Sunday, December 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኤድስ መያዝንና ሞትን መቀነስ የሚለው የሚሌኒየሙ ግብ መሳካቱን ተመድ አስታወቀ

በኤድስ መያዝንና ሞትን መቀነስ የሚለው የሚሌኒየሙ ግብ መሳካቱን ተመድ አስታወቀ

ቀን:

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በኤችአይቪ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥርና ከኤድስ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን ሞት ለመቀነስ ያስቀመጠውን የሚሌኒየም ግብ ማሳካቱን አስታወቀ፡፡ እንደ ድርጅቱ ገለጻ፣ እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ ባሉት ጊዜያት በኤችአይቪ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በ35 በመቶ መቀነስ ተችሏል፡፡ ከኤድስ ጋር በተያያዘ የሚደርሰው ኅልፈት ደግሞ በ41 በመቶ ቀንሷል፡፡

ባለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ዜናውን ይፋ ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን ናቸው፡፡ ‹‹ዛሬ ላይ 15 ሚሊዮን ሰዎች ፀረ ኤችአይቪ ህክምና እየተደረገላቸው ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከበሽታው እንደተጠበቁ ነው፡፡ በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብም እየዳነ ነው፡፡ ያለምንም ጥርጥር ሕክምናውን ማሳደግ እንደምንችል አረጋግጠናል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ከኤችአይቪ ነፃ ወደሆነ ትውልድ እየተቃረብን ነው ማለት ነው፤›› ብለዋል በመግለጫቸው፡፡

ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች በዓለም ላይ በኤድስ ከሚጠቁ አገሮች ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡ አሁን ግን ይህ እየተለወጠ ነው፡፡ እንደ ምሳሌ ከሚነሱ አገሮች አንዷ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ናሚቢያና ሴኔጋልም ይጠቀሳሉ፡፡

በሦስቱ አገሮች በኤችአይቪ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፡፡ ድርጅቱ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ለበሽታው የሚሰጠው ህክምና በዓለም ላይ ወደ 7.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ታድጓል፡፡ ሕክምናው ወደ 1.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት ቫይረሱ ከእናቶቻቸው እንዳይተላለፍባቸው አስችሏል፡፡

የዩኤን ኤድስ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ሚካኤል ሲዲቤ እንደተናገሩት፣ ከስድስት ወይም ስምንት ወራት በኋላ ኤችአይቪ ያለባቸው ሰዎች በየቀኑ መድኃኒት መውሰድ ያቆማሉ፡፡

ዳይሬክተሩ ‹‹በቅርቡ በአራት ወይም በስድስት ወር አንዴ የሚወሰድ ክትባት ይኖራል፡፡ ይህም ለድሃ ሰዎች መድኃኒቱን የምናደርስበትን መንገድ የሚቀይር ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

ክትባቱ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የሚያወጡትን ወጪ ይቀንሳል፡፡ ታማሚዎች ረጅም እንዳይጓዙ፣ በየቀኑ መድኃኒት መውሰድ ካልቻሉ ሊደርስባቸው የሚችለውን የአቅም መዳከም እንደሚያስወግድም አክለዋል፡፡

የበሽታውን ስርጭት በመቀነስ ረገድ የተመዘገበው ውጤት አበረታች ቢሆንም አሁንም ሌሎች ዕርምጃዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በ2014፣ 2 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል፡፡ ከ13 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት አንዱን ወይም ሁለቱንም ቤተሰቦቻቸውን ከኤድስ ጋር ተዛማጅ በሆኑ ምክንያቶች አጥተዋል፡፡

በዚህ ዓመት ማገባደጃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚሌኒየሙን ግብ በዘላቂ ልማት ግቦች (በሰስቴነብል ዴቨሎፕመንት ጐልስ) ይተካል፡፡ በ2030 የኤድስ ወረርሽኝ ማብቂያ እንደሚሆንና በወቅቱ ሁሉም ታማሚ ሕክምናውን ማግኘት እንደሚችል ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ በ2015፣ 15 ሚሊዮን ሰዎች ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ተጠቃሚ ለማድረግ ማለሙ ይታወሳል፡፡ እስካሁን ለኤችአይቪ መድኃኒት ባይገኝም በሽታውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚረዱ መድኃኒቶች ተገኝተዋል፡፡ የቫይረሱን መጠን ዝቅ ለማድረግ የሚያስችሉ ወደ 25 የሚደርሱ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶች በኤፍዲኤ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...