Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየካሳ ክፍያ ጥያቄው የፍትሕና የክብር ነው

የካሳ ክፍያ ጥያቄው የፍትሕና የክብር ነው

ቀን:

በአያሌው አስረስ

ጣሊያኖች ቀንና ሁኔታ እያመቻቹ፣ የሚያገኙትን አጋጣሚ እየተጠቀሙ ከአሰብ ምፅዋ፣ ከምፅዋ አስመራ ዘልቀዋል፡፡ የቅኝ ግዛታቸውን እስከ መረብ ምላሽም አስፍተዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለሦስት ለመቀራመት ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ ጋር የተዋዋሉት የበርሊን ውል ቢኖርም፣ ጠቅልሎ ለመያዝና የዓደዋን ቂም ለመወጣት ተዘጋጅተዋል፡፡ የዝግጅቱ አንድ መስመር ከቀላል እስከ ከባድ ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎችን ማምረት ነው፡፡ ሁለተኛው በመላው ኢትዮጵያ ባሰማሩዋቸው ‹‹የወንጌል መልዕክተኞች›› አማካይነት የአገሪቱን መልከዓ ምድር ማጥፋትና የጣሊያንን ኃያልነትና አሠልጣኝነት መስበክ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየቦታው ባስቀመጣቸው ቆንስላዎች ከንጉሠ ነገሥቱ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር ቅሬታ ውስጥ የገቡ መኳንንትንና መሳፍንትን አይዟችሁ በማለት፣ በሥልጣን ተስፋ በመደለል ከእነሱ ጎን ማሰለፍ ነው፡፡

በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል ጦርነት እንዳይቀሰቀስ መንግሥት በሥጋት ላይ ባለበት ጊዜ እንግሊዞች ወሰን ለመከለል ተነሱ፡፡ ታሪክ ጸሐፊው ተድላ ዘዮሐንስ ‹‹ኢጣሊያ ለኢትዮጵያ›› በተባለው መጽሐፋቸው ለምን ይህ ጊዜ ተመረጠ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ የሁለቱ አገሮች ወሰን የበላይ ባለሥልጣናት ለእነሱ የጥበቃ አገልግሎት ለመስጠት፣ በጉርስሙ አበጋዝ በፊታውራሪ አለማየሁና በጅጅጋው አበጋዝ በፊታውራሪ ሸፈራው የሚመራው ጦር ወልወል ከመድረሱ በፊት፣ ጣሊያኖች ወሰን ጥሰው 250 የሰው ኃይል ያለው ጦር ወልወል ላይ አሰፈሩ፡፡ ሮም ‹‹የኢጣሊያ ሠራዊት እግር የረገጠው መሬት የጣሊያን ግዛት ነው›› ብላ አዋጅ አስነገረች፡፡ ጣሊያኖች ወልወል የእኛ መሬት ነው አሉ፡፡

ወልወል 96 ኪሎ ሜትር ወደ መሀል ገብቶ በኢትዮጵያ የግዛት ክልል ውስጥ ያለ፣ በአፄ ዘርዓ ያቆብ ዘመን የተቆፈሩ 359 የውኃ ጉድጓዶች የሚገኝበት ለግጦሽ የተመቸ አካባቢ ነው፡፡

ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም. የኢጣሊያ ወታደሮች በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ጦርነት ከፈቱ፡፡ ጦሩን በምድር በእግረኛ ሠራዊት፣ በታንክና በመድፍ፣ ከአየር በጦር አውሮፕላን በቦምብ ደበደቡት፡፡ የያዙትን መሬት ሳይለቁ ኢትዮጵያውያን በጀግነነት ተዋጉ፡፡ 45 ኢትዮጵያውያን ሲቆስሉ 96 በጀግነት መስዋዕትነት ከፈሉ፡፡ በጣሊያኖች በግፍ ወረራ የኢትዮጵያዊያን ለነፃነት መሞት እንዲህ ሀ ብሎ ጀመረ፡፡

ሞሶሎኒ ዋቢ ሸበሌ አካባቢ ሙስታሂል፣ ዋርዴር፣ ቀብሪደሃር እንዲያዙ አዘዘ፡፡ ቆራሄ ላይ መሽጎ በሚገኘው በደጃዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማያት ጦር ላይ ጣሊያኖች ስድስት ክፍለ ጦር አዘመቱበት፡፡ ሃያ የጦር አይሮፕላኖች ለተከታታይ ሦስት ቀናት እየተመላለሱ ያለማቋረጥ ደበደቡት፡፡ ጳውሎስ ኞኞ፣ ‹‹ለብዙዎች የውሸት ታሪክ ሲነገር ለእሳቸው ግን እውነተኛው ታሪካቸው እንኳ አልተነገረላቸውም፤›› በማለት መቆርቆሩንና ማድነቁን የገለጠላቸው ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማያት ምሽጋቸውን ለቀው ላለመውጣት ወስነው አምርረው ተዋጉ፡፡ ደጀዝማች አፈወርቅ ተመተውና ክፉኛ ቆስለው ደማቸው እየፈሰሰ ወደ ሕክምና ለመሄድ አልፈለጉም፡፡ ጠላትን ሲዋጉ የሰነበቱበበትን የአየር መቃወሚያ እንደተደገፉ ሕይወታቸው አለፈ፡፡ ከዚያች ቦታ ላለመነቃነቅ እንደሳቸው የወሰኑ የጦሩ አባላት ከእሳቸው ጎን ወደቁ፡፡ የኢትዮጵያዊያን ለነፃነት መሰዋት እንዲህ ጠቀለ፡፡

ለነገር ምክንያት አለው፡፡ ታሪክ ጸሐፊ ባልሆንም የታሪክ ነገር እንዳነሳ ያደረጉኝ፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጀቱ ናቸው፡፡ ልጅ ዳንኤል ሰኔ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ የኢጣሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ስለፈጸመው የግፍ ወረራ ስለከፈለው ካሳ ጉዳይ አንስተው፣ ‹‹አንድ አነስተኛ የቆቃ ግድብ መገንባት ምንም ማለት አይደለም፤›› በማለት ሐሳቡን አጠናክረው፣ ‹‹የካሳ ክፍያው በዚህ ብቻ መወሰን የለበትም፤›› በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ሐሳባቸው ለልጅ ዳንኤል ያለኝን አክብሮት የምገልጠው አስቀድሜ ነው፡፡ በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል አሁን ላለው መለካም ግንኙት ከፍተኛ ዋጋ እንደምሰጥም አስቀድሜ የማስረዳው ከልብ ነው፡፡

‹‹ጣሊያኖች ለኢትዮጵያ የከፈሉት የጦር ጉዳት ካሳ እንደገና መተያት አለበት፡፡ ካሳው ከደረሱት ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን ይገባል፤›› የሚለው ሐሳብ በኢትዮጵያዊያን አዕምሮ ውስጥ መመላለስ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ጥያቄውን ያነሱት የሕዝብ ወገኖች ናቸው፡፡ ሕዝብ በዜግነቱ ልጁን ወደ ጦር ሲልክ ለአርበኛው መረጃ ሲሰጥ፣ ስንቅ ሲያቀብልና ጥይት ሲገዛ አምስት ዓመት ኖሯል፡፡ አምስት ዓመት ሙሉ ደግሞ አርበኛ አስጠግተሃል፣ ስንቅ አቀብለሃል እየተባለ በጣሊያኖች ቁም ስቅሉን አይቷል፣ ተዘርፏል፣ ተገድሏል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለተፈጸመባቸው የግፍ ወረራና ለደረሰባቸው ጉዳት መካስ አለባቸው፡፡

ከካሳ ጠያቂው ሕዝብ ውስጥ እኔና ዘመዶቼ አለንበት፡፡ እናቴ ሦስት ወንድሞቻቸውን በጦርነት አጥተዋል፡፡ ሦስቱ ማለትም ግራዝማች እምሩ አሰን፣ ልጅ ሰብስቤ አሰንና መኮንን አሰን የተገደሉት ወግዲ ላይ በስቅላት ነው፡፡ እናቴ ወደ ጎጃም የመጡት በደብረሲና (ወሎ ቦረና) እስር ቤት ወንድማቸውን ቀኛዝማች አረጋን አሰብረው ለማምለጥ ነው፡፡ አረጋ ዓባይ ላይ በባንዳዎች ተገድለዋል፡፡ የእኔ መወለድ ምክንያት ጦርነቱ ነው፡፡

ይህ የካሳ ጥያቄ አዲስ አይደለም፡፡ ‹‹ትብብር ለኢትዮጵያ›› የተባለ በአሜሪካ የሚገኝ የበጎ ፈቃደኞች ስብስብ በሺሕ በሚቆጠር የድጋፍ ፊርማ እያስባሰበ ያለበት ጉዳይም ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት እኔም ያለሁበት አዲስ አበባ ላይ አንድ ኮሜቴ ተቋቁሞ ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ጋር ለመሥራት መሞከሩን፣ ሁኔታው ስላልተመቸም የኮሚቴ አባላት መበታተናቸውን አስታውሳለሁ፡፡

ወደ ጦርነቱ እንመለስ፡፡ ‹‹በሺሕ የሚቆጠሩ ወታደሮች በማጣት ምክንያት ዓደዋ ላይ ተሸንፈናል፡፡ ይህን ሰህተት መድገም የለብንም፡፡ በማነስ ሰህተት ከመፈጸም በማብዛት ሰህተት መፈጸም ይሻላል፤›› ያለው ሞሶሎኒ ለጦርነቱ የተዘጋጀው እጅግ ከፍ ባለመጠን ነው፡፡ የነፍስ ወከፍ መሣሪያው፣ መትረየሱ፣ መድፉ፣ ታንኩ፣ የጦር አውሮፕላኑ፣ ቦምቡ፣ የመርዝ ጋዙ፣ የማጓጓዣ ተሽከርካሪው ሁሉም የተዘጋጀው በገፍ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ጦርነቱን ለማስቀረት የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ንጉሠ ነገሥቱ መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም. ወረራውን ለመከላከል የክተት አዋጅ አወጁ፡፡ በኋላም ወደ ማይጨው ዘመቱ፡፡

በእንዳባጉና፣ በተምቤን፣ በአምባረዶም፣ በአምባላጌ በተካሄዱት ጦርነቱቶች አንድ ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ሌላ ጊዜ ጣሊያኖች አሸናፊ ሲሆኑ ቆይተዋል፡፡ በማይጨው ጦርነቱም መጀመርያ ላይ ኢትዮጵያዊያን አሸናፊ በመሆን አምስት ያህል ምሽጎች ማስለቀቅም ችለው ነበር፡፡ ጣሊያኖች ባላቸው የመሣሪያ ብልጫ ሊቋቋሙት ያልቻሉትን የኢትዮጵያን ጦር ከአየር በቦምብና በመርዝ ጋዝ ያለ ርህራሔ ደበደቡት፡፡ ከሃያ ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያን በማለቃቸው ጦሩ ተፈታ፡፡ ወደ ኋላ ተመልሶ ቦታ ይዞ ለመዋጋት የነበረው አቅሙ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ሁሉም በየአቅጣጫው ወደ የአካባቢው ለመመለስ ጉዞ ጀመረ፡፡

