የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ዓመታዊ የትርፍ ዕድገትና አገልግሎት መስፋፋት የመንግሥት ገቢን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገ መጥቷል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 16ቱ የግል ባንኮችና የሦስቱ የመንግሥት ባንኮች እያስመዘገቡ ያሉት ውጤት በተለያየ መንገድ ከግብር የሚያገኘውን የመንግሥት ገቢ በማሳደግ ላይ ናቸው እየተባለም ነው፡፡ የባንክ ዘርፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመንግሥት የግብር ገቢን በማሳደጉ ረገድ እየታየ ያለው ዕድገት ከሌሎች ኢኮኖሚ ዘርፎች እየተገኘ ነው ከሚባለው ገቢ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት እያሳየ ነው የሚል እምነት አለ፡፡ በተለይ የባንኮች ዓመታዊ ትርፍ መጠን ሳያቋርጥ እያደገ መምጣቱ በ30 በመቶ ተሰልቶ ለመንግሥት የሚከፈለው የትርፍ ግብር ብቻ በዓመት መቶ ሚሊዮኖች ብሮችን አልፎ ወደ ቢሊዮን ብሮች ተሸጋግሯል፡፡
በ2006 ዓ.ም. 16 የግል ባንኮች ከታክስ በፊት ወደ 4.6 ቢሊዮን ብር በላይ ያተረፉ ሲሆን፣ ከዚህ ትርፍ 30 በመቶን ወይም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የትርፍ ግብር ለመንግሥት ማስተላለፋቸው ይጠቀሳል፡፡
የ2007 በጀት ዓመትም ለትርፍ ግብር ብቻ የሚከፈሉት ገንዘብ ከቀደመው በጀት ዓመት የበለጠ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ የበጀት ዓመቱ የባንኮች አፈጻጸም ሲታይም በ2007 በጀት ዓመት ለትርፍ ግብር ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ይከፍላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ይኖረዋል፡፡ የግል ባንኮች የ2007 በጀት ዓመት ግርድፍ የፋይናንስ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በጥቅል ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ እንደሚያውጁ ይጠበቃል፡፡
በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባንኮች በየዓመቱ ያልተቋረጠ ትርፍ እያስመዘገቡና የትርፍ ምጣኔያቸውም እያደገ መምጣቱ ለመንግሥት የሚከፍሉት የትርፍ ታክስ እየጨመረ እንደሚሄድ የሚጠቁምም ነው፡፡ ከግል ባንኮች ቀዳሚ አትራፊ የሚባሉት ባንኮች ባለፉት ሦስት ዓመታት ከትርፍ ግብር ብቻ በዓመት በአማካይ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ከፍለዋል፡፡ ለምሳሌ ዳሸን ባንክ በ2006 በጀት ዓመት 241.1 ሚሊዮን ብር የትርፍ ግብር መክፈሉ ይጠቀሳል፡፡
ባንኮች ከጠቅላላ ዓመታዊ ትርፋቸው 30 በመቶውን ለመንግሥት የሚከፈሉ ሲሆን፣ ከትርፍ ግብር ባሻገር በተለያዩ የታክስ ዓይነቶች ለመንግሥት የሚያስገቡት ገቢም በተመሳሳይ እየጨመረ ስለመምጣቱ ያነጋርናቸው የባንክ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
የባንኮች አገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ያለመሆኑን የሚገልጹት እኚሁ የባንክ ባለሙያዎች፣ በተለይ የባንኮች አሠራር ቁጥጥር የሚደረግበት፣ በውስጥና በውጭ ኦዲተሮች የሚመረመርና እያንዳንዱ ሒደት ሕጋዊ መንገድን የተከተለ መሆኑ ዘርፉ የሚያስገኘውን የመንግሥት ገቢ እያሳደገው መጥቷል ይላሉ፡፡ ባንኮች ኢኮኖሚ ውስጥ እየፈጠሩ ያሉት ተፅዕኖ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚገልጹት የሕብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ፣ የፋይናንስ ተቋማት አስተዋጽኦ በቀጥታ በታክስ መልክ ከሚያስገቡት ገቢ ባሻገር በተዘዋዋሪ መንገድ የመንግሥት የግብር ገቢ ዕድገት እንዲኖረው በማድረግ እያበረከቱ ያሉት አስተዋጽኦ በርካታ ማሳያዎች አሉት ይላሉ፡፡
ከሠራተኞች የሚሰበሰብ የሥራ ግብር ከአገልግሎትና ከንብረት ግዥ የሚሰበሰብ የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢ ሳይቀር የመንግሥትን ገቢ ማሳደጉን የተለያዩ ምሳሌዎች በመግለጽ ያብራሩት የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ መንድማገኝ ነነራም፣ የመንግሥትን ገቢ በማሳደጉ ረገድ የባንኮች ሚና ከፍተኛ ነው ይላሉ፡፡
ሁሉም የግል ባንኮች በአሁኑ ወቅት ወደ 20,000 የሚጠጉ ቋሚ ሠራተኞችን ይዘዋል፡፡ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻውን ከ23,000 ያላነሱ ሠራተኞችን ይዞ እየተጓዘ ነው፡፡ ልማት ባንክና የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክም ከ4,000 ያላነሱ ሠራተኞች አሉዋቸው፡፡ በመሆኑ የባንክ ዘርፉ ብቻ ወደ 50,000 የሚጠጉ ሠራተኞችን ይዘዋል፡፡ እነዚህ ሠራተኞች ደግሞ ደመወዛቸው ክፍያ የሚያስከፍሉት የሥራ ግብር፣ የባንክ ዘርፉ ለመንግሥት የሚመነጨው የግብር ክፍያ ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያልም ተብሏል፡፡
የባንኮች ዓመታዊ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ በዓመት ውስጥ የባንኮች ዋነኛ ወጪያቸው የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ነው፡፡ የተሻለ ባለሙያዎችን ለመቅጠር ባለው ውድድር የፋይናንስ ተቋማት ሠራተኞች ደመወዝ በየዓመቱ በሚባል ደረጃ እያደገ በመምጣቱ፣ አብዛኛው ደመወዝተኛ ከደመወዙ 35 በመቶ ለደመወዝ ግብር የሚከፍል መሆኑንም ኃላፊዎቹ ያስታውሳሉ፡፡ ቀሪው ሠራተኛም ቢሆን ከሁለት ሺሕ ብር ባነሰ ደመወዝ የማይቀጠር በመሆኑ፣ ከባንኮች የደመወዝ ግብር ብቻ የሚገኘው ግብር ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከዚህም በላይ ሊጠቀስ የሚችልባቸው መገለጫዎች ያሉ መሆኑን የሚጠቁሙት አቶ ታዬ፣ በቀጥታ ከሚያስገቡት ግብር ሌላ ባንኮች ብድር የሚሰጣቸው የንግድ ድርጅቶች በብድሩ ሠርተውና አትርፈው የሚከፍሉት ግብርም ሊታወስ ይገባል ይላሉ፡፡ እያንዳንዱ የባንክ ባለአክሲዮኖች በየዓመቱ ከሚያገኙት የትርፍ ክፍፍል አሥር በመቶ ታክስ የሚከፍሉ መሆኑ፣ ባንኮች ለገቢ ግብር ዕድገት ያላቸው አስተዋጽኦ የሰፋ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የግል ባንኮች ከ50,000 በላይ ባለአክሲዮኖች እንዳሉ ይታወቃል፡፡
ባንኮች በጨረታ ከሚሸጡዋቸው ንብረቶችም መንግሥት የራሱ ድርሻ እንዳለው የሚጠቁሙት አቶ ወንድማገኝ፣ ባንኮች ዘመናዊ መሣሪያዎችና የአገልግሎት ግዥዎች ሲፈጽሙ መንግሥት የራሱ ድርሻ ስለሚኖረው ባንኮች ለገቢ ዕድገት በርካታ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ይላሉ፡፡
ከግል ባንኮች ውጭ ያሉ ሦስቱ መንግሥታዊ ባንኮችም በተመሳሳይ የአገሪቱን የታክስ ገቢ በማሳደጉ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡ ከግል ባንኮቹም የበለጠ በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር ግብር ያስገባሉ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ካሉት ከ23,000 በላይ ሠራተኞች ደመወዝ ተቆርጦ ለመንግሥት የሚከፈለው የሥራ ግብር ብቻ በመቶ ሚሊዮኖች ብሮች የሚገመት መሆኑም ዘርፉን አስተዋጽኦ ያሳያል ተብሏል፡፡
ባንኮች በግብር መልክ ከሚከፍሉት ከፍተኛ ገንዘብ ባሻገር በወጪና ገቢ ንግድ ላይ ካለ አገልግሎት በሚገኝ ገቢ እያንዳንዱ ባንክ 1.5 በመቶ በቀጥታ ለብሔራዊ ባንክ የሚከፍል በመሆኑም የመንግሥት ገቢን በማሳደጉ ረገድ ሌላ ማሳያ ነው፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ደግሞ የአገሪቱ ባንኮች በአገራዊ ኢኮኖሚው ላይ የሚያሳርፉት መልካም ተፅዕኖ እንዲሁም በግብርም ሆነ በሌላ መንገድ ለመንግሥት የሚያስገቡት ገቢ ከፍተኛ ስለመሆኑ ቢያምኑም የተለየ አስተያየት ግን አላቸው፡፡ ባንኮች በየትኛውም አገር የሚያስኙት አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን የፋይናንስ ዘርፉ አሁን እያስገኘ ነው ከሚባለውም በላይ ውጤት ሊመዘገብ የሚችለው የውጭ ባንኮች በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ቢካተቱ ነው ይላሉ፡፡
ይህ ዘርፍ ለውጭ ባንኮች እስካልተፈቀደ ድረስ አሁን ያሉት ባንኮች አገኙ ወይም አስገኙ የሚለውን ውጤት እንደ ትልቅ ነገር መመልከት ብቻ ተገቢ ይሆናል የሚል እምነት የላቸውም፡፡
ምክንያቱም አሁን ያሉት ሁሉም የአገሪቱ ባንኮች ቢጨፈለቁ አንድ የውጭ ባንክ ሊኖረው የሚችለውን ያህል አቅም ስለማይኖራቸው፣ ዘርፉን ለማሳደግና የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ከተፈለገ ዘርፉ ለውጭ ባንኮቹም ክፍት መሆን ይኖርበታል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ሆኖም ግን በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው ሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የባንክ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች ክፍት እንደማይሆን አረጋግጠዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዶክተር ቆስጠንጢኖስ ዓይነት ሐሳቦችን የማይቀበሉበት ዋነኛ ምክንያት ሲገልጹ፣ የውጭ ባንኮች ለአገር ውስጥ ተበዳሪዎች ምንም ገንዘብ ስለማያቀርቡ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች ለአገር ውስጥ አነስተኛና መካከለኛ ተበዳሪዎች ከሚያበድሩት ብድር ሃምሳ በመቶውን የሚሰጡ ከሆነ ግን ዘርፉ ለእነሱም ክፍት እንደሚሆን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በአፍሪካ የባንክ ኢንዱስትሪውን ለውጭ ባንኮች ክፍት አድርጎ የተቀመጠ አገር ካለ ጥሩልኝ፤›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
የግል ባንኮች በኢኮኖሚው ላይ የራሳቸው አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ የማይካድ መሆኑን የሚያስረዱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ በሌላ በኩል ግን ለባአክሲዮኖቻቸው እየከፈሉ ባሉት ዲቪደንድ ላይም የተለየ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የግል ባንኮች እየከፈሉ ያሉት ዲቪደንድ በየትኛውም አገር የግል ባንኮች የሚታይና አካሄዳቸውም በይበልጥ ባለአክሲዮኖቻቸውን የሚጠቅም ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ እስከ 60 በመቶ ዲቪደንድ እየከፈሉ ያሉ ባንኮች አሉ ያሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፣ ይህ እጅግ ብዙ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡ የዲቪደንድ ክፍያ መጠናቸው ማነስ ወይም ከትክክለኛው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጋር የተቃኘ መሆን ይኖርበታል በማለትም ገልጸዋል፡፡
ከዶ/ር ቆስጠንጢኖስ የተለየ አመለካከት ያላቸው የባንክ ባለሙያዎች ደግሞ የግል ባንኮች ለባለአክሲዮኖች ከሚከፍሉት ትርፍ የበለጠ እየሰጡ ያሉት አገልግሎት በተለየ ሊታይ ይገባል ይላሉ፡፡ የሚከፈለው የትርፍ ክፍፍል ክፍያ በንጽጽር ይቀመጥ ከተባለም አነስተኛ መሆኑን በማስረዳት የሚከራከሩም አሉ፡፡
እንደ አቶ ታዬ ገለጻ ከሆነ ደግሞ ባንኮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወደ መንግሥት እንዲገባ የሚያደርጉት ከፍተኛ ገንዘብና ባለአክሲዮኖች ያገኛሉ ከሚባለው ገንዘብ ጋር በንጽጽር ሲቀመጥ የመንግሥት ተጠቃሚነት ብልጫ አለው፡፡ አንድ ባንክ ለባለአክሲዮኖቹ ሊከፍል ከሚችለው ዲቪደንድ የበለጠ ለመንግሥት በግብር መልክ ብቻ የሚከፍለው ገንዘብ ሁለት ሦስት እጅ ብልጫ እንዳለውም ያመለክታሉ፡፡
ከባንኮች ዓመታዊ ትርፍ የበለጠውን እጅ የሚያገኘው መንግሥት መሆኑ በግልጽ የተቀመጠ መሆኑን በማስታወስ ከዶ/ር ቆስጠንጢኖስ የተለየ ምልከታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ አቶ ታዬ አፅዕኖት ሰጥተው እንደገለጹትም፣ የአገራችን የግል ባንኮች በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እያደረጉ ያሉት ተጨባጭ ተግባር የሥራቸውን ያህል ያልተነገረላቸው ናቸው፡፡ የባንኮችን አስተዋጽኦ እንዲህ በቀላል የሚታይ ያለመሆኑን ተናገረዋል፡፡ መንግሥት ቅድሚያ በማይሰጣቸው የብድር ዘርፎች የግል ባንኮች ክፍቱን በመሙላት እየሠሩ ነው፡፡ በተለይ የግል ዘርፉን ደጋፊ መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ወንድምአገኝም የግል ባንኮች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለመሆኑ ገልጸው፣ ተገልጋዩ በሚፈልገው መጠን መድረስ ተችሏል ግን ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡ ‹‹ዛሬም በርካታ ፋይናንስ የሚፈልጉ ኢንቨስትመንቶችና የኢንቨስትመንት ሐሳቦች አሉ፡፡ ግንባታቸው ተጀምረው የቆሙ ሕንፃዎች ሳይቀሩ ፋይናንስ የሚሹ መሆኑን ስናይ ገና ብዙ ይቀረናል ቢባልም፣ የግል ባንኮች አሁን እያበረከቱ ያሉት አስተዋጽኦ ግን የላቀ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የፋይናንስ ዘርፍ ትልቁ የመንግሥት ገቢ ምንጭ ስለመሆኑም ያምናሉ፡፡