

ለምሳሌ ያህል አሁን በኮብልስቶኑ መንገድ መሀል ለመሀል እየተቀበረ ያለው የመፋሰሻ ፒቪሲ (ፕላስቲክ ቱቦ) ስፋቱ በአግባቡ ያልታየ ይመስላል፡፡ ለመሆኑ ወደፊት አካባቢው በመልሶ ማልማት ተነሺ በሚሆንበትና በዘመናዊ ሕንፃዎች (ኮንዶሚኒየም) ሲቀየር፣ የሚወጣውን ፍሳሽ በአግባቡ ሊያስታናግድ ይችላል ወይ? ይህ ጉዳይ በአግባቡ ሊጤን ይገባዋል፡፡ አሁን ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት በመቀበር ላይ ያለው ቱቦ በመልሶ ማልማቱ ወቅት ሊፈጠር የሚችለውን ፍሳሽ ማስተናግድ መቻል አለበት፡፡ በመልሶ ማልማቱ ወቅት ሊፈጠር የሚችለውን ፍሳሽ በአግባቡ ማስተናገድ ካልቻለ ትርፉ ኪሳራ ይሆናል፡፡ ዘላቂ የሆነ ሥራ ሊከናወን ይገባል፡፡ በአጠቃላይ በከተማ ልማቱ ተግባር  የቅንጅትና የቁጥጥር ሥርዓት ሊፈጠር ይገባል፡፡ የከተማችን በጀት ያለ አግባብ ሊፈስ አይገባውም፡፡ ወጪ ቆጣቢ የሆነ ቅንጅትና ቁጥጥር ሊፈጠር ይገባል፡፡ የከተማችን መስተዳድር ይህንን ችግር በአግባቡ ሊፈትሸው ይገባዋል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP) አፈጻጸም ዘመን ላይ በተለይም ደግሞ ከ2008 የበጀት ዘመን ክንውን ጀምሮ ዕውን ሊሆን ይገባዋል፡፡ የምንሠራው ሥራ ችግር ፈቺና ዘላቂ መሆን አለበት፡፡ «ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ» መሆን አይገባውም፡፡ «አሥር ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ» የሚለው ሙያዊ አባባልም በሥራ ላይ ሊውል ይገባል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአግባቡ ሊታይ የሚገባው «በጀት» የሚባለው ጉዳይ «ግብር» ከሚባለው ጋር በእጅጉ ተያያዥ ስለመሆኑ ነው፡፡ ለበጀት የሚሆነውን ግብር (ገንዘብ) ለመሰብሰብ ያለውን ጣጣና ውጣ ውረድን በአግባቡ ማስተዋል ይገባል፡፡ በስንት መከራና ችግር የተሰበሰበውን ገንዘብ ባልተጠናና ዘላቂ ባልሆነ ሥራ ላይ (ነገ ሊፈርስ በሚችል ግንባታ ላይ) ልናውል አይገባም፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር (ስህተት) ከሥር መሠረቱ ሊቀረፍ ይገባል፡፡ ከትናንት ስህተት ላይ ተነስተን ብዙ ትምህርት ልንወስድና ጥንቃቄ ልናደርግም ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ «ዘላቂ የሆነ ሥራ ሊታሰብና ሊሠራ ይገባል» የሚለው ነባራዊ ጉዳይ በአግባቡ ሊጤን ይገባዋል፡፡ ዛሬ ተሠርቶ ነገ ከነገ ወዲያ መፍረስ የለበትም፡፡ የአገር ገንዘብና ኢኮኖሚ ያላግባብ መጥፋት የለበትም፡፡ ይህን ጉዳይ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ተመሥርቼ ለመግለጽ ሞከርኩ እንጂ፣ ችግሩ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ላይ ብቻ እንዳልሆነም ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ይልቁንም «በሁሉም ዘርፎች ላይ ያለ ተግዳሮት ነው» በማለት መግለጽ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል የመንገድ ዳር አትክልቶችን ተከላና እንክብካቤውን ብቻ ልብ ብለን ብንመለከት፣ ይህም እንደ ኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ተመሳሳይ የሆነ ችግር ያለበት ነው፡፡ እነዚህና የመሳሰሉት ዘርፎች በሙሉ ቅንጅትና ቁጥጥር የሌላቸው አሠራሮች ሆነው ሊቀጥሉ አይገባም፡፡ ስለሆነም የከተማችን አስተዳደር በአዲሱ የበጀት ዘመን ከሥር መሠረታቸው ሊቀርፋቸው ይገባቸዋል እላለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...