Friday, April 19, 2024

በፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ላይ የቀረቡ አጀንዳዎች በሙሉ ስምምነት እንዲፀድቁ የኢትዮጵያ ሚና ትልቅ እንደነበረ ተገለጸ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

–  በስምምነቱ ያልተደሰቱ አገሮች ነበሩ

ለሦስተኛ ጊዜ የተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ በስኬት መጠናቀቁን መንግሥት አስታወቀ፡፡ ለጉባዔው የቀረበው የአዲስ አበባ የድርጊት አጀንዳ ሰነድም በ193 አገሮች ስምምነት ተደርጎበት መፅደቁ፣ የኢትዮጵያ የአስታራቂነት ሚና ታክሎበት እንደሆነ ተገለጸ፡፡

የጉባዔውን ዝግጀት በብሔራዊ ደረጃ የመሩት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ባለፈው ዓርብ ሐምሌ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አዳራሽ በሰጡት መግለጫ፣ በሀብታም አገሮችና በማደግ ላይ ባሉት አገሮች መካከል ለስምምነት ያስቸገሩ የመደራደሪያ ነጥቦችን በመሸምገልና አስታራቂ ሐሳቦችን በማቅረብ፣ የመጨረሻው ሰነድ ስምምነት ተደርጎበት እንዲወጣ ኢትዮጵያ ሚና ነበራት ብለዋል፡፡

ሚኒስትሮቹ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንዳስታወቁት፣ የአዲስ አበባው የድርጊት አጀንዳ ሰነድ የሁሉንም አገሮች ፍላጎቶች አካቶ ፀድቋል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ የፀደቀው ሰነድ በሙሉ ስምምነትና ሰጥቶ በመቀበል መርህ መሠረት ለውጤት የበቃ ቢሆንም፣ ለሁሉም አገሮች ሙሉ ለሙሉ በጣም ጥሩ ይዘት ያለው ነው ብሎ መደምደም እንደማይቻልም አስታውቀዋል፡፡ 193 አገሮች ያላቸውን ፍላጎት በሙሉ ያሟላ ስምምነት ቢሆንም የተወሰኑ አገሮች ቅሬታ እንዳቀረቡ ዶ/ር ቴድሮስ አክለዋል፡፡

አቶ ሱፊያን በበኩላቸው፣ ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ከተወሰነ በኋላ መንግሥት ከሁለት ወራት በኋላ በኒውዮርክ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ይፀድቃል የተባለውን ሰነድ አገሮች ተስማምተውበት እንዲሄዱ ለማድረግ መንግሥት ሲዘጋጅ እንደነበር፣ ለጉባዔው ስኬታማነትም በአዲስ አበባና በኒውዮርክ የተቋቋመ ቡድን እንቅስቃሴ ሲያድርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

በ134 አንቀጾች የተጠቃለለው የአዲስ አበባ የድርጊት አጀንዳ ሰነድ፣ በዋናነት በሰነዱ ለተካተቱት የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገው ፋይናንስ ከየት ይገኛል? እንዴት ይገኛል? የሚሉ ውድይቶች ለበርካታ ጊዜያት ሲደረጉ ቆይተው፣ በኢትዮጵያው ጉባዔ እልባት አግኝተዋል በማለት አቶ ሱፊያን ሲገልጹ፣ የፋይናንስ ምንጮች ይሆናሉ ከተባሉት መካከልም የግሉ ዘርፍ፣ ኦፊሴሊያዊ የልማት ዕርዳታዎች፣ የአገሮች የታክስ ገቢ መጨመርና በግሉ ዘርፍና በመንግሥታት በጋራ የሚደረግ ቅይጥ የፋይናንስ ምንጮች የዘላቂ የልማት ግቦችን ፋይናንስ ለማድረግ ይታሰባል፡፡ ለዚህም ስምምነት ተደርጓል ሲሉ አቶ ሱፊያን አስረድተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የሲቪል ተቋማት የአዲስ አበባው ጉባዔ መልካም አጋጣሚዎችን ያመከነና ታዳጊ አገሮችን የሚጎዳ ስምምነት የተደረገበት እያሉ ሲያጣጥሉት ከርመዋል፡፡ በተለይ ዓለም አቀፍ የታክስ ተቋም እንዲቋቋምና የግሉ ዘርፍ እንደ ባለድርሻ አይካተት የሚሉ ጥያቄዎች ጎልተው ወጥተዋል፡፡ ይህንን በማስመልከት ማብራሪያ የሰጡት ዶ/ር ቴድሮስ፣ በሲቪል ማኅበራቱ የተነሱት ነጥቦች ስህተት ናቸው ባይባሉም፣ በድርድርና በሰጥቶ መቀበል ሒደት ውስጥ የሁሉንም ፍላጎት የሚያሟሉና የሚያስማሙ ነጥቦች በሁሉም አገሮች ዘንድ ፀድቀው መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሲቪል ተቋማቱ ጉባዔው ሲካሄድ በነበረበት ወቅት በስብሰባ አደራሾች አካባቢ ያደርጉ የነበረውን የተቃውሞ ሠልፍም በመመልከት የሚያነሷቸውን ነጥቦች፣ በዶ/ር ቴድሮስ የተመራው ዓብይ ኮሚቴ መከታተሉን አስታውቀዋል፡፡  

በአዲስ አበባ ስምምነት የተደረገበት የተመድ የድርጊት አጀንዳ ከዚህ ቀደም በሜክሲኮ ሞንቴሬ ከተማና በኳታር ዶሃ ከተካሄዱት ሁለት ጉባዔዎች የተሻለ ውጤትና አዳዲስ ስምምነቶችን ያካተተ፣ በይዘቱም ሰፊ መሆኑን ሚኒስትሮቹ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ካልነበሩት መካከል የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት የፋይናንስ ድጋፍ ማድረጊያ ሥልቶች፣ የቴክኖሎጂ ፋሲሊቲና የቴክኖሎጂ ባንክ ማቋቋም ጽንሰ ሐሳብ፣ የተዘረፉ የድሆች አገሮችን ሀብት ማስመለስና የገንዘብ ማሸሽ ተግባራትን ለመከላከል ስምምነት መደረጉ፣ የአዲስ አበባውን ጉባዔ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ሁሉ የተለየ ሆኖ እንዲታይ የሚያደርጉት መሆናቸውን ዶ/ር ቴድሮስ አብራርተዋል፡፡ ስምምነት የተደረገበት የአዲስ አበባው የድርጊት አጀንዳ ሰነድ 134 አንቀጾች ውስጥ ሃያዎቹ ወሳኝና መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡ መባላቸውንም ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ ጉባዔው ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሚናዋን የተጫወተችበት መድረክ ነው ሲሉት፣ በአገሮች መካከል የተነሱ የልዩነት ነጥቦችን ከመሸምገል ባሻገር አገሪቱ በትልልቅ አጀንዳዎች ላይ ዕምነት የሚጣልባት እንድትሆን ያስቻለ ነው በማለት አቶ ሱፊያን የጉባዔውን ስኬታማነት ገልጸዋል፡፡

ከወጪ አኳያ ለማንኛውም ስብሰባ የሚደረገው የመስተንግዶ፣ የተሽከርካሪ አቅርቦትና የሰው ኃይል ወጪ መውጣቱንና ይህም ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ አቶ ሱፊያን አስታውቀው፣ ከወትሮው የተለየ የቪዛና የኢሚግሬሽን አገልግሎት አሰጣጥ ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ወቅታዊ ገጽታ የሚያስተዋውቅ ‹‹የኢትዮጵያ መንደር›› የተሰኘ ዓውደ ርዕይ መካሄዱ፣ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ያሳዩ ሥራዎች መሆናቸውን በመጥቀስ የጉባዔውን በስኬት መጠናቀቅ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -