በግብይት ሥርዓት ውስጥ በርካታ አስገራሚ የምንላቸው አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ፡፡ የተዘበራረቀ የግብይት ሥርዓት ያለ ስለመሆኑ በግልጽ የሚያመለክቱ አጋጣሚዎችንም እንመለከታለን፡፡ ምንም የአቅርቦት እጥረት የሌለበት አንድ ምርት ሳይታሰብ ዋጋው ተሰቅሎ ይገኛል፡፡ የምርት እጥረት ያለ ለማስመሰል የሚፈጠሩ ትርምሶችንም በተደጋጋሚ ተመልክተናል፡፡ እንዲህ ያሉ በገበያ ሕግ ሳይሆን በጥቂቶች የሚፈጠር መተረማመስ በሸማቾች ትከሻ ላይ ሲጫን ቆይቷል፡፡ ከገበያ ሥርዓት ውጪ ያሉ ግብይቶችን በተመለከተ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ጥቅል የግብይት ሥርዓቱን ትተን ሰሞኑን በአንዳንድ ምግብ ነክ ምርቶች ላይ በተከታታይ እየጨመረ ያለውን ዋጋ እንመልከት፡፡
እነዚህ ተወደዱ የተባሉ ምርቶች ገበያ ውስጥ እንደልብ አሉ፡፡ አከፋፋዮች ወይም ጅምላ ሻጮች ለቸርቻሪዎች ያቀርባሉ፡፡ የጅምላ መሸጫ መጋዘኖች ለቸርቻሪዎች የሚሸጡት ምርት አላጡም፡፡ ከቀድሞ አሠራራቸው የተለየ የሚባለው ነገር ቢኖር በቀናት ልዩነት የመሸጫ ዋጋቸው እየጨመረ መምጣቱ ብቻ ነው፡፡ እጥረት ታይቶባቸዋል የተባሉ ምርቶች ሁሉ በገበያ ውስጥ እንደ ልብ ከተገኙ እጥረቱ የቱ ጋ ነው? ያስብላል፡፡ ለምንስ ዋጋቸው ናረ? የሚለው ጥያቄ ሁላችንንም ማስደመሙ አይቀርም፡፡ በምግብ ነክ ምርቶች በተለይም ‹‹ሰማይ እየነኩ ናቸው›› የተባሉት እንደ በርበሬ፣ ሽሮ፣ ምስርና የመሳሰሉት ምርቶች ለሸማቾች አስደንጋጭና እንግዳ የሆነ ዋጋ ለመያዝ የበቁበት ዋነኛ ምክንያት፣ የምርት እጥረት መሆኑን በተለያዩ መንገዶች ሰምንተናል፡፡ ለዋጋው መወደድ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በቂ ምርት ስለሌ ነው የሚለውን ለመቀበል ይቻላል፡፡ በዚህ ወቅት የእነዚህ ምርቶች መወደድ የተለመደ ነው የሚል ምክንያትም ቢቀርብ ያስኬዳል፡፡ ችግሩ ግን ዋጋ ጭማሪው ከዚህ ቀደም ከሚታየው የተለየ አሳማኝ ያልሆነ ወይም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ዛላ በርበሬ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል፡፡ ሁሌም ክረምቱ መጣሁ መጣሁ በሚልበት ወቅት የተወሰነ የዋጋ ለውጥ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡
ወደ ኅዳርና ታኅሳስ አካባቢ ደግሞ አዲሱ ምርት ወደ ገበያ ስለሚቀርብ ለተከታታይ ወራት ዋጋው ወደታች ይወርዳል፡፡ ይህ የተለመደ ሒደት ነው፡፡ ችግሩ የተፈጠረው ግን መጠነኛ የዋጋ ዕድገት ይታይበታል ከተባለው የክረምቱ ወቅት የመሸጫ ዋጋ፣ ከክረምቱ በፊት ከነበረው ቀደም ብሎ ባልተለመደ ፍጥነት ዋጋው መገስገሱ ነው፡፡ የምስርና የሽሮ ወይም የጥራጥሬ ምርቶችም በተመሳሳይ የሚታዩ ናቸው፡፡ እነዚህ ምርቶች ግን ወደ ገበያ ወጣ ብሎ ለተመለከተ እንደልብ መገኘታቸውን ሲታዘብ፣ የዋጋ ጭማሪው ነገር ብዙ ትርጉም አይሰጥም፡፡
የሁላችንም ጥያቄ ይኼው ነው፡፡ ገበያው የሚያሳየን እጥረት ስለተፈጠረ ዋጋቸው ጨመረ የተባሉት ምርቶች ይኼ ነው የሚባል እጥረት ሳይታይባቸው በየገበያው እንደልብ ከተገኙ ለምን ዋጋቸው ተሰቀለ? ይህ ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ ነው፡፡ እነዚህን ምርቶች የሚቸረችሩ መደብሮችም ቢሆኑ ምስርም ሆነ በርበሬ የለንም አይሉም፡፡ እንደቀድሞ ምርቶቹን ይዘዋል፡፡ ግን ዕለታዊ የማከፋፋል ዋጋቸው እየጨመረ ነው፡፡ በዚህ ሒደት እየጨመሩ አንድ ኪሎ ምስር ክክ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ 60 ብር ደርሷል፡፡ የአንድ ኪሎ ዛላ በርብሬ የችርቻሮ ዋጋ ከ170 ብር በላይ ዘሏል፡፡ ነገሩ በዚሁ ከቀጠለ የበርበሬና የምስር ዋጋ ዕድሜ ልክ ትልቁ ዋጋ ተብሎ ሊመዘገብ ይችላል፡፡
ከጥቂት ወራት ወዲህ ዋጋቸው እያሻቀበ የመጡት ምርቶችን በተመለከተ የታየውን ችግር ተከትሎ ጉዳዩ የሚመለከታቸው እንደ ንግድ ሚኒስቴርና የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን በተለያዩ ሚዲያዎች ሲናገሩ እንደሰማነው፣ የበርበሬና የምስር ምርት እጥረት በተወሰነ ደረጃ ያለ ቢሆንም ለምርቶቹ መወደድ ምክንያት ግን ሸፍጥ የታከለበት መሆኑ ነው፡፡ የተጋነነ ዋጋ እየታየባቸው ናቸው የተባሉ ምርቶች እንደ ዛሬው ባልባሰበት ወቅት ከሚሸጡበት በላይ ዋጋቸው ሊሰቀል የቻለው በሰው ሠራሽ በሆኑ ምክንያት ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አጋጣሚን ተጠቅመው የዋጋ ግለቱ እንዲፈጠር አድርገዋል የተባሉ ነጋዴዎች ላይም ዕርምጃ ወደ መውሰድ እንደሚገባ በይፋ ተነግሯል፡፡ ነገር ግን እስካሁን የተወሰደ ዕርምጃ ስለመኖሩ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ በዚያው ልክ ዋጋው መቀጠሉን ግን አላቆመም፡፡ ገበያውን የማረጋጋት ብሎም ለገበያው አለመረጋጋት ምክንያት የሆኑ ጋሬጣዎችን የማስወገድ፣ ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ወደ ዕርምጃ አለመግባት በገበያ ውስጥ እንደልብ እየተሸጡ ያሉት ምርቶች ዋጋቸው እያደገ እንዲመጣ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡
ሁለቱ የመንግሥት ተቋማት ችግሩ ሰው ሠራሽ መሆኑን ካረጋገጡ ደግሞ ፈጻሚዎቹ ላይ ዕርምጃ ባለመውሰዳቸው ለዋጋ ንረቱ ራሳቸው በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ አድርገዋል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ በተጠቃሚዎች ዘንድ ዘወትር የሚፈለጉ ምርቶች በገበያ ውስጥ የዚያን ያህል ዋጋ መቀጠላቸው የሚፈጥሩት ጫና ቀላል ባይሆንም፣ ገበያውን ለማረጋጋት ጥረት አለማድረጋቸውን ያሳየም መስሏል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ምርቶች የዋጋ ንረት ላይ እነዚህ የመንግሥት አካላት ተገቢውን ዕርምጃ ባለመውሰዳቸው ሊጠየቁ ይገባል፡፡
በተለይ እንዲህ ያሉ ያልተጠበቁ የዋጋ ጭማሪዎች ትክክለኛ መንስዔአቸውን አውቆ ኅብረተሰቡ በቂ መረጃ እንዲኖረው የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ይታወቃል፡፡ ሆኖም አለ ስለሚባለው ዕጥረትም ሆነ እያሻቀበ ስለመጣው ዋጋ መንስዔ ያሳውቁን፡፡ ገበያውን ያረጋጉልን፡፡
ከአገራችን የግብይት ሥርዓት አንፃር ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ በማድረግ የተፈጠረውን ትርምስ ወደ ቦታው የመመለስ አሠራር ባለመኖሩም፣ በአንድ ወቅት በሆነ ምክንያት በአንድ ምርት ላይ የተጨመረ ዋጋ ተፈጠረ የተባለው ችግር ከተቀረፈ በኋላ በዚያው ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ዕርምት እንዲወስዱ እንጠይቃለን ብቻ ሳይሆን እንለምናለን፡፡