Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንንቦጫረቅ?

እነሆ ከአራት ኪሎ ወደ ቦሌ ድልድይ እየተጓዝን ነው። ድጥ ዘለልን ስንል ማጥ መጥለቅ ሆኖ ሥራችን፣ ተነግሮ በማያልቅ ወኔና ተስፋ ስንጓዝ ሳለን እነ ሐምሳ እግር፣ እነ ኤሊ ሪከርድ እየሰበሩ ያስቸገሩበት ጎዳና ላይ ነን። ከየማዕዘናቱ እንደ አሸን የሚፈላው ሥጋ ለባሽ የዕለት ጉርሱንና የወር ቀለቡን ለመስፈር ዶፍ መሀል ይሮጣል። አስፋልቱ ገላውን ታጥቦ እጣቢውን ተራማጁ እያንቦጫረቀ ይጓዛል። ዕድፍ ለዕድፍ ስንተሻሽ ዘመን ህልማችንን እንደ ምስጥ ቀስ በቀስ አኝኮ ሳይጨርሰው መቅረቱን እንጃ። “ቦሌ ነው?” ከጉልበቱ በታች በውኃ የራሰ ተሳፋሪ ወያላውን ጠየቀ። ታክሲያችን ቆመችለት። ገባና ጉዟችንን ቀጠልን። ተጀመረ እንግዲህ!

“አዬዬ! ሐምሌ እንደ ልማዱ እንደ አልቃሻ ልጅ ዓይኑን አጨንቁሮ ሲያላዝንብን መዋል ሊጀምር ነው፤” አለ ከመግባቱ ከሾፌሩ ጀርባ ከአንድ ጎልማሳ አጠገብ እየተቀመጠ። “እኔን ደግሞ እያሳሰበኝ ያለው  በጎርፍ ውስጥ አረማመድ ለማሳመር ሲጥር የማየው ሰው መብዛት ነው። ‘ሰው ብርቱ ነው በጎርፍ ውስጥ አረማመድ ያሳምራል’ ያለው ገጣሚ ለካ ወዶ አይደለም፤” ጎልማሳው ትግ ትጉን ጀመረው። አንዱ የነገር ክንዱን ባያነሳ ካልመከትኩ የሚል ይኖር ነበር? አዲስ የገባው ተሳፋሪ መልሶ፣ “ያለ ዛሬም ጎርፍ ውስጥ አረማመድ ስለሚያሳምሩ ዜጎች ሰምቼ አላውቅም፤” አለው። ጎልማሳው፣ “እም! እኔ ደግሞ ይገርምሃል አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ የሚሆነው ሰው የሚያጋጥመኝ ብዙ ጊዜ ነው። ይኼም ጎርፍ መሀል አረማመድ ከማሳመር ጋር የሚቆጠር ነው፤” አለው። የተቀረነው ተሳፋሪዎች የሁለቱ ነገር ነገር የሚሸት የቃላት ምልልስ አልጣመንም። እናም ከጎልማሳውና ከአዲሱ ተሳፋሪ ጀርባ አጠገቤ የተቀመጡት አዛውንት፣ “ቸር አሰማን ቸር አውለን!” እያሉ አሥር ጊዜ ወደ ሁለቱ ነገረኞች ያያሉ። እያደር የሚብስብን ሥጋትና ሽብር የኑሮ ትግሉን ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ አድርጎብናል። የስንቱን ስሜት አዳምጠን፣ በስንቱ በርግገን፣ በስንቱ ደንግጠን እንዘልቅ ይሆን?

እየተጓዝን ነው። ይህ ዕረፍት የሚሳነው ጎዳና ዕፎይታ የከዳው መንገድ፣ እያንከለከለን ሳናስበው ከተገኘንበት አቅጣጫ አስብን የምንደርስበት ወደ መሰለን መስመር ይወስደናል። ለምሳሌ ሦስተኛው መቀመጫ ላይ የተሰየመ አንድ ለአገሩ እንግዳ የሆነ ባይተዋር ፈረንጅ ከወያላው ጋር ይጨቃጨቃል። “ቦሌ ስል እየሰማ ገብቶ ሚካኤል ይለኛል? አንደኛህን የአገርህን ታክሲ ይዘህ አትመጣም ከመጀመሪያው? ምን ዓይነት ነገር ነው እባካችሁ? ፈረንጅም ደንቁሮ ማደናቆር ያውቃል ለካ!” ይላል ወያላው ተማሮ። “ከቻልክ በተለይ መጨረሻ ላይ ያልካትን ወደ እንግሊዝኛ ተርጉመህ ለራሱ መንገር ነው። አለዚያ ዝም ነው፤” ይላል ሾፌሩ እየሳቀ። “ሰላይ ሊሆን ይችላል አደራ እንዳታስበላን ከአፍህ ምንም አይውጣ፤” መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት ወጣቶች አንዲት ፍልቅልቅ ወያላውን አውቃ ‘ታስቦካው’ ጀመር። “ከተበላንማ ቆየን፤” ጋቢና ያለው ነው ይኼን የሚለው።

“ሰላይ?!” አዛውንቷ ፈረንጁን አፍጥጠው እያዩ ቃሉን ደጋገሙ። ፈረንጁ አጠገቡ ወደተቀመጠችው ተሳፋሪ ዞሮ፣ “what’s going on?” ይላል። ከእንግሊዝኛ ይሁን ከነገር ሽሽት ማንም የሚመልስለት ሰው ጠፋ። ያቺ ነገረኛ ፍልቅልቅ ሆነ ብላ ያስነሳቸው የጥርጣሬ ወሬ በአንዴ ታምኖ ዋና መነጋገሪያ ርዕስ ሆነ። “ምን ይታወቃል ኦባማ አዲስ አበባ ሊመጡ ጥቂት ቀን ነው የቀራቸው። እስኪ የመንገዱንም የሰውንም አካሄድና አጠማዘዝ ቃኘው ብለው ልከውት ይሆናል!” ሲል አንዱ፣ “ታዲያ ሠልፍ በሠልፍ እንደሆንን ለምን አሁኑኑ አንድ ላይ ተባብረን አናስረዳውም? እ? ጎበዝ! በቢሮክራሲና በዴሞክራሲ ሠልፍ፣ በትራንስፖርት እጦት ሠልፍ፣ በመኖሪያ ቤት እጦት ሠልፍ እንዲያው በሁሉ ነገር ሠልፍ ላይ መሆናችንን ከነገርነው ይናገራል፤” ይላል ሌላው። ፈረንጁ አንዴ ወደ ተናጋሪው አንዴ ወደ አድማጩ እያማተረ ተደናግጦ ተቀምጧል። መቼም በገዛ አገራችን ተሳቀን የሰው አገር ሰው ስናሳቅቅ የሚደርስብን ያለ አንመስልም። ወይ እንግዳ ተቀባይነት!

“የለም የለም! ይኼ ሰውዬ በቀጥታ ከኦባማ ቢሮ ተልኮ የመጣ ነው ካላችሁ ማስገንዘብ ያለብን ስለሠልፉ ብዛት አይደለም። ስለመንገዱም አይደለም፤” አለ መጨረሻ ወንበር ከተመቀጡት ተሳፋሪዎች አንደኛው። “እና ታዲያ?” የተመካከሩ ይመስል ተሳፋሪዎች በአንድነት ጠየቁት። “መናገርና ማሳሰብ ያለብን በዓመት የመኖሪያ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለሚያመለክቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች ኮንግረሱ እንዲሰጥ የሚፈቅደው መኖሪያ ፈቃድ ኮታ እንዲጨምር የሚል መሆን አለበት። አለበለዚያ አጉል ቀንድ ነክሰን መግቢያ መውጫ ማጣት ነው፤” ብሎ ሐሳቡን አብራራ። “ሐሳቡ መልካም ይመስላል። ግን የሚጎለው ነገር አለ፤” አለች ከፈረንጁ አጠገብ የተቀመጠችው ተራዋን። “እኮ ምንድነው የሚጎለው? መቼም እኛ የጎደለ እንሙላ በሚል ሰበብ ሐሳብ መበታተንና ኅብረት ማለያየት ይቀናናል፤” አላት ሐሳቡን ያመጣው ወጣት።

“ምን እሱ ብቻ? ሐሳብ መቀበልና ራስን ለማረም መቼ ዝግጁ ሆነንስ እናውቀለን?” ብላ ወጋ አደረገችው  ከጎኑ። “የጎደለው ምን መሰላችሁ? የጉርሻ ገበያ መውጣት ነው፤” ከማለቷ፣ “ምን? ምን ማለቷ ነው?” ብሎ ተሳፋሪው ግራ ተጋብቶ እርስ በርሱ ተገለማመጠ። “እውነቴን ነው በአንድ ጉርሻ 50 ሳንቲም የሚያስከፍሉ አሉ እኮ? አዳሜ በቤት ኪራይና በእህል ውድነት ጉድ ብሎ ሳይጨርስ ጉርሻ ገበያ ወጣና አረፈው፤” ስትል ተሳፋሪዎች ተገርመው “ይኼ ምን አዲስ ነው? እየቀለደች ነው?” ይባባሉ ጀመር። ጋቢና የተቀመጡ ተሳፋሪዎች ደግሞ ተራቸውን በማሽሟጠጥ “ታዲያ ይኼን ማመልከቻችን ውስጥ ከማስገባት ለምን የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚያስገኝበት መንገድ ካለ አናስብም? መቼም መተቸት እንጂ ማሰብ አይቀናንም፤” ተባብለው ሳቁ። ምናችንም ያልጣመው ፈረንጅ ተኮላትፎ “ወራጅ አለ!” አለና ወርዶ ሹልክ አለ። አይገባው አማርኛ አይስማማበት ነገረኛ ሲሆንበት ታዲያ ምን ያድርግ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላችን ሒሳብ እየተቀበለ ነው። ድንገት ታክሲያችን አቅጣጫዋን ቀይራ ወደ አንድ ገባር መንገድ ታጠፈች። ተሳፋሪዎች ተንጫጩ፣ “ወዴት እየወሰድከን ነው? ምንድነው እሱ?” ሾፌሩ ላይ መዓት ለማውረድ ተጣደፉ። ሾፌሩ ሞተር አጠፋና ወርዶ ትንባሆ ለኮሰ። ወያላው፣ “ተረጋጉ እንግዳ ስለሚያልፍ መንገድ ተዘግቶ ነው። የተለመደው እንግዳ ተቀባይነታችሁን ለማሳየት ትጉ፤” አለ እንደ ንጉሥ አፈ ቀላጤ። ወዲያው ሌሎች መኪኖች እየታጠፉ መጥተው ከኋላና ከፊት ተደረደሩ። “ታዲያ ይኼን ስታውቁ አማራጭ መንገድ አትመጡም ነበር? ሆን ብላችሁ ለሱሳችሁ ጊዜ ለማግኘት እንጂ፤” አለ ጎልማሳው። ይኼን ጊዜ አዛውንቷ፣ “ሱስ የሌለበት አለ ብለህ ነው? የሲጋራ ሱስ ባይኖርብህ የወሬ ሱስ ይኖርብሃል። አንዱን ካንዱ በሆነ ባልሆነው የሚያጣምድ ጦር ሳይሰብቅ ድባቅ እንደመታ የሚያስለፍፍ ማለቴ ነው። ደግሞ የወሬ ባይኖርብህ የገንዘብ ሱስ ያለበት አለ። አገር ምድሩን በጠራራ ፀሐይ ‘ሸጉጡልኝና ጉዳያችሁ አሥር ደቂቃ ሳይሞላው ያልቃል’ እያለ የሚያንገላታ። ሁላችንም የምንገኝበት ነገር አናጣም ልጄ!” አሉት።

እዚህ ሱስና ዓይነቶቹ ‘የሜኑ ሊስት’ ሲወጣላቸው ከኋላችን ያቺ የደስ ደስ ያላት ወጣት፣ “ደስ አይልም። እኛ ወደ እነሱ አገር እንደምንጋጋው እነሱ ወደ እኛ አገር ሲንጋጉ ማየት፤” ትላለች። “እኛስ እኛ ነን። እነሱ ግን እነማን ናቸው?” ከአጠገቧ አንዱ ሲጠይቃት፣ “ኃያላኑ ናቸዋ። በአሁኑ ጊዜ እኮ የዓለማችን ወሳኝ ወሳኝ ሰዎች በመዲናችን ውስጥ ነው የሚገኙት፤” ትለዋለች። “እ እነሱን ነው እንዴ?” ብሎ ጥቂት ሲብሰለሰል ቆይቶ፣ “ታዲያ የእነሱ አመጣጥና የእኛ አካሄድ አንድ ነው? እኛ ብንሄድ ብድር ለመለመን፣ ተምሮ እንዳልተማረ አውቆ እንዳላወቀ አንገት ደፍቶ ለመጠግረር ነው። እነሱ ሲመጡ ይኼው እንደምታይው ነው። መቼም ለገጽታ ግንባታ ነው መንገድ የምንለቀው እንዳትይኝ?” ከማለቱ ተሳፋሪዎች ፈገግ አሉ። በቃ በየታጠፍንበት መንገድ የሚያጥወለውለን ነገር አናጣም? ጉድ እኮ ነው!

  ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። መንገድ ከመከፈቱ ሾፌራችን ታክሲዋን ታስሮ እንደተፈታ ውሻ እያንቀለቀለ ይነዳታል። “ኧረ ቀስ በል በለው! ደግሞ የእኛ አልበቃ ብሎ የትራፊክ አደጋችንን አሰቃቂነት ለእንግዶቻችን ልታሳይብን ነው?” አዛውንቷ እንደመቆጣት ብለዋል። “ቀስ በል ማለት አይበቃም የምን ማስፈራራት ነው?” ወያላው መለሰላቸው። “ለነገርማ አንደኞች ናችሁ ሳንቲሜን ሳትመለስ ደግሞ ታወራለህ?” ቢሉት ቀና ብሎ ሳያያቸው ሳንቲማቸውን ወረወረላቸው። “ባጭር ያስቀርህ እንዳልልህ የምሰማው ይኼ መለኛ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያሳሳኛል። ልቦና ይስጥህ ልበል እንጂ ሌላ ምን እላለሁ?” ብለው አንገታቸውን ወዘወዙ። ይኼኔ መጨረሻ ወንበር የተቀመጡት ወጣቶች፣ “ቆይ ግን ሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድና መርሐ ግብር ለምን ይሆን በኢመደበኛ የትምህር ሥርዓት የኅብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ለማዳበር፣ በአስተሳሰብ ለመቀየርና ለማሠልጠን ያጠነጠነ አስተምህሮ ያልተካተተበት?” አለች አንደኛዋ። “ ‘ቻፓ’ ባይኖረው ነዋ። ምርትና ምርታማነት እኮ ነው ኢኮኖሚያችንን በሁለት አኃዝ እያስወነጨፈ ዓለምን ከዳር ዳር ያስጨበጨባት። እንዴት ነው የምታስቢው?” አላት ከጎኖ የተቀመጠው። “ነው እንዴ? አይ ልበ ቢሷ። አየህ የዳበረና የነቃ የዜጎች ህሊና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሠለፍ ከምንጥላቸው ጥሎሾች መሀል እንደማይመደብ ልብ ሳልል ነው የተናገርኩት። ይቅር በለኝ!” ብትል ወጣቱ ቀበል አድርጎ፣ “የለም እኔ ዘንድ ሳይሆን ገና ነፍስ አባትሽን ጠርተሽ መናዘዝ ይገባሻል፤” አላት። “በሥጋ ተሳስታ ለምድነው በነፍስ የምትጠየቀው?” ብሎ ጎልማሳው ከወዲያ ሲጠይቀው፣ “እሷስ ለምንድነው ሥጋ ሥጋቸውን ብቻ አዩ ብላ በነፍስ የምትከሳቸው?” ብሎ መለሰለት። ወያላው “መጨረሻ” ብሎ ሲበትነን እያሳሰበኝ የነበረው የሐሳቦቻችንና የአስተሳሰቦቻችን ጉዳይ ነው፡፡ የተሻሉ ስንፈልግ የወዳደቁ፣ በወዳደቁት ቅር ስንሰኝ ፈገግ የሚያደርጉን አይጠፉም፡፡ የውጣ ውረዶቻችን መገለጫዎች ስለሆኑ ሁሌም አብረውን አሉ፡፡ ክረምት አይደል? እንንቦጫረቅ! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት