Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመድረክ የአባላቱ እስራትና ሞት ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ

መድረክ የአባላቱ እስራትና ሞት ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ

ቀን:

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተከናወነው አምስተኛውን ዙር ጠቅላላ ምርጫ በኋላ፣ በአባላት፣ በአመራሮችና በምርጫ አስፈጻሚ ግለሰቦች ላይ በተጠናከረ ሁኔታ እየደረሰ ያለውን ወከባ፣ እስራትና ግድያን በተመለከተ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት፣ በጉዳቱ ላይ ቁርጠኛ ውሳኔ ለመስጠት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አስታወቀ፡፡

የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው፣ ‹‹እስካሁን የተፈጠሩ ሁኔታዎችን በሚመለከት ጠቅላላ ጉባዔ እንጠራለን፡፡ በየአካባቢው ያሉትን መረጃዎች አጠናቅረን ምን መደረግ አለበት የሚለውን ለመወሰን መድረክ ጠቅላላ ጉባዔውን በዚህ ወር መጨረሻ ያደርጋል፤›› በማለት ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

መድረክ እየደረሰ ነው ባለው ከፍተኛ ወከባና እስራት ከምርጫው ወዲህ አምስተኛው የመድረክ አባል ሰሞኑን መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ በደቡብ ክልል በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ በአድዮ ካካ ምርጫ ክልል፣ በጎጃብ ምርጫ ጣቢያ የመድረክ ምርጫ ታዛቢና ወኪል ሆነው የሠሩት አቶ አሥራት ኃይሌ፣ ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በተፈጸመባቸው አሰቃቂ ድብደባ ሕይወታቸው ማለፉን መድረክ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

‹‹በአቶ አሥራት ላይ ድብደባ የተፈጸመው በተጠቀሰው ዕለት ጎረቤቶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ወደ ገበያ ሄደው ሳለ፣ ቦንጋ ከተማ 01 ቀበሌ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ብቻቸውን እያሉ ከረፋዱ በአራት ሰዓት ቤታቸው በመጡና ለጊዜው ማንነታቸው በትክክል ባልታወቁ ሰዎች ሲሆን፣ ሕይወታቸው ያለፈው ግን ወደ ጅማ ሆስፒታል ተወስደው በሕክምና ላይ እያሉ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ማታ ነው፤›› ሲል የመድረክ መግለጫ አትቷል፡፡

በከፋ ዞን ከፍተኛ የምርጫ ፉክክር የተደረገው በኢሕአዴግ ዕጩ በዶ/ር መብራቱ ገብረ ማርያምና በግል ዕጩ ተወዳዳሪው ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ መካከል ነበር፡፡ በመሆኑም የመድረክ የምርጫ ታዛቢ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ስለመገደላቸው ያለው ማረጋገጫ ምንድነው? በማለት ጥያቄ ከሪፖርተር የቀረበላቸው አቶ ጥላሁን፣ ‹‹እንግዲህ ታዛቢ ሆኖ በቅስቀሳ ከፍተኛ ሥራ የፈጸመ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ከዚያ በተረፈ ደግሞ የተለየ ጠላትም ሆነ ቅራኔ የለውም፡፡ ምርጫው ከተፈጸመ በኋላ የአባላቶቻችን ድብደባ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ እርሱ ሞተ እንጂ ሌሎች በርካቶች ታስረዋል፡፡ አሁንም ቢሆን እስር ቤት የሚገኙ አሉ፡፡ መድረክን እንዲለቁ ማስፈራሪያና ዛቻ የሚደርስባቸውም እንዲሁ በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ነው ግድያው ከምርጫው ጋር የተገናኘ ነው የምንለው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በተጨማሪም ከዚህ ጋር በተያያዘ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ የጻፍን ቢሆንም፣ ያገኘነው ምንም ዓይነት ምላሽ የለም፤›› በማለት ከምርጫው በኋላ እየደረሱ ያሉት ወከባዎች፣ እስራት፣ ግድያ፣ ከሥራ መባረርና ከእርሻ መሬት መፈናቀል ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ ጥላሁን አስረድተዋል፡፡

‹‹ገዥው ፓርቲ ምን እየፈለገ እንደሆነ አይገባንም፤›› ያሉት አቶ ጥላሁን፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ በእውነቱ የምንናገረው ነገር እየጠፋብን ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም ምን እየተፈለገ እንደሆነ አልገባንም፡፡ በአባሎቻችን ላይ ይህ ጥቃት እየተሰነዘረ ያለው ከአሁን በኋላ በፍፁም መድረክን ለቀው እንዲወጡ ከመፈለግ ነው፤›› በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

መድረክ ባወጣው መግለጫ ላይ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አስተያየት እንዲሰጡን የተደረገው መኩራ አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