ሪያ ኢትዮጵያ የሚያዘጋጀው የተራራ፣ ውኃ እና የጫካ ውስጥ ሩጫ ለሁለተኛ ጊዜ አብያታ ሻላ ፓርክ ውስጥ ነሐሴ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲካሄድ ለተፈጥሮ ሀብት ትኩረት እንዲሰጥ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እንደተካተቱበት አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡
የሪያ ኢትዮጵያ መሥራቾች አትሌት ገብረ እግዜአብሔር ገብረ ማርያምና አቶ ቃለአብ ጌታነህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለቱሪዝሙ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በታመነው የጫካ ውስጥ ስፖርታዊ ውድድር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭ ዜጎች ተሳታፊነታቸው ተጠናክሮ የቀጠለ ቢሆንም፣ የአገር ውስጥ ተሳታፊ ቁጥር ግን ውስን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተፈጥሮ እንክብካቤን በሚገባው መጠን በመላው ሕዝብ ዘንድ ለማስረጽ እንቅፋት መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸው፣ በተፈጥሮ እንክብካቤ ላይ ከሚሠሩ የፌዴራልና የክልል ተቋማት ጋር በማቀናጀት ሁለተኛውን ዙር ውድድር በተለየ መልኩ ለማካሄድ መታቀዱን ጭምር ተናግረዋል፡፡
እስካሁን በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭ አገር ዜጎች ምዝገባቸውን አጠናቀው የውድድሩን መጀመር የሚጠባበቁ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ተሳታፊ ቁጥር ማነስ ግን የታሰበውን የሁለትዮሽ ግብ ለመምታት እንደሚያስቸግር ግን አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡ በሦስት መንገዶች ተከፍሎ በሚካሄደው ውድድር 47 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው፡፡ ትልቁ ውድድር ዋና ዋናን አቀበት መውጣትንና ቁልቁለት መውረድን የሚያካትት ሲሆን፣ ይህም በላንጋኖ ሐይቅና በአብያታ ሻላ ፓርኮች ውስጥ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
በዘንድሮው ውድድር የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣንና የኦሮሚያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ በአጋርነት የሚሳተፉ ሲሆን፣ ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ተሳታፊዎች ናቸው፡፡