Saturday, September 24, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ከስኬት በስተጀርባ የመሸጉ ነውሮች መፍትሔ ይፈለግላቸው!

  ኢትዮጵያ አገራችን በዓለም አደባባይ ግርማ ሞገስ የሚያጎናፅፏት ደስ የሚያሰኙ በርካታ ስኬቶች ያሉዋትን ያህል፣ በኃፍረት አንገቷን የሚያስደፍዋት እንከኖችም አሉዋት፡፡ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያችን ለዘመናት ከነበረችበት አስከፊ አረንቋ ውስጥ በመውጣት፣ ክብርና ዝና የሚያጎናፅፋት ደረጃ ላይ እያደረሰች ነው፡፡ በረሃብና በልመና የምትታወቅ አገር የተበላሸ ገጽታዋ እየተለወጠና በአፍሪካ አኅጉር ከቀዳሚዎቹ ተርታ እየተሠለፈች ነው፡፡ ለዜጎቿም መነቃቃት እየተፈጠረላቸው ነው፡፡ ነገር ግን እየታየ ካለው ስኬታማ ለውጥና ዕድገት በስተጀርባ የመሸጉ ነውሮች አሉ፡፡ እነዚህ ነውሮች አገሪቷን ግማሽ ልጩ ግማሽ ጎፈሬ አድርገዋታል፡፡ ለእነዚህ ነውሮች መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ተራ በተራ እንቃኛቸዋለን፡፡

  1. የመልካም አስተዳደር እጦት

  የመልካም አስተዳደር እጦት በዚህ ዘመን ዋነኛው ነውር ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ መዋቅሮች በፍፁም ሊፈቱት ያልቻሉትና የአገሪቱን የዕድገት ጉዞ የሚፈታተን ፀር ሆኗል፡፡ ከአገሪቱ መሪ እስከ ታችኛው አካል ድረስ የመልካም አስተዳደር እጦትን በተመለከተ ብዙ ቢሉም፣ ቃልና ተግባር አልገናኝ ብለው ሕዝብን እያስመረሩ ናቸው፡፡ አንድ ዜጋ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ያገኙ መብቶቹን በሚጠይቅበት ወቅት፣ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ ሹማምንት ኢሰብዓዊ ተግባር ይፈጽሙበታል፡፡ መብትን መጠየቅም ሆነ ቅሬታ ማቅረብ የማይቻል ይመስል በየተደረሰበት ቦታ ሁሉ በየደረጃው ያለ ሹም ራሱ ሕግ ሆኖ ይቀርባል፡፡ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ እየተደፈጠጠ ዜጎች እንዲሸማቀቁ ይደረጋሉ፡፡ ሐሳብን በነፃነት መግለጽም ሆነ መብትን መጠየቅ ኃጢያት እየሆኑ ነው፡፡

  የተለያዩ ጉዳዮች ያሉባቸው ዜጎች በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ለሚያጋጥሙዋቸው ችግሮች ተጠያቂ የለም፡፡ በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚዎች ሁሉንም ነገር በሥልጣናቸው የመጣባቸው እያደረጉ አፈናን ማስፈን ይፈልጋሉ፡፡ ሰዎችን ያስፈራራሉ፡፡ የተቀመጡበት ወንበር በሕዝብ ፈቃድ የተገኘ መሆኑን ረስተው የአምባገነንነት ባህሪያቸውን ያሳዩበታል፡፡ ቅሬታ ተቀብሎ በመመርመር ውሳኔ የሚሰጥበት አሠራር ባለመስፈኑ፣ ሕዝቡ ምሬቱንና አቤቱታውን የሚያቀርበው ወደ ፈጣሪው ነው፡፡ ሕዝብ ብሶት የሚያሰማባቸው ጉዳዮች ወደ ሚዲያ ሲቀርቡ ርብርቡ ለማስተባበል ነው እንጂ መፍትሔ ፍለጋ አይደለም፡፡ የአገልጋይነት መንፈስ ጠፍቶ ትናንሽ አምባገነኖች እየፈሉ ነው፡፡

  አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና በተቸራቸው ታላላቅ መድረኮች ላይ ከመሳተፍ አልፋ ራሷ አዘጋጅ መሆን በቻለችበት በዚህ ወቅት፣ ለመልካም አስተዳደር እጦት መፍትሔ አለመፈለግ በጣም ያስገርማል፡፡ ከማስገረም አልፎም ያሳዝናል፡፡ ዜጎች ተበደልን ወይም የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ደረሰብን ሲሉ አዳማጭ ከሌለ መንግሥት ማንን እያስተዳደረ ነው? ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ ያሉ መዋቅሮች ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ሲያቅታቸው ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በላይ ማን ተጠያቂ ሊሆን ነው? አገሪቱ በኢኮኖሚ ዕድገቷ ግስጋሴ ስሟ በሚጠራበት በዚህ ዘመን፣ ለዜጎች ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ያቃታቸው መንግሥታዊ ተቋማት በሕዝቡ እስከ መቼ እየቀለዱበት ይቀጥላሉ? ዜጎች በመልካም አስተዳደር እጦት የተነሳ በገዛ አገራቸው ሲመረሩ ዝም ብሎ ማየት ያስጠይቃል፡፡ በተለይ የገዥው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ይኼ አስመራሪ ችግር ሊያሳስባቸው ይገባል፡፡ ሥርዓቱ እንደ ሥርዓት መቀጠል የሚችለው ችግሮችን መፍታት ሲችል ብቻ ነው፡፡ መፍትሔ መፈለግ ካልተቻለ ውጤቱ የከፋ ይሆናል፡፡

  1. የፍትሕ እጦት  

  ዜጎች በተለያዩ ጉዳዮች ችግር ሲገጥማቸው በፍትሕ ሊመኩ ይገባል፡፡ የሕግ የበላይነት አለ በሚባልባት አገር ውስጥ የፍትሕ ተደራሽነት ሲስተጓጎል አደጋ ነው፡፡  በፍትሕ እጦት የሚንገላቱ ዜጎች አቤቱታዎች በተለያዩ መንገዶች ሲሰሙ፣ ዘመኑ ወርቃማው ፍትሕ የሰፈነበት ነው ብሎ መናገር ያስተዛዝባል፡፡ በመላ አገሪቱ ፍትሕ ተነፍገናል ብለው አቤቱታ የሚያሰሙ በርካታ ዜጎች አሉ፡፡ ፍትሕን በገንዘብ በመዘወር፣ የዳኝነት ነፃነትን በመጋፋትና በመሳሰሉት ምክንያቶች መብቶቻቸው የተደፈሩባቸው ዜጎች ያለቅሳሉ፡፡ አፋጣኝ መፍትሔ ይፈልጋሉ፡፡

  ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ተማምነው ሥራቸውን ማከናወን የሚችሉት ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሲከበሩ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትም በትክክል ሲረጋገጥ ነው፡፡ “አንድ ንፁኃ ዜጋ ያላግባብ ከሚታሰር ይልቅ አንድ ሺሕ ወንጀለኞች ቢለቀቁ ይሻላል” የሚለው የሕግ አባባል ካልተከበረ፣ ንፁኃን የሚተማመኑበት የፍትሕ ሥርዓት አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ የነበሩት ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ጉዳይ የሰሞኑ መነጋገሪያ አጀንዳ ነው፡፡ ከዘጠኙ ታሳሪዎች መካከል አምስቱ በድንገት በፍትሕ ሚኒስቴር ትዕዛዝ ተፈተዋል፡፡ በምን ምክንያት እንደተፈቱ አይታወቅም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች መፈታታቸውን እንጂ ነፃ መሆናቸውን አያውቁም፡፡ ነገ ክሱ ይቀጥል አይቀጥል አያውቁም፡፡ ይኼ ምን ማለት ነው? ለአንድ ዓመት ያህል ክስ ሳይመሠረትባቸው ሰሞኑን የተለቀቁት ሌሎች ታሳሪዎች ጉዳይም አጠያያቂ ነው፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይም ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡  

  በርካታ ዜጎች በተለያዩ የሽብር ድርጊቶች በመጠርጠር እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ መንግሥት በመረጃና በማስረጃ በመደገፍ ክስ መመሥረቱን በተለያዩ ጊዜያት ሲናገር፣ ተከሳሾቹ መብታቸውን በመጠየቃቸው ምክንያት ብቻ ስቃይ እንደደረሰባቸው በተደጋጋሚ ጊዜያት አስታውቀዋል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን ገለልተኝነትና ነፃነት የሞገቱ በርካታ ክስተቶችም ታይተዋል፡፡ ለዘብ ያሉ ተቃውሞዎችን ማስተናገድ ያቃተው ሥርዓት ሁሉንም ነገር ወዳልተገባ አቅጣጫ እየገፋ ነው ተብሎ በተደጋጋሚ ሲተች፣ መንግሥት ቆም ብሎ ችግሮችን መመርመር አለበት፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር በፍትሕ ሥርዓቱ አንተማመንም ብለው በገሐድ ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ጥያቄ ሲነሳበት በፍጥነት ችግሮችን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች የሚማረሩበት የፍትሕ እጦት ከሰላማዊ ፖለቲከኞችና በሥርዓቱ ላይ የመረረ ጥላቻ ካላቸው ተቃዋሚዎች ጋር በሚደረግ እልህ የሞላበት ፍትጊያ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ገጽታ እንዳይበላሽ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡

  በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀር የተመሰከረለት የአገሪቱ አስደናቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ በፍጥነት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የድህነት ቅነሳና በማኅበራዊ ዘርፎች የሚታየው መነቃቃት፣ መንግሥት ዘወትር በሚወቀስበት የሰብዓዊ መብት ረገጣ ምክንያት ሲታወክ በጣም ያሳዝናል፡፡ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ መብት ረጋጮች ዝርዝር ውስጥ የአገሪቱ ስም ሲሰፍር በጣም ያበሳጫል፡፡ ይህ አሳዛኝ ገጽታ ለአገሪቱ ክብርና ለዚህ ጨዋ ሕዝብ ሲባል መቀየር አለበት፡፡

  1. እየተባባሰ ያለው ሙስና

  ሙስና የዜጎች ብቻ ሳይሆን ለሥርዓቱም ጠንቅ የሚሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እንደ በፊቱ “በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው” ያለው የሚለው አባባል አይሠራም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከተላላኪ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት ሹም ድረስ መተመዳዳሪያቸው ሙስና እየመሰለ ነው፡፡ በየተደረሰበት የመንግሥት ተቋም ውስጥ ያለሙስና ጉዳይ ማስፈጸም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ከተራው ዜጋ እስከ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች ድረስ ከፍተኛ ምሬት እየፈጠረ ነው፡፡ የመንግሥት ግዥዎችና ንብረት አስተዳደር ላይ የሚታየው ሥርዓት ያጣ ተግባር ምን ያህል ሙስና እንደተንሰራፋ ማመልከቻ ነው፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በርካታ የተዝረከረኩ አሠራሮችን የሚያሳይባቸው ሪፖርቶች ይኼንን ችግር ያመላክታሉ፡፡

  የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተጠናቆ ሁለተኛው ሊጀመር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተከናወኑ በርካታ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ በርካታ ሐሜቶች አሉ፡፡ የወደፊቱም የተለየ እንደማይሆን ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በረጂም ጊዜ በሚታይ ሥራ ሳይሆን በአጭር ጊዜ በሙስና የከበሩ እንደ አሸን መፍላታቸው ነው፡፡ በተለያዩ ፕሮጀክቶች፣ በመሬት ወረራ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ባሉ ብክነቶችና መጓተቶች፣ በግብር ስወራና በመሳሰሉት በርካታ ሌቦች እየከበሩ ነው፡፡ በሙስና ምክንያት የተወሰኑ ሰዎች ቢታሰሩም ከእስር ቤት ውጪ ያሉ ሙሰኞች ግን ተግባራቸውን አፋፍመው ቀጥለዋል፡፡ በአንድ በኩል አገር ለማሳደግ የሚማስኑ ንፁኃን በችግር ውስጥ ይኖራሉ፡፡ በሌላ በኩል በአገር ሀብት የሚበለፅጉ ሙሰኞች በቅንጦት ጠያቂ ሳይኖርባቸው ይንደላቀቃሉ፡፡ ለሙስና መፍትሔ ካልተፈለገና በቁርጠኝነት መታገል ካልተቻለ ሥርዓቱን ገዝግዞ ይጥለዋል፡፡

  አገራችን እንድታድግ፣ እንድትበለፅግ፣ የዜጎቿ የጋራ መኖሪያ እንድትሆን፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖርባት፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት መከበር ስሟ እንዲነሳ፣ የጥቂቶች ሳይሆን የብዙኃን እንድትሆን የምንፈልግ ከሆነ ውስጥ ለውስጥ የሚገዘግዟትን ነውሮች እናስወግድላት፡፡ በዚህ ዘመን አንገቷን ቀና እያደረገች ቢሆንም፣ እነዚህ ነውሮች ግን መልሰው አንገቷን ያስደፉዋታል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሊመጡ ሲሉ እስረኞች ትፈታለች ከምትባል ይልቅ፣ ዜጎች በአደባባይ አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚራመዱባት አገር መሆኗን ማሳየት ይመረጣል፡፡ ስሟን በክፉ የሚያስነሱና ከስኬቷ በስተጀርባ የመሸጉ ነውሮች ዕድገቷንም ስለሚያሰናክሉ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለውጭ ባንኮች የፀደቀው ፖሊሲ ብዥታ እንደፈጠረበት የመድን ሰጪዎች ማኅበር ገለጸ

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በቅርቡ ያፀደቀው የፖሊሲ...

  ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

  የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ተመንን የተቃወሙ አምራቾች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅሬታቸውን አቀረቡ

  ንግድ ሚኒስቴር በወጣው የዋጋ ተመን ብቻ መሸጥ እንዳለባቸው በድጋሚ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

  ለቻይናው ፖሊጂሲኤል ኩባንያ የተሰጠው ውል ተቋረጠ

  የማዕድንና ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ አልምቶ ኤክስፖርት...

  የሕግ ክልከላዎችና የሚያስነሱት ቅሬታ

  በኢትዮጵያ የአገርና የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ተብለው የሚወጡ አንዳንድ ሕጎች፣...

  ለውጭ ባንኮች የፀደቀው ፖሊሲ ብዥታ እንደፈጠረበት የመድን ሰጪዎች ማኅበር ገለጸ

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በቅርቡ ያፀደቀው የፖሊሲ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት...

  ሴረኝነት የሰላም ጠንቅ ነው!

  በአዲሱ ዓመት የመላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ደኅንነት የሚያስጠብቁ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መተኮር ይኖርበታል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በወታደራዊና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ የሕዝባችንን ፍላጎት...