Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መቂ ባቱ ዩኒየንና የዓመታት ውጥኑ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መቂ ባቱ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች የኅብረት ሥራ ዩኒየን በዋናነት በቲማቲም አምራችነታቸው የሚታወቁ አርሶ አደሮችን የያዘ ሲሆን በሥሩ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬዎችን የሚያመርቱ ከ150 የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበራት የተደራጁ 8,360 በላይ አርሶ አደሮችን ያቀፈ ነው፡፡ ከአባል አርሶ አደሮቹ የሚረከባቸውን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በተለያዩ ከተሞች ሱቅ በመክፈት ጭምር በመሸጥም ይታወቃል፡፡ ግብይቱን ዘመናዊ ለማድረግ የተለያ ጥረቶችን የሚያደርገው ይህ ዩኒየን፣ የሚያመርተውን ምርት በቀጥታ ለገበያ ከማቅረብ እሴት በመጨመር አቀነባብሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከዓመታት በፊት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተለይ በከፍተኛ ደረጃ የሚመረተው የቲማቲም ምርት በቀላሉ እየተበላሸ አርሶ አደሮችን በማክሰሩ፣ ማቀነባበሪያ ወደ መክፈት ሐሳብ አሸጋግሮታል፡፡ የቲማቲም ድልህ ለማምረት የሚያስችለውን ፋብሪካ ለመገንባትም ከአንድ የጀርመን ኩባንያ ጋር እስከመዋዋል ደርሶ ነበር፡፡ በወቅቱ ግን ዩኒየኖች እንዲህ ያለ የቢዝነስ ጥምረት መፍጠር አይችሉም የሚል ክልከላ አለ በመባሉ፣ ከጀርመኑ ኩባንያ ጋር ተደርሶ የነበረው ውል እንዲፈርስ መደረጉን  የዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቱሬ ቀሲም ይገልጻሉ፡፡ የቀደመው ጥረቱ ባይሳካም በአሁኑ ወቅት የዓመታት ሕልሙን ለማሳካት የሚያስችለውን የአጋርነት ስምምነት በኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ አዋዋይነት ማግኘት ተችሏል፡፡

መቂ ባቱ ዩኒየን ከፍተኛ የቲማቲም ምርት አቅርቦት አቅም ያለውና  የቲማቲም ማቀነባበሪያ ድርጅት ለማቋቋም የገንዘብ አቅም የነበረው ቢሆንም፣ የማቀነባበር ክህሎት፣  በተቀነባበሩ ምርቶች ግብይት ዕውቀትና የማቀነባበሪያ ክዋኔ (ኦፕሬሽን) አቅም ውስንነት የተነሳ ከበፊት ጀምሮ የቲማቲም ማቀነባበሪያ ለማቋቋም  የነበረውን ምኞት እውን ማድረግ አለመቻሉን ስምምነቱን አስመልክቶ የላከው መግለጫ ይናገራል፡፡

በኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ አገናኝነት መቂ ባቱ ዩኒየን፣ ጆርዳና ኪችን ከተባለው ኩባንያ ጋር የተዋዋለው ውል የመቂ ባቱን የዘመናት ምኞት ያሳካ ነው ተብሏል፡፡ ውሉን አስመልክቶ የተሰጠው መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ መቂ ባቱ ይህንን በጥምረት ለመሥራት የተዋዋለው ጆርዳና ኪችን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ደግሞ የማቀነባበሪያ ተቋም በመገንባትና በተቀነባበሩ ምርቶች ግብይት ተጨባጭ ተሞክሮ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ጆርዳና ያለበትን የለጋ ቲማቲም አቅርቦት እጥረት ለመፍታት ብሎም የማቀነባበሪያ ድርጅት ለመትከል የሚያስፈልገውን የገንዘብ ግብዓት ማሟላት ያልቻለ ነበርም ይላል፡፡

ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ተመጋጋቢ ፍላጎቶች በማጤን፣ የአዋጭነት ጥናት ከማካሄድ ጀምሮ እንዲሁም የሁለቱን ተዋዋዮች በጥምረት እንዲሠሩ ለማድረግ ሊያዋውላቸው ችሏል፡፡

በጥምረት ለሚሠራው ሥራ ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ የመቂ ባቱ ዩኒየን በድምሩ 43,285,085 ብር ወጪ በማውጣት ሙሉ በሙሉ  ለቲማቲም ማቀነባበሪያ የሚሆነውን ፋብሪካ ይገነባል፡፡ ለግንባታ ከሚወጣው ወጪ ውስጥ 24,979,948 ብሩ ከባንክ በብድር የሚሸፍንለት ይሆናል ተብሏል፡፡

ጆርዳና ኪችን ደግሞ በማቀነባበሪያው በሚውሉ ማሽኖች ግዥና ተከላ ሒደት ቴክኒካዊ እገዛ በመስጠት የለጋ ቲማቲም አቅርቦት ላይ የእሴት ሥርዓትን ለመንደፍ፣ ሙከራ ለማካሄድና ለመዘርጋት እንዲሁም የማቀነባበሪያ አመራር ሥርዓትንን ለመቅረፅና ለመዘርጋት የሚያስችሉ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ከዚህም ሌላ የድኅረ ሰብል አያያዝና የግብይት ስትራቴጂ ለመተግበር የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ተስማምቷል፡፡

በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረሰው ስምንት መሠረት ማቀነባበሪያ ፋብሪካው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ይጠናቀቃል፡፡ ፋብሪካው በምሥራቅ ሸዋ መቂ ከተማ በዩኒየኑ ይዞታ ላይ የሚተከል ነው፡፡ አቶ ቱሬ ለሪፖርተር እንደገለጹትም ለፋብሪካው ተከላ የሚሆን ወደ 2,000 ካሬ ሜትር ቦታ ተዘጋጅቷል፡፡

መቂ ባቱ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ቱሬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የዚህ ፋብሪካ እውን መሆን አርሶ አደሮች በየዓመቱ በቲማቲም ምርት ይገጥማቸው የነበረን ኪሳራ ያስቀራል፡፡ ከዚህም ሌላ 4300 ካሬ ሜትር መስኖ ገብ ማሳ ያላቸውንና ዓመታዊ ገቢያቸው ከ15 ሺሕ እስከ 46 ሺሕ ብር የሚደርስ አነስተኛ ማሳ የቲማቲም ገበሬዎችን በዋናነት ተጠቃሚ በማድረግ ገቢያቸውን እስከ 20 በመቶ ሊያሳድግላቸው እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

ማቀነባበሪያው እሴት በመጨመር ከሚያስገኘው የገንዘብ ትርፍ በተጨማሪ እስከ 35 በመቶ የሚደርሰው የቲማቲም ድኅረ ሰብል ይበላሽ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ከዚህም ሌላ የፋብሪካው ሥራ መጀመር  በግብይት ሰንሰለቱ  ውስጥ የሚባክነውን ከፍተኛ ጊዜ እንደሚያስቀር ከስምምነቱ በፊት የተደረ ገጥናት ያስረዳል፡፡ በቅብብሎሹ  ውስጥ የሚገኙ እሴት አልባ ተዋናዮችን  እንዲሁም አሁን የሚታየውን ቅጥ የለሽ የቲማቲም የዋጋ መዋዠቅ በማስቀረት ረገድም የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ እንደ ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ መግለጫ፣ ይህ ስምምነት አነስተኛ የቲማቲም ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች አማራጭ እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በላይ ሚዛናዊና ወቅታዊ ገበያ እንዲያገኙና በድርድር ምርታቸውን ለመሸጥ ያስችላቸዋል ይላል፡፡

ቲማቲም በቶሎና በቀላሉ የሚበላሽ ምርት እንደመሆኑ ረዥም ጊዜ ጠብቆ ለማቆየት በእንያንዳንዱ የማከማቻና የማጓጓዣ እርከኖች የግድ የሚል ማቀዝቀዣ  እንደልብ አለመገኘት እንዲሁም የአቅርቦቶች አለመኖር ከግብይት መሠረተ ልማቶችና ክህሎቶች እጥረት ጋር ተዳምሮ፣ የቲማቲም ድኅረ ሰብል ውድመት ያስከትል የነበረውን ኪሳራ በማስቀረት ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ማቀነባበሪያው ሥራ ሲጀምር በዓመት እስከ 18 ሺሕ ቶን ዋጋ ቲማቲም በማቀነባበር የቲማቲም ልቁጥ፣ የቲማቲም ድልህ፣ የቲማቲም ማባያ ወጥና የቲማቲም ጭማቂን ጨምሮ በርካታ የቲማቲም ተዋፅዕዎችን ለማምረት የሚችል ነው፡፡ መሰል የቲማቲም ምርቶችን ከውጭ ከማስገባት እየፈሰሰ ያለውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በከፊል በማዳን ጭምር ጠቃሚ መሆኑን የሚያመለክተው የኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ መረጃ፣ ከከተሞች ዕድገት ጋር ተያይዞ የሚታየውን ከፍተኛ ፍላጎት ለመሸፈንም ያስችላል ይላል፡፡ እንደ አቶ ቱሬ ገለጻ  ደግሞ በተለየ ደረጃ የሚመረተው ድልህ  በአብዛኛው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው፡፡ ምርቱ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የጥራት ደረጃ እንደሚኖረው ለማድረግም ከወዲሁ ዝግጅት ተጀምሯል ይላሉ፡፡ የማሽነሪ መረጣ ሥራዎች በሙሉ በመጠናቀቃቸው በቶሎ ወደ ግንባታ በመግባት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ግንባታውን እናጠናቅቃለን ይላሉ፡፡

ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ የቢዝነስ ተቋማት መዋህዳቸውን እንዳያፈርሱ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶችና ሥጋቶች መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ አንዱ ተግባሩ መሆኑን የድርጅቱ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ አዋጭ የቢዝነስ ሞዴሎችን በመሞከርና ሁነኝነታቸውን በማረጋገጥ እንደቻሉ ኪሳራን በመጋራት መርኅ የፈጠራ አካል ከሆኑ አካላት ጋር ተጣምሮ በመሥራትና ግብይቶች የሚቃኑበትን አሠራር የሚያመቻች ጭምር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ከመቂ ባቱ ጋር የተፈጸመው ስምምነት ዋነኛው ፋይዳ  በድህነት የሚኖሩ ሴቶች ምርታቸውን በሚያቀነባብረው ድርጅት ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው በማስቻሉ የተሻለ ግብይት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግና የውሳኔ ሰጪነት አቅማቸውን ማጎልበት ነው፡፡

ይህም ዕውን የሆነው ወሳኝ የግብይት ክህሎቶች ካሉት ከጆርዳና ኪችን ጋር በተፈጠረ አጋርነት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ፈጠራ አከል የቢዝነስ ሞዴል የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አልፎ በአገሪቱ ዙሪያ ያሉ አሥር ሺሕዎች ሴቶችን የቤተሰቦቻቸውን ገቢ ለቀጣይ በርካታ ዓመታት የሚያሳድግ ነውም ይላሉ፡፡  

የመቂ ባቱ ዩኒየን የሥራ ኃላፊዎችም ‹‹ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ ያለብንን ክፍተት አጥንቶ በራሱ ተነሳሽነት እያንዳንዳችንን ካለንበት ፈለግ በማቀራረብና ለውጤታማ አጋርነት ስላበቃን ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ የተፈጠረው አጋርነት ከምኞት ውጭ ወደ ተግባር እንድንሸጋገር ያስችለናል፤›› በማለት መናገራቸውን በመግለጫው ሰፍሯል፡፡ መቂ ባቱ በ1994 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን ካፒታሉ ከ515 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡

ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ በኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ ለማጎልበት፣ ፈጠራን ለማበረታታ በተመረጡ አራት ዘርፎች በመሥራት ላይ የሚገኝ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ነው፡፡ በጥጥና ጨርቃ ጨርቅ፣ በቁም እንስሳትና ቆዳ፣ በአትልክትና ፍራፍሬና በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የግል ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራትና እገዛ በማድረግ ለግሉ ዘርፍ መጎልበት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ ተቋም እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች