Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንዳያዳልጠን!

ሰላም! ሰላም! ይኼውላችሁ ሰሞኑን ሠፈራችን ዝናብ አልጥል ብሎ ጉድ ሲባል ሰነበተ። አንድም በኑሮ አንድም በሸረኞች ጫና ሰው ራሱን ሲጥል እየታዘብን ግን ጉድ አንልም። እና ስንት የዘጋን ወዳጅ ዘመድ እያለ፣ ስንት ሥራ ያውጣችሁ ያለን ሹም ለተጠያቂነት ሳይጠራ፣ ዝናብ ዘጋን ተብሎ ስብሰባ ተጠራ። ግን አይገርማችሁም ለቡና መጠራራት እየተውን በረባ ባረባው ለስብሰባ ስንቀላቀል? ኧረ የጉድ ነው ዘንድሮስ! ስንት የወደቀ ነገራችንን ሳናነሳና ሳናስተካክል በማያገባን ጉዳይ መንጓገዋለል ይቀናናል መቼም። አይገርማችሁም? ውሎ ሳያድር ደግሞ ባሻዬ ስብሰባውን እንዲመሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አደረጉ ተባለ። “እኔ በእግዜር ሥራ አልገባም’ አሉ፤” አሉ። ገሚሱ “ደግ አደረጉ!” ሲላቸው ገሚሱ፣ “የአየር ንብረት ለውጥ እንዴት አያሳስባቸውም?” ብሎ ተቀየማቸው ተባለ። ይኼ ለድጋፍና ለተቃውሞ መጣደፍ የሚለቀን ግን መቼ ይሆን? መጥኔ!

ስለስብሰባው የሰሙ ዲግሪ የጫኑ ወጣቶች ደግሞ ሥራ ፈልግልን እያሉ አላስቆም አላስቀምጥ ብለውኛል፡፡ (ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ ሕገወጥ ደላላ ሊሉኝ እኮ ነው) “ዝናብን እኮ አምላክ አያዘንበውም… ደመና ተንኖ ቅብጥርሶ…” ብለው ኧረ የት ሄደን ተግባር ላይ እናውለው እያሉ የሚንገዋለሉበትን የዕውቀት ጫና ባሻዬ ላይ ለማራገፍ መታተራቸው ተሰማ። ‘ዕውቀት ሲበዛ አመድ ገንፎ ነው ያስብላል’ ያለው ማን ነበር? ጠፋኝ ብቻ። ተብሎ ተብሎ የስብሰባውን ‘ሪፖርት’ ባጭሩ የባሻዬ ልጅ ሲያጫውተኝ ቧልተኞች ተናገሩት የተባለው ቀልቤን ስቦት ነበር። ምን አሉ አትሉም? “መንገድ የተዘጋበት ሰሞን ስለሆነ እስኪ ትንሽ እንታገስ? እንግዶቻችን ወደ አገራቸው ሲሄዱ ይዘንብልን ይሆናል?” አሉ ብሎ አጫወተኝ።

ወዲያው የስብሰባው አጀንዳ ፖለቲካዊ ሆነ አሉ። ገሚሱ፣ “ተው እንጂ እናንተ! ደግሞ ፈረንጅም ደብተራ አለው ልትሉ ነው? ኧረ በሰላም እንኑርበት፤” እያለ ሲርበተበት ሌላው፣ “እኛ ሳንሰማ ሰማይም የመንግሥት ሆነ እንዴ?” እያለ ተንሾካሾከ። በበኩሌ ከሁሉ ከሁሉ የሚገርመኝ ይኼ ‘አንዳንድ’ የሚባሉ ነዋሪዎች ትልም ነው። ሁልጊዜ ሳያስፎግሩ ይሰበሰቡና አስፎግረው ይበተናሉ። ‘አልዘንብ አለ እኮ? የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ገላቸውን ታጥበው አይጨርሱም ወይ’ ብለው ተሰብስበው፣ ‘ኢሕአዴግ የሳሙና እጥረት ስለገጠመው ነው’ ዓይነት ወሬ አውርተው ይለያያሉ። በተቸገርንባቸው ነገሮች መፍትሔ የምንለውን ከማቅረብ ደግሞ ፎክሮና ተመፃድቆ የመለያየት አባዜያችን፣ እንደ አክሊሉ ለማ ዓይነት ‘ጂኒየስ’ እንዴት ዳግመኛ ተፈጥሮ የሳሙና እጥረቱን ሊፈታልን እንደሚችል አያወያየንም። መቼም የሳሙናው ምሳሌ ይገባችኋል? ወድጄ አይደለም የምሙለጨለጭባችሁ፡፡ ተግባባን?

ነገርን ነገር ያነሳዋል። ለነገረኛም ነገረኛ ያዝለታል። አላዝልን እያለ የተቸገርነው በበሽታችን ልክ መድኃኒት ብቻ ነው። “በሽተኛው በዛ መድኃኒት አነሰው…” ያለው ዘፋኙ ወዶ መሰላችሁ? ‘ማንም የወደደውን ያገባና የዘፈነ የለም’ እንዳትሉኝና እንዳልስቅ። ውዷ ማንጠግቦሽ ሰሞኑን በገባች በወጣች ቁጥር “ሐዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ሄጄ ያየሁሽ…” እያለች ትሞዝቅላችኋለች። እኔ ደግሞ ‘መልዕክት ይኖረው ይሆን? ሽርሽር አማረኝ እያለችኝ ይሆን?’ እያልኩ መጨነቅ። አሥር ጊዜ የባንክ ደብተሬ ወጪና ገቢ ላይ ማፍጠጥ። ስቀንስ ስደምር፣ የሆቴል፣ የምግብና የትራንስፖርት ሳባዛ ሳካፍል መዋል። ግን ለምንድነው ዘንድሮ ሽርሽር ለመጓዝ ሲታሰብ ገና ድካም የሚተርፈን? የኢኮኖሚው ዕድገት ማሳያ ይሆን እንዴ? ቢጨንቀኝ እኮ ነው የምጠይቃችሁ። ኋላ ታዲያ አስቤ አስቤ ሲደክመኝ የባሻዬን ልጅ፣ “ምን አባቴ ባደርግ ይሻለኛል?” ብዬ ማማከር። ምን ይለኛል፣ “ቆይ ትንሽ ታገስ ማንጠግቦሽ ብቻ አይደለችም ሐዋሳ ላንጋኖ እያለች የምትዘፍነው። ሁሉም ነው፤” አለኝ።

“እንዴት ሁሉም?” ስለው፣ “ኦባማ ሲመጡ ድፍን አዲስ አበባ ጭር ትላለች እየተባለ ስለሆነ ሰውየው የመጡበትን ጉዳያቸውን ፈጽመው እስኪመለሱ መንግሥት ወጪያችንን ሸፍኖልን ወጣ ብለን ተናፍሰን እንምጣ እያልን ነው፤” አለኝ። በቃ ነዳጅ ብናወጣ ነው ብዬ፣ “ታዲያ ምነው እንዲህ ያለውን የምሥራች ቀደም አድርገህ ሳትነግረኝ?” ስለው፣ “ምን ይታወቃል? ‘የህዳሴው ግድብ ሳይጠናቀቅ በቦናፓርቲዝም ልታጨመላልቁን ነው ወይ?’ የሚል መልስ ከመጣስ ብዬ ነዋ!” አይለኝ መሰላችሁ? ጉድ እኮ ነው እናንተ! “ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ፤” አለች አሉ (ማን ነች ግን እሷ?)። “እኔ እኮ ነዳጅ ያወጣን መስሎኝ ነው። በመንግሥት በጀት ነው ላንጋኖን ያለማችኋት?” እለዋለሁ፣ “ተው እንጂ በማለም መብታችንማ አትምጣ፤” ብሎ ተቆጣኝ። ኧረ እንዴት ነው ነገሩ? ይኼ ዓለም እያደር የህልም ዓለም ሆነ እኮ ጎበዝ!

ሽርሽሩንም በጀት መመደቡንም ትቼላችሁ እንደ ወትሮዬ ወደ ድለላዬ ሮጥኩ። አንድ ደንበኛዬ ያገለገለ ከባድ መኪና ከአውሮፓ ገዝቶ ከሚያስመጣ ሰው ጋር እንዳገናኘው ስለጠየቀኝ ወዲያው ደዋውዬ አገናኘኋቸው። ስለሚጫነው የመኪና ዓይነት በደንብ ተነጋገሩ። ያው ዘመኑ የሚሊዮኖች ነውና የምትሰሙዋቸው ቁጥሮች በጠቅላላ ባለሰባት ‘ዲጂት’ ናቸው። እኔን የሚገርመኝ ታዲያ ግለሰቦች ሰባት ‘ዲጂት’ እያገላበጡ ሥራ ሲሠሩ እያየንና እያመንን ባለሁለት ‘ዲጂቱ’ን የኢኮኖሚ ዕድገት መጠራጠራችን ነው። እውነቴን እኮ ነው። አንድ ወዳጄን እንዲህ ስለው፣ “ሲሠራን ቁንዶ በርበሬያችንን መጠራጠር አድርጎት ነው፤” አለኝ። ስለአፈጣጠራችን ለመፈላሰፍ ካልጠፋ ቅመም ቁንዶ በርበሬን ስቅ የሚያስብለው ሰሞኑን የሥጋ እጥረት ስለተከሰት ይሆን ብዬ ትክ ብዬ አየሁት። ምክንያቱም ይኼ ወዳጄ ቁርስ፣ ምሳና ራቱ ሥጋና ሥጋ ብቻ ነው። ሌላ ምግብ አይታየውም።

ብዙ ጊዜ ስታዘበው ይገርማችኋል ታላላቅ አገራዊ ጉዳዮች ተነስቶ እየተወራ፣ ነገር ማብራራት የሚቀናው በሥጋና ምግብ ነክ በሆኑ ቅመማ ቅመሞች ነው። የአማልክት ስም ጠርቶ ምፅዋት ከሚጠይቀው የኔ ብጤ ይልቅ ‘ከብቶቼ አልቀው በሬዎቼ ሞተው ተሰድጄ ነው’ ላለው ድፍን አሥር አሥር ብር ይመፀውታል። አንዳንዴ የምናውቀውን ሰው በሌለበት ስንሸረድድ፣ “ቁርጥ አትቁረጡና ከሰው ተቆራረጡ፤” ብሎ ያፌዝብናል። ግን መቆራረጥ ከአፈጣጣራችን ሳይሆን ከምናዘወትረው አመጋገብ የተነሳ ይሆን እንዴ? አለመተማመን፣ ለራስ ሥጋ ማድላት፣ አገርንና ሕዝብን በንብረቱና በጥቅሙ መበደል ምንጩ ከምንጎርሳት ጉርሻ አቀማመም ጋር ግንኙነት እንዳለውስ? በሚሊዮን እየተጫወትን ዝርዝር ሳንቲም ብቻ ኪሳቸው ውስጥ ያለውን ችላ የምንልበት ምክንያቱም እኮ ከጉርሻችን ጋር አብሮ መጠናት አለበት። አይደለም እንዴ? ‘ኤግዛክትሊ!’ በሉ እንጂ!

እናላችሁ በቅርቡ ከባድ መኪናውን አስመጥቶ ከሚሸጠው ደንበኛዬ ጠቀም ያለ ‘ኮሚሽን’ እጄ እንደሚገባ እያሰብኩ ራሴን በተመለከተ አንዳንድ የ‘ትራንስፎርሜሽን’ ዕቅድ መተለም ጀመርኩ። ካፖርቴ ቅያሪ ያስፈልጋታል። የጫማዎቼ ሶሎች አልቀዋል። እግሬ እስኪቀጥን እየተጓዝኩ ዳሩ ቀድሞኝ የሚያልቀው ጫማዬ እየሆነ ተቸግሬያለሁ። ለሁሉም ‘ሾፒንግ’ ያስፈልገኛል። እናም አንድ የልብስና የጫማ ሱቅ ዘው ብዬ ገባሁ። “ይኼ ጫማ ስንት ነው?” ብዬ ከመጠየቄ ደንበኛ ለማስተናገድ ሳይሆን ደመኛ ለማፍራት የተቀጠረች የምትመስል ቆንቋና ገጿን አጨፍግጋ “ስድስት ሺሕ” አለችኝ። “አቤት?” የምር አልሰማኋትም። አንዳንዴ እኮ አይሰማችሁም። “ስድስት ሺሕ አልኩህ!” ተነጫነጨች። የንጭንጯ ሰበቡ ገባኝ። በቀን ስድስት ሺሕ ጊዜ ይኼን ጥሪ እየጠራች አንድም ሰው ሳይገዛት ስለሚሄድ መሆን አለበት አልኩ። “ቅያሪ አለው ማለት ነው?” ታዲያ ምን ልበላት?- “የምን ቅያሪ ነጠላውን ነው እንጂ። ከገዛህ መግዛት ነው፤” ብላ ፊቷን አዞረችብኝ።

“እሺ የስንት ዓመት ‘ጋራቲን’ አለው?” ልላት ብዬ የስንትስ ዓመት ቢኖረው አሁን ይኼን ጫማ አድርጌ የሠፈር ሰው ቢያየኝ ሠርቶ ገዛው ብሎ ያምነኛል ብዬ ተውኩት። በቃ ባዶዬን ከምወጣ ካልሲ ምናምን ልግዛ ብዬ ካልሲ ስጠይቃት አንድ ካልሲ 250 ብር ገብቷል። እንዲህ የሚረባውም የማይረባውም እየጨመረማ እኛም ብልጠት ሳንጨምር ‘ጉድ እያሉ መኖር’ አያዋጣንም አልኩና ስከንፍ መርካቶ ሄጄ ኪሮሽ ገዛሁ። አንገቷ ላይ ያለቀች ካፖርቴን አስገልብጬ ለማሰፋት ወስኜ ለሰፊ አቀበልኳት። ኪሮሹን ደግሞ ለማንጠግቦሽ ወስጄ ሰጠሁና ጊዜ ስታገኝ ካልሲ እንድትሠራልኝ ነገርኳት። ታዲያ በዚህ ኑሮ ላይ ‘ኢምፖርትድ’ ዕቃዎች እየሸመትን ‘ኤክስፖርት’ ለመደረግ ሳንበቃ ‘ኤክስፓየርድ’ እናድርግ እንዴ? ከዚህ የተሻለ የ‘ትራንስፎርሜሽን’ ዕቅድ ያለው ሐሳቡን ‘ሼር’ ማድረግ ነው። ‘ፌስቡክን’ም ስንሰዳደብበት ከምንውል ለ‘ትራንስፎርሜሽን’ ዕቅዳችን መሳካት ብንጠቀምበት ጥሩ ነው። የእናንተን ባላውቅም!

በሉ እንሰነባባት። ሐምሌ ያጉረመርማል። ‘መንገዱን ከፍተውት ነው ማለት ነው’ እያልኩ በውስጤ የስብሰባው ነገር ትዝ ብሎኝ ፈገግ ስል ባሻዬ መንገድ ላይ አገኙኝ። “አንተንም ጀመረህ?” አሉኝ ለሰላምታ እጃቸውን ዘርግተው። “ምኑ?” አልኳቸው። “ለብቻ መዋለሉ?” ብለው ተራቸውን ፈገግ አሉ። እንዳልገባኝ ስነግራቸው፣ “ና ወደ ቤቴ እየሸኘኸኝ እነግርሃለሁ፤” ብለውኝ መጓዝ ጀመርን። “እንዲያው ሕመሙ የጋራ ጥያቄው ሁሉ የወል፣ ማግኘቱ፣ ማጣቱ፣ መታፈኑ መተነፍሱ፣ መጨነቅ መባዘኑ የሁላችን የሕይወት አካል ሆኖ ሰው ብቻውን ሲተክዝ ብቻውን ሲያወራ ብቻውን ሲያብድ ሆኗል የማየው። አንተም እንደዚያው የሆንክ ስለመሰለኝ እኮ ነው፤” ሲሉኝ ያስፈገገኝን ነገር አጫወትኳቸው።

አዛውንቱ ባሻዬ ከወትሮው በተለየ ከተከሻቸው ጎብጠው በረጂሙ ተነፈሱና “አንበርብር?!” አሉኝ። “አቤት!” አልኳቸው። “ምን እንደሰለቸኝ ታውቃለህ?”— “ምን ባሻዬ?” ስጓጓ እያዩኝ ጥቂት በሐሳብ ተጉዘው ቆይተው፣ “በማያንገዋልለው የሚንገዋለለው፣ በማይቸግረው የሚቸገረው ሰው ብዛት። እንዴ ምንድነው እንደዚህ ነገር ሰንጣቂው የበዛው? እንጨት እየሰነጠቁ፣ ሥራ እየሠሩ ጎጆ የሚያጠብቅ ማገር ማቅናት አይሻልም? በነፈሰው ሁሉ ሆ?! በየቀኑ ጭፈራ? በየቀኑ ስላቅ? በየቀኑ ቧልት? አይሰለችም እንዴ?” ብለው ሳይጨርሱ ቤታቸው ደርሰን ነበር። ድንገት ቆም ብለው፣ “አደራ ለራስህ እያወቅክበት። ቁም ነገር ተረስቷል። ቢተች የማይሰለቸው፣ ቢዝት የማይደክመው ሰው በዝቷል። ሰውን ሰው ያረገው ግን ሥራና ቁም ነገር ነው። ደህና እደር!” ብለውኝ ቤታቸው ገቡ። እኔም ተለይቻቸው ስጓዝ ሰውን በእርግጥ ሰው ስለሚያስብለው ነገር እያሰብኩ ነበር። የማሰብ መብታችንን ሳንጠቀምበት ለምን ለአፍ ወለምታና እንደምንቸኩልም ማሰብ ስለፈለግኩ ቶሎ ወደ ቤቴ ስገባ ማንጠግቦሽ ኪሮሿን ይዛ ተቀምጣለች። እንዲህ ነው እንጂ ‘ትራንስፎርሜሽን!” ስላት፣ “ገና ኤክስፖርት እናደርጋለን እባክህ! ይልቁንስ ሰው ለመሆን ከፈለግክ ሰውን ሰው ያደረገው ምን እንደሆነ ዕወቅ!” ስትለኝ ግጥምጥሞሹ አስገረመኝ፡፡ ውኃ ልኩ ጠፋ እንጂ ይኼ መቼ ይጠፋናል? በሽተኛው በዝቶ መድኃኒት አነሰን እንዴ? እንዳያዳልጠን ማለት አሁን ነው፡፡ መልካም ሰንበት!       

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት