– ለፕሮግራሙ 300 ሚሊዮን ዶላር ይፈልጋል
በዋና ዋና ከተሞች በጎዳና የወደቁና ምንም ዓይነት ገቢ የሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የከተሞች ሴፍቲኔት ፕሮግራም ይፋ ሊደረግ ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ፣ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙና የመኖሪያ ቤት ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግን ያጠቃለላል፡፡
በከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባለቤትነት እየተዘጋጀ ያለው ይህ ፕሮግራም በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋና በትላልቅ የክልል ከተሞች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የፌዴራል መንግሥት እያዘጋጀ ካለው ከዚህ ግዙፍ ዕቅድ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በቅርቡ እንደገለጹት እስካሁን ይፋ ከተደረጉት አራት የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች በተጨማሪ፣ ቋሚ ገቢ የሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚስተናገዱበት የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች እየተቀረፁ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እያሱ ማርቆስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይፋ ከተደረጉት የቤት ፕሮግራሞች በተጨማሪ አምስት አዳዲስ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡
በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ስለሚተገበረው ዕቅድም አቶ እያሱ ሲገልጹ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ከአገሪቱ ልማት ተጠቃሚ የሚሆኑበት የከተሞች ሴፍቲኔት ፕሮግራም እየዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲኖራቸው የሚሠራ ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል ይኖራል፡፡
ይህንን ግዙፍ ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ ከሦስት መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን የዓለም ባንክ ፋይናንስ እንደሚያደርገው እየተገለጸ ይገኛል፡፡
መንግሥት ባለፉት ዓመታት በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል ተንሰራፍቶ የነበረውን ረሃብ ለማጥፋትና አርሶ አደሩንም ሆነ አርብቶ አደሩን በምግብ ራሱን እንዲችል፣ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ይህ ተሞክሮ ውጤታማ እንደነበር አቶ እያሱ ተናግረው፣ ፕሮግራሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ማግኘቱን አስታውሰዋል፡፡ መንግሥት ከዚህ የገጠር ተሞክሮና ከሌሎች አገሮች ልምድ በመውሰድ ይህንን አዲስ ፕሮግራም መቅረፁን አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት ግንባታ በተለይ በከተማ ልማት ቀላል የማይባሉ ተግባሮችን አከናውናለች፡፡ ነገር ግን የዚያኑ ያህል ምንም ገቢ የሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ፣ መንግሥት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት ማድረግ እንዳለበት መግባባት ላይ መድረሱን የሚኒስቴሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በዚህ መሠረት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ይህንን ችግር ከሥሩ ለመፍታት፣ መንግሥት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተለዩ ጥናቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህንን ፕሮግራም የሚያስፈጽም መንግሥታዊ ኤጀንሲ ለማቋቋም የተለያዩ መዋቅሮችን እየፈተሸ መሆኑ ተመልክቷል፡፡