Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየአዲስ አበባ ከተማ አመራር ማጠቃለያ ግምገማ የይስሙላ እንዳይሆን

የአዲስ አበባ ከተማ አመራር ማጠቃለያ ግምገማ የይስሙላ እንዳይሆን

ቀን:

በደንድር ተመስገን ተክሉ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዘንድሮ እንደተለመደው የ2007 በጀት ዓመት አጠናቋል፡፡ በቅርቡም በከተማ ደረጃ ከፍተኛ አመራሩ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ግምገማውን ከሐምሌ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በፊት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የከተማ አመራር አባላት የያዙት ሥልጣን ምንጩ በሕዝብ መመረጣቸው መሆኑን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም እንዳለባቸው ግንዛቤ የላቸውም ማለት አይቻልም፡፡

ለከተማው ከፍተኛ አመራር የተስተካከለ የሕዝብ አገልጋይነት አመለካከትና የአመራር ክህሎት እንደሚያስፈልግ ማንም አይስተውም፡፡ ከዚህ አንፃር የከተማው ከፍተኛ አመራር የሥልጣን ምንጭ በሕግ የሚሰጥ ቢሆንም፣ ከዚህ በተጨማሪ ከተቋም ሕጋዊ ሥልጣን የሚመነጭ፣ የመልካም ሰብዕና ከፍተኛ አመራሩ ወይም ተቋሙ በሌሎች ዘንድ ባለው እምነት በገነባው ተቀባይነት የሚመነጭ፣ የልዩ ፈጠራ አንድ ተግባርን ለመፈጸም ካለ የሀብት አጠቃቀምና የተለያዩ የሥልጣን ምንጮችን የማቀናጀት ችሎታ የሚመነጭ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ውጤታማ መሪዎች ዜጎች እንዲሳተፉና ለማኅበረሰቡ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ለሕዝባቸው ከለላ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ኅብረተሰቡ የራሱን ችግር በራሱ እንዲፈታ አቅም ይፈጥራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የከተማችን ከፍተኛ አመራሮች የተሰጣቸው የአመራር ሥልጠና ምን ያህል ክፍተታቸውን ሞልቷል የሚለውን የከተማው አስተዳደር ጥናት ማድረግ የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ በዘንድሮ ግምገማ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በከተማው ለተመዘገቡ ውጤታማ የልማት ተግባራት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ ግልጽ ነው፡፡

ነገር ግን በከተማችን ከውጤታማ ተግባራት ጎን ያገጠጡ ተግዳሮቶችና የታዩ  ድክመቶች ተሸፍነው ማለፍ የለባቸውም፡፡ ችግሩ ግን በሚዲያ የሚቀርብን አስተያየት ቀንጭበው የሚያቀርቡት ቁጥራቸው የተወሰኑ የሚዲያ ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ እነሱም የሚያቀርቡት ስለከተማው አስተዳደር የተጻፉ የውዳሴ ጽሑፎችን በአጭሩ በማሳጠር እንደ መሰላቸው ርዕስ በመምረጥ ነው፡፡ ስለከተማው የተጻፉ አስፈላጊ አስተያየቶችና ጥቆማዎች መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ስለሚጠቅሙ፣ አመራሩ በትርፍ ጊዜው ስለከተማው የተጻፉ ጽሑፎችን ማንበብ ልምድ ሊያደርግ ይገባል፡፡

በመሆኑም ከያዝነው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በሚደረጉ የግምገማ መድረኮች፣ አስተዳደሩ ባለፈው የበጀት ዓመት ያከናወናቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ጥንካሬና ድክመት ይገመግማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይሁንና ይህ ግምገማ ጥሩ ሠርተናል በማለት በጅምላ ከመሞጋገስ ብስሉን ከጥሬው እንዲለይ ተደርጎ ችግር ፈቺ እንዲሆን ተደርጎ መታቀድ አለበት፡፡

በዚህ አግባብ እኔም እንደ ዜጋ በ2007 የበጀት ዓመት በተለይ ከፍተኛ አመራር ላይ ያሉት የሚጠበቅባቸውን ውሳኔ ከመስጠታቸው በፊት፣ የችግሮችን ምንጭና መነሻዎች በመለየትና በመተንተን አማራጭ መፍትሔዎችንም ከማስቀመጥ አንፃር፣ የነበራቸው አፈጻጸም ጥንካሬና ድክመት መፈተሽ ይገባቸዋል የሚል አስተያየት አቀርባለሁ፡፡ በተጨማሪም የከተማው ከፍተኛ አመራር አባላት የከተማው ፖሊሲ አውጪ አካላት እንደመሆናቸው መጠን፣ ከዚህ አንፃር የነበራቸው ጥንካሬና ድክመት መፈተሽ ይገባቸዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ለየሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተመደበ ውሱን የመንግሥት በጀት አጠቃቀማቸው ውጤታማ፣ ሀብት ቆጣቢና ሕጋዊ የአፈጻጸም ውጤት ለማረጋገጥ የተለያዩ የቁጥጥር ሥልቶችን መተግበራቸውን መረጋገጥ ይገባዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሰፊ ችግር ያለባቸው የሥራ ኃላፊዎችን አመራሩ በሥራ ግምገማው መለየት ይገባዋል፡፡ ለዚህም የከተማው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ቢሮው እንደተለመደው በዓመት አንድ ቀን ለከፍተኛ አመራሩ ስለበጀት አጠቃቀም ሥልጠና መስጠት ብቻ አይበቃም፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት (Transparency and Accountability) በከተማው የግልጽነትና የተጠያቂነት ሥርዓት ካልተዘረጋ፣ ሙሰኝነትና መሰል ድርጊቶች መኖራቸው አይቀርም፡፡ የሙስና ተግባር የከፋና ተቋማዊ የሚሆነው በኅብረተሰብና በድርጅት ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ግለሰብ በዝምታ ለተግባሩ ዕውቅና ሲሰጥ ብቻ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ከዚህ አንፃር ከፍተኛ አመራሩ ለመካከለኛና ለዝቅተኛ አመራሩ አርዓያ መሆን ሲገባው፣ ባሳለፍነው በጀት ዓመት በግንቦትና በሰኔ ወር ውድ የሆኑ የቢሮ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የመንግሥት በጀት ተመላሽ እንዳይሆን ተደርጓል፡፡ ከፍላጎት በላይ ዕቃዎችን በሩጫ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ተሯሩጠው የገዙ፣ ለቢሮ ኪራይ ከተመደበላቸው በጀት በላይ ተጨማሪ በጀት በማዘዋወር አዲስ ቢሮ የተከራዩና ለተከራዩት ቢሮ በአንድ በካሬ ሜትር የቀረበን ዋጋ ብቻ በማየት በቀረበው ውል ብቻ ትክክለኛ ስፋቱን ሳያረጋግጥ በጀት መፍቀዱ የቢሮው ችግር ነበር፡፡

ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ምሽት በአዲስ ቲቪ ከከተማው ሁለት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ፣ ጋዜጠኛው ለምንድነው የከተማው አስተዳደር ቢሮዎች በኪራይ የመንግሥት በጀት እንዲያወጡ የሚደረገው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ተቸግረው ታይተዋል፡፡ በከተማ ደረጃ ያሉትን ቢሮዎች ብቻ እንኳን ብናይ በኪራይ የሚጠቀሙ ቢሮዎች በጠቅላላ የሚከፈለው በትክክል የሚጠቀሙበትንና ከሕንፃው ስፋት ጋር የሚጣጣም ስለመሆኑ ሳያረጋግጥ በጀት ዝውውሩን መፍቀዱ፣ ከሕንፃ አከራዮች ጋር የተወሰኑ አመራሮች ተገቢ ያልሆነ የጥቅም ድርድር እንዲፈጥሩ በር ከፍቷልና በአግባቡ ሊታይ ይገባል፡፡

ይህ ያገጠጠ ችግር በተወሰኑ በከተማ ደረጃ ባሉ ቢሮዎች የተስተዋለ ቢሆንም፣ ነገ ወደ ክፍለ ከተማና ወረዳ ጽሕፈት ቤቶች ላለመቀጠሉ ምንም ዋስትና የለም፡፡ በ2004 ዓ.ም. የከተማው ስፖርት ኮሚሽን በኪራይ ይገለገል የነበረበትን ሕንፃ ኪራይ ችግር አለበት ለሚለው ጥቆማ በወቅቱ የነበረው አስተዳደር ለማጣራት የወሰደው ዕርምጃ የሚያስመሰግነው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዕርምጃ አሁምን ችላ ሊባል አይገባውም እላለሁ፡፡

ከዚህ ሌላ በበጀት ያልተደገፈና ያልተፈቀደ የውጭ አገር ጉዞን በተመለከተ በከተማው ለሚገኙ አንድ ከፍተኛ ኃላፊ በ2006 በጀት ዓመት ዘጠና ሺሕ ብር ለውጭ ጉዞ ተከፍሎ፣ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ሒሳቡን ካላወራረድክ ተብሎ ከፍተኛ ንትርክ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ችግር ባለመታረሙ ዘንድሮም ይህ ባልተፈቀደ የውጭ ጉዞ የመንግሥት በጀትን በማውጣት ለራሳቸው ከፍተኛ ውሎ አበል ከመንግሥት ካዝና ወስደው ሒሳብ እንዲወራረድ ያደረጉ ጽሕፈት ቤቶች፣ የተፈቀደ የሒሳብ መደብ ሳይኖር ሒሳብ እንዴት አወራረዱ አለማለቱ የቢሮው ችግር ነበር፡፡ በበጀት ርዕስ 6417 ለግለሰብ የሚሰጥ ድጋፍ ለማን እንዴት ተሰጠ የማይባልበት፣ ሕጋዊ ደረሰኝ የማይቀርብበት በመሆኑ ቢሮው ክትትል ሊያደርግ ይገባዋል፡፡

የከተማው ከፍተኛ አመራሮችና  የመንግሥት ኃላፊዎች የሚወስኑት ውሳኔ በሕዝብ ላይ አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ በመንግሥት ቢሮዎች የሚሾሙ ኃላፊዎች ለመምረጥ የወንዶች የበላይነት  (ተፅዕኖ)  የነገሠበት ሁኔታ በከተማችን ከፍተኛ አመራር ዘንድ ይታያል፡፡ ከዚህ አግባብ ሹመት አሰጣጣችንስ እንዴት  ነበር ብሎ አስተዳደሩ ራሱን በድፍረት መፈተሸ አለበት፡፡

ከፍተኛ አመራሩ ቁልፍ ሥራ በአግባቡ አከናውኛለሁ በማለት ተቋማዊ ግንባታ ማለትም ዕውቅና በተሰጣቸው የመልካም አስተዳደር መርሆዎችና ስትራቴጅዎች ላይ ተመሥርቶ፣ ሴክተሩ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እያንዳንዱ ከፍተኛ አመራር ዘላቂነት ያለውን አመራር ስለመስጠቱ በአግባቡ መፈተሸ ይገባዋል ፡፡

በሌላ በኩል ለተገልጋይ ተገቢ የሆነ ውሳኔ በወቅቱ ያለመስጠት ችግር በብዙ  አመራሮች ዘንድ ይስተዋላል፡፡ በመርህ የተመሠረተ ውሳኔ መስጠትን ባለመፈለግ ባለጉዳይ እንዲጉላላ ያደረገ አመራር ሊጠየቅ ይገባዋል፡፡ የከተማው ከፍተኛ አመራሮች በየደረጃው ላለው አመራር ድጋፍና ክትትል ማድረግ የሚጠበቅባቸው በመሆኑ፣ ብቃትን በመጠቀም ንቅናቄ በመፍጠር ተግባራቸውን ስለማከናወናቸው፣ በዚህ አግባብም  የታሪክ አሻራቸውን (ሌጋሲያቸውን) በአግባቡ ስለመወጣታቸው መፈተሸ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር እያንዳንዱ አመራር በተለመደው ሁኔታ ብቃት ያለው ክትትልና ድጋፍ አላደረግኩም በሚል የተለመደ የማያስቀጣ ግለሂስ እያደረገ ሌላውን ችግር እንደ ችግር ሳያይ፣ ለሁሉም “A” እና “B” ደረጃ እየተሰጠ የይስሙላ ግምገማን ለማጠናቀቅ ሳምንት የሚፈጅ ግምገማ ማድረግ የለበትም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]   ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...