‹‹ኑ እናንብብ›› ያለፈው ሳምንት ማገባደጃ (ሐምሌ 11 እና 12) የተካሄደ ፌስቲቫልና ትኩረቱን ሕፃናትን ለንባብ ማነሳሳት ላይ ያደረገ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ባህል ማዕከል በተካሄደው ፌስቲቫል የሕፃናት መጻሕፍት ለገበያ ቀርበዋል፡፡ ሕፃናትን የሚያዝናኑ ጨዋታዎች፣ ቴአትሮች እንዲሁም ሌሎችም ክንውኖች የፌስቲቫሉ አካል ነበሩ፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው እንዲያነቡ ለማበረታታት በፌስቲቫሉ የተገኙ ወላጆች እንዲሁም ሸዋፈራሁ ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎችም ታዋቂ ግለሰቦች ለሕፃናት መጽሐፍ እንዲያነቡ ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኢቢኤስ) ላይ የኢትዮጲስ ጊዜ በተሰኘው የሕፃናት መርሐ ግብር የምትታወቀው ኢትዮጲስም የተገኘች ሲሆን፣ በሕፃናት መካከል ልዩ ልዩ ውድድሮች በማካሄድ መጻሕፍት ሸልማለች፡፡ ከውድድሮቹ መካከል ሥዕል መሳል አንዱ ነበር፡፡
የኢትዮጲስ ፕሮግራም ማናጀር ወ/ሮ አንድነት አማረ እንደምትናገረው፣ ልጆች የንባብ ባህላቸውን እንዲያዳብሩና ወላጆቻቸው እንዲያበረታቷቸው ለማነሳሳት ያለመ ፌስቲቫል ነው፡፡ ከ20 በላይ የሕፃናት መጻሕፍት ሻጮች ተገኝተዋል፡፡ ልጆች እየተዝናኑ ስለንባብ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርጉ መርሐ ግብሮችም ተካተዋል፡፡ ሕፃናቱን እንዲያዝናኑ የተሰናዱ ዝግጅቶች ንባብ ተኮር ቢሆኑም የታቀደውን ያህል መጻሕፍት እንዳልተሸጡና በልጆች ትኩረቱ የተሰጣቸው መዝናኛዎቹ እንደነበሩ ትናገራለች፡፡ ዓላማቸው ወላጆች መጻሕፍት እንዲገዙ ማበረታታት እንደነበረና ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አለመሳካቱን ትገልጻለች፡፡
ቢሆንም ግን መሰል ፌስቲቫሎችን በተከታታይ በማዘጋጀት ስለንባብ ያለውን ግንዛቤ ማስፋት እንዳለባቸው መገንዘባቸውን ትናገራለች፡፡ ‹‹ንባብ ያለውን ጠቀሜታ ደጋግሞ በመናገር፣ መጻሕፍት ወደሚሸጥባቸው ድንኳኖች ልጆች እንዲሄዱ በማድረግ፣ ለሕፃናት መጻሕፍት በመሸለምና በንባብ ተምሳሌት መሆን የሚችሉ ልጆችን በማስተዋወቅ ፌስቲቫሉን ንባብ ተኮር ለማድረግ ሞክረናል፤›› ትላለች ወ/ሮ አንድነት፡፡ ቢሆንም የጠበቁትን ያህል መጻሕፍት ባለመሸጣቸው መጻሕፍት ሻጮችም ተስፋ ቆርጠው ፌስቲቫሉን አቋርጠው ለመውጣት ተገደዋል፡፡
ከ5,000 ሰዎች በላይ የታደሙበት ፌስቲቫሉ፣ ብዙዎችን ያዝናና እንደነበር የምትገልጸው ወ/ሮ አንድነት፣ ለመጻሕፍት የሚሰጠው ትኩረት ግን የተሻለ እንዲሆን በማሳሰብ ነው፡፡ በተለይም የሕፃናት የንባብ ባህል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ትገልጻለች፡፡ ፌስቲቫሉን ቢያንስ በየሦስት ወሩ ለማካሄድ ማቀዳቸውን ታክላለች፡፡ ‹‹ኢትዮጲስን የሚወዷት ሕፃናት በርካታ ስለሆኑ ይህንን ተጠቅመን የንባብ ባህልን የማዳበር መልዕክታችንን ማስተላለፍ እንፈልጋለን፤›› ትላለች፡፡
ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው የሚታደሟቸው ንባብ ተኮር ፌስቲቫሎች መበራከት እንዳለባቸው ትገልጻለች፡፡ መሰል ዝግጅቶችን ስፖንሰር የሚያደርጉ ድርጅቶች አነስተኛ መሆናቸውን በመጥቀስ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ትናገራለች፡፡ ‹‹ኑ እናንብብ›› ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ውስጥ ጐተ ኢንስቲትዩት ይጠቀሳል፡፡