Wednesday, September 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ኋላቀሩ የግብይት ሥርዓት ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል!

  በአገራችን ኋላቀር የግብይት ሥርዓት ውስጥ የሚታዩት በርካታ ችግሮች የሥር ነቀል ለውጥ ያለህ እያሉ ነው፡፡ ይህ ከዘመኑ ጋር እኩል መራመድ ያቃተው በሴራና በአሻጥር የተተበተበ የግብይት ሥርዓት ለሕዝቡ አቅም በላይ ሆኖበታል፡፡ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ ሰሞኑን የልኳንዳ ነጋዴዎች ለተጠቃሚዎች ሥጋ ባለማቅረባቸው ምክንያት የተፈጠረው ክስተት እንደ አንድ ማሳያ ሆኖ አንዳንድ ጉዳዮችን እንድንቃኝ ያደርገናል፡፡ ዋና ዋና የሚባሉትን እንደሚከተለው እንመለከታቸዋለን፡፡

  1. የግብይት ሥርዓቱ በሥርዓተ አልበኞች ተወሯል

  ጤነኛ የሚባል የግብይት ሥርዓት ዋነኛ ተዋናዮቹ ማለትም ሸማች፣ ነጋዴና መንግሥት እየተናበቡበት በሥርዓት ይካሄዳል፡፡ እነዚህ ሦስት አካላት በሚገባ ካልተናበቡ የግብይት ሥርዓቱ ይታወካል፡፡ በተለይ ኢኮኖሚው በነፃ የገበያ ሥርዓት ይመራበታል በሚባልበት አገር ውስጥ የግብይት ሥርዓቱ ከታወከ በሥርዓተ አልበኞች ለመወረሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ ሦስቱ አካላት ካላቸው ሚናና ኃላፊነት አንፃር የሚታዩትን ችግሮች እናብራራው፡፡

  በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ ነጋዴዎች ጤናማና ፍትሐዊ በሆነ ውድድር መፎካከር አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በስፋት የሚታየው አልጠግብ ባይ ነጋዴዎች የመወዳደሪያ ሜዳውን መውረራቸው ነው፡፡ በአምራችነት፣ በአስመጪነት፣ በጅምላ አከፋፋይነትና በቸርቻሪነት ሥራዎች ውስጥ የተሰማሩ የተወሰኑ የተደራጁ ኃይሎች ጤናማ ውድድር እንዳይኖር እያደረጉ ነው፡፡ የምርትና የአቅርቦት ሰንሰለቶችን በመቆጣጠር ዋጋ እንደፈለጉ ይወስናሉ፡፡ የአቅርቦትና የሥርጭት መስመሮችን ይዘጋሉ፡፡ ሰው ሠራሽ እጥረት በመፍጠር ዋጋ ይቆልላሉ፡፡ ሰላማዊና ጤናማ መሆን የሚገባውን የውድድር ሜዳ በማጣበብ ሕገወጥነትን ያሰፍናሉ፡፡ እነዚህ የተደራጁ ኃይሎች የግብይት ሥርዓቱን ከዘመናዊ አሠራር ጋር በማጣላት ሕዝቡን ይበዘብዛሉ፡፡

  እነዚህ ወገኖች እዚህ ኋላቀር የግብይት ሥርዓት ውስጥ ዘለው ከገቡ ሕገወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር፣ ጤናማ ውድድር እንዳይኖር እያደረጉ ነው፡፡ ደላላ ትልቁን ሚና የሚጫወትበት ይህ ሥርዓት አልባ የንግድ ሥርዓት፣ በተጨማሪም ስውር የንግድ ተዋንያንን ያሳትፋል፡፡ የመንግሥት ግብርና ቀረጥ ያልተከፈለባቸው ሸቀጦችን ገበያ ውስጥ የሚያስገቡ እነዚህ ስውር ተዋንያን የሚደገፉት በደላላ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሥርዓተ አልበኞች ሕግና ደንብ አክብረው በሚሠሩ ታታሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ከመፍጠራቸውም በላይ፣ የሕዝቡን ኑሮ እያናጉ ነው፡፡

  የነፃ ገበያ ሥርዓት ትርጉሙ ተዛብቶ ሥርዓተ አልበኝነት ሲነግሥ እያየን ነው፡፡ አልጠግብ ባዮች በምግብ ምርቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰው ሠራሽ ጭማሪዎች ሲያደርጉ፣ መሠረታዊ የሚባሉ የፍጆታ ዕቃዎች ከሸማቾች ማኅበራት ሳይቀር በሕገወጥ መንገድ እያወጡ በተጋነነ ትርፍ ሲሸጡ፣ በኔትወርክ የተሳሰሩ ስግብግቦች ምርቶችን ሲደብቁ፣ ባዕድ ነገሮች ምርቶች ውስጥ ሲደባልቁና እጅግ በጣም አሳፋሪ የሆነ የሚዛን ማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ እንዴት ጤናማ የግብይት ሥርዓት ይኖራል? እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡

  1. የቁጥጥር መላላት የግብይት ሥርዓቱን መረን ለቆታል

  መንግሥት ፍትሐዊ የሆነ የውድድር ሜዳ በማመቻቸት የግብይት ሥርዓቱን ጤናማነት የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት፡፡ የሸማቾችና የንግድ ሥራዎች ውድድር ሕግ በማውጣት ይህንን ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ይኼ መረን የተለቀቀ የግብይት ሥርዓት ልጓም ተበጅቶለታል ወይ? ሕግ ቢኖርም የቁጥጥር ሥርዓቱን የሚያስፈጽሙ አካላት ወይም ግለሰቦች በብቃት ሥራቸውን እየሠሩ ነው ወይ? ኃላፊነት የማይሰማቸው አልጠግብ ባይ ነጋዴዎችና የእነሱ ቢጤ የሆኑ የመንግሥት ሹማምንት ያልተገባ ግንኙነት ይታወቃል ወይ? ድንገተኛ ክስተቶች ሲያጋጥሙ በዘመቻ የሚፈጸመው ቅጣት ነው? ወይስ ፍትሐዊ የመወዳደሪያ ሜዳ ለማስፈን ነው ጥረት የሚደረገው? የመሳሰሉት ጥያቄዎች ምላሽ ይሻሉ፡፡

  ሰሞኑን የልኳንዳ ባለቤቶች ለሚገዙዋቸው የቁም እንስሳት ሕጋዊ ደረሰኝ ማግኘት ባለመቻላቸው ምክንያት የሥጋ አቅርቦት ተስተጓጉሎ ነበር፡፡ በመረጃ እጥረት ይሁን ወይም ለማደናገር ለዕርድ የተጋነነ ክፍያ በመጠየቁም ሥራቸውን ማቆማቸው ተሰምቷል፡፡ የልኳንዳ ነጋዴዎች ለመንግሥት የሚከፍሉት ግብር ከቁም እንስሳት ነጋዴዎች በሚያገኙት ሕጋዊ ደረሰኝ ተሰልቶ ከሆነ፣ የቁም እንስሳት ነጋዴዎችን ደረሰኝ እንዲያቀርቡ ለምን ማስገደድ አልተቻለም? መንግሥት እነዚህን ዝም ብሎ ልኳንዳ ነጋዴዎቹ ላይ ብቻ ማፍጠጡ ተገቢ አይደለም፡፡ ሁሉንም ወደ ታክስ ሥርዓቱ እንዲገቡ ማድረግ ፍትሐዊ አሠራር ነው፡፡ የልኳንዳ ነጋዴዎች መብታቸውን በሕጋዊ መንገድ ማስከበር ሲገባቸው፣ በአድማ ለበላተኛው ሥጋ እንዳይቀርብ ማድረጋቸው የተዝረከረከው የግብይት ሥርዓት ውጤት ለመሆኑ አንዱ ማረጋገጫ ነው፡፡ ቁጥጥሩ የላላ ባይሆን ኖሮ ይህ ድርጊታቸው ለከፋ ቅጣት ይዳርግ ነበር፡፡

  ለቁጥጥሩ መላላት የመጀመሪያው ምክንያት መንግሥት በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያለውን መረጃ በትክክል አለማወቁ ነው፡፡ መንግሥት ያለው የመረጃ ተዓማኒነት ላይ ችግር አለ፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ከግብይት ሥርዓቱ ጋር የሚያያዙ ችግሮች ሲፈጠሩ፣ የሚወሰደው ዕርምጃ እሳት የማጥፋት ይመስላል፡፡ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ከገበያ ውስጥ ሲጠፉ ለቅጣት የሚዳረገው ታች ያለው ቸርቻሪ ነው፡፡ ነገር ግን የአቅርቦት መስመሩን አንቀው የሚይዙት የተደራጁ ኃይሎች ማንም አያገኛቸውም፡፡ የግብይት ሥርዓቱን ጤናማ እንዳይሆንና ፍትሐዊ ውድድር እንዳይኖር አሻጥር የሚፈጽሙ ኃይሎች ተፅዕኖ በጣም የበረታ በመሆኑ፣ የማስፈጸም አቅሙም እጅግ  የተዳከመ ነው፡፡ ይኼም ያሳስባል፡፡ አፋጣኝ መፍትሔም ይፈለጋል፡፡

  1. የትርፍ ሕዳግ አለመኖር ሌላው ችግር ነው

  የግብይት ሥርዓቱ ኋላቀር በመሆኑ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል ሲባል፣ በዲሲፕሊን የሚመራ የትርፍ ሕዳግና ጥቅም የማግኘት ባህል አለመኖሩ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች አንስቶ፣ አልባሳትና መጫሚያዎች፣ የቤትና የቢሮ መገልገያ መሣሪያዎች፣ ወዘተ የመሳሰሉት ከተገዙበት ዋጋ በላይ የእጥፍ እጥፍ ይተረፍባቸዋል፡፡ ይኼ ደግሞ ንግድ ሳይሆን ዘረፋ ነው፡፡ ጤናማና ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ ቢኖር ኖሮ መንግሥት ፈጽሞ ጣልቃ ሳይገባ፣ በጤናማ የውድድር መርህ መሠረት ተግባራዊ ይደረግ ነበር፡፡ አልጠግብ ባዮች ሌላው ቀርቶ ቀረጥ ያልከፈሉባቸውን ምርቶች ሳይቀር በተጋነነ ዋጋ እየሸጡ ግብይቱን ያተራምሳሉ፡፡ ሕጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ ያስወጣሉ፡፡

  በመንግሥት አሠራር ረገድ ደግሞ ቀልጣፋ የሆነ የወጪና ገቢ ንግድን በዘመናዊ የጉምሩክ ሥርዓት ማስተናገድ አለመቻል ሌላው ችግር ነው፡፡ በተለይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በዓለም ገበያ ያላቸው ወቅታዊ ትክክለኛ ዋጋ አለመታወቅ፣ ከዋጋ በታችና በላይ የሆኑ ሪፖርቶች በደፋርና በስግብግብ ነጋዴዎች ሲቀርብ ችላ ማለት ወይም መመሳጠርና የመሳሰሉት ችግሮችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተደማምረው የግብይት ሥርዓቱ ስለትርፍ ሕዳግ እንዳያውቅ ሲደረግ፣ የሥርዓተ አልበኞችና የሕገወጦች መጫወቻ ይሆናል፡፡ ጤናማ ውድድር በሌለበት ጤናማ ትርፍ ስለማይታሰብ ገበያው የዘራፊዎች ሲሳይ ይሆናል፡፡ የአገር ጥቅም ይጎዳል፡፡

  1. የሸማቾች አቅም ኮስምኗል

  ፍትሐዊና ጤናማ የግብይት ሥርዓት በሌለበት ዋናው ተጎጂ ሸማቾች ናቸው፡፡ በአገራችን ጠንካራ የሸማቾች ማኅበራት ወይም ወኪሎች ስለሌሉ፣ ሸማቾች የአልጠግብ ባዮች ሰለባ ናቸው፡፡ በንግድ ማኅበረሰቡ ውስጥ ሕግና ሥርዓት ጠብቀው ሸማቾችን የሚያገለግሉ ያሉትን ያህል፣ በስግብግብነት የሚመዘብሯቸው ሞልተዋል፡፡ ሸማቾች ገበያው ውስጥ ሲገቡ ለመብቶቻቸው የሚከራከሩ ወኪሎች ስለማይኖሩዋቸው የተጋለጡ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ጥራታቸው ለተጓደሉ ምርቶች የተጋነነ ዋጋ ሲጠየቁ፣ በሚዛን ሲዘረፉና የተለያዩ እንግልቶች ሲደርሱባቸው እንቢተኛ መሆን አይችሉም፡፡ የተጋነነ ዋጋን የጥራት መለኪያ አድርገው ይቀበላሉ፡፡ የተደራጁ ስግብግቦች በሚፈጥሩት ወከባ ምክንያት ስለማይረጋጉ የተጠየቁትን ሳይወዱ በግድ ይከፍላሉ፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ኋላቀር በመሆኑ መተማመኛ የላቸውም፡፡ ወቅታዊ የተብራራ መረጃ ስለማያገኙና ገበያውን ውዥንብር ስለሞላው የተጠየቁትን ከማድረግ ውጪ አማራጭ የላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት አቅማቸው የኮሰመነ ነው፡፡

  በአጠቃላይ ይኼ ኋላቀርና ከዘመኑ ጋር መራመድ ያቃተው የግብይት ሥርዓት በዚህ ሁኔታ መቀጠል የለበትም፡፡ በተለይ መንግሥት ከዘመኑ ጋር የሚራመድ የፖሊሲ ማዕቀፍ አውጥቶ፣ የቁጥጥር ሥርዓቱን የሚያግዙለት አሠራሮችን ማስፈን አለበት፡፡ በሠለጠነ የሰው ኃይልም ሆነ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ይኼንን ኋላቀር የግብይት ሥርዓት ማፍረስ አለበት፡፡ ጤናማና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዲኖር ሕገወጦችና ስውር ተዋናዮች ከሜዳው ውስጥ መወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ በደላላ የሚመራ የግብይት ሥርዓት አገር ያጠፋል፡፡ ሕዝቡን ያራቁታል፡፡ በመሆኑም ይኼ ኋላቀር የግብይት ሥርዓት ሥር ነቀል ለውጥ ይካሄድበት!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

  ‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

  የአገር ውስጥ የፍራፍሬ ገበያን ፍላጎት ይሸፍናል የተባለለት የብላቴው እርሻ ልማት

  መንግሥት የግብርና ምርታማነትና የፍራፍሬ ምርትን ለማሳደግ በ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› በሚል...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ጦርነቱና ውስጣዊ ችግሮች

  መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው...

  መኖሪያ ሸጦ መዞሪያ!

  እነሆ ከመካኒሳ ወደ ጀሞ ልንጓዝ ነው። ቀና ሲሉት እየጎበጠ...

  በምግብ ራሳችንን የመቻል ፈተና

  በጋሹ ሃብቴ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ በምግብ ራሳችንን መቻል እጅግ በጣም የተወሳሰበ...

  የግሉ ዘርፍና የሕፃናት ማቆያዎች ዕጦት

  የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑ ሴቶች ለትምህርት ያልደረሱ ልጆቻቸውን የሚያውሉበት ማቆያ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡ ከዚህ ኢፍትሐዊ ዓለም መፍትሔ ይገኛል ብሎ መጠበቅ የማይቻልበት ጊዜ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ የዓለምን ሚዛን ያስጠብቃሉ...

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...