የመልስ ጉዞው ሰላማዊ አልነበረም፡፡ በጣሊያኖች ስብከት የተደለለው የራያና አዘቦ ሕዝብ ጦሩን በየደረሰበት ገደለው፡፡ ከሞት የተረፈው ቀን ቀን በየጫካው እየተጠለለ ለሊት ለሊት መጓዝ ያዘ፡፡ ጣሊያኖች ‹‹ንጉሡን እንጂ እናንተን አንፈልጋችሁም›› የሚል ወረቀት ከአየር በተኑ፡፡ ይህን ቃል አምኖ ቀን ጉዞ የጀመረውን ሠራዊት አሸንጌ ሐይቅ አካባቢ ጠብቀው መሸሻ አሳጥተው ከአየር በቦምብ በመትረየስ ደበደቡት፡፡ በመርዝ ጋዝ ለበለቡት፡፡ በዚህ ድበደባ በጦር አውሮፕላን አብራሪነት የተሠለፈው የሞሶሎኒ ልጅ ቪክቶር ሞሶሎኒ የሚፈሰውን የኢትዮጵያውያን ደም የገለጠው ‹‹አቤት ደስ ሲል›› በማለት ነው፡፡ ለኢጣሊኖች የደስታ፣ ለኢትዮጵያውያን የመከራ ቀን በሆነው በዚያን ዕለት ያለቁትን ወገኖቻችንን ቁጥር በግምት ያስቀመጠ አልገጠመኝም፡፡ በአጠቃላይ በማይጨው ጦርነት ዘመቻ የደረሰውን ጉዳት ግን 25,000 ጦር ይዞ ወደ ዘመቻ ወጥቶ መጨረሻ ላይ 300 ሰው ብቻ የቀረውን የራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ጦር ማሰብ ሁኔታውን በግልጽ እንደሚያስረዳ አምናለሁ፡፡

ጣሊያኖች ደሴን አንድ ጥይት ሳይተኩሱ ያዙ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ገሰገሱ፡፡ ደብረሲና ላይ በባሻ ወልዴና በደጃዝማች ተሰማ እርገጤ የሚመራ ጦር ያልጠበቁትን ጥቃት አደረሰባቸው፡፡ የኃይለ ማርያም ማሞ ጦር ደብረ ብርሃን ላይ ሰባት ተሽከርካሪዎች አቃጥሎ 140 ጣሊያኖችን በመግደል ደገማቸው፡፡ የኢትዮጵያ መሬት እንዳሰቡ እንዳሻቸው የሚፈነጥዙበት እንደማይሆን ምልክቱ ታየ፡፡

ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. ጣሊያኖች አዲስ አበባ ገቡ፡፡ በዕለቱ 1,500 ሰዎች ተገደሉ፡፡ ግንቦት ላይ ከኢጣሊያ ሶማሊ ላንድ የተነሳው በጄኔራል ናዚ የሚመራው ጦር አዲስ አበባ ገባ፡፡

‹‹በማናውቀው አገር መጣብን›› ያሉት ኢትዮጵያውያን የጣሊያን የጦር ትጥቅ የበላይነት ያስከተለውን ጉዳት አይተውና አንገታቸውን ደፍተው ተገዥነትን ለመቀበል አልተዘጋጁም፡፡ ድሮ አንደኛው መስፍን በሌላው ላይ የነበረውን ጦር የማደራጀትና የማመፅ ባህል ለአገር ነፃነት ተጠቀሙበት፡፡ ለነፃነቱና ለአገሩ ክብር ከጎናቸው መሠለፍ የነበረበት ወገን ለጠላት አድሮ ጠቋሚና መንገድ መሪ፣ ይባስ ብሎ ታጥቆ ቢዘምትባቸውም በየአካባቢያቸው የአርበኝነት ትግሉን አቀጣጠሉት፡፡

ሚያዝያ አዲስ አበባ ገብተው በዓመቱ ሐምሌ ላይ ጣሊያኖችን ከከተማው ለማስወጣት በአዲስ አበባ አካባቢ የነበሩ አርበኞች ተሰማሙ፡፡ ደጃዝማች አበራ ካሳ በእንጦጦ፣ ባላንባራስ አበበ አረጋይ በቀበና አቦ፣ ደጃዝማች ባልቻ በልደታ፣ ደጃዝማች ፍቅረ ማርያም በራጉኤል በኩል እንዲያጠቁ ተወሰነ፡፡ በክረምቱ ዝናብና በመረጃ ችግር እንደታሰበው ባይሳካም አንዳንዶቹ የቻሉትን ያህል ገፉ፡፡ በዚህ ጦርነት ላይ የተሳተፉት አቡነ ጴጥሮስ በጠላት እጅ ወደቁ፡፡ በስምንት አልሞ ተኳሾች ፈት ቆመው በጥይት እንዲደበደቡ ተደረገ፡፡ አንድ የጣሊያን መኮንን አልሞቱም ብሎ በሦስት ጥይት ራሳቸውን ፈለጠው፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ አስገዳይ ኮሎኔል ራሳቸውን ማየት ቀፎት ሰቅጥጦት ‹‹የት ነው የሚቀበረው?›› ሲል ጮኸ፡፡ በዕለቱ መሣሪያ ለአርበኞች አቀብላችሁኋል የተባሉ አራት ወንዶችና አንዲት ሴት ጊዮርጊስ ሰንበቴ ቤት መሰቀላቸውም ይታወሳል፡፡ ሞት እንዲህ ነው የቀጠለው፡፡

ደጃዝማች አበራ ካሳ በጦርነቱ የማረኳቸውን ስድስት ጣሊያኖች በነፃ ከመልቀቃቻው በላይ፣ ለጄኔራል ግራዚያኒ ሰላማዊ ሆነው መኖር የሚፈልጉ መሆኑን በመግለጥ ደብዳቤ ጻፉ፡፡ እሳቸውና ወንድማቸው ደጃዝማች አስፋወሰን ካሳ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይደርሳቸው በራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት በኩል ተነገራቸው፡፡ ሌላው ወንድማቸው ደጃዝማች ወንድወሰን ካሳ ተመሳሳዩን አደረጉ፡፡ ሦስቱም እጅ ሰጡ፡፡ ነገ አይተኙንልም ብለው የሰጉት ጣሊያኖች ሦስቱንም ገደሉዋቸው፡፡ በሰላም እጃቸውን የሰጡትን የገደሉ ጣሊያኖች ለጦር ምርኮኞቻቸው ያዝናሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ እነ ራስ ደስታና ሌሎችም የተገደሉት ከተማረኩ በኋላ ነው፡፡

እዚህ ላይ ኢትዮጵያውያን ጦርነቱን እንዴት ተዋጉ? ምን ያህልስ መስዋዕትነት ከፈሉ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለጣሊያኖች ብቻ ሳይሆን ለጣሊያን ካበሩ ባንዳ ወገኖቻቸው ጋር ተዋግተዋል፡፡ በእነሱም ተገድለዋል፡፡ ጣሊያኖችን የገጠሙት በተመሳሳይ ወይም በተቀራረበ የጦር መሣሪያ ሳይሆን፣ እጅግ ኋላ በቀረ በአንድ ተኳሽ ውጅግራ፣ በጦርና በጎራዴ ስለነበር ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ “ሐበሾች በዚያ እሳት መሀል ጦር፣ ጎራዴና ጩቤ እየያዙ በሩጫ ይመጡብናል፡፡ ወደ እኛ እየሮጡ የሚመጡትም ብዙ ሬሳዎች እየዘለሉ ነው፤” የሚለው የጄኔራል ባዶሊዮ ቃል የሚያረጋግጠው ኢትዮጵያውያን የተዋጉት ሕይወታቸውን መሣሪያ አድርገው ነው፡፡ የሚያስረዳውም እንደ ቅጠል እየረገፉ ለነፃነታቸው ያሳዩትን ቁርጠኝነት ነው፡፡ በአጭሩ ኢትዮጵያውያን ለነፃነት በገፍ እየሞቱ ነበር፡፡

ግድያው በጦር ሜዳ ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ደጃዝማች አበራ ካሳ ሐምሌ 24 ቀን 1929 ዓ.ም. ለግራዚያኒ በላኩት ደብዳቤ ላይ “የኢጣሊያ መንግሥት ባላገሮችን እየያዘ ፍርድ ሳይታይ በሞት ይቀጣ ጀመር፤” ሲሉ ግድያው ተራው ገበሬ መንደር ድረስ የወረደ መሆኑን መስክረዋል፡፡

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ጄኔራል ግራዚያኒ እነ አብርሃም ደቦጭ በወረወሩት ቦምብ ቆሰሉ፡፡ በዚህ ቀን ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ 35,000 ሜትሮ ፖሊታንት፣ 40,000 ጥቁር ሐበሻ፣ 3,000 የሊቢያና 5,000 የኤርትራ በድምሩ  83.000 የወታደር ኃይል ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ መሣሪያ ባልያዘ ሕዝብ ላይ አንተኩስም ብለው ያመፁት ኤርትራዊያን ናቸው፡፡ ከእነሱም የተወሰኑት ተገድለዋል፡፡ የፋሽስቱ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጉዲያስ ኮርቴስ፣ “ዛሬ ድል ማድረጋችንና የበላይነታችን ማሳወቂያችን ነው፡፡ በዚህ ሦስት ቀን ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አጥፉ፤” ብሎ አዘዘ፡፡ ጥቁር ለባሾች በየአቅጣጫው ዘመቱ፡፡ አንዱ ወታደር በአንድ ጣሳ ቤንዚን አሥር ቤቶች እንዳቃጠለ፣ ሌላው ቦምብ በመወርወር ክንዱ እንደዛለ፣ ደግሞ ሌላው ሰባና ሰማኒያ ሰዎች እንደገደለ ተናገረ፡፡ በመቆጨት ሊሆን ይችላል ሁለት ብቻ ነው የገደልኩት በማለት አንድ ወታደር መናገሩን  ታሪክ ይናገራል፡፡ ተኩሶ የማያውቅ ጣሊያን ተኩስ በተለማመደበት በዚያ ቀን በየመንገዱ በጥይትና በቦምብ ተደብድበውና ከነቤታቸው በእሳት ተቃጥለው ያለቁት እናቶችና አባቶች፣ አዕሩግና ሕፃናት 30 ሺሕ እንደሚሆኑ ተገልጾል፡፡ ጣሊያኖች ሕዝቡን ለመጨረስ ያላቸው ፍላጎት፣ ከተማው ውስጥ የነበራቸው የወታደር ኃይል፣ የግራዚያኒ ጭካኔ ሲደመር የሟቾች ቁጥር በዚህ የሚቆም አይሆንም ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በደም አፍሳሽነቱ የሚታወቀው የፋሽስቱ ፓርቲ ጥቁር ለባሽ ወታደር እያንዳንዱ ሁለት ሁለት ቢገድል የሟቾች ቁጥር 80,000 ይደርሳል የሚል እምነት አለኝ፡፡

የሦስት ተከታታይ ቀናት ግድያ በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በሴራው አሉበት ተብለው የተጠረጠሩ 320 የደብረ ሊባኖስ መምህራንና መነኮሳት ተገድለዋል፡፡ በእምነት አባቶች ላይ የተነሳው የጣሊያኖች እጅ ዝቋላ ላይ 100፣ ጎንደር ላይ 150 ካህናትና መነኮሶችን ፈጅቷል፡፡

በየደረሱበት ሰው እንደ ጨፈቃ እያቆሙ በአጨዳ ተኩስ የብዙዎችን ሕይወት ሲቀጥፉ የነበሩት ጣሊያኖች፣ የታወቁ አርበኞችን አንገት በፋስ በመቁረጥ የራስ ቅላቸውን እንደ ኳስ የጉግስ መጫወቻ አድርገዋል፡፡ ይህን የትዕቢትና የግፍ አገዳደላቸውን ያቆሙት ፊታውራሪ ወልደ ፃድቅ ዘውዴ የተባሉ አርበኛ እሳቸውም በውጊያ የገደሏቸውን ጣሊያኖች አንገት ቆርጠው ለመጫወቻ በማድረጋቸው ነው፡፡

በሲቪልም ሆነ በወታደራዊ ሙያ አገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት ካስተማረቻቸው ወጣቶች ውስጥ ከመቶ ሰባ አምስቱን የገደሉት ጣሊያኖች፣ ደብረ ማርቆስ ውስጥ ቡስታ አካባቢ በሚገኝ የውኃ ጉድጓድ ውስጥ ሰዎችን ከነሕይወታቸው በመክተት ይገድሉ ነበር፡፡ ሌላው ቅጣታቸው ሰዎችን በመኪና ላይ እያሰሩ፣ መኪናዎቹን ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲሄዱ እያደረጉ ሰዎቹ ተበጣጥሰው እንዲሞቱ ማድረግ ነው፡፡

የ‹‹ጎንደሬ በጋሻው›› ጸሐፊ ገሪማ ታፈረ፣ ጎንደር አመጅ በተባለ ቦታ ኗሪ የነበሩት ብላታ ገፊ ጣሊያን ቢቆይ አምስት ዓመት ነው መሣሪያችሁን አታስረክቡ ብለው ትንቢት ተናግረዋል ተብለው መገደላቸው፣ የእሳቸው ልጅ ወልዴ ገፊ እሱና ሌሎች አሥራ አንድ ሰዎች በእሳት ተቃጥለው መገደላቸውን፣ አንድ ካርታ ጥይት ስለተገኘበት ብቻ አበሬ የተባለ ሰው እንጨት በላዩ ላይ ተከምሮ በቃጠሎ መሞቱን ይስረዳሉ፡፡

ደራሲ ተመስገን ገብሬ የካቲት 12 ቀን 1929 የጭፍጨፋ ሰሞን ተይዘው ከታሰሩት ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ተመስገን ካለበት የሴረኛ ስብሰባ ውስጥ የፕሮቴስታንት ዕምነት ተከታዮች በጥቆማ እያወጡ መገደላቸውን ይናገራል፡፡ ከካቶሊክም ከሙስሊሙም ወገን ሆነው ያልተገኘት አቶ አርዓያ የፕሮቴስታንት ዕምነት ተከታይነታቸውን ገለጡ፡፡ ጣሊያኖች እግራቸውን ከመኪናው የኋላ ፓራውልት ጋር አስረው ጎተቷቸው፣ ወደቁ፡፡ ከነነፍሳቸው በመኪና እየጎተቱ ወደ ሆለታ መወሰዳቸውን፣ በመጨረሻ ሆለታ የደረሰው ከመኪናው ጋር የታሰረው እግራቸው ብቻ መሆኑን ተመስገን ገብሬ በግል የሕይወት ታሪኩ ላይ ጽፏል፡፡ ግፉ ይብቃን ወደ ካሳ ጥያቄው እንለፍ፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ‹‹ሕይወቱና የኢትዮጵያ ዕርምጃ›› በተባለው ጥራዝ ሁለት መጽሐፋቸው በአምስቱ ዓመት የጣሊያን ወረራ ስለደረሰው ጉዳት በተደረገው ጥናት፣ ‹‹750 ሺሕ ሰዎች መገደላቸውን፣ 500 ሺሕ ቤቶች ከነንብረትቸው መቃጠላቸውን፣ 2,000 ቤተ ክርስቲያኖች መበዝበዛቸውንና መፍረሳቸውን፣ ወደ 14 ሚሊዮን የቁም ከብቶች ማለቃቸው፣ እንዲሁም ከተማሩት ወጣቶች ውስጥ ሰባ አምስት በመቶ የሚሆኑት መገደላቸውን›› ማሳየቱን ገልጠዋል፡፡ ጥናቱ ግን በቂ ነው የሚባል አልነበረም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ ለደርግ ባቀረቡት ማስታወሻ፣ ‹‹ዝርዝር ጥናቱ መደረግ ነበረበት፣ ያንን ለማድረግ ስታስቲክስ የለም፤ የተማረ ሰው የለም፤›› በማለት የገለጡት ሐሳብ በጥናቱ ላይ የብቃት ጉድለት መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ጣሊያኖች የጀርመን ደጋፊና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሸናፊ አገር ናቸው፡፡ ፋሺዝምን አስወግደን በዴሞክራሲ የሚመራ መንግሥት አቋቁመናል በማለት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤርትራን፣ ሊቢያን፣ ሶማሊ ላንድን በሞግዚትነት እንዲያስተዳድሩ እንዲሰጠቸው ይጠይቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ተካፋይ አገሮች ዝርዝር ውስጥ እንድትገባም ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ ነፍሳቸውን ይማረውና አፋቸውን ያስያዙዋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ ናቸው፡፡ እንዲህ በማለት፣ ‹‹ከጣሊያን ጋር በ1935 ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ በጦርነት ላይ ነን፡፡ የሰላም ውል አላደረግንም፡፡ ጣሊያን ሰላም አልፈልግም በጦርነት እቀጥላለሁ ካለ ጦርነቱ እንዲቀጥል ዛሬውኑ አዲስ አበባ ለጃንሆይ ቴሌግራም አደርጋለሁ፡፡ በዚህ አኳኋን በኢትዮጵያ የሚገኙት ወደ 300,000 የሚሆኑ ጣሊያኖች ለሚደርስባቸው ሁሉ ኃላፊ አንሆንም፤›› ካሳው የተጠየቀው እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡

ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. በተካሄደው የኢጣሊያ ወረራ ኢትዮጵያ ለደረሱባት ልዩ ልዩ ጉዳቶች በአጠቃላይ የጠየቀችው ካሳ 186 ሚሊዮን ፓውንድ ነበር፡፡ ‹መንገድ ሠርተናል፣ ከተማ አልምተናል› በማለት ጣሊያኖች ካሳ ላለመክፈል አጥብቀው ቢከራከሩም፣ በመጨረሻ 6.25 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ካቀረበችው ጥያቄ ጋር ሲተያይ እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ አዚህ ግባ የሚባል ካሳ አይደለም ቢባል ነገሩን ማጋነን አይሆንም፡፡

የተቃጠሉትንና የተመዘበሩትን ቤተ ክርስቲያኖች፣ የወደሙትን መኖሪያ ቤቶች፣ ያለቁትን የቤት እንስሳት ጉዳይ ትተን የተከፈለውን ገንዘብ የደም ዋጋ አድርገን ብናየው፣ ለእያንዳንዱ ሰው ሞት የተከፈለው የነፍስ ዋጋ ዘጠኝ ፓውንድ እንኳ አይሞላም፡፡ በዛሬው ምንዛሪ 267 ብር ማለት ነው፡፡ የሰው ነፍስ እንዲህ ርካሽ መሆኑ ያሳፍራል፡፡

ጣሊያኖች ከፈጸሙት ወረራና የግፍ ግድያ የሚይካካስ ተመጣጣኝ የካሳ ክፍያ እንዲያደርጉ፣ የጦር ወንጀለኛነታቸውን ተቀብለው ይቅርታ ይጠይቁ ዘንድ መጠየቅ ተገቢ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡

እኛ ተገቢ ፍርድ ያጣን ሕዝቦች መሆናችን ልብ ሊባል ይገባል፡፡ መታወቅ ያለበትም ጠብ እየቀሰቀስን ሳይሆን ሚዛናዊ ፍርድ እየጠየቅን መሆኑን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ተገቢ ፍትሕ እንፈልጋለን፣ እንጠብቃለንም፡፡

ኢትዮጵያዊያን በምርኮ የተያዙ ወገኖቻቸው በገፍ ተገድለውባቸዋል፡፡ በ1933 ዓ.ም. ባደረጉት የድል አድራጊነት ጦርነት በማረኳቸው ብዙ ሺሕ ጣሊያኖች ላይ እጃቸውን አላነሱም፡፡ ይህ ሕዝብ መከበር የለበትም? የካሳ ጥያቄው ይህን ሁሉ ሐሳብ ውስጥ ያስገባ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ በእኔ ዕምነት ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ጣሊያናውያንም ሊደግፉት የሚገባ ጥያቄም ነው፡፡ በአጭሩ ጉዳዩ ትክክለኛ የፍትሕ ጥያቄ ነው እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡  

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...