– አፈጻጸሙ ታይቶ ይጨመርልታል ተብሏል
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በ2008 በጀት ዓመት ላቀዳቸው ሥራዎች እንደሚያስፈልገው ካቀረበው ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ የበጀት ጥያቄ፣ ግማሽ ያህሉ ብቻ ተፈቀደለት፡፡
የባለሥልጣኑ ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ ለተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች ማስጀመሪያና ለተለያዩ የመንገድ ዲዛይን ሥራዎችን ጨምሮ በጥቅል ለዓመቱ ክንውን ያስፈልገኛል ብሎ ካዘጋጀው ከ12 ቢሊዮን ብር በጀት፣ ሊደገፍለት የቻለው ስድስት ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡
ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው የበጀት ጥያቄ ሳይደገፍ መቅረቱ ብቻ ሳይሆን፣ ለ2008 በጀት ዓመት የተፈቀደለት በጀት በ2007 በጀት ዓመት ተፈቅዶለት ከነበረው በጀት ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2007 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የመደበው በጀት 6.4 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ዘንድሮ ለመንገድ ዘርፍ የተመደበው በጀት ከቀድሞው ያነሰ ሆኗል፡፡
እንደ ፌዴራል በጀት ድልድል ሁሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ከሌሎች ዘርፎች በተለየ ከፍተኛ በጀት ሲመደብለት የቆየው ለመንገድ ዘርፍ ቢሆንም፣ በ2008 በጀት ዓመት ግን ሊመደብለት ይገባ የነበረውን ያህል በጀት ማግኘት እንዳልቻለ ታውቋል፡፡ አስተዳደሩ ለመንገድ ዘርፍ የመደበው በጀት ባለሥልጣኑ እንዲፈቀድለት ካቀረበው በጀት ያነሰ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ እየታየ ተጨማሪ በጀት እንደሚለቀቅለት ቃል እንደተገባለት ታውቋል፡፡
የበጀት ጥያቄው ማነስ ባለሥልጣኑ አከናውናቸዋለሁ ብሎ ያቀዳቸውን ሥራዎች እንደሚያስተጓጉልበት የተገለጸ ሲሆን፣ ለአንዳንድ ፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ ግን ቃል በተገባለት መሠረት በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ላይ ተጨማሪ የበጀት ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ተጨማሪ የበጀት ጥያቄ ማቅረቡ የተለመደ ሲሆን፣ አስተዳደሩ የመጠባበቂያ ብሎ ከሚይዘው በጀት ላይ በተወሰነ ደረጃ ጥያቄውን ሲመልስ ቆይቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ2008 በጀት ዓመት 31.8 ቢሊዮን ብር ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በጀት ውስጥ 19.98 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪ የተመደበ ነው፡፡ ለመደበኛ ወጪ 10.7 ቢሊዮን ብር ሲመደብ፣ የመጠባበቂያ በጀቱ ደግሞ 1.99 ቢሊዮን ብር ወይም ከጠቅላላ በጀቱ 6.6 በመቶ እንዲይዝ ተደርጐ ተደልድላል፡፡
የአስተዳደሩ የዘንድሮ በጀት ካለፈው ዓመት በጀት ዓመት በአራት ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ ሲሆን፣ የጥቅል በጀቱ ዕድገት አነስተኛ መሆን በአስተዳደሩ ሥር ያሉ በጀት ጠያቂ መሥሪያ ቤቶች ይፈቀዳል ብለው ካቀረቡት ጥያቄ በእጅጉ ያነሰ በጀት እንዲደገፍላቸው እያደረገ ነው እየተባለ ነው፡፡
አስተዳደሩ በ2007 በጀት ዓመት ከፍተኛ በጀት ከተያዘላቸው መካከል ለመንገድ ልማት 6.4 ቢሊዮን ብር፣ ለመጠጥ ውኃ ልማት 4.36 ቢሊዮን ብር፣ ለቤቶች መሠረተ ልማት 1.63 ቢሊዮን ብር፣ ለትምህርት 1.41 ቢሊዮን ብር መድቦ ነበር፡፡
ባለፈው ዓመት ከተመደበው ጠቅላላ 27.94 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ 8.20 ቢሊዮን ብር ወይም 29.4 በመቶው ለመደበኛ፣ 18.32 ቢሊዮን ብር ወይም 65.6 በመቶ ሰደግሞ ለካፒታል ወጪ፣ እንዲሁም 1.41 ቢሊዮን ብር ወይም አምስት በመቶ ደግሞ ለመጠባበቂያ በጀት ተይዞ እንደነበር አይዘነጋም፡፡