Friday, December 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየተስፋ በር

  የተስፋ በር

  ቀን:

  ክረምት እንደመሆኑ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ በመሆኑም በማዕከሉ ውስጥ የሚኖሩና ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ሕፃናት የማዕከሉ ወቅታዊ ፕሮግራም የሆነውን የሥነ ሕይወት ትምህርት በመከታተል ላይ ናቸው፡፡ ጥቂት የማይባሉ ዕድሜያቸው ለትምህርት ያልደረሰ ሕፃናት ደግሞ በየማደሪያ ክፍላቸው ይቦርቃሉ፡፡ የተኙ ሕፃናትም አሉ፡፡ መካኒሳ አካባቢ ቫቲካን ኤምባሲ ጎን በሚገኘው ኤሆፕ የሕፃናት ማሳደጊያ ቅጥር ሁሉም ነገር እንደተለመደው ይመስላል፡፡

  ከደቂቃዎች በኋላ ግን ነገሮች መልካቸውን ቀየሩ፡፡ በአንድ ክፍል ሆነው የዕለቱን ትምህርት ሲከታተሉ የነበሩ ሕፃናት ወጥተው መቦረቅ ጀመሩ፡፡ ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ዳና ሀይዲ እና ሎረል ኬሪ ከአሜሪካ የመጡ ልዑኮች ከጉባኤው ጎን ለጎን ማሳደጊያውን ጎብኝተው ነበር፡፡ ለሕፃናቱ የሚሆን ልዩ ልዩ ስጦታዎችም አበርክተዋል፡፡

  ማሳደጊያው የዛሬውን ስያሜ ከመያዙ አስቀድሞ እናት የሕፃናት ማሳደጊያ ይባል ነበር፡፡ እናት በ1996 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን 47 የሚሆኑ ወላጅ አልባ ሕፃናት ያስተዳድር ነበር፡፡ ብዙዎቹም ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ነበሩ፡፡ ነገር ግን በነበረበት የአስተዳደር ችግር ተቋሙ ፈረሰ፡፡ ወዲያውም በአዲስ አደረጃጀት ኤሆፕ ኢትዮጵያ በሚል ስያሜ ዳግም ተመሠረተ፡፡ በእናት የሕፃናት ማሳደጊያ የነበሩ ሕፃናትና ብዙዎቹ ሠራተኞች ዳግም በኤሆፕ ተሰባሰቡ፡፡ በወቅቱ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት እንደዛሬው በቀላል የሚገኝ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ‹‹ሕፃናቱ ያላቸውን ቀሪ ሕይወት በደስታ እንዲያሳልፉ›› በሚል ልጆቹን መንከባከብ ነበር ዋናው ጉዳይ፡፡ ቀጣይ ሕይወታቸውን በተመለከተ ብዙ የሚያስቡት አልነበረም፡ ብዙ ጊዜም የሕፃናቱን በሽታ የመከላከል አቅም የሚገነቡ የምግብ ዓይነቶችን በማቅረብ ላይ ያተኩሩ ነበር፡፡ በዚህ የተወሰነ መከላከል ቢችሉም ፈተናው ግን ከባድ ነበር፡፡ በማዕከሉ ከሚኖሩ ሕፃናት በአማካይ በሳምንት እስከ ሁለት ሕፃናት ሕይወታቸው ያልፍ ነበር፡፡ ይህም በመላው ሠራተኛና ሕፃናቱ ከባድ ስሜት ይፈጥር ነበር፡፡

  የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት በቀላሉ መገኘት ሲጀምር ግን ለማዕከሉ እፎይታ ሆነ፡፡ የሚሞቱ ሕፃናት ቁጥር ቀነሰ፡፡ ዛሬ ላይ የሕፃናቱ ቁጥር 230 ሲሆን በዚህኛው ማዕከል 90 የሚሆኑ ወላጅ አልባ ሕፃናት ይኖራሉ፡፡

  የአሥር ዓመቷ ሕፃን በማዕከሉ ከሚኖሩ መካከል ነች፡፡ እናቷን በሞት የተነጠቀችው ሕፃን አባቷን አታውቀውም፡፡ እናቷ በጠና ታምማ በነበረበት ወቅት ከአባቷ ቤተ ዘመዶች ጋር ልታገናኛት ፍላጎት የነበራት ቢሆንም፣ ህልሟን ሳታሳካው ሞት ቀደማት፡፡ ከዚያም ታዳጊዋ የበረታ ችግር ይገጥማትም ጀመረ፡፡

  ታላቅ እህቷ ኑሮን ለማሸነፍ ብዙ ብትጥርም አልተሳካላትም፡፡ የነበራት ብቸኛ አማራጭም ሴትነቷን ሽጣ ኑሮን መግፋት ነበር፡፡ በዚህ የእህቷ ሥራ ምክንያት የልጅ አእምሮዋ ሊረዳውና ሊሸከመው የማይችለውን ብዙ ነገር ተመልክታለች፡፡

  ሁኔታው ያስጨንቃት ስለነበርም በትምህርቷ ደካማ ነበረች፡፡ ከሌሎቹ ተማሪዎችም የተለየ ባህሪ ታሳይ ነበር፡፡ ሁኔታዋን በትኩረት ይከታተል የነበረ አንድ መምህር ቀርቦ አናገራት፡፡ ጉዳዩንም በልጅ አንደበቷ አስረዳችው፡፡ በመሀልም በጠና ታምማ ስለነበር በአንድ ሆስፒታል ተኝታ ሕክምና ተከታትላለች፡፡

  በተደረገላት የደም ምርመራም የኤችአይቪ ቫይረስ በደሟ ውስጥ መኖሩ ታወቀ፡፡ ታዳጊዋ የተለየ እንክብካቤ የሚያሻት ቢሆንም እህቷ ግን ልታስታምማት አልቻለችም፡፡ ከጎኗ የቆመው መምህሯ ብቻ ሆነ፡፡ ‹‹የምፈልገውን ነገር ያደርግልኝ ነበር፡፡ ድኜ ከወጣሁኝ በኋላም እሱ ጋር ኖሬአለሁኝ፡፡ በትምህርት እንድጎብዝ ይረዳኝ ነበር፤›› ትላለች፡፡ ሊረዳት የሚችል ድርጅት በማፈላለግ ላይ ሳለም ኤሆፕ የሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከልን አገኘ፡፡ ወደ ማዕከሉ ከመጣች ሦስት ወር ሆኗታል፡፡ በጥሩ እንክብካቤ ላይ እንደምትገኝ ከሁኔታዋ መረዳት ይቻላል፡፡ ሰውነቷ ሞላ ያለ ነው፡፡ አመድማ ሹራብ ደርባለች፡፡ ፀጉሯ ተላጭቷል፡፡ አናቷን እንዳይበርዳትም የሹራብ ኮፍያ ጣል አድርጋለች፡፡ በማዕከሉ ካሉት ሁሉ ፈጣን በመሆን ትታወቃለች፡፡ የረዳትን አስተማሪዋን ከነቤተሰቦቹ ዓለምን የማስጎብኘት ፍላጎት እንዳላት ትናገራለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ‹‹ሳድግ አውሮፕላን አብራሪ መሆን እፈልጋለሁ፤›› በማለት ትልቅ ውለታ ያደረገላትን መምህሯን ማስደሰት ህልሟ መሆኑን ትገልጻለች፡፡

  በማዕከሉ ያገኘነው ሌላው የ9 ዓመቱ ታዳጊ ስለ ወላጆቹ ብዙ አያውቅም፡፡ ለዓመታት የኖረው በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ነበር፡፡ እንዴት ወደ ሆስፒታሉ ሊገባ እንደቻለ ባያውቀውም ከማዕከሉ መረጃዎች ማግኘት ተችሏል፡፡ ወላጅ እናቱ በጠና ታማ ስለነበር ሆስፒታል ተኝታ በመታከም ላይ ነበረች፡፡ በወቅቱ ቢበዛ የሁለት ዓመት ሕጻን የነበረው ልጇ የሚንከባከበው ሌላ ሰው አልነበረም፡፡ ስለዚህም ከእናቱ ጋ ሆስፒታል ለመቆየት ተገደደ፡፡

  አስፈላጊው ሕክምና ቢደረግለትም የወላጅ እናቱን ሕይወት ማትረፍ አልተቻለም፡፡ ሕፃኑ በሆስፒታሉ ቀረ፡፡ ሕፃኑን ከሆስፒታል አውጥቶ የሚያሳድግ ቤተሰብ አልተገኘም፡፡ የሕክምና ባለሙያዎቹም ሕፃኑን በሆስፒታሉ ከመንከባከብ ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ ውሎና አዳሩ ከሐኪሞች ጋር ሆነ፡፡ ሐኪሞቹ ከሥራቸው ጎን ለጎን ሕፃኑን ማልበስ፣ ማብላት ማጠጣት የዘወትር ሥራቸው ሆነ፡፡ ዕድሜው ከፍ እያለ ሲመጣም እንደ ቤተሰቡ የሚቆጥራቸውም የሚንከባከቡትን የሕክምና ባለሙያዎች ሆነ፡፡ በዚህ መልኩ ዓመታት አለፉ፡፡ በመሀል ግን አንዳች ችግር ገጠመው፡፡

  ወላጅ እናቱ የሞተችው በኤችአይቪ ቢሆንም በሕፃኑ ደም ውስጥ ቫይረሱ ይገኛል ብሎ የጠረጠረ አልነበረም፡፡ በአንድ ወቅት ግን በጠና ታምሞ ተኛ፡፡ በተደረገለት የደም ምርመራም ቫይረሱ በደሙ ውስጥ እንደሚገኝ ታወቀ፡፡ በተደረገለት ክትትልም አገግሞ ተነሳ፡፡ ባለሙያዎቹም ሰዓቱን ጠብቀው ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቱን ይሰጡት ነበር፡፡ ነገር ግን በቂ እንክብካቤ የሚያገኝበትን ቦታ ማፈላለግ ግድ ሆነ፡፡ በመሆኑም ወደ ኤሆፕ የሕጻናት መንከባከቢያ ድርጅት ወሰዱት፡፡ በማሳደጊያው መኖር ከጀመረ ሁለት ዓመት ይሆነዋል፡፡

  ሲስተር የትናየት ከፈለኝ በማዕከሉ በመምህርትነት ከአምስት ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ሕፃናት በእጅጉ የተጎዱ፣ ቆዳቸው የቆሳሰለ፣ በጣም ከሲታ የሆኑና የሲዲ ፎር መጠናቸው እስከ 68 ድረስ የወረደ  በሞትና ሕይወት መካከል የሆኑ ሕፃናት ናቸው፡፡ በማዕከሉ በሚደረግላቸው እንክብካቤም የብዙዎቹ ጤና የሚመለስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

  ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎችን ማግለልና አድሎ ይደርስ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን የአብዛኛው ሰው አመለካከት ተቀይሯል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ የማግለሉ አጋጣሚ በማዕከሉ በሚኖሩ ሕፃናት ላይ ይደርሳል፡፡

  በአንድ ወቅትም ይማሩበት የነበረው ትምህርት ቤት ቫይረሱ በደማቸው መኖሩን ሲያውቅ አባሯቸዋል፡፡ አቶ መንገሻ ሽብሩ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር እንደሚሉት ድርጅቱ መሠረታዊ የገንዘብ እጥረት አለበት፡፡ ብዙ ጊዜም ለሠራተኞች በቂ ደመወዝ መክፈል ስለማይቻል ብዙ ጊዜ ሠራተኞች ይለቃሉ፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...