Sunday, June 16, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኤርትራ መንግሥትና ኢትዮጵያ – ሥጋትና መልካም አጋጣሚዎች

ክፍል ሁለት

           በአዳነ አበራ

  ባለፈው ሳምንት የክፍል አንድ ጽሑፍ በኤርትራ የተጨናገፈውን ተስፋና የአገር ግንባታ ሙከራ፣ አላላውስ ያለው የግለሰብ አምባገነንነትን፣ የኢሳያስ መንግሥት ዴሞክራሲን እንደ ቅንጦት ማየቱን፣ በኤርትራ የሕግ የበላይነት አለመኖሩንና በተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምክንያት የሌለ ጠላት መፍጠርን በተመለከተ ቀርቧል፡፡ አሁን ሁለተኛው ክፍል የተለያዩ ጉዳዮች ተስተናግደውበታል፡፡

የወታደር ክፍሎችና የሕግዴፍ አመራሮች ያለውን ያስቀጥላሉ?

እንደ ዓለም አቀፍ የቀውስ [አጥኚ] ቡድን ሪፖርት በሕግዴፍ (ሻዕቢያ)፣ በመከላከያ ኃይሉና በደኅንነቶች የጥቅም ትስስር ሊኖር ይችላል። ሀብትን ማከማቸት የትስስሩ ዓላማ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ አካባቢያዊ ሰላምና ትብብር እንዳይታሰብ ያደርገዋል። እንደ ኢሳያስ ሁሉ እነዚህ አካላት የወረራ ሥጋት ወሬን ወታደሮችን ለመመልመል ይጠቀሙበታል። የግጭት ውጫዊ ፖሊሲም የባለጊዜው አሠራር (modus operandi) ሆኖ ይቀጥላል። ታጣቂ ኃይሎችንም መርዳቱን በእምቢተኝነት ይገፋበታል። ይህ የወታደሮች አምባገነንነት በአካባቢው በተለይም ለኢትዮጵያ አደጋን ይዞ ይመጣል። በዚህ መሀል በሕግዴፍ፣ በመከላከያ ኃይሉና በደኅንነቶች መካከል ሽኩቻ ሊኖር እንደሚችል መገመት ቀላል ነው።

ኤርትራ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት መልካም ልታደርግ ትችላለች?

ይኼ የመላምት ሐሳብ ከላይኛው ጋር በከፊል ተመሳሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት ሥልጣን ከላይ በጠቀስናቸው አካላት ሊያዝ ይችላል የሚል እሳቤ አለ። ይሁን እንጂ ከጎረቤት አገሮች የሚደርሰውን አፀፋ በመሥጋት ወይም በመነጠልና በማዕቀቦች አቅም መፍረክረክ፣ የውጭ ግንኙነቱን ሰላማዊ በማድረግ ትብብርን ሊፈጥር ይችላል። ይህም ዴሞክራሲ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲሰፍን ብቻ ነው እውን የሚሆነው።

በኢሳያስ የሥልጣን ዘመን ለውጥ ማሰብ አዳጋች እንደሆነ ሁሉ፣ በእኩል ይህን ዓይነቱም ለውጥ በወታደሮቹና የሕግዴፍ አመራሮች ይመጣል ብሎ ማሰብ ቀላል አይደለም። ምክንያቱንም ዓለም አቀፍ የቀውስ [አጥኚ] ቡድን ሲገልጽ፣ የፖሊሲ ለውጥ ማምጣት ማለት እስካሁን የቆየው ኤርትራ በወራሪዎች ተከባለች ፕሮፓጋንዳን ሊያከስም፣ ወታደሮችን ማሰናበትንና የፖለቲካ መድረኩን ክፍት ማድረግን፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ በኢኮኖሚው ላይ ከባድ ተፅዕኖን ስለሚያመጣ ዕውን መሆኑን ጥርጥር ውስጥ ይከተዋል።

የእርስ በርስ ጦርነት

ዳን ኮኔል እ.ኤ.አ. በ2011 ‘’From Resistance to Governance፡ Eritrea’s Trouble with Transition’’ በሚል በጻፉት ጽሑፍ፣ ከኢሳያስ በኋላ በአገሪቱ ላይ የእርስ በርስ (በተለይም በወታደሩ ክፍል) ሊከሰት እንደሚችል ገምተዋል። እንደ ዓለም አቀፍ የቀውስ [አጥኚ] ቡድን ሪፖርት የዚህም መነሾ በሽግግር ወቅት መሣሪያ የያዙ ክፍሎችን ገለልተኛ በማድረግ፣ ሰላምን ሊያመጣ የሚችል በአገሪቱ ላይ አቅም ያለው ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ አለመኖር ነው። ይህ አደጋ ሊገዝፍ የሚችለው ደግሞ ብሔር ተኮር ታጣቂ ኃይሎች አስቀድሞ ብረት ማንሳታቸው፣ በሙስሊሙና በክርስቲያኑ፣ በደጋውና በቆላው ነዋሪ መካከል ያለው ቅራኔ ነው። ይህንን ቅራኔ ተቀናቃኝ የጦር አባላት ለመቀስቀስ ከሞከሩ የሚፈጠረው ችግር ከፍተኛ ይሆናል። ሀብታሙ አለባቸው እንደገለጹትም በኤርትራ በአብዛኛው ወታደራዊ ልምድ ያለው ሕዝብ መኖሩ አሥጊ ነው።

ይህ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ሥጋትን ይደቅናል። ምክንያቱም ሁለቱ አገሮች ድንበር እንደ መጋራታቸው አሸባሪ ቡድኖች ሊፈነጩበት ወደ ኢትዮጵያም መግቢያ ቀዳዳ እንዲያገኙ ሊያስችላቸው ይችላል።

የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት

ኤርትራ በብጥብጥ የምትታመስ ከሆነ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንደሚኖር መገመት ይቻላል። የውጭ ኃይሎች ስንል ከአካባቢው (ሱዳን፣ ጂቡቲና ኢትዮጵያ) እና ከዓለም አቀፍ በተለይም አሜሪካ ማለታችን ነው። ጣልቃ የመግባት ሐሳብም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስጠበቅና ጽንፈኝነትን ለመከላከል ይሆናል። 

አሜሪካ በኤርትራ ላይ የሚኖራት ፖሊሲ ምን ሊሆን እንደሚችል ዳን ኮኔል በ2009 “Eritrea and the United States: towards a new US Policy’’ በሚል ጥናታቸው ገልጸዋል። እንደ ኮኔል ገለጻ አሜሪካ ሦስት አማራጮችን ልትጠቀም ትችላለች እነዚህም፡-

  1. በኤርትራ ሰበብ ብጥብጥና ሽብር ወደ ሌሎች የአካባቢው አገሮች እንዳይዛመት መከላከልና መነጠል (Isolation and Containment)፣
  2. ጽንፈኝነትና አክራሪነትን ለመከላከል ከኤርትራ መንግሥት ጋር ቁጥብ ገንቢ ግንኙነትን ማድረግ፣
  3. የመንግሥት ለውጥ ከውስጥ እንዲመጣ መደገፍ የሚሉ ናቸው።

የአውሮፓ ኅብረት በዓለም አቀፍ የቀውስ [አጥኚ] ቡድን ተደጋጋሚ ሪፖርቶች (2010፣ 2013 እና 2014) ጥቆማ መሠረት የገበያና አጠቃላይ የልማት እገዛን በማድረግ ጣልቃ ሊገባ ይችላል። ቱርክ፣ ኳታር፣ ኢራን፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ እያንዳንዳቸው ኤርትራ ላይ ባዩት ጥቅም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እጃቸውን ሊያስገቡ ይችላሉ።

ከዚህ በላይ የኢሳያስ መንግሥት እንዲሁም የመሪ ለውጥ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለመመልከት ሙከራ አድርገናል። ቀጣዩ ክፍል እነዚህ ያነሳናቸው የመላምት ሐሳቦች በኢትዮጵያ ላይ የሚኖራቸው አንድምታ ምን ሊሆን እንደሚችል እናስሳለን። በተጨማሪም ለሚመጡ ለውጦች የኢትዮጵያ መንግሥት ምን ያድርግ የሚለውን እናያለን።

በኢትዮጵያ ላይ የሚኖረው አንድምታና የስትራቴጂ አማራጮች

በክፍል አንድ በኤርትራ የሚከሰቱ ክስተቶች በኢትዮጵያ ላይ በአንድም በሌላም መንገድ በጎም ይሁን ክፉ አንድምታዎች እንዳላቸው ጠቁመን አልፈናል። ኤርትራ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሥልጣን ዘመንና ከኢሳያስ በኋላ በሚል የመላምት ሐሳቦችን በማንሳት ተነጋግረናል። ከዚህ በመነሳት በዚህኛው ክፍል በኤርትራ የሚከሰቱ ለውጦች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚኖራቸውን አንድምታ ለመዳሰስ እንሞክራለን።

ሁሉም አገሮች በዓለም አቀፍ ግንኙነት ለአገሬ የሚለውን ብሔራዊ ጥቅም በመቅረፅ ለማስጠበቅ ይንቀሳቀሳል። የኢትዮጵያ መንግሥትም አገሪቱ በውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴዋ መጠበቅ የምትሻውን ብሔራዊ ጥቅም በውጭ ጉዳይና በአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ገልጾታል። ስለሆነም በኤርትራ የሚከሰቱ ለውጦች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አንድምታና ተፅዕኖ ለመረዳት መነሻችን ይኼው ሰነድ ይሆናል።

ለአገሪቱ ለአደጋ መጋለጥ ዋነኛ ምንጩ ውስጣዊ ሲሆን፣ ይኼም ከፍተኛ ድህነት፣ የዴሞክራሲ እጦትና ሰላም አለመኖር የሚያስከትሉት እንደሆነ የሚያምነው መንግሥት ለውጭ ተጋላጭነታችን ከዚህ የሚመነጭ እንደሆነ ይገልጻል። በውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ላይ በጉልህ እንደተገለጸው፣ ኢትዮጵያ አካል የምትሆንባቸው ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ለአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም(ሞች)ን ለማስገኘት የታለሙ ናቸው። እንደ ኤፌዲሪ መንግሥት እነዚህ ብሔራዊ ጥቅሞች ተብለው የተጠቀሱትም ፈጣን፣ ዘላቂና ፍትሐዊ ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም ናቸው።  እንደ  መንግሥት እምነት እነዚህ ዓላማዎች የአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሻቸው ናቸው። በመሆኑም በኤርትራ ጊዜ የሚያመጣቸው አዎንታዊም ሆኑ አሉታዊ ለውጦች ከዚህ ማዕዘን የሚታዩ ናቸው።

ኢሳያስ የሚመሩት መንግሥት አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ፣ እንዲሁም ኢሳያስ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ የሥልጣን ወንበሩን የሕግዴፍ አመራሮች፣ ጄኔራሎችና ሚስጥራዊ የደኅንነት ኃይሎች ከያዙት በኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ቡድኖች የተባሉት ኃይሎችን ኤርትራ መርዳቷ እንዳለ ይቀጥላል። ኤርትራ የተጣሉባትን ማዕቀቦች ችላ በማለት በፋይናንስ፣ በፖለቲካ፣ በሥልጠናና በሎጂስቲክስ አልሸባብን ጨምሮ ነፍጥ ያነገቡ ተቃዋሚ ኃይሎችን በመደገፍ የኢትዮጵያን ልማትና ሰላም ልታደናቅፍ ትችላለች። ከዚህ በተጨማሪም የኤርትራ መንግሥት በአገሪቱ የሚደረጉ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች በሰርጎ ገቦች አማካይነት በማጥቃት አገሪቱን በውጭው ዓለም የሥጋት ሥፍራ ተደርጋ እንድትወሰድ ሊንቀሳቀስ ይችላል። ለዚህም ከማዕድን ዘርፍ እያገኘ ያለው ገቢ አቅሙን ይጨምርለታል።

