ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በተካሄደው ሦስተኛው የፋይናንስ ለልማት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለመካፈል ጎራ ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን፣ እግረ መንገዳቸውን በሴንተር ፎር አክርዴትድ ውመን ኢኮኖሚክ ኢምፓዎርመንት ፕሮጀክት የታቀፉ፣ ከ1,500 በላይ ወጣት ሴቶችና አረጋውያን የሥራ እንቅስቃሴን ሐምሌ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ተዘዋውረው ተመልክተዋል። ኢትዮጵያ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማስፋት የምታደርገውን ጥረትም ማድነቃቸውን ሲደውሩ ከሚያሳየው ፎቷቸው ጋር የዘገበው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ነው፡፡ ‹‹ናኑ ናኑ ነይ…ናኑ ናኑ ነይ ካንቺ አለኝ ጉዳይ፤ አባቴ ሸማኔ እኔ ጥበብ ሠሪ፤ ልቧን ወሰድኩና አረግኩት ደዋሪ፤›› እያለ ዝነኛው ድምፃዊ ሙሉቀን መለሰ ማቀንቀኑን ለባንኪ ሙን የነገራቸው ይኖር ይሆን???
***
እኔ ነኝ
መከራ እንዳይሠለጥን – ጽዋዋን ከ’ሷ ያራቅሁት
እኔ ነኝ የቀውጢ ቀኗ – ለጌጧ ማቅ የለበስኩት
ለሳቋ ደም ያነባሁት – ለክብሯ የተዋረድኩት
እንድትኖር – ሞቷን የሞትኩት …
***
በገዛ አብራክ ልጆቿም – የግልብጥ የተከሰስኩት
በድሏ ማግሥት የፊጥኝ – ታስሬ ፊቷ የቆምኩት
እኔው ነኝ ክርስቶሳዊው – መስቀሏን የተሸከምኩት …
***
እኔው ነኝ ባንዳ ሹቅ ባሹ – በጐበዝ ሞት የፈረድኩት
ሆድ አደር አድር ባይ ሆኜ – ለጠላት መንገድ የሆንኩት
እኔው ነኝ አንዱ ሰው ማለት – ገሀነምና ገነት
የገዳይ የሟችም እውነት
በብዙ ሰዎች ትከሻ – የአንዲት ኢትዮጵያ አንገት፡፡
- አበባው መላኩ ‹‹እኔ ነኝ›› (2007)
*******
‹‹እጅግ ሞኝ ሰው ያጋጠመህ ዕለት ለእሱ ስጠው››
አንድ ሰው ለመሞት በሚያጣጥርበት ሰአት ወንድ ልጁን ጠርቶ:- ‹‹ልጄ ሆይ! መቶ መልህቅ ወርቅ አስቀምጫለሁ ይህን ወርቅ ትወስድና በዚህ ምድር ላይ እጅግ ሞኝ ሰው ያጋጠመህ ዕለት ለእሱ ስጠው ይህ ኑዛዜዬ ነው፤›› በማለት ይሞታል፡፡
ልጅም በአባቱ ኑዛዜ መሠረት ወርቁን ተሸክሞ የምድሪቱን ሞኝ ፍለጋ ሲዞር ይከርምና በአንድ ቀን በአንዲት ከተማ ይደርሳል:: በርካታ ሕዝብም በአደባባይ ተሰብስቦ ይመለከታል፡፡ ተጠግቶ ሲጠይቅም የአገሪቱ ሚኒስትር ንጉሡ ስላዘነበት አንገቱ ተቆርጦ እንዲሞትና በሱም ሬሣ ላይ አዲሱ ሚኒስትር እንዲራመድ ስላዘዘው ይህን ሥርዓት የሚፈፅምበት ቀን መሆኑን ይነግሩታል፡፡
ንጉሡን ያሳዘነው ሚኒስትር አንገት በሰይፍ ተቆርጦ የወደቀውን ሚኒስትር ሬሣ አዲሱ ሚኒስትር ተራምዶ ሲያልፍ ሕዝቡ በእልልታ ያጅበዋል፡፡ ይህን ጊዜ ወጣቱ ወደ አዲሱ ሚኒስትር ሄዶ የተሸከመውን መቶ መልህቅ ወርቅ ተረከበኝ ይለዋል፡፡ አዲሱ ሚኒስትርም ተገርሞ፡- ‹‹በርግጥ በኔ ሹመት ተደስተህ ነው ይህን ሁሉ ወርቅ የምትሰጠኝ?›› ቢለው፡- ወጣቱም፡- ‹‹አይደለም! አባቴ በኑዛዜው ሰዓት በዓለም ላይ እጅግ ሞኝ ሰው ፈልገህ ይህን ወርቅ ስጥልኝ ባለው መሠረት ነው የምሰጥህ ……›› ይለዋል፡፡
ሚኒስትሩም በልጁ መልስ ግራ ተጋብቶ፡- ‹‹እንዴት እንዲህ ትለኛለህ?›› አለው፤ ‹‹ዛሬ ተራምደው የተሾሙት ሚኒስትር ሬሣ ነገ የእርስዎን ሌላ እንደሚራመደውና እንደሚሾምበት ሳያውቁ የቀሩ በመሆንዎ ለኔ ከዚህ በላይ ሞኝ ሰው ላገኝ አልችልም፡፡ ስለዚህ ይህ ወርቅ ላንተ ነው የሚገባው…..›› በማለት ጥሎለት ሄደ፡፡
- ነፀብራቅ በዛብህ በገጹ እንዳወጋው
******
ሦስቱ የድንጋይ ክምሮች
ከሲድኒ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው የሰማያዊ ተራራ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ሦስት የድንጋይ ክምሮች አሉ፡፡ የበርካታ ቱሪስትም መስህብ ናቸው፡፡ ታዲያ የነዚህ ሦስት የድንጋይ ክምሮች አፈጣጠር ላይ በአውስትራሊያ የሚነገር የቆየ ተረት እንዲህ ይላል ፡-
አንድ አስማተኛ ሰው ከሦስት እህቶቹ ጋር የመዝናናት የእግር ጉዞ ያደርግ ነበር፡፡ በመሀሉ በአካባቢው ስሙ በጣም የገነነ ተዋጊ ጋር ተጋጠሙ፡፡
ተዋጊው የአስማተኛውን ሰው እህቶች ቆንጆዎች ስለሆኑ በምኞት እየተመለከታቸው፡-
‹‹ከነኝህ ውብ ኮረዶች መካከል አንደኛዋን ማግባት አለብኝ›› አለው፡፡
አስማተኛውም በተዋጊው ፍላጎት ብዙም ሳይደናገጥ በመረጋጋት እንዲህ መለሰለት፡- ‹‹ከሦስቱ አንደኛዋ ብቻ ካገባች የቀሩት ሁለቱ አስቀያሚ እንደሆኑ በማሰብ ስሜታቸው ይጐዳል፡፡
ስለዚህ ተዋጊዎች ሦስት ሚስት በአንዴ እንዲያገብ የሚፈቅድ ጐሳ እየፈለግሁ ስለሆነ አልድርልህም›› ብሎት በጉዛው ገፋበት፡፡
ለበርካታ ዓመታትም በመላዋ አውስትራሊያ እንዲህ ያለውን ሦስቱን እህቶቹን በአንዴ የሚያገባ ጐሳ ፍለጋ ብዙ ቢንከራተትም ሊያገኝ ግን አልቻለም፡፡ ‹‹ቢያንስ አንደኛችን እኮ ደስተኛ መሆን እንችል ነበር›› ከእህትማማቾቹ አንደኛዋ ለወንድሟ ተናገረች፡፡
ይሄኔ ዕድሜያቸው ገፍቶ፣ ውበታቸውም ደብዝዞ ብዙ በመንከራተትም ተዳክመውና ተሰላችተው ነበር፡፡
‹‹መሳሳቴን መካድ አይቻለኝም…›› ሲል አስማተኛው መንድማቸው ስህተቱን አመነ፡፡ ‹‹አሁን ግን ጊዜው ረፍዷል፡፡››
ይህን ካለ በኋላ ሦስቱን እህቶቹን በአስማት ወደ ሦስት የድንጋይ ክምሮች ቀየራቸው፡፡ የነዚህ የብዙ ቱራስቶች መስህብ የሆኑት ሦስቱ የድንጋይ ክምሮች አፈጣጠር እንግዲህ ይህንን ይመስላል፡፡
የአንድ ሰው ደስታ በትክክል የሌሎች ሐዘን ያለመሆኑን መመልከት የሚሻ ሁሉ ሄዶ ሊጐበኛቸው ይችላል፡፡ ዋናው መልክቱ ይኸው ነው፡፡
- ከነፀብራቅ ወጎች
*****
በጋ ለክረምት
ሁሉ ሰው ለነገ ያስባል፡፡ የመጨረሻው ግድ የለሽ ነኝ ባይ ነገን እያሰበ ይጨነቃል፡፡ እንቅልፍ ይነሳዋል፡፡ ዛሬ ማንም ሰው ሲተኛ ነገ እንደሚነቃ ጠብቆ ነው፡፡ እራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች እንኳን ነገን አስበው ነው ነገ እንደማይቀናቸው አስበው ነው- የነገው መልከ ቀና ቀጠሮ እንደማይሰምር ተሰምቷቸው ነው፡፡ ለነፍሴ አደርኩ የሚሉ ቅዱሳን እንኳን ነገ፣ ከነገ ወዲያ መምጫው የማይታወቅ እግዚአብሔር በመንግሥቱ እንዳይረሳቸው ይመኛሉ…….ዛሬ ደሞ ይሠራሉ፣ ዛሬ ይራባሉ፣ ዛሬ ይጠማሉ፣ ዛሬ ይቀድሳሉ ይዘምራሉ፣ ዛሬ ይመፀውታሉ፣ ዛሬ ደግ ይናገራሉ፡፡
ጉንዳንና ነፍሳት ዛሬ በዚህ በጋ ለፍተው ማስነው ለክረምት መኖቸውን ይደብቃሉ፡፡ መንቆራሪቶችና ጉርጦች በጋ ሲመጣ አፈር ለብሰው ከርመው በጋ አልቆ ጠል መውረድ ሲጀምር ከተኙበት ይነሳሉ፡፡ ነገ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ነገ ለዓለም ሕዝብ ህመም ነው፡፡ ከፕሬዝዳንት እስከ ለፕሬዝዳንት እስከሚያጨበጭበው፡፡ ከሰው እስከ እንስሳት የነገ ነገር የማያሳስበው የለም፡፡ ቢለያይ ‹‹የነገዎች›› እርዝመት ነው፡፡ ቢለያዩ ሊሰየም በሚከብድ ደረጃቸው ነው እንጂ የነገ ነገር የማያስደነግጠው የነገ መምጣት የማያባባው የለም፡፡
- አዳም ረታ ‹‹ግራጫ ቃጭሎች›› (1998)
*****
ህልም ረጋጭ እግሮች
በዚህ ሁል ጎዳና ፡ በዚህ ሁሉ መንገድ
በወጪና ወራጅ ፡ በሚመጣ እሚሄድ
ያቀናል በማለት ፡ ላገር ቀን ያወጣል
መሬት ላይ ያኖርነው ፡ ስንት ‘ልም ይረገጣል።
- በደመቀ ከበደ (ፌላሙኔሙኒም)
********
የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ወዳጆች የታሉ?
ወዳጆቼ…ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ቀንዲል ናት ሲባል እንዲሁ ወሬ እንዳይመስላችሁ። የዛሬን አያድርገውና ኢትዮጵያ ለጥቁሮች የኩራታቸው ምንጭ ነበረች። በዚያን ዘመን እንኳን ፈረንጅ ሊገዛው ፈረንጅ ምን እንደሆነ የማያውቅ ሕዝብ በዓለም ላይ አለ ከተባለ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነበር። እናም እንዲህ የሚኮሩባትን ሃገር ላንበርክክ ብሎ ጣሊያን መሬቷን የረገጠ ጊዜ ጥቁሮች ተቆጡ። ወዳጅነታቸውንና አጋርነታቸውን ለማሳየትም ተነሱ።
‹‹Race and U.S. Foreign Policy from 1900 Through World War II›› የተባለውን ሰነድ ጠቅሶ ዋይኔ ኤድዋርድ ማዶክ (Wayne Edward Maddock) አፍሪካ አሜሪካውያን ምን እንዳደረጉ ይህንን ታሪክ ያስነብበናል። (በዚያውም የዛሬዎቹ ጥቁሮች ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ከነመፈጠሯስ ያውቁ ይሆን? ብለን እንጠይቃለን።)
እ.ኤ.አ በጁላይ 14, 1935 ሃርለም ውስጥ በአፍሪካዊው ስደተኛ ሳሙኤል ዳንኤል የተመሠረተው ‹‹Pan African Reconstruction Association (P.A.R.A)›› የተባለ ተቋም አንድ ማስታወቂያ ለጥፎ ነበር።
ይህ ማስታወቂያ አፍሪካ አሜሪካውያን ኢትዮጵያን በግፍ የወረረውን ጣሊያንን ለመከላከል እንዲሰለፉ የሚጠይቅ የበጎ ዘማች ወታደሮች ምዝገባ ነበር። ማይክል ክሪን (Michael L. Kreen) የተባለው ደራሲ እንደጻፈው ከሆነ ከሳምንት በኋላ የወጡት የአፍሪካ አሜሪካውያን ጋዜጦች እንዳተቱት በኒውዮርክ ከተማ ብቻ አንድ ሺህ የሚጠጉ ወዶ ዘማች ጥቁሮች ኢትዮጵያን ከጣሊያን ወረራ ለመከላከል በሚደረገው ዘመቻ ላይ በፍቃደኝነት ለመዝመት ተመዝግበዋል።
ይህ ብቻ አይደለም። በሌሎቹ የአሜሪካ ግዛቶችም ብዙ ጥቁሮች ከጣሊያን ጋር በመዋጋት ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት ተመዝግበዋል።ለምሳሌ በቺካጎ 8ሺህ፣በዲትሮይት 5ሺህ፣ በካንሳስ ሲቲ 2ሺህ፣ በፊላደልፊያ 1ሺህ 500 ወዶ ዘማቾች መመዝገባቸውን ጋዜጦቹ አትተዋል።
ይህ ምዝገባ ከመጠናቀቁ በፊት ታዲያ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ማስጠንቀቂያ ሰጡ። ‹‹ማኅበሩ የሚያካሂደው ምዝገባ አሜሪካውያን ዜጎች አሜሪካ ወዳጅ የሆነቻቸውን መንግሥታት ለመውጋት በሚደረግ ጦርነት ላይ ለመሳተፍ እንዳይመዘገቡ የሚከለክለውን የፌዴራሉን ሕግ መጣስ በመሆኑ ድርጊቱ ወንጀል ነው›› አሉ። (በወቅቱ ጣሊያን የአሜሪካ ወዳጅ ሃገር ነበረች)።
በዚህ የተነሳ ማኅበሩ የወዶ ዘማቾቹን ምዝገባ ለማቋረጥ ተገደደ። ኢትዮጵያ ዛሬስ እንዲህ ዓይነት ወዳጆች ይኖሯት ይሆን?
- መላኩ ብርሃኑ በገጹ እንደከተበው