Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት ግምገማ ጀመሩ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት ግምገማ ጀመሩ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔን ጨምሮ በአስተዳደሩ ሥር የሚገኙ ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች አመራሮች ባለፈው ሐሙስ የማጠቃለያ ግምገማ ጀመሩ፡፡ ግምገማው ለአምስት ተከታታይ ቀናት የተዘጋጀ በመሆኑ፣ በዋናነት በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ዕቅዶች አፈጻጸምና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የነበሩ እንቅፋቶች በግምገማው ትልቅ ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በከተማው አስተዳደር ክልል ውስጥ የታዩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችና በግንቦት ወር በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ የነበረው አፈጻጸም ይገመገማል ተብሏል፡፡ በግምገማው የመጨረሻዎቹ ሁለት ቀናት ባለሥልጣናቱና የበታች ሠራተኞች የነበራቸው የሥራ አፈጻጸም ድክመት ወይም ውጤት በተናጠል ግምገማ እንደሚካሄድበት ታውቋል፡፡

ከዚህ በኋላ ከሐምሌ 15 እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በማዕከል ደረጃ የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማና የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች የሚመሩት ግምገማ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

በዚህ የግምገማ መድረክ የከተማው ባለሥልጣናት እንደ ሥራ አፈጻጸማቸው ደረጃ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ባሉበት ወይም ለተሻለ ኃላፊነት ይታጫሉ፡፡ በሙስና የተጠረጠሩ እንደሚቀርብባቸው ማስረጃ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ መረጃ ያልተገኘባቸው ባለሥልጣናት ደግሞ ድርጅቱ (ኢሕአዴግ) በሚመድባቸው ቦታ ይዛወራሉ ተብሏል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተካሄዱት የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና የምክር ቤቱ ጉባዔዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግር መኖሩ ከነዋሪዎች ተነስቷል፡፡

በመልካም አስተዳደር በኩል በወረዳ፣ በክፍለ ከተማ፣ በማዕከል እንዲሁም በዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ችግሩ ከመሻሻል ይልቅ እየተንሰራፋ መምጣቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ በተለይ ወረዳና ክፍላተ ከተሞች በአዋጅ የተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ቢኖርም፣ ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ ማጉላላት እንደሚቀናቸውና ከማጉላላትም የበለጠ ደግሞ ነዋሪዎች ጉዳያቸውን ይዘው ወደ ማዕከል እንዲሄዱ ይገፉዋቸዋል ተብሏል፡፡

ይህ ክስተት መኖሩን ለማስረዳት ከአነስተኛ እስከ ትላልቅ ጉዳዮች ድረስ ወደ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የሚጎርፉ መሆናቸውን፣ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ባለጉዳዮችን በሚያስተናግድበት በሳምንት ሁለት ቀናት፣ በርካታ ባለጉዳዮች ጽሕፈት ቤቱን ሲያጥለቀልቁ ማየት የተለመደ መሆኑ በችግርነት ይነሳል፡፡

ከንቲባ ድሪባ የዓመቱን ማጠቃለያ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅትም የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎቱ አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት ጥናት እየተደረገ ቢሆንም፣ አሁንም ችግሩ በሚፈለገው ደረጃ ባለመፈታቱ ቀጣይ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ይሆናል ብለዋል፡፡ ከንቲባ ድሪባ በትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውይይት ላይም፣ “ከፊታችን የተደቀነውን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ታግለን ማሸነፍ እንችላለን፤” ካሉ በኋላ፣ “ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማጥፋት ቁርጠኝነት አለው፡፡ በየደረጃው በውስጣችን ሌቦችና ዘራፊዎች አሉ፡፡ በመንግሥት እየማሉና እየተገዘቱ የሚመነትፉ አሉ፡፡ መንግሥት እነዚህን አካላት ለማጥፋት ቁርጠኛ ነው፡፡ ውስጣችን ሆነው የሚያደናቅፉትን ማጥራት ይኖርብናል፤” በማለት ጠንከር ባለ አገላለጽ ችግሩን አስረድተዋል፡፡

ምንጮች እንደሚገልጹት፣ አሁን የሚካሄደው ግምገማ ጠንከር ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ነዋሪዎች ባገኙት አጋጣሚ የከተማውን የመልካም አስተዳደር ችግር ከማንሳታቸው በተጓዳኝ፣ በቅርቡ በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት በምርጫ ካርዳቸው ላይ በርካታ ችግሮችን በማስገባት ወቀሳቸውን በተዘዋዋሪ ሰንዝረዋል፡፡

“ይህ ለኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የሚያስተላልፈው መልዕክት ኅብረተሰቡ  ከፍተኛ ቅሬታ እንዳለው ነው፡፡ ሥር የሰደደውን ችግር ለመበጣጠስ የሐምሌ ወሩ ግምገማ ከፍተኛ ቦታ ይኖረዋል፤” በማለት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የአስተዳደሩ ምንጮች ይናገራሉ፡፡

በተለይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተንሰራፍተው የሚገኙት በግል ይዞታ፣ በመሬት፣ በንግድ፣ በገቢ፣ በግዥ፣ በፕሮጀክቶች ጥናት፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚመደብ በጀትና ጥቅማ ጥቅምን ላልተገባ ዓላማ ማዋል የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

በፖለቲካ ረገድ በከተማው አለ የተባለው ችግር ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ሐሳብ መግለጫ መድረክ ማሳጠትና የሃይማኖት አክራሪነት አዝማሚያ መታየት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የግምገማው ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ በብሔራዊ ፓርቲዎች ቀጣይ ግምገማ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡ ብሔራዊ ፓርቲዎች የሚባሉት ሕወሓት፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴግ ናቸው፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...