Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልዳግም የተቃኘው የጃኖ ባንድ ሕልም

ዳግም የተቃኘው የጃኖ ባንድ ሕልም

ቀን:

ጃኖ ባንድ የሚገኝበትን ግቢ በር አልፈን ስንገባ በለሆሳስ የሚሰማው ሙዚቃ እንኳን ደህና መጣችሁ የሚል ይመስላል፡፡ ያገኘናቸው አንድ የትግርኛ ዘፈን በመለማመድ ላይ ሳሉ ነበር፡፡ አንዳንዴ እየተከራከሩ፣ እርስ በርስ እየተራረሙና እየተሞጋገሱም ሙዚቃውን ደጋግመው ይለማመዱ ነበር፡፡

ባንዱ በአሁኑ ወቅት በኤችቱኦ ክለብ ውስጥ እየተጫወተ ነው፡፡ ለአንድ ወር ያህል ዘወትር ማክሰኞና ሐሙስ ሙዚቃዎቻቸውን ያስደምጣሉ፡፡ ወሩን ‹‹ጁላይ ዊዝ ጃኖ›› የሚል መጠሪያ ሰጥተውታል፡፡

በመጭው ዓመት መባቻ ላይ ገበያ ላይ እንደሚውል የሚጠበቀው ሁለተኛ አልበማቸውን ምክንያት በማድረግ በክለቡ ይጫወታሉ፡፡ ለጥቂት ጊዜ ከመድረክ መጥፋታቸውን ታሳቢ በማድረግም አዲሱ አልበም ዳግም ከሕዝብ ጋር እንደሚያገናኛቸው ተስፋ አድርገዋል፡፡

በቀድሞው ማናጀራቸው አዲስ ገሠሠ ተመልምለው ባንዱን የተቀላቀሉ ሙዚቀኞች አሥር ነበሩ፡፡ ‹‹አይራቅ›› የተሰኘውና በአጭር ጊዜ ተወዳጅነት ያተረፈው ነጠላ ዜማም ከሕዝብ ጋር አስተዋውቋቸዋል፡፡ የመጀመርያ አልበማቸውን ‹‹ኤርታሌ›› ከለቀቁ በኋላ ከአባላቱ መካከል ጥቂቱ ለቀዋል፡፡ አሁን ስምንት ናቸው፡፡ ሊድ ጊታሪስትና ሚዩዚካል ዳይሬክተር ሚካኤል ኃይሉ፣ ኪቦርዲስትና ባንድ ሊደር ኪሩቤል ተስፋዬ፣ ድራመሩ ዮሐንስ መኮንን፣ ቤዚስቱ ዳንኤል ነጋሽ እንዲሁም ድምፃውያኑ ሔዋን ገብረወልድ፣ ዲበኩሉ ታፈሰ፣ ሃሌሉያ ተክለፃዲቅና ኃይሉ አመርጋ ናቸው፡፡

ጃኖዎች ከ‹‹አይራቅ›› በኋላ በይበልጥም በወጣቱ ዘንድ ተደማጭነት አግኝተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች የተለየው ኢትዮ-ሮክ መለያቸው ሆኗል፡፡ ‹‹ኤርታሌ›› ከተለቀቀ በኋላ ከአልበሙ ነጥረው የወጡ ዘፈኖችም ነበሩ፡፡ በርካታ አድማጮች በልዩ ልዩ መድረኮች ባቀረቧቸው ኮንሰርቶች የበለጠ ተማርከዋል ለማለት ይቻላል፡፡ የጃኖዎች ተሰጥኦ ጎልቶ የታየው በነዚህ መድረኮች ነው የሚል አስተያየት የሚሰነዝሩም አሉ፡፡

አባላቱም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ አልበሙ ገበያ ላይ ከመዋሉ አስቀድሞ በአይቱንስ መለቀቁና በተገቢው ሁኔታ አለመተዋወቁ የተጠበቀውን ያህል ምላሽ እንዳያገኙ ካደረጓቸው ምክንያቶች እንደሚጠቀስ ኪሩቤል ይናገራል፡፡

አባላቱ ከሚጠቅሷቸው ኮንሰርቶች መካከል አዲስ አበባ በላፍቶ ሞልና ትሮፒካል ጋርደን የተካሄዱት ይገኙበታል፡፡ ‹‹ሰለብሬቲንግ ዘ ፕራይድ ኦፍ ኢትዮጵያን ሚውዚክ›› በሚል ጎንደር፣ አዳማ፣ ሐዋሳ፣ መቐለ፣ ጅማና ባህር ዳር ተዘዋውረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ጀርመን፣ እስራኤልና ባህሬን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አሜሪካ ውስጥም በ12 ስቴቶች ኮንሰርት አቅርበዋል፡፡

በተከታታይ በበርካታ አገሮች ቢዘዋወሩም ለተወሰነ ጊዜ ተቀዛቅዘው ነበር፡፡ እንደ ባንድ ስለመቀጠላቸው ጥያቄ ያነሱም ነበሩ፡፡ አዲሱ አልበማቸው ተስፋ የጣሉበት ነው፡፡ ቢያንስ 15 ዘፈኖች የሚኖሩት ሲሆን፣ የአራቱን የባንዱ ድምፃውያን ሥራዎች ያካተተ ነው፡፡ በግጥምና ዜማ ቀድሞ በ‹‹አይራቅ›› የተሳተፈው ይልማ ገብረአብና ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡ የሙዚቃ ቅንብሩ የተሠራው በሚካኤል ሲሆን፣ አልበሙ ፕሮዲውስ የተደረገው በባንዱ ነው፡፡ ‹‹ኤርታሌ›› በአሜሪካዊው  ቤዚስትና ፕሮዲውሰር ቢል ላስዌል ፕሮዲውስ መደረጉ ይታወሳል፡፡ የአክሰስ ሪል ስቴቱ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የገንዘብ ድጋፍም ተጠቃሽ ነው፡፡

ጃኖ የሚታወቅበት ኢትዮ-ሮክ እንዳለ ሆኖ ለሕዝብ ጆሮ ቅርብ የሚባሉ ሙዚቃዎች በአዲሱ አልበም እንደተካተቱ ዲበኩሉ ይናገራል፡፡ ‹‹የጠለቀ ይዘት ያላቸው፣ እኛን የሚገልጹና የአድማጭን ቀልብም የሚገዙ ሥራዎች ተካተዋል፤›› ይላል፡፡

ኪሩቤል የመጀመርያው አልበም ታሳቢ ያደረገው የውጭ አገር ገበያ እንደነበር ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ አገር ውስጥ ያለው ገበያና የአድማጩ ፍላጎት ከዚህ የተለየ ነው፡፡ አሁን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ከማማተራቸው አስቀድሞ አገር ውስጥ ተቀባይነት ማግኘትን ዓላማ አድርገዋል፡፡ ‹‹ኤርታሌ›› ሕልማቸውን ከእውነታው ጋር ያስተያዩበት አልበም መሆኑንም ይናገራል፡፡

ገበያውን ታሳቢ በማድረግም አገር ውስጥ የሚደመጥ አልበም መሥራታቸውን ኪሩቤል ያስረዳል፡፡ ‹‹አዲሱ አልበም መድረክ ላይ የምናሳየው ብቃት እንደሚታይበት አምናለሁ፤›› ሲል ያክላል፡፡

‹‹የመጀመርያው አልበም ትርፋማ አልነበረም፤ ሙሉ በሙሉም ተቀባይነት አላገኘም፤›› የሚለው ሚካኤል፣ የአባላቱ የረዥም ጊዜ አብሮነት በአዲሱ አልበም አሻራውን እንደሚያሳርፍ በማመን ነው፡፡ ከቆይታ ብዛት እርስ በርስ መግባባትና መናበብ መቻላቸው ለሙዚቃዎቻቸው ጥራት የራሱን አስተዋጽኦ እንዳበረከተም ይገልጻል፡፡

ባንዱ አሁን ያለበት ደረጃ ከቀድሞው ጋር ሲነፃፀር መጠናከሩን ሔዋንም ትስማማበታለች፡፡ ‹‹ሙዚቃን ሳስብ ጃኖን አስባለሁ፤›› የምትለው ሔዋን፣ አልበሙ በግጥምና በዜማ እንደሚገልጻቸው ትናገራለች፡፡ አዲሱ አልበም ታሳቢ ያደረገውም ወጣቶችን ነው፡፡

