Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አለ በጅምላ ዓመታዊ ሽያጩን ወደ 700 ሚሊዮን ብር ሊያሳድግ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ከተፈቀዱለት አሥር የጅንአድ መጋዘኖች ስምንቱን ተረክቧል

በኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት ሥር የተዋቀረውና የሸቀጦችን ዋጋ ለማረጋጋትና ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለማስፈን የተቋቋመው አለ በጅምላ፣ በ2008 በጀት ዓመት 12 ቅርንጫፎችን በማከል ዓመታዊ የሽያጭ መጠኑን ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ ማቀዱን አስታወቀ፡፡

ከአለ በጅምላ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በ2007 በጀት ዓመት በስድስት ቅርንጫፎቹ 239.4 ሚሊዮን ብር ሽያጭና ከ382 ሚሊዮን ብር በላይ የሸቀጦች ግዢ ፈጽሟል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ግን የግዢ መጠኑን ወደ 800 ሚሊዮን ብር በማሳደግ፣ ሽያጩን ሊያሳድጉለት የሚችሉ ቅርንጫፎችን በመክፈት ዓመታዊ ሽያጩን ወደ 700 ሚሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱን፣ የአለ በጅምላ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኑረዲን መሐመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የቀረው የ100 ሚሊዮን ብር ሸቀጥ ደግሞ ለመጠባበቂያነት ይቀመጣል ተብሏል፡፡

አለ በጅምላ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከደረሰበት ግዢና ሽያጭ ለማካሄድ አቅዶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኑረዲን፣ የመንቀሳቀሻ ካፒታልና የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የሽያጭ መጠኑን ሊያሳድጉለት የሚችሉ ሦስት ቅርንጫፎች አለመከፈታቸው በዓመታዊ የሽያጭ መጠኑ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡

ከመንግሥት ሊለቀቅለት የሚገባው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ባለመለቀቁ በቂ መንቀሳቀሻ ካፒታል እንዳይዝ ቢያደርግውም፣ ከባንክ ባገኘው ብድር ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል ተብሏል፡፡ ድርጅቱ ከባንክ የተበደረው ከ590 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ ከአዲስ አበባ ውጪ ተጨማሪ ሦስት ቅርንጫፎች ለመክፈት አቅዶ በዕቅዱ መሠረት ሊጓዝ ያልቻለው፣ ከጅንአድ ወደ አለ በጅምላ መተላለፉ የነበረባቸው መጋዘኖች ርክክብ መጓተት ምክንያት ነው፡፡

በመንግሥት ትዕዛዝ ጅንአድ ለአለ በጅምላ እንዲያስተላልፍ ውሳኔ የተሰጠባቸው በጅማ፣ በደሴ፣ በሻሸመኔ፣ በባህር ዳር፣ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በመቐለና በአዲስ አበባ የሚገኙ ሦስት የጅንአድ መጋዘኖች ናቸው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ከአዲስ አበባ ውጪ ካሉት መጋዘኖች ርክክባቸው ተፈጽሞ አለ በጅምላ እጅ የገቡት የደሴ፣ የባህር ዳር፣ የሐዋሳ፣ የሻሸመኔና የጅማ መጋዘኖች ናቸው፡፡

የድሬዳዋና የመቐሌን መጋዘኖች እስካሁን ርክክባቸው ያልተፈጸመ ሲሆን፣ የጅማና የደሴ መጋዘኖችንም ርክክባቸው የተፈጸመው ዘግይቶ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ በበጀት ዓመቱ መከፈት የነበረባቸው ተጨማሪ ቅርንጫፎች ለአዲሱ በጀት ዓመት እንዲሸጋገሩ ተደርጓል፡፡

በአዲሱ በጀት ዓመት ግን በ2007 ዓ.ም. መክፈት የነበረባቸውን ቅርንጫፎች ጨምሮ የደሴ፣ የጅማ፣ የአዳማ፣ የመቐለ፣ የድሬዳዋ፣ የጎንደርና ሌሎች አዳዲስ ቅርንጫፎች ይከፈታሉ ተብሏል፡፡ እንደ አቶ ኑረዲን ገለጻ፣ በ2008 በጀት ዓመት አለ በጅምላ የሚከፍታቸው አጠቃላይ አዳዲስ ቅርንጫፎች 12 ይደርሳሉ፡፡

አለ በጅምላ የተመሠረተበትን ዓላማ በማሳካት ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ኑረዲን፣ አንዱ ማሳያ በአሁኑ ጊዜ ባሉት ስድስት ቅርንጫፎች የሚገለገሉ ወይም ከአለ በጅምላ ሸቀጦችን ወስደው የሚቸረችሩ ደንበኞች ቁጥር እያደገ መምጣቱ ነው፡፡ እንደ አቶ ኑረዲን ገለጻ፣ በ2008 በጀት ዓመት የሚከፈቱት ቅርንጫፎች የደንበኞችን ቁጥር በማሳደግ ወደ 16,033 ለማድረስ ያስችላሉ ተብሎ ታቅዷል፡፡ አለ በጅምላ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ሥራ ሲገባ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ሊኖረኝ ይገባል ብሎ አቅዶ የነበረው የደንበኞቹ ቁጥር 4,128 ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ 7,544 የተመዘገቡ ደንበኞችን በመያዝ ከዕቅድ በላይ መሄዱን አቶ ኑረዲን አስረድተዋል፡፡

በሠራተኞች ረገድ ግን አለ በጅምላ ይቀጥራል ተብሎ የታሰበው 454 ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የያዛቸው ሠራተኞች 374 መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቀጣዩ ዓመት ዋና ዋና የክልል ከተሞችን የመድረስ ዕቅድ ያለው አለ በጅምላ፣ ለቸርቻሪዎች የሚሸጣቸው የምርት ዓይነቶችንም በየጊዜው በመጨመር ላይ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ሥራ የጀመረው 147 የምርት ዓይነቶችን በማቅረብ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የሚያሠራጫቸው የምርት ዓይነቶች 515 እንደደረሱ አቶ ኑረዲን ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ አነስተኛ የሆነ የትርፍ ህዳግ በመያዝ የሚሠራ ቢሆንም፣ ዓመታዊ የሥራ እንቅስቃሴው አትራፊ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ ድርጅቱ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ ሥራ ያስገባቸው ቅርንጫፎች ያስከተሉት የግንባታ ወጪ፣ ለአማካሪ ድርጅት የሚፈጸም ክፍያና የባንክ ዕዳ ክፍያ ከካፒታሉ እጥረቱ ጋር ተያይዞ ትርፉን ገድቦታል፡፡ ቀደም ብሎ በተያዘው ዕቅድ መሠረትም ቢሆን በመጀመርያውና በጥቂት ተከታታይ ዓመታት ትርፍ የማይጠብቅ ቢሆንም ሥራውን እያስፋፋ ይሄዳል ተብሏል፡፡

አለ በጅምላ በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ገበያን ለማረጋጋት የተቋቋመ ኩባንያ ሲሆን፣ በሒደትም በግል ዘርፍ ተዋንያኖች እንደሚተካ የረዥም ጊዜ ዕቅድ አለው፡፡ ይህንን ዕቅዱን ዳር ለማድረስም በ2008 በጀት ዓመት በአለ በጅምላ ቅርፅና ይዘት ወደ ሥራ ሊገቡ ለሚፈልጉ 100 ለሚሆኑ የግሉ ዘርፍ አባላት ሥልጠና የመስጠት ፕሮግራም ይዟል፡፡ ወደ ሥራ የሚገቡ ከሆነም አለ በጅምላ ሙሉ እገዛ እስከማድረግ የሚደርስ ዕቅድ እንዳለው አቶ ኑረዲን አስረድተዋል፡፡ አለ በጅምላ በኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት ሥር ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት የሚመሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ጉዳይ አማካሪ አቶ ነዋይ ገብረአብ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች