Wednesday, March 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ምስክር ሆነው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጠ

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ምስክር ሆነው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጠ

ቀን:

–  ሞትና የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው መብታቸው ተሽሯል የሚላቸው መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

ከአንድ ዓመት በፊት ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከየመን ሰነአ አውሮፕላን ማረፊያ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በመከላከያ ምስክርነት ሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 19ኛ ወንጀል ችሎት አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የሰጠው ሐምሌ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በሽብር ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦባቸው እንዲከላከሉ ውሳኔ የሰጠባቸው እነዘመኑ ካሴ (አሥር ሰዎች)፣ ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር የተገናኘ የወንጀል ድርጊት ፈጽማችኋል የሚል ክስ ስለተመሠረተባቸው፣ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡላቸው በመጠየቃቸው ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀው ከግንቦት 7 ጋር ከፍተኛ ግንኙነት እንዳላቸው፣ ኤርትራ ውስጥ ሆነው ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር በመገናኘት ኢትዮጵያ ውስጥ ሽብር ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል ተብለው የሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ዘመኑ ካሴ፣ አቶ አሸናፊ አካሉ፣ አቶ ደህናሁን ቤዛ፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን፣ አቶ አንሙት የኔዋስ፣ አቶ ደሳለኝ አሰፋ፣ ምክትል ኢንስፔክተር ሙልዬ ማናዬ፣ አቶ ዓለም አካሉና አቶ ሙሉዓለም ሲሳይ ናቸው፡፡

ከተከሳሾቹ መካከል አቶ አሸናፊ አካሉ፣ አቶ ደህናሁን ቤዛ፣ አቶ ምናዬ ጥላሁን፣ አቶ አንሙት የኔዋስና አቶ ደሳለኝ አሰፋ በእነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል የክስ መዝገብ [ቅንጅት] የዕድሜ ልክ እስራትና በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ የሞት ቅጣት ከተፈረደባቸው አቶ አንዳርጋቸው ጋር ኤርትራ ውስጥ ይገናኙ እንደነበር በክሱ ተዘርዝሯል፡፡

ተከሳሾቹ ኤርትራ ውስጥ ሥልጠና በመውሰድ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች እንዴት መጠቀም እንደሚገባቸው በማጥናት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው አባላትን መመልመላቸውን በክሱ ተዘርዝሯል፡፡ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃምና በተለያዩ አካባቢዎች ጫካ ገብተው ጦርነት ለመክፈት በማቀድ፣ በማደራጀትና ተልዕኮ በመስጠት አመራሮችን ለመግደል ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክስ ዝርዝሩ ያስረዳል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት አምስቱ ተከሳሾች በተለይ ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር መገናኘታቸውንና የተለያዩ ምክርና ሥልጠናዎችን መውሰዳቸው በክሱ ስለተገለጸ፣ አቶ አንዳርጋቸው አገር ውስጥ ስላሉ ቀርበው የመከላከያ ምስክርነት እንዲሰጡላቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት እንዳይቀርቡ አጥብቆ ተቃውሟል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ለምን እንደተቃወመ ሲያስረዳ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 123 (ሀ) መሠረት አቶ አንዳርጋቸው ከሕዝባዊ መብታቸው በተለይም ከመራጭነት መብት፣ በአንድ ምርጫ ተካፋይ መሆንና ለሕዝብ አገልግሎት ሥራ ከመመረጥ፣ ወይም በውል ስምምነት ላይ ምስክርና ዋስ ከመሆን፣ ለፍርድ ሥራ ልዩ አዋቂ ወይም ኗሪ ሆነው ከመሥራት መብታቸው መሻራቸውን አስረድቷል፡፡ ይህንን መብታቸውንም እንዲያጡ የተደረገው በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የክስ መዝገብና በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ የዕድሜ ልክ እስራትና የሞት ቅጣት ስለተወሰነባቸው መሆኑንም ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ብይን እንደገለጸው፣ አቶ አንዳርጋቸው እንዲቀርቡ የተጠየቀው ለዋስትና ወይም ልዩ አዋቂ ምስክር ሆነው ሳይሆን፣ ‹‹ነበሩበት›› በተባሉበት ጉዳይ እንዲናገሩ ለምስክርነት ነው፡፡ ምስክርነት ግዴታ እንጂ መብት ባለመሆኑ አቶ አንዳርጋቸው ሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ፣ ለፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ትዕዛዝ እንዲጻፍ ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...