Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሕብረት ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ 11.8 ቢሊዮን ብር ደረሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ከታክስ በፊት 370 ብር አትርፏል

ሕብረት ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ2.4 ቢሊዮን ብር በማሳደግ 11.8 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉ ተገለጸ፡፡ በ2007 በጀት ዓመት 2.4 ቢሊዮን ብር የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ከሦስት የግል ባንኮች መካከል አንዱ መሆን መቻሉንም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ በቀደመው ዓመት መጨረሻ ላይ የነበረው ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 9.4 ሚሊዮን ብር እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሌሎች የባንክ አገልግሎቱም ከቀደመው ዓመት ብልጫ ያለው ውጤት እንደተመዘገበ የሚያመለክተው መረጃ፣ በ2007 በጀት ዓመት የሰጠው ብድርም 6.86 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ባንኩ ለተቀማጭ ገንዘቡና የብድር መጠኑ ዕድገት አዳዲስ ቅርንጫፎችን መክፈቱና አዳዲስ ዘመናዊ አገልግሎቶችን ሥራ ላይ ማዋሉ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ባንኩ በ2007 በጀት ዓመት ወደ ሥራ ካስገባቸው አዳዲስ አገልግሎቶች መካከል የኤጀንት ባንክ ወይም የወኪል አገልግሎት ባንክ ቀድሞ መጀመሩ ይጠቀሳል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በመላ አገሪቱ ከ100 በላይ የወኪል ባንኮችን ሥራ ያስጀመረ ሲሆን፣ የማስተር ካርድ አገልግሎቱም በበጀት ዓመቱ የተጀመረ ነው፡፡ እንደ አዲስ የተጀመረው የሕብር ኦንላይንና ሕብር ሞባይል አገልግሎቶችን ደግሞ ከቀድሞ በበለጠ በማደራጀት በበጀት ዓመቱ በሰፊው የተሠራባቸው በመሆኑ፣ ለተቀማጭ ገንዘብ ዕድገቱ አመርታ የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡

ከጠቅላላ አገልግሎቱም ከቀደመው ዓመት የተሻለ ትርፍ ያስመዘገበ ስለመሆኑ ከኩባንያ የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡ የበጀት ዓመቱ ግርድፍ ትርፉ ከታክስ በፊት 370.3 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የቀደመው ዓመት ትርፍ 361 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ብድር ሰጥተዋል ከተባሉ ባንኮች መካከል አንዱ ኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ከ6.3 ቢሊዮን ብር በላይ ሰጥቷል፡፡ ይህ የብድር መጠን ከቀዳሚው ዓመት ከ60 በመቶ በላይ ብልጫ ያለው ነው ተብሏል፡፡ በቀዳሚው በጀት ዓመት የሰጠው ብድር 3.6 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

በአንድ ዓመት ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻለው አንበሳ ባንክም በ2007 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 4.7 ቢሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ ታውቋል፡፡ አንበሳ ባንክ በ2006 በጀት ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ ማሰባሰብ ችሎ የነበረው ተቀማጭ ገንዘብ 580 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከ2007 በጀት ዓመት ማሰባሰብ ከቻለው 1.7 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች