Sunday, July 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ትርዒት ዝግጅትና እየተሰቀለ የመጣው የጨረታ ዋጋ አነጋጋሪነት

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የከተማዋ ብቸኛ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች የዝግጅት ሥፍራ ተደርጐ ይወሰዳል፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ይህ ማዕከል፣ ይኼ ነው የሚባል የይዘት ለውጥ ሳይደረግበት በየዓመቱ ወደ 50 የሚጠጉ የተለያዩ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች ይሰናዱበታል፡፡

የንግድ ትርዒት ዝግጅቶች በይዘትም ሆነ በቅርፅ የተለዩና የተሻሉ ለማድረግ ያስችላሉ የተባሉ መሠረተ ልማቶች አለው ለማለት አይቻልም፡፡ ዘመናዊ የንግድ ትርዒት ማዕከል ባለመሆኑም፣ የንግድ ትርዒት ዝግጅቶች ተመሳሳይ ይዘት የሚታይባቸው ሆነዋል፡፡ ማዕከሉ ይኼ ነው የሚባል የንግድ ትርዒት ማስዋቢያ ግብዓቶች የሌሉበትና ልቅ አዳራሾችን ብቻ የያዘ ነው ማለትም ይቻላል፡፡ የማዕከሉ ዋነኛ ገቢ እነዚህን አዳራሾችና በግቢው ውስጥ ያለውን ክፍት ቦታ በማከራየት የሚመነጭ ነው፡፡   

ማዕከሉ ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በተከታታይ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮችን በቋሚነት መዘጋጀት ቢጀምርም፣ የንግድ ትርዒቶችን በማዘጋጀት የሚታወቁ ኩባንያዎች ቁጥር ግን ሁለትና ሦስት ብቻ ነበሩ፡፡ በንግድ ትርዒትና ባዛሮቹ ላይ የሚሳተፉም የንግድ ድርጅቶች ቁጥርም አነስተኛ እንደነበር የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በንግድ ትርዒትና ባዛር ዝግጅት ቀዳሚ ስም ካላቸው ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ሴንቸሪ ፕሮሞሽን ኃላፊዎች እንደገለጹት፣ ተሳታፊ የንግድ ድርጅቶችን ማግኘት ከባድ ነበር፡፡

የንግድ ትርዒቶች ተሳታፊዎችን የሚመለከቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ 20 እና 30 ተሳታፊ ድርጅቶችን የያዙ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች ነበሩ፡፡ ከ15 ዓመታት በፊት በአንድ የፋሲካ በዓል ተንተርሶ በተዘጋጀ የንግድ ትርዒትና ባዛር ላይ 30 ድርጅቶች ብቻ የተሳተፉበት እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡  

አሁን ግን በተለይ የአዲስ ዓመት፣ የገናና የፋሲካ በዓላትን ተንተርሶ በሚዘጋጅ አንድ የንግድ ትርዒትና ባዛር ላይ ብቻ ተሳታፊ የሚሆኑ ድርጅቶች ቁጥር ከ400 በላይ ደርሷል፡፡ በቂ ቦታ ቢኖር ከዚህም በላይ ተሳታፊዎች ይካተቱ እንደነበር ይጠቀሳል፡፡ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት አድማሱ እንደገለጹት፣ የማዕከሉ አገልግሎት በሁሉም ረገድ እየሰፋና እያደገ መጥቷል፡፡ የተሳታፊዎች ቁጥር ብቻ ሳይሆን የንግድ ትርዒትና ባዛሮችን የሚያሰናዱ ኩባንያዎችም ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡

የንግድ ትርዒትና ባዛር ጠቀሜታን ሁሉም እየተረዳ ሲመጣ በተለይ ትላልቅ ዓውደ ዓመቶችን ተከትለው በሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች ላይ የተሳታፊ ድርጅቶች ቁጥር እያደገ መምጣት የማዕከሉን ገቢ እንዲጨምር ረድቶታል፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት ማዕከሉ በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ሥር መተዳደር ከመጀመሩ በፊት በንግድ ትርዒትና ባዛር አዘጋጅነት የሚታወቁ ኩባንያዎች አሥር የማይሞሉ እንደነበር አቶ ታምራት ይገልጻሉ፡፡ አሁን ግን በቋሚነትና ያዝ ለቀቅ ባለ አሠራር በንግድ ትርዒት ዝግጅት ለማሰናዳት የሚሳተፉ ኩባንያዎች 250 አካባቢ ደርሰዋል ይላሉ፡፡

ከበዓላት ውጪ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ዘርፎችና ስያሜዎች የሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶች ቁጥር እየጨመሩ መምጣት ማዕከሉ ዓመቱን በሙሉ በንግድ ትርዒቶች፣ ባዛርና መሰል ዝግጅቶች እንዲያዝ ያደረገ መሆኑን አቶ ታምራት ገልጸዋል፡፡

ዓመቱን በሙሉ በተለያዩ ስያሜዎችና ደረጃዎች የሚሰናዱና በተለያዩ ኩባንያዎች የሚካሄዱ የንግድ ትርዒቶች ቁጥር ማደጉ በተለይ የአዲስ ዓመት፣ የገናና የፋሲካ በዓላትን ተንተርሰው የሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮችን ለማዘጋጀት የሚሹ የንግድ ትርዒት አዘጋጅ ኩባንያዎች በመበራከታቸው ማዕከሉ ሥራውን በጨረታ ወደ መስጠት ገብቷል፡፡

በተለይ የገና፣ የፋሲካና የአዲስ ዓመት ዋዜማዎችን ተንተርሰው የሚሰናዱ የንግድ ትርዒቶችን ለማዘጋጀት ለሚሹ ኩባንያዎች ጨረታ መውጣት ከጀመረ ወደ አሥር ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን፣ ተወዳዳሪ ኩባንያዎች ዝግጅቱን ለማሰናዳት የሚሰጡት የጨረታ ዋጋም በየጊዜው እያደገ መጥቷል፡፡

ማዕከሉ ለኩባንያዎቹ ዝግጅት ጊዜ ለመስጠት ጨረታውን ቀደም ብሎ የሚያካሂድ ሲሆን፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊትም የ2008 የገና፣ የፋሲካና የአዲስ ዓመት የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮችን ለማዘጋጀት ባወጣው ጨረታ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ሊሰጥ ችሏል፡፡

ቀደም ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከ10 እስከ 15 ቀናት ለሚቆይ ዝግጅት ማዕከሉን ተከራይቶ ለመጠቀም ይሰጥ የነበረው ዋጋ አሁን እየተሰጠ ካለው ዋጋ ጋር ፈጽሞ የሚገናኝ አይደለም፡፡ ለሁለትና ሦስት ሳምንት ዝግጅት ማዕከሉን ተከራይቶ የንግድ ትርዒትና ባዛር ለማዘጋጀት እየተሰጠ ያለው ዋጋ እየናረ መምጣቱ ግን አነጋጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡

ከአሥር ዓመት በፊት በርካታ ጐብኝዎች ያላቸው በሦስቱ በዓላት ዋዜማ ወይም በዓላትን ተንተርሰው የሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች ለማሰናዳት አዘጋጅ ኩባንያዎች ይከፈሉ የነበረው ዋጋ አንድ ሚሊዮን ብር እንኳን የማይሞላ ነበር፡፡ የዛሬ አሥር ዓመት አካባቢ ጨረታ ሲጀመር ለአንድ የበዓል ዝግጅት ከአንድ እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ተሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህ መልክ የጨረታ ዋጋ ብዙም ዕድገት ሳያሳይ ቆይቶ በ2004 የገና በዓል 2.5 ሚሊዮን ብር መሰጠቱ ከፍተኛ ዋጋ ተብሎ ተመዝግቦ ነበር፡፡ በዚሁ ዓመት የፋሲካ ዋዜማ የንግድ ትርዒት ዝግጅት ደግሞ ሦስት ሚሊዮን ብር ተሰጥቶ ነበር፡፡ በ2005 ለገናና ለፋሲካ በዓላት ግን 3.6 ሚሊዮን ብር በመሰጠቱ የጨረታው ዕድገት እየፈጠነ መምጣቱን አሳይቷል፡፡

የ2007 የገና የንግድ ትርዒትና ባዛር ዝግጅት ባወጣው ጨረታ አሸናፊ የሆነው ኩባንያ 6.1 ሚሊዮን ብር ሲሰጥ፣ የፋሲካው አሸናፊ ደግሞ 4.5 ሚሊዮን ብር በመስጠት ከቀደመው በጀት ዓመት ከሁለት ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ዋጋ ሊቀርብ ችሏል፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሦስቱ በዓላት ዝግጅት እየተሰጠ ያለው ዋጋ ዕድገት እየጨመረ መጥቷል፡፡ የዋጋ ዕድገቱ ብቻ ሳይሆን የተፎካካሪ ኩባንያዎች ቁጥር ጨምሮ እስከ 15 ሊደርስ ችሏል፡፡

ለ2008 በጀት ዓመት ለሦስቱ በዓላት ዋዜማ የተደረገው ጨረታ ውጤት እንደሚያሳየው ደግሞ፣ የንግድ ትርዒት ዝግጅት የጨረታ ዋጋን የተለየ አድርጐታል፡፡ በ2008 የገና፣ የፋሲካና የአዲስ ዓመት ዋዜማ ዝግጅት ማዕከሉ ባወጣው ጨረታ አሸናፊ የሆኑት ኩባንያዎች ከፍተኛ ዋጋ የሰጡበት ሆኗል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ይፋ የተደረገው ውጤት እንዳሳየው፣ ለ2008 የገና በዓል የንግድ ትርዒት ዝግጅት አዩ አለሙ የተባለው ተጫራች ኩባንያ 12.6 ሚሊዮን ብር በመስጠት የጨረታው አሸናፊ ሆነዋል፡፡ በዚሁ ዕለት ለ2008 ፋሲካ በዓል የንግድ ትርዒትና ባዛር ዝግጅት የተከፈተውንም ጨረታ ይኸው ኩባንያ በ9.6 ሚሊዮን ብር ዋጋ በመስጠት አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡ አዩ አለሙ ለሁለቱ በዓላት የንግድ ትርዒትና ባዛር ዝግጅት የሰጠው ዋጋም ከቀደመው ዓመት ከተሰጡት ዋጋዎች ጋር ሲነፃፀር የሦስት ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡ የ2008 አዲስ ዓመት ዝግጅት አሸናፊ የሆነው ሐበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ሲሆን፣ የሰጠው ዋጋ 9.2 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ይህ ለንግድ ትርዒቶች ዝግጅት እየተሰጠ ያለው ዋጋ ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ እያደገ መጥቶ አሁን ያለበት ደረጃ መድረሱ ጤናማ አይደለም የሚል አስተያየት እየተሰጠበት ነው፡፡

በማዕከሉ ታይቶ የማይታወቅ ዋጋ ነው የተባለው የማሸነፊያ ዋጋ፣ የንግድ ትርዒትና ባዛር ዝግጅቶችን በከፍተኛ ደረጃ ወጪ የሚያሳድግ መሆኑ ደግሞ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ያስከትላል እየተባለ ነው፡፡

የጨረታ ዋጋው ከፍ ማለት ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል የሚሉ ወገኖች እንደሚገልጹት፣ ከባዛር መገለጫዎች አንዱ የሆነውን በተመጣጣኝ ዋጋ ሸመታ ማድረግን ይጎዳል ይላሉ፡፡ በባዛሮች ከመደበኛው ገበያ ያነሰ ዋጋ ምርታቸውን ለሸማቾች እንዳይቀርብ ያደርጋል ይላሉ፡፡

ዝግጅቱን ለማሰናዳት ውድድር የሚገቡ ኩባንያዎች የጨረታ ዋጋ እያደገ መምጣት፣ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና ለመሸጥ ከአሸናፊው ኩባንያ ጋር ቦታ የሚከራዩ ድርጅቶች የኪራይ ዋጋ ከፍ ስለሚል ተሳታፊ ኩባንያዎች ምርታቸውን በአነስተኛ ዋጋ ላያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ይህም በተከታታይ እየታየ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

ከአንዳንድ ተሳታፊ የንግድ ድርጅቶች እንደተገለጸው፣ ከጥቂት ዓመት በፊት ለበዓላት ዋዜማ ዝግጅት በካሬ ሜትር ከ100 ያነሰ ብር ይከፈል ነበር፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ደግሞ በካሬ ሜትር 60 ብር በመክፈል ድርጅቶች ምርትና አገልገሎታቸውን ያስተዋውቁና ምርቶቻቸውንም ይሸጡ ነበር፡፡ በዚህ ዋጋ መሠረት ስድስት ካሬ ሜትር የፈለገ የንግድ ድርጅት የሚከፈለው ክፍያ 600 ብር የሚደርስ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ቢበዛ የአንድ ካሬ ሜትር ዋጋ 200 እስከ 300 ብር የደረሱባቸው ጊዜያት አሉ፡፡ ይህ ግን አሁን ተቀርፏል፡፡ ለበዓላቱ ዝግጅት የሚሰጠው ዋጋ ተሳታፊዎችን የቦታ ኪራይ ዋጋ አንሮታል፡፡

ከአሥር ዓመት ወዲህ ግን ይህ ዋጋ እያደገ መጥቶ ባለፈው ዓመት ለፋሲካ የንግድ ትርዒት በአዳራሽ ውስጥ ምርትና አገልግሎቱን ለማስተዋወቅ እንዲሁም ምርቱን ለመሸጥ የሚፈልግ ተሳታፊ ድርጅት በአንድ ካሬ ሜትር ከሦስት ሺሕ ብር  በላይ ተጠይቋል፡፡ በዚም ዋጋ በማዕከሉ አዳራሽ ውስጥ ዘጠኝ ካሬ ሜትር ለመጠቀም የሚፈልግ ድርጅት ለዘጠኙ ካሬ ሜትር ቦታ 29,000 ብር ይከፈላል ማለት ነው፡፡ ተሳታፊዎቹ ድርጅቶች የውጭ ኩባንያዎች ከሆኑ ደግሞ ዋጋቸው የሚጨምር በመሆኑ በአዳራሽ ውስጥ ዘጠኝ ካሬ ሜትር የያዘ የውጭ ኩባንያ ደግሞ 34,200 ብር ይከፍላል፡፡

እንዲህ እያደገ በመጣ የኪራይ ዋጋ ቦታ ተከራይቶ ምርቱን ለመሸጥ የሚመጣው ድርጅት ምርቱን ምን ያህል ቢሸጠው ያዋጣዋል ሲባል፣ ከመደበኛውም ዋጋ በላይ ስለሚሆንበት ለበዓላት ተብለው በሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶች ላይ በቅናሽ ዋጋ እሸጥለታለሁ የሚለው ነገር እንዳይሠራ ያደርገዋል የሚል ሥጋት አለ፡፡

የብዙዎችም ሥጋት እዚህ ላይ ነው፡፡ የኢግዚብሽን ማዕከልን ተረክቦ የንግድ ትርዒት ለማዘጋጀት የሚሰጠው የጨረታ ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ እያደረገው ነው፡፡ በካሬ ሜትር እስከ ሦስት ሺሕ ብር የጠየቀው አሸናፊ ኩባንያ ከስድስት ሚሊዮን ብር ባልበለጠ ዋጋ ጨረታውን አሸንፎ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ አሁን ግን ከዚህ በላይ እስከ 12 ሚሊዮን ብር በመክፈል ማዕከሉን የተከራየ ኩባንያ፣ ተሳታፊ ድርጅቶች ለሚያከራዩት ቦታ የሚጠየቁት ዋጋ ይንራል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡  

አቶ ታምራት ግን ከዚህ የተለየ አስተያየት አላቸው፡፡ እየተሰጠ ያለው የጨረታ ዋጋ ገበያው ያመጣው ነው ይላሉ፡፡ እንደውም ወደፊት ከዚህም በላይ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ኩባንያዎቹ ለጨረታ የሚያቀርቡት ዋጋ ስለሚያዋጣቸው ነው ይላሉ፡፡ ተሳታፊዎች ላይ ጫና ያሳድራል የሚለውን ሥጋትም አይቀበሉትም፡፡ ዋጋው ቢጨምርም አዘጋጆቹ ለዝግጅቱ ከፍተኛ ወጪ ያስወጣቸዋል፡፡ አዳዲስ ነገሮችንም ለማቅረብ የሚያደርጉት ጥረት ወጪ ስላለው በተወሰነ ደረጃ ዋጋ መጨመሩ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ ከባሩ ጐን ለጐን ያለውና የመዝናኛ ፕሮግራም የራሱ ወጪ ያለውና ጐብኝዎችም የሚፈልጉት በመሆኑ፣ ክፍያው የተጋነነ ይሆናል የሚል እምነት የላቸውም፡፡   

የጨረታ ዋጋ ከፍ እያለ መምጣት ግን ለማዕከሉ ገቢ ዕድገት በር ከፍቷል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከአሥር ዓመት በፊት ማዕከሉን ለማስተዳደር ሲረከብ የማዕከሉ ዓመታዊ ገቢ 4.5 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡

በ2007 በጀት ዓመት መዝጊያ ላይ ግን የማዕከሉ ዓመታዊ ገቢ 38 ሚሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡ ከዚህ ገቢ ውስጥ በርካታ ኩባንያዎች የሚፎካከሩበት የገና፣ የፋሲካና የአዲስ ዓመት ዋዜማ ዝግጅት የሚከፈሉ ክፍያዎች 60 በመቶውን ይይዛሉ፡፡

ማዕከሉ በአዲስ አበባ አስተዳደር ባለቤትነት ሥር የሚተዳደር ቢሆንም፣ ከዓመታዊ ገቢው አስተዳደሩና ንግድ ምክር ቤቱ እኩል ተካፋይ ናቸው፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች