Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኢትዮጵያ ከአምስት ቢሊዮን በላይ ልዩ ልዩ የዛፍ ችግኞች ይተከላሉ

በኢትዮጵያ ከአምስት ቢሊዮን በላይ ልዩ ልዩ የዛፍ ችግኞች ይተከላሉ

ቀን:

በመላ ኢትዮጵያ በዚህ ወር ውስጥ ከ5.3 ቢሊዮን በላይ ልዩ ልዩ ዓይነት ችግኞች ይተከላሉ፡፡ ችግኞቹ የሚተከሉት በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋና በሁሉም ክልሎች ሲሆን፣ 80,000 አገር በቀል የዛፍ ችግኞች የሚተከሉት በእንጦጦ የተፈጥሮ ፓርክ ውስጥ ይሆናል፡፡

በሁለቱ ከተሞችና ክልሎች የሚካሄደውን የችግኝ ተከላ የሚያስተባብሩት የአካባቢ ጥበቃ ተቋማት ሲሆኑ፣ በተፈጥሮ ፓርክ ውስጥ የሚከናወነውን ተከላ ደግሞ የሚያቀናጀው የኢትዮጵያ የቅርስ ባለአደራ ማኅበር ነው፡፡

አቶ ደባሶ ባይለየኝ የአካባቢና ደን ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንደገለጹት፣ የችግኝ ተከላው ከመከናወኑ በፊት በተካሄደው የቅድመ ተከላ ወቅት ላይ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል፡፡ በሁለቱ ከተሞች አስተዳደርና በሁሉም ክልሎች በተከናወነው የጥናት ዳሰሳ፣ ለችግኝ ማፊያ የሚስማሙ ቦታዎችን በመምረጥና በችግኝ አፈላል፣ ችግኞቹ ለምን አገልግሎት እንደሚውሉ በመለየት፣ በዕቅድ ሥራ፣ ለችግኝ ማፍያ በሚያስፈልገው በጀት፣ በሠለጠነ የሰው ኃይልና በጉድጓድ አዘገጃጀት እንቅስቃሴ ላይ የተወሰኑ እጥረቶች መኖራቸው ተደርሶበታል፡፡

እነዚህ እጥረቶች ቢኖሩም በተከላ ወቅት የደረሱ ችግኞች እየተወሰዱ እንደሚተከሉ፣ አቶ ደባሶ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሪት መሶበወርቅ ቅጣው የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደገለጹት፣  ማኅበሩ ያዘጋጀው ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ አገር በቀል የዛፍ (ግራር፣ ጥድ፣ ኮሶ፣ ወይራ ወዘተ) ችግኞች መሆኑን ጠቅሰው፣ ችግኞቹም የሚተከሉት የማኅበሩ አባል ለሆኑና አባል ላልሆኑ ድርጅቶች በመስጠት ነው፡፡

ችግኞቹን የሚረከቡ ድርጅቶች እንጦጦ ተራራ ላይ ተከልሎ በተሰጣቸው ሳይት ላይ እንዲተክሉ፣ ከተከላውም በኋላ በየወቅቱ እየተመላለሱ እንዲንከባከቡ  ይመከራል፡፡ ተከልሎ በተሰጣቸው ሳይት ውስጥ የድርጅታቸው ስም የተጻፉባቸው ሰሌዳዎች ወይም ማስታወቂያዎችም ይተከላሉ፡፡ ችግኞቹ ፀድቀው ካደጉ በኋላ የየድርጅቶቹ ሠራተኞች እየመጡ የሚናፈሱበት፣ የሚዝናኑበትና የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ቦታ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር በእንጦጦ ተራራ ላይ አገር በቀል ደንን በማልማት የተፈጥሮ ፓርክ ለማቋቋም እንዲረዳው 1,300 ሔክታር መሬት በ1988 ዓ.ም. ከመንግሥት እንደተሰጠው ሥራ አስኪያጇ ጠቅሰው፣ እስካሁን ባካሄደው እንቅስቃሴ በ500 ሔክታር መሬት ላይ የነበረውን ባህር ዛፍ በማምከን በምትኩ ለአካባቢው ተስማሚ በሆኑ አገር በቀል ዛፎች እንዲለማ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ባህር ዛፎቹ እንዲከስሙ የተደረገበት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት ብዝኃ ሕይወትን በመመለስ የተፈጥሮ ፓርክ ለማቋቋም ሲሆን፣ ሁለተኛው  ምክንያት ደግሞ ባህር ዛፍ ሥሩ በመሬት ውስጥ እየተስፋፋ ስለሚሄድ አፈርን የመሸርሸር፣ ውኃን የመምጠጥና በአቅራቢያው ያሉትንም ዕፅዋቶች እንዲሞቱ ወይም እንዳያድጉ የማድረግ ባህሪ ስላለው ነው፡፡

በዚህም የተነሳ ማኅበሩ እስካሁን ድረስ በአገር በቀል ዛፎች እንዲለሙ ባደረጋቸው አካባቢ ምንጮች መፍለቃቸውን፣ ሚዳቋና አነር የመሳሰሉት ልዩ ልዩ ዓይነት የዱር እንስሳትና አዕዋፋት መኖር መጀመራቸውንና በአሁኑ ጊዜም ወደ 13 ምንጮች መጎልበታቸውን ተናግረዋል፡፡

ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ትልቅ አደጋ ውስጥ በወደቀበት ሰዓት ይህ ዓይነቱን የተፈጥሮ ሥራ ማከናወን ትልቅ ግምት ይሰጠዋል፡፡ ማኅበሩ ባከናወነው የተፈጥሮ ጥበቃ ሥራ በ2002 ዓ.ም. ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር ተወዳድሮ በአዲስ አበባ ደረጃ አንደኛ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ሁለተኛ በመሆን ልዩ ልዩ ሽልማት ተቀብሏል፡፡

አቶ ተስፋዬ ኃይሉ በማኅበሩ የተፈጥሮ ቅርስ ልማት ጥበቃና ክትትል ምክትል ሥራ አስኪያጅ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሚገኙና ለሙከራ በተመረጡ 52 የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለተቋቋሙት የኢንቫይሮንመት ክበብ አባላት በየትምህርት ቤቶቻቸው አገር በቀል ዛፎች እንዲያለሙ ማኅበሩ ሁሉን አቀፍ ማበረታቻ አድርጎላቸዋል፡፡

‹‹አረንጓዴ ትውልድ መቅረጽ›› በሚለው መርሕ መሠረት፣ ማኅበሩ ማበረታቻ ያደረገው ችግኞችንና ለልማት ሥራ የሚውሉ ልዩ ልዩ ዓይነት የመገልገያ መሣሪያዎችን በነፃ በመስጠት ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ለእንቅስቃሴው አበርክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...