ኃይሉ በዓለም አቀፍ መድረኮች ካቀረቧቸው ኮንሰርቶች ያገኙትን ተሞክሮ ያነሳል፡፡ ‹‹ዕውቀት የቀሰምንባቸውና መሄድ ያለብንን አቅጣጫ ያመላከቱን ናቸው፤›› ይላል ስለ ኮንሰርቶቹ ሲናገር፡፡ ከበርካታ ተመልካቾች ጋር ከመገናኘታቸው ባሻገር ከታላላቅ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር የመሥራት ዕድል ያገኙበት እንደሆነ የሚገልጸው ኃይሉ፣ የደረሱበት ደረጃ በአልበሙ እንደሚያንፀባርቅ ያምናል፡፡

ጃኖዎች በሁለተኛው አልበማቸው መለቀቅ ዜና በመገናኛ ብዙኃን ዳግም ብቅ ብቅ ከማለታቸው በፊት የተፈጠረው መቀዛቀዝ አንድም ከገንዘብ እጥረት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ቋሚ የሆነ የገቢ ምንጭ አለማግኘታቸው ተፈታትኗቸዋል፡፡  ኪሩቤል እንደሚናገረው፣ በወቅቱ የነበረው ማኔጅመንት ጠንካራና ደካማ ጎን ቢኖረውም፣ በባንዱ የተፈጠሩ ክፍተቶች ከአስተዳደሩ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ አሁን በወቅቱ የነበሯቸውን ጠንካራ ጎኖች ተመርኩዘው እንደ አዲስ ተጠናክረው መሥራት እንደጀመሩም ያስረዳል፡፡

ከባንዱ ኃላፊ ሳሙኤል ተፈራ  ጋር ራሳቸውን እያስተዳደሩ ባንዱ ከተዳከመበት ጊዜ በተሻለ እንደበረቱ ከተቀሩት አባላት ገለጻ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ሕልማቸውንም ዳግም የቃኙት ይመስላል፡፡ ‹‹ከባዱን ጊዜ አልፈናል፤ ጃኖ ብዙ በሮች የተከፈቱለት ባንድ ነው፤ ይህን እየተጠቀምን መሄድ አለብን፤›› ይላል ባንድ ሊደሩ ኪሩቤል፡፡

በባንዱ አባላት ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ሮክ ኤንድ ሮል በተለያየ መንገድ ይገልፁታል፡፡ ነባራዊው ሁኔታ የሚንፀባረቅበትና በጎ መልዕክት የሚተላለፍበት መሆኑ የሚያስማማቸው ሐሳብ ነው፡፡ መድረክ ላይ ሲወጡም ይህንን መንፈስ የሚያነግቡ ይመስላል፡፡

ለስላሳውን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከሮክ ጋር ማዋሀድ ፈታኝ የሚሆንበት አጋጣሚ እንዳለ ኪሩቤል ይናገራል፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶችና በሮክ መካከል ያለውን ልዩነት አጣጥመው ለማቅረብ ሲጣጣሩ ከሙዚቀኞቹ ዝንባሌ በተጨማሪ ገበያ ማግኘትን ታሳቢ ያደርጋሉ፡፡ ‹‹ጃኖ ይዞ የመጣውን አዲስ ዘዬ አድማጩ ስለሚፈልገው ተቀዳሚ ምርጫችንም እሱ ነው፤›› ይላል፡፡

ሚካኤል እንደሚለው፣ በተለይ በተለያዩ ከተሞች ኮንሠርት ሲያቀርቡ የሙዚቃ ዘዬአቸው አዲስ በመሆኑ ለአድማጭ ጆሮ ሊከብድ እንደሚችል ገምተው ነበር፡፡ ‹‹የነበረውን የሙዚቃ ጥም የተረዳንባቸው መድረኮች፤›› በሚላቸው ኮንሠርቶች ያገኙት ምላሽ ከጠበቁት የበለጠ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ለሮክ የሚሰጠው ግምት የተሳሳተ መሆኑን ሳይናገር ግን አላለፈም፡፡ ዘዬው መልካም መልዕክት የሚተላለፍበት መሆኑን ይናገራል፡፡

ዲበኩሉም ሐሳቡን ይጋራል፡፡ ‹‹ወጣቶች እንደመሆናችን ከወጣትነት ጋር በተያያዙ ርእሰ ጉዳዮች ላይ እናተኩራለን፤›› ይላል፡፡ ሙዚቃዎቻቸው በመንፈሰ ጠንካራነት፣ በለውጥ፣ በፍቅርና በበጎነት ላይ እንደሚያጠነጥኑ ይጠቅሳል፡፡ ሙዚቃዎቻቸው ሕይወታቸውን የሚያንፀባርቁበትና ስላለፉት ውጣ ውረድ የሚናገሩበት እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ከብዙኃኑ ጋር የሚጋሯቸው ሰዋዊ ስሜቶች በሙዚቃዎቻቸው እንደሚደመጡ ያክላል፡፡

‹‹ሮክ በሁከትና ጫጫታ ጥላቻ የሚገለጽበት አይደለም፡፡ ሮክ የሚሰጠውን ጉልበት ከኢትዮጵያ ቅላፄ ጋር አጣምረን መልካም ነገርን እናስተላልፋለን፤›› ይላል፡፡ ሔዋን እንደምትናገረው፣ መድረክ ላይ ከሚጠቀሟቸው አልባሳት ጀምሮ የኢትዮጵያን ባህል ማንፀባርቅ ይሻሉ፡፡ የሚወዱት ዘዬ ሮክም ለዚህ የተመረጠ ነው፡፡

‹‹ያለፍንበትን ሕይወት ያሳያል፤ ይወክለናልም፤›› በማለት የሚገልጹት አዲሱ አልበማቸው ተቀባይነት እንደሚያገኝ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ‹‹በሙሉ ልብ የሠራነው አልበም ስለሆነ እንደሚሳካ አምናለሁ፤›› ይላል ሚካኤል፡፡ በኮፒ ራይት ሳቢያ ከአልበሙ ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ አስተማማኝ ባይሆንም ከኮንሠርቶች የሚገኘውን ገቢ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ቅድሚያ የሚሰጡት ተደማጭነት ማግኘትና ከአድናቂዎቻቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ማጠናከር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

አልበማቸው ለሕዝብ ጆሮ ከበቃ በኋላ በበርካታ አገሮች የመዘዋወር ዕቅድ አላቸው፡፡ ከአገር ውስጥ ድሬዳዋ ከተማ በኮንሰርት ዕቅዳቸው ተካታለች፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪም ያልሄዱባቸውን አገሮችን እንደሚያዳርሱ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

ኃይሉ ስለአብሮነታቸው ሲናገር ‹‹ራሳችንን መፈለጋችንና ራሳችንን አውቀን መሥራታችን የኅብረታችን መሠረት ነው፤›› በማለት ነው፡፡ የእነሱን ፈለግ መከተል ለሚፈልጉም ‹‹ጥሪያችሁን ፈልጋችሁ አግኙ፤ የስኬት ቁልፍ ነው፤›› ይላል፡፡

ከጃኖዎች መካከል በሙዚቃው መልካም ስም እያተረፉ ያሉና በግላቸው በሚሠሩት ሥራ የሚታወቁ ይገኙበታል፡፡ ቢሆንም ኅብረታቸው የበለጠ እንደሚያስደስተው ኪሩቤል ይናገራል፡፡ በተለይ ከወጣት አድናቂዎቻቸው የሚያገኙት ምላሽ የባንዱን አብሮነት ያጠናክረዋል ይላል፡፡

‹‹እኛ ያለነው በአድናቂዎቻችን ምክንያት ነው፤ ባንዳችን ፈርሶ ሌላ ነገር ሊፈጠር አይችልም፤›› ሲልም ያክላል፡፡ እነሱን ተምሳሌት በማድረግ የሙዚቃውን ዓለም የሚቀላቀሉ ቢበራከቱ ምኞታቸው ነው፡፡ ‹‹እኛ ባንኖርም ጃኖን ሌላ ትውልድ ይዞት እንዲቀጥል እንፈልጋለን፤›› የሚለው ኪሩቤል ሲሆን፣ የተቀሩት የጃኖ አባላትም ይህንኑ ያንፀባርቃሉ፡፡

 

      

      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...