Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊብሮድካስት ባለሥልጣንና ዛሚ ራዲዮ የፈጠሩት ውዝግብ በባለሥልጣኑ ቦርድ ውሳኔ ተፈታ

ብሮድካስት ባለሥልጣንና ዛሚ ራዲዮ የፈጠሩት ውዝግብ በባለሥልጣኑ ቦርድ ውሳኔ ተፈታ

ቀን:

–  ባለሥልጣኑ በጣቢያውና በኢትዮፒካሊንክ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ውድቅ ተደርጓል

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በዛሚ 90.7 ኤፍኤም ራዲዮ ጣቢያ በሚተላለፈው ኢትዮፒካሊንክ ፕሮግራም ላይ የቀረበን አቤቱታ ምክንያት በማድረግ ሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሬዲዮ ጣቢያው የጻፈው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያና ኢትዮፒካሊንክ የተባለው ፕሮግራም ላይ የሰጠው ዕግድ ትዕዛዝ ውድቅ ተደረገ፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎች በኢትዮፒካሊንክ ፕሮግራም ላይ መልስ የመስጠት መብታቸው እንዲከበር ሲልም ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

      በሬዲዮ ጣቢያውና በብሮድካስት ባለሥልጣን መካከል ተፈጥሮ ለነበረው አለመግባባት ምክንያቱ አቶ ዳንኤል ተገኝና አቶ አብርሃም ግዛው የተባሉ ግለሰቦች፣ በሬዲዮ ጣቢያው በሚተላለፈው ኢትዮፒካሊንክ ፕሮግራም ላይ ያላግባብ ስማቸው መጥፋቱን በመግለጽ ያቀረቡት አቤቱታ ነው፡፡

ጉዳዩን እንደመረመረ የገለጸው የብሮድካስት ባለሥልጣን ለሬዲዮ ጣቢያው ግንቦት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ኢትዮፒካሊንክ የተባለው ፕሮግራም መታገዱን፣ እንዲሁም ሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሬዲዮ ጣቢያው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡

በድርጊቱ ተገቢነት ያላመኑት የጣቢያው ባለቤቶችና ሥራ አመራሮች ጉዳዩን በይግባኝ ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የበላይ ለሆነው ቦርድ አቅርበዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በሆኑት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ የሚመራው ቦርድ ጉዳዩን መርምሮ ሐምሌ 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ፣ ባለሥልጣኑ ለዛሚ ሬዲዮ የሰጠውን ማስጠንቀቂያና በኢትዮፒካሊንክ ላይ የሰጠውን የዕግድ ትዕዛዝ ውድቅ ማድረጉን፣ የብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ ማክሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮፒካሊንክ ፕሮግራም የሚተላለፈው ‹ውስጥ አዋቂ› የተሰኘው ፕሮግራም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው፣ ይህንንም ውሳኔ ዛሚ ራዲዮ ጣቢያ እንዲያስፈጽም ቦርዱ ውሳኔ መስጠቱን አቶ ልዑል ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለቅሬታ አቅራቢዎች አቶ ዳንኤል ተገኝና አቶ አብርሃም ግዛው በተመጣጣኝና በተመሳሳይ ጊዜ መልስ የመስጠት መብት እንዲሰጣቸው ቦርዱ ውሳኔውን አሳልፏል፡፡

ባለሥልጣኑ በተቋቋመበት አዋጅ መሠረት የብሮድካስት ጣቢያዎች በሚያሰራጩት ፕሮግራም ‹‹ሰብዓዊ መብቴ ተነክቷል ወይም ሰብዓዊ ክብሬ ተነክቷል›› የሚሉ ግለሰቦች ለባለሥልጣኑ ወይም ለፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችሉ የገለጹት አቶ ልዑል፣ በዚህ መሠረት በቀረበው አቤቱታ ባለሥልጣኑ ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ውሳኔውን በመቃወም ሬዲዮ ጣቢያው ለቦርዱ አቤቱታ በማቅረቡ፣ የባለሥልጣኑ ውሳኔ ላይ ከላይ የተገለጸውን ውሳኔ ቦርዱ ማሳለፉን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቦርዱ በሰጠው ውሳኔ ሁላችንም ተምረናል፤›› ያሉት አቶ ልዑል፣ ‹‹ሕግ አክብሮ የመሥራት ተገቢነትን ለሚዲያ ተቋማት ማስተማሩን፣ ቅሬታዎች ለብሮድካስት ባለሥልጣን መቅረብ አንደሚችል ለኅብረተሰቡ እንደሁም የባለሥልጣኑ ውሳኔ ላይ ለቦርዱ ይግባኝ ማለት እንደሚቻል የተማርንበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዛሚ ሬዲዮ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ተሾመ፣ ‹‹በጉዳዩ ላይ ብንጠየቅ ልንሰጠው የምንችለውን ምላሽ ባለሥልጣኑ በሰጠው መግለጫ ሰጥቷል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይግባኝ በማለታችን በፕሮግራሙ ላይ ባለሥልጣኑ የላከው የዕግድ ትዕዛዝም ሆነ ለጣቢያው የሰጠው ማስጠንቀቂያ በቦርዱ ተነስቷል፤›› ያሉት አቶ ዘሪሁን ውሳኔውን ተገቢ ብለውታል፡፡

ከዚህ ውጪ ቅሬታ አቅራቢዎቹ በቀረበው ፕሮግራም ላይ ያላቸውን መልስ የመስጠት መብት ከአንድም ሁለት ጊዜ ጣቢያውም ሆነ የፕሮግራሙ አዘጋጆች መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁንም ቅሬታ አቅራቢዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዘሪሁን፣ በመጀመርያም ቢሆን የቀረበውን አቤቱታ በመግባባት መፍታት እንደሚቻል፣ በኢትዮጵያ የሚዲያ አያያዝን በተመለከተ ተቆጣጣሪ አካላት ለየት ያለ ትዕግሥትን ተላብሰው የመቻቻልና የማግባባት ሥራ ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮፒካሊንክ ፕሮግራም ባለቤት የሆነው አክሱም ፒክቸርስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኔ ንጉሴ፣ ‹‹ጉዳዩ እዚህ ደረጃ መድረሱ አሳዝኖኛል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ችግሮች ሲከሰቱ ባለሥልጣኑ የማግባባት ሥራ እንደሚሠራ የተናገሩት አቶ ብርሃኔ ቅሬታው ገና ከሥሩ መስተካከል ይችል እንደነበርና የተሄደበት መንገድ ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑ፣ ይልቁኑም ‹‹የሚዲያ ተቋማትን የሚያሸማቅቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...