በኤርትራ መሠረታዊ የፖሊሲ ለውጥ ሳይመጣ ማዕቀቡ የሚነሳ ከሆነ፣ ለኢትዮጵያ አደጋን ይጋብዛል። የማዕቀቡ መነሳት ለኤርትራ መንግሥት የልብ ልብ የሚሰጠው ሲሆን፣ እጅግ ድብቅ በሆነ ዘዴ ማሸበሩን እንዲቀጥል ይረዳዋል።

ሌላው ኤርትራ በእርስ በርስ ሽኩቻ ከቀጠለችና መዳከም ካገኛት እንደ አልሸባብ ላሉ የጽንፈኛ ተዋጊዎች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ሲሆን፣ ከዚህ ተነስቶ ኢትዮጵያን ለማጥቃትና ዜጎችን ለማፈን ሊረዳው ይችላል።

ሌላው ኤርትራ የጂቡቲ መንግሥት ተቃዋሚዎችን በመርዳት ወይም ጦርነት በመክፈት የኢትዮጵያን የገቢና የወጪ ንግድ ዋና መስመር የሆነውን የጂቡቲ ወደብን  ልታሰናክል ትችላለች። ሌተና ኮሎኔል ተመስገን ግደይ (2012) ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ በጂቡቲ በኩል በመሆኑ፣ በዚህ የንግድ መስመር ላይ የሚፈጠረው ችግር ለኢትዮጵያ ጉዳት ይዞ ይመጣል ሲሉ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የሰላምና የፀጥታ አንድምታ ባጠኑበት ጥናታቸው ገልጸዋል። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ በጂቡቲ ያለውን እጅግ ጠቃሚ የንግድ መስመርን ከጥቃት ለመከላከል ዝግጁ እንደሆነች መግለጻቸው ይታወሳል።

ያልተቋጨው የአልጀርስ ስምምነትም በሁለቱ አገሮች መካከል ችግር ሊቀሰቅስ ይችላል። የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔን ተከትሎ ኢትዮጵያ በውሳኔው ላይ ውይይት መጠየቋ፣ እንዲሁም ኤርትራ ከድንበር ማካለሉ በፊት ለምንም ዓይነት ውይይት አሻፈረኝ ማለቷ የአልጀርስ ስምምነትን ሰዓት ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ አድርጎታል። ኤርትራ የድንበር ማካለሉ በአፋጣኝ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲደረግ ጫና ለመፍጠር በኢትዮጵያ ድንበሮች ላይ ጥቃቶችን ልትፈጽም ትችላለች።

የኢሳያስ መንግሥት ለውጥ ያመጣል ብሎ ለመገመት አዳጋች ቢሆንም፣ በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ግፊቶች ለውጥ ካመጣ ለአካባቢው በተለይም ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ፣ ጊዜ ሳይባክን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር ዝግጅት ያስፈልጋል። 

ለኢትዮጵያ ሥጋት በመሆን ግዝፈት ያለው ኢሳያስ ከሥልጣን በአንድም በሌላም መንገድ ከተወገደ በኋላ ሊፈጠር የሚችለው የሥልጣን አለመደላደል ነው። የሥልጣን ክፍተቱን ለመሙላት የሕግዴፍ አመራሮች፣ ጄኔራሎችና ሚስጥራዊ የደኅንነት ክፍሎች ሽኩቻ ውስጥ ከገቡ፣ በተለይም የብሔርና የሃይማኖት ቅሬታን ለፖለቲካ ጥቅማቸው እነዚህ አካላት ከተጠቀሙበት፣ የሚፈጠረው መተላለቅ ለአሸባሪ ቡድኖች መልካም አጋጣሚ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያም ለመግባት ቀዳዳ ሊያገኙ ይችላሉ።

ከኢሳያስ በኋላ በሚተኩ አመራሮች ለውጥ ከመጣ ለኢትዮጵያ ጥሩ ሁኔታን ይፈጥራል። በመሆኑም ፈጣን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች ለመተባበር፣ እንዲሁም በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት መትጋት ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ያለውን እንቅስቃሴ በንስር ዓይን ማየት ይገባዋል። በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ላይ እንደተቀመጠው ዋናው ግብ ልማትን ማረጋገጥና ዴሞክራሲን መገንባት እንደመሆኑ ሥጋቱ እነዚህን ግቦች ለማሳካት የእንቅፋት ድንጋይ ሆኖ የሚመጣው ነው። የኤርትራ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሥጋት መሆኑ እሙን ነው። በመሆኑም ሥጋቱን ለመቀነስ አልያም ጉዳቱን ለማጨናገፍ  መንግሥት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ሊጠቀም ተገቢ ነው። ስለሆነም ከዚህ በታች መወሰድ ስላለባቸው ጉዳዩች የተወሰኑ አማራጮችን እንጠቁም።

የኤርትራ መንግሥት የተጣለበትን ማዕቀብ ለማስነሳት እያደረገ ያለውን ጥረት ውጤታማ እንዳይሆን በንቃት መሥራት ተገቢ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰኑ የውጭ አገር አዛኞች የማዕቀቡ ቢነሳ ጥያቄ ተደፋፍረው የኤርትራ ዲፕሎማቶች በተለያዩ አገሮች በመዞር ማዕቀቡ እንዲነሳ እያደረጉ ያለው ጥረት በንቀት የሚታይ አይደለም። መሠረታዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሳይደረግና ታጣቂ ኃይሎችን መርዳቱን እስካላቆመ ድረስ ማዕቀቡ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ በተለያዩ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ልታደርግ ይገባል። ለዚህም የዲፕሎማሲ አቅሟን ማሳደግ፣ የኤርትራ መንግሥት ተግባርን የሚያወግዙ ወዳጅ አገሮችን ማስፋት ሊወሰዱ ተገቢ የሆኑ ዕርምጃዎች ናቸው።

ሌላው የአገሮች ጉባዔን (Multilateralism) ለዚሁ ተግባር ልንጠቀምበት ይገባል። ኢትዮጵያ በርካታ አገሮችን በሚያሳትፉ መድረኮች በሙሉ አቅም በመሳተፍ በኤርትራ ላይ ያላት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ከግብ ልታደርስ አስፈላጊ ነው። ሥጋቱ በኢትዮጵያ ብቻ እንደማይገደብ በማሳወቅ በአኅጉርና በዓለም አቀፍ ጉባዔዎች (ኢጋድ፣ አፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ተመድ እና ሌሎች) ላይ ያሉ መልካም አጋጣሚዎች ኤርትራ ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር እስካልቻለች ድረስ፣ ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንድትነጠል የነውጥ ተግባሯም ከፍተኛ ውግዘት እንዲደርስበት ማድረግ መልካም ነው።

አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ትኩረት ካደረገ ዲፕሎማሲ ከፍ ወዳለ ደረጃም ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ ይታያል። በዓለም አቀፍም ሆነ በአኅጉር ደረጃ ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች ላይ ሙሉ በሙሉ ከመተማመን፣ ግለሰቦቹ የወከሏቸው አገሮች ሐሳብ እንዲሆን ማድረግ ጥሩ ውጤት ያመጣል። አምባሳደሮችን ማዕከል ማድረግ የሚያስገኘው ለውጥ የለም ባይባልም፣ ግለሰቦች በተለያዩ ጊዜያት መለዋወጣቸው የኢትዮጵያ ዓላማ የሚጠበቀውን ግብ እንዳይመታ ሊያደርገው ይችላል።

ሽብርና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ከአሜሪካ ጋር አጠናክሮ መቀጠልም አወንታዊ ውጤት ያስገኛል። በተለይም በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲቀጥል የአሜሪካ ድጋፍ ተፈላጊ ነው።

እንደ ስትራቴጂ አማራጭ እጅግ ሚዛን የሚደፋው አሁን ያለው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኤርትራውያን ስደተኛ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ማስተናገድ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ይህ ድርጊት የኢሳያስን ‘የጠላት ኢትዮጵያ’ እሳቤን በመሸርሸር ለኢትዮጵያ በአንድ በኩል ሕዝብ ለሕዝብ ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል፣ ሁለተኛ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ምሥጋናን ያስገኝላታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኤርትራ ጋር ግንኙነትን በመፍጠር ላይ ከሚገኙት አገሮች ጋር የቀረበ ወዳጅነት መፍጠርም ያሻል። እ.ኤ.አ. የ2013 የኦክስፎርድ አናላይቲካ ዴይሊ ብሪፍ (Oxford Analytica Daily Brief) የኤርትራ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተስፋዋን ከፍ አድርገውታል ሲል ገልጿል። ለዚህም ግብ ገጽታዋን ለመቀየር በዋነኛነት ከውጭ አገር የማዕድን አምራች ተቋማት ጋር ግንኙነትን በመፍጠር ላይ ትገኛለች። የኤርትራ መንግሥት በወርቅና በፖታሽ ምርት ላይ ማተኮሩ ከተለያዩ ማዕቀቦች ራሱን እንዲያድን ይረዳዋል።

ኳታር በቅርቡ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በተለይም በኤርትራ  ቁልፍ ተጫዋች ለመሆን እየተንቀሳቀሰች ነው። ከኢንቨስትመንት በተጨማሪ የፋይናንስ ዕርዳታ ለኤርትራ የምታደርገው ኳታር ነች። ኢራንም ተመሳሳይ ድጋፍን ለኤርትራ መንግሥት ታደርጋለች። የኦክስፎርድ አናላይቲካ ዴይሊ ብሪፍ እንደጠቆመው፣ ኢራንና ኤርትራ ለምዕራባውያን ባላቸው ጥላቻ ማበራቸው የማይቀር ነው። ከአፍሪካ አኅጉር ደቡብ አፍሪካ በኤርትራ የማዕድን ልማት ለመሳተፍ ፍላጎት አድሮባታል። ፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ አስመራ የቀጥታ የአውሮፕላን በረራ መጀመር፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ለተፈጠረው ግንኙነት አመላካች ነው። ለዚህም ይመስላል ደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ. በ2011 በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ልዝብ እንዲሆን (Waterdown) ድምፅ የሰጠችው።

ሩሲያና ቻይናም ለኢኮኖሚና ለጦር ልምምድ ኤርትራን አማትረዋል። እ.ኤ.አ. በ2009 እና በ2011 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሩሲያና የቻይና መኖር ኤርትራን ረድቷታል። እ.ኤ.አ. በ2011 በተጣለው ማዕቀብ ሩሲያ ድምፀ ተአቅቦ በማድረግና ማዕቀቡን በማለዘብ አጋርነት አሳይታለች። ቻይና በሁለቱም ማዕቀቦች ድምፀ ተአቅቦና ማለዘብ አድርጋለች። ከዚህ በተጨማሪም በማዕድን ሴክተሩ ላይ ሊጣል የታሰበውን የመመርያ ሰነድ በተደጋጋሚ ተቃውማለች።

በቅርቡ ጊሳፊካ ኦንላይን የተባለ ድረ ገጽ አንድ የኤርትራ ዲፕሎማትን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ሩሲያ በኤርትራ የጦር ልምምድ ልታደርግ ነው ብሎ ነበር። በጦር ልምምድ ብቻም ሳይገታ በኤርትራ ቀይ ባህር ላይ ወታደራዊ ቤዝ እንዲኖራት ዕቅድ እንዳላትም አስነብቧል።

ኢትዮጵያ ከላይ ከጠቀስናቸው አገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በማድረግ መነጋገር ይኖርባታል። ይህም ኤርትራ በአካባቢው በተለይም በኢትዮጵያ ላይ የምታደርሰውን ብጥብጥ እንድታቆም ማግባባት እንዲችሉ ለማድረግ ይሆናል።

የዚህ ጽሑፍ መደምደሚያ የሚሆነን የፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ (1998) ገለጻ ነው። ሕገ መንግሥትና የሕዝብ ሸንጎ የማይገዛው፣ ያልተሰናበቱ ወታደሮችና ወታደሮችን ባለማቋረጥ በመመልመል ራሳቸውን ያበለጸጉ አመራሮች ባሉበት፣ የፖለቲካም ሆነ የሕግ ቁጥጥር የሌለበት የኤርትራ አመራር ባሻው ጊዜን ጦርነት ሊያውጅ ይችላል። በእርግጥ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ቋሚ ሥጋት ሆኖ ይቀጥላል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles