Monday, April 15, 2024

አዲስ አበባ ካስተናገደችው ጉባዔ መንግሥት ጆሮ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አዲስ አበባ ባስተናገደችው ሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ሁሉንም ወገን በሚያስደሰት ሁኔታ ስምምነት ያልተደረሰበት ጉዳይ፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን (Illicit Financial Flights) ለመግታትና አፍሪካውያንን ለመታደግ ዓለም አቀፍ የታክስ ተቋም እንዲመሠረት የቀረበው ጥያቄና ግፊት ተቀባይነት አለማግኘቱ ነው፡፡

ሰባ ሰባት አገሮችን ያቀፈው ቡድን 77 (G77) አገሮች ስብስብ በደቡብ አፍሪካው የፋይናንስ ሚኒስትርና የቡድኑ ተወካይ አማካይነት፣ ዓለም አቀፍ የታክስ ተቋም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) መዋቅር ውስጥ የመመሥረቱ አስፈላጊነትን ጉባዔው እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ባለፈው ማክሰኞ አቅርበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኃያላን አገሮች ማለትም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመንና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች የታክስ ተቋም የመመሥረቱ አስፈላጊነትን አልተቀበሉትም፡፡

ቡድን 77 የተባሉት አገሮች ያነሱት ዓለም አቀፍ የታክስ ተቋም የመቋቋም ሐሳብ በዓለም ታዋቂ በሆኑ ከ30 በላይ ሲቪክ ማኅበራት ከፍተኛ ተቀባይነትን በማግኘቱ፣ ኃያላን አገሮች እንዲቀበሉትም ሲቪክ ማኅበራቱ ግፊት ሲያደርጉ ነበር፡፡

ዓለም አቀፍ የታክስ ተቋም ቢመሠረት የታክስ ማጭበርበር የረቀቁ ሥልቶችን መከላከል፣ ታክስን የመደበቅ እንቅስቃሴን የማጋለጥ፣ እንዲሁም ተደራራቢ ታክስን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው አሠራርን ማስፈን ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመንና ሌሎች ምዕራባውያን አገሮች ይህንን ጥያቄ ሳይቀበሉ ውድቅ አድርገውታል፡፡

ጥያቄውን ውድቅ ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ታክስንም ሆነ ሌሎች የኢኮኖሚ ጉዳዮችን የሚመለከት የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት (OECD) የተፈለገውን ተልዕኮ መወጣት ይችላል በማለት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና የሀብት ማሸሽን ለመግታት ጥረት እያደረገ ነው የሚል መከራከርያ ያቀርባሉ፡፡

‹‹ዓለም አቀፍ ፍትሕ ለታክስ›› በተባለ ሲቪክ ማኅበር አስተባባሪነት ጫና እየፈጠሩ ያሉ ሲቪክ ማኅበራት፣ በታክስ ዙሪያ ዓለም አቀፋዊ ትብብር የለም የሚል መከራከርያ አለማቅረባቸውን ይናገራሉ፡፡ በርካቶቹ ኃያላን አገሮች ከጥቂት ታዳጊ አገሮች ጋር የታክስ ትብብር እንዳላቸው ግልጽ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

‹‹ታክስ አገራዊ ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ከምንም በላይ የጎላ ዋስትና ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ሁሉንም የዓለም አገሮች ባሳተታፈ መንገድ እንጂ፣ ጥቂት አገሮች እንዳሻቸው የሚያደርጉት መሆን የለበትም፤›› በማለት የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት (OECD) የተባለው ድርጅት የታዳጊ አገሮችን በተለይም የአፍሪካ አገሮችን ጥቅም የሚያስከብር አይደለም በማለት፣ በአዲስ አበባው ጉባዔ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት (OECD) ከተመሠረተ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ አባል አገሮቹ 34 ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አንድም የአፍሪካ አገር ወይም በማደግ ላይ የሚገኙት የእስያ አካባቢ አገሮች አባል አይደሉም፡፡

‹‹ዓለም አቀፍ የታክስ ሥርዓቶች በሀብታሞችና በኃያላን ብቻ የሚወሰኑ ከሆነ፣ ውሳኔው የሚካሄደው የእነሱን ፍላጎትና ጥቅም በጠበቀ መንገድ ነው፡፡ አጠቃላይ ዓላማውም በአፍሪካና በሌሎች ታዳጊ አገሮች የተሰማሩ የኃያላኑ ኩባንያዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ነው፤›› ሲሉ የሲቪክ ማኅበራቱ ይከራከራሉ፡፡

ክርስቲያን ኤይድ የተባለው ዓለም አቀፍ ሲቪክ ማኅበር በአዲስ አበባ በተካሄደው ሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ በመገኘት ዓለም አቀፍ የታክስ ተቋም እንዲመሠረት ግፊት ካደረጉት ሲቪክ ማኅበራት መካከል ይገኝበታል፡፡

በማኅበራዊ ድረ ገጹም ‹‹ዓለም አቀፍ የታክስ ተቋም እንዳይመሠረት እንግሊዝ ከኃያላኑ ጋር መተባበሯ አሳፋሪ ነው፤›› ብሏል፡፡ ኦክስፋም ኢንተርናሽናል የተባለው ሲቪክ ማኅበር በበኩሉ፣ ‹‹በንግድ ጉዳይ ላይ ለምን ዓለም አቀፍ ተቋም ኖረ? ለምን በጤና ጉዳይ ላይ? ለምን በእግር ኳስ?›› የሚል መከራከሪያውን በትዊተር ገጹ ላይ አውጥቷል፡፡

በሁለቱም ወገኖች በኩል ያለው መከራከሪያ ዓለማው ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርንና የሀብት መሸሸግን መከላከል ነው፡፡ ራሱ “OECD” የተባለው ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2014 ባወጣው ጥናት፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና የሀብት ማሸሽ ምን ያህል ታዳጊ አገሮችን እየጎዳ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ መቀመጫውን በአሜሪካ ዋሽንግተን ያደረገው ግሎባል ፋይናንሺያል ኢንተለጀንስ ያወጣውን ሪፖርት የጠቀሰው የ‹‹OECD›› ጥናት፣ እ.ኤ.አ. ከ2001 እስከ 2010 ባሉት ዓመታት ብቻ በዚህ የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሀብት ማሸሽ ታዳጊ አገሮች 5.8 ትሪሊዮን ዶላር ማጣታቸውን ገልጿል፡፡ ይህም እያንዳንዱ የአፍሪካ አገር በዓመት ከኃያላን አገሮች ከሚያገኘው የልማት ዕርዳታ በእጥፍ ይበልጣል ማለት ነው፡፡

ከተጠቀሰው እጅግ ግዙፍ የሆነ ገንዘብ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ተጓዘ የሚባለው ወደ ቻይና ነው፡፡ በሁለተኛነት የገንዘብ መዳረሻ ተብላ የተጠቀሰችው ደግሞ ሜክሲኮ ናት፡፡ ገንዘቡ የሚወጣበት መንገድ የተለያየ ቢሆንም ታክስ መሰወር፣ ታክስ ማጭበርበር፣ በሕገወጥ መንግድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ ማድረግ (Money Laundering) ይገኙበታል፡፡

ሁለቱም ወገኖች በዋናው ችግር ላይ ቢግባቡም፣ መፍትሔውን በተመለከተ ግን ይለያያሉ፡፡ የኢኮኖሚው ትብብርና ልማት ድርጅት (OECD) ‹‹አዲስ ምዕራፍ ለታክስ ግልጽነት›› የሚል ኢንሼቲቭ በመቅረፅ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ፣ ይህም የአፍሪካ አገሮች ለልማት የሚያስፈልጋቸውን ፋይናንስ ከታክስ ሥርዓቱ አሟጠው እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል ይላል፡፡

የታክስ ግልጽነት ሥርዓቱ አገሮች በታክስ ጉዳይ ላይ ያላቸውን መረጃ በመለዋወጥ እንዲተባበሩ፣ ኃያላን አገሮች የታክስ ሥርዓት ተሞክሯቸውን በሥልጠና ለታዳጊ አገሮች እንዲያካፍሉ፣ የታክስ መርማሪዎችን፣ ዳኞችንና ዓቃቢያነ ሕጎችን ማሠልጠን የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ይህንን አሠራር የጀመረው እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ መሆኑን ከኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ እስካሁን በተደረጉት የታክስ ትብብሮች ደቡብ አፍሪካ 62.2 ሚሊዮን ዶላር እ.ኤ.አ. በ2013 በተደረገ የመረጃ ልውውጥ ማዳኗን ያመለክታል፡፡

በኮሎምቢያ አንድ ኩባንያ ላይ በትብብር በተደረገ የታክስ ኦዲት፣ ኩባንያው እ.ኤ.አ. እስከ 2011 ድረስ አሳንሶ ሲከፍል የነበረው ሦስት ሚሊዮን ዶላር እ.ኤ.አ. ወደ 33.2 ሚሊዮን ዶላር ማደጉን ይገልጻል፡፡

በሁለቱ ወገኖች በኩል የተካሄደው ሙግት ምንም እንኳን ሲቪክ ማኅበራት ከታዳጊ አገሮች ጎን ቢሠለፉም፣ የኃያላን አገሮቹን የበላይነት መቋቋም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በመሆኑም በኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ሥር የታክስ ትብብር እንዲመሠረትና የአገሮች የታክስ ሥርዓት መደገፍ፣ ሥልጠና መስጠትና መረጃ መለዋወጥ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና የሀብት ማሸሽ በአፍሪካ አገሮች ላይ ለፈጠረው ችግር የታዘዘ መከላከያ መፍትሔ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ ምን ልትማር ይገባታል?

ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተክነውባቸዋል የሚባሉት ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ማለትም ታክስ መሰወር፣ ታክስ ማጭበርበርና የመሳሰሉት አፍሪካውያን የተፈተኑበት ችግር ኢትዮጵያን አልነካም ማለት አይቻልም፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአመዛኙ በግብርና ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ መንግሥት ይህንን የግብርና ኢኮኖሚ በአበባ ልማት ዘርፍ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ባደረገበት ወቅት ይህ ችግር ተከስቷል፡፡

በ1990ዎቹ አጋማሽ ትኩረት የተሰጠው የአበባ ልማት በርካታ የአውሮፓ ኩባንያዎችን መሳቡ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች አብዛኞቹ 30 በመቶ መነሻ ካፒታል በመያዝ፣ 70 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ስለመበደራቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኩባንያዎቹ ግን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡትን ትክክለኛ የአበባ መሸጫ ዋጋን ከመንግሥት በመደበቅ፣ ልዩነቱን በውጭ ባንኮቻቸው ያስቀምጡ እንደነበር በወቅቱ የወጡ መረጃዎች የመለክታሉ፡፡

ይህንን ተግባር በመጨረሻ የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አማካይነት ባወጣው መመርያ አንድ ዘንግ አበባ በየትኛውም የውጭ ገበያ ከአሥር ሳንቲም ዶላር በታች እንዳይሸጥ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ለውጭ ገበያ የቀረበ የአበባ ሽያጭ ገቢ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ገቢ እንዲደረገም በመመርያው ወስኗል፡፡

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ትንሽ የማይባሉ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ መውጣታቸው ይታወሳል፡፡ በ2007 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለፓርላማ አቅርበው የነበሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው፣ በኢትዮጵያ የቆዳ ምርቶች ኤክስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ስምንት ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡት በውጭ ለሚገኙ እህት ኩባንያዎቻቸው መሆኑንና ለግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን የሚያስገቡት በተመሳሳይ ከእህት ኩባንያዎቻቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህ መሆኑ ችግር እንደሌለው፣ ነገር ግን የታክስ ማጭበርበሪያ መንገድ ሊሆን እንደሚችል ወይም በትርፍነት የተገኘው ዶላር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የሚደረግ ሥልት እንደሆነ መገመት እንደሚቻል በመጥቀስ፣ ኩባንያዎቹ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ አደርገዋለሁ ባለችው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ፕሮግራም የሞት የሽረት የተባለ ትኩረት የተሰጠው ኢንዱስትራላይዜሽን፣ ከሚፈልጋቸው ጥንቃቄዎች አንዱ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሀብት ማሸሽ ዋነኛው ነው፡፡

በተለይ መንግሥት በኢንዱስትሪው ዘርፍ መሠረት ለመጣል በተለያዩ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ መንደሮችን እየገነባ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ በቅርቡ እንደተናገሩት፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ የኢንዱስትሪ ፕሮግራም ለውጭ ኩባንያዎች ቅድሚያ ትኩረት እንደሚሰጥና መሠረቱ የሚጣለውም በእነዚህ ኩባንያዎች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያውያን የተሻለ ዘለቄታዊ ጥቅም ኖሯቸው ሳይሆን፣ በፍጥነት ወደ ገበያው ለመግባት የሚያስችል የገበያ ሰንሰለትን የፈጠሩ፣ አቅምና ልምድ ያላቸው በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡

ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የሀብት ማሸሽ፣ ታክስ ስወራና ሌሎች የመሳሰሉት ማጭበርበሮች አፍሪካውያንን እንዴት እየበዘበዙ እንደሆነ ሦስተኛው የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ፍንትው አድርጎ አሳይቷል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በሁለተኛው የጂቲፒ ዕቅድ ውስጥ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ማስቆም የሚችል ጠንካራ የታክስ ተቋም ማደራጀት፣ ዓለም አቀፍ የታክስ ትብብሮችን መፍጠር፣ የፋይናንስ ተቋማቱን የቁጥጥር አቅም መጎልበትን ከወዲሁ ማየትና መፈተሽ እንደሚገባው ያስገነዘበ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -