Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአቶ ዓሊ ሲራጅ (ከ1964 - 2007)

አቶ ዓሊ ሲራጅ (ከ1964 – 2007)

ቀን:

የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ዓሊ ሲራጅ ቅዳሜ ሐምሌ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በድንገት ካረፉ በኋላ፣ እሑድ ሐምሌ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ኮልፌ በሚገኘው የሙስሊም መቃብር የቀብር ሥርዓታቸው ተፈጽሟል፡፡

የ43 ዓመቱ አቶ ዓሊ ሲራጅ በአዳማ በጨፌ ኦሮሚያ ስብሰባ ላይ እንዳሉ በድንገት ታመው ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም፣ ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት ሕይወታቸው አልፏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ ለኩ ጩሜ ቀበሌ የተወለዱት የአቶ ዓሊ የሕይወት ታሪክ እንደሚያስረዳው፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሊሙ ጩሜ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሊሙ ገነትና በአጋሮ ተከታትለዋል፡፡

በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርነት ሠልጥነው በአዳማ ከተማ ለሦስት ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማኔጅመንት እንደወሰዱ የሕይወት ታሪካቸው ያመለክታል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለማግኘት በማርኬቲንግ የትምህርት ዘርፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተከታተሉ እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ኦሕዴድን በመቀላቀል ከወረዳ ጀምሮ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች የሠሩ ሲሆን፣ ከ1987 እስከ 1990 ዓ.ም. የሊሙ ገነት አስተዳዳሪ፣ ከ1991 እስከ 1992 ዓ.ም. ድረስ የጅማና የምሥራቅ ሸዋ ዞኖች የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በ1993 ዓ.ም. ደግሞ የጅማ ዞን አስተዳዳሪ በመሆን ማገልገላቸውን የሚገልጸው የሕይወት ታሪካቸው፣ የአዲስ አበባ ካቢኔ አባልና የአስተዳደሩ ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ በመሆን ለሦስት ዓመት አገልግለው እንደነበር ያስረዳል፡፡

የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ከመሾማቸው ቀደም ብሎ ለአራት ዓመታት የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ሥራቸው ጐን ለጐን በተለያዩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና በቦርድ አባልነት እያለገሉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት (አለ በጅምላ) ምክትል የቦርድ ሊቀመንበር ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ኤጀንሲና የኢትዮጵያ ነዳጅ ኢንተርፕራይዝ የቦርድ አባል በመሆንም በማገልገል ላይ እንደነበሩ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ አቶ ዓሊ በሥራቸው ትጉ መሆናቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡

አሮጌ ቤቶች በበዙበት በደጃች ውቤ ሠፈር አዲስ አበባ ሬስቶራንት አካባቢ በሚገኝ የመንግሥት ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት አቶ ዓሊ፣ ዜና ዕረፍታቸው ከተሰማ በኋላ ለእንግዶች ማስተናገጃ የሚሆን ድንኳን መጣያ የሌለው ጠባብ ግቢና አነስተኛ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ይህም አቶ ዓሊ ለግል ሕይወታቸው ብዙ የማይጨነቁ መሆኑን ያሳያል ያሉም አሉ፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ፣ ቤታቸው ከሁለት ሺሕ ብር በላይ ስላልነበረ የዕዝን ወጪ በወዳጆቻቸው ነበር የተሸፈነው ተብሏል፡፡

በወር 180 ብር ይከፈልበታል የተባለው መኖሪያ ቤታቸው አንድ ሚኒስትር ይኖርበታል ተብሎ የማይጠበቅ እንደነበረና የተሻለ ቤት እንዲሰጣቸው እንኳን ያልጠየቁ ናቸው በማለትም የገለጹዋቸው አሉ፡፡ በቅርብ የሚያውቋቸው እንደሚሉት ደግሞ አቶ ዓሊ ለሥራቸው እንጂ ለግል ሕይወታቸው ትኩረት የማይሰጡ፣ በሁሉም ወዳጆቻቸው የሚወደዱ ነበሩ፡፡ የቅርብ ባልደረቦቻቸው፣ አቶ ዓሊ ግልጽ፣ ቀጥተኛና ያመኑበትን ፊት ለፊት የሚናገሩ ናቸው ይሉዋቸዋል፡፡ የተሳሳቱበት ነገር ቢኖር በግልጽ ይቅርታ የመጠየቅ ባህሪ እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በፍርድ ቤት ውሳኔ በባለአደራ ቦርድ እንዲተዳደር፣ አቶ ዓሊ የባላደራ ቦርዱ ሰብሳቢ በመሆን ሠርተዋል፡፡ በዚያን ወቅትም አብረዋቸው የሠሩ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላትም የአቶ ዓሊን እርጋታ የተመላበትን አመራር ሲያደንቁ ተሰምተዋል፡፡ በቀብር ሥርዓታቸውም ላይ የንግድ ኅብረተሰቡ መሪዎችና የንግድ ምክር ቤቶች ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች በመገኘት ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዓሊ በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ በአዲስ አበባ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው አሸናፊ መሆናቸውም ይታወቃል፡፡ አቶ ዓሊ ባለትዳርና የሁለት ሴቶችና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡

የአቶ ዓሊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ሲፈጸም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር፣ ሚኒስትሮች፣ የኦሮሚያ ክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል፡፡

     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...