Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሕይወት የማዳን ሩጫ

ሕይወት የማዳን ሩጫ

ቀን:

ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ነበር የስምንት ዓመቱ ታዳጊ አልአዛር ደገፋ እንደተለመደው ከትምህርት ቤት ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ አመሻሽ ላይ ሽንቱ አልወጣ ብሎ ያስቸግረዋል፡፡ ሲሸናም ባልተለመደ መልኩም ሽንቱ ይደፈርሳል፡፡ እናቱ ወይዘሮ ማሜ ወልደፃዲቅ ትደናገጣለች፡፡ ትምህርት ቤት ውስጥ ሲጫወት ወድቆ ከሆነ ወይም ፊኛው አካባቢ ተመትቶ ከሆነ ጠየቀችው፡፡ ምንም እንዳልሆነ ገለፀላት፡፡ ባየችው ነገር ግራ ተጋብታ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ወሰደችው፡፡ የሕክምና ባለሙያዎቹ ‹‹የኩላሊት ሕክምና እየተከታተለ ያለው የት ነው?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡላት የበለጠ ተደናገረች፡፡ የኩላሊት ሕክምና ተደርጎለት እንደማያውቅም ገለፀችላቸው፡፡

ከባለሙያዎቹ የተሰጣት ምላሽ የልጇን ሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ መሆኑን እንድትረዳ አደረጋት፡፡ የአልአዛር ሁለቱም ኩላሊቶች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡ ለሕክምና 5,500,000 ብር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ሕክምናውን ባስቸኳይ ማግኘት አለበት፡፡

የአልአዛር አባት ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ እናቱ ኑሮን ለብቻዋ መግፋት ስላልቻለች ወንድሟ ቤት ተጠግተው ነው የሚኖሩት፡፡ ቡና እያፈላች በመሸጥ ራሷንና ልጇን የምታስተዳድረው ማሜ፣ ልጇን ለማሳከም አቅም የላትም፡፡ አልአዛር ትምህርቱን አቋርጦ ለጥቂት ጊዜ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተኝቶ ይታከም ነበር፡፡ አሁን በሽታው ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰበት ነው፡፡ ማሜ ሀኪሞች አልአዛር በአፋጣኝ ከተቻለ አሜሪካ ካልሆነም ህንድ አገር ሄዶ መታከም እንዳለበት እንደገለጹላት ትናገራለች፡፡

‹‹ዓይኔ እያየ ልጄ አይሞትም፤›› ብላ ልጇን ይዛ በየመንገዱ መለመን ጀምራ እንደነበር ትገልጻለች፡፡ ጉዳዩን የተገነዘቡ የአካባቢዋ ነዋሪዎች አብረዋት እስከመለመን እንደደረሱም ትናገራለች፡፡ ከዚህም ከዚያም ብላ ያጠራቀመችው ገንዘብ አሁንም ለሕክምና የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን አይችልም፡፡ የአልአዛር የጤና ሁኔታ ደግሞ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ማሜ ‹‹እኔ ዙሪያው ገደል ሆኖብኛል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ፤ ወላድ ይፍረደኝ፤›› ትላለች በሐዘኔታ ተሞልታ፡፡

የ38 ዓመቷ ትዕግስት ክፍሌ የሁለት ልጆች እናት ስትሆን፣ ለዓመታት በልብ ሕመም ስትሰቃይ ኖራለች፡፡ መጋቢት ላይ ሐኪሟ በሽታው እጅግ እንደተባባሰባት ነገራት፡፡ በአፋጣኝ ቀዶ ሕክምና ካላገኘች በሽታው ለሕይወቷ አስጊ እንደሆነና ለቀዶ ጥገናው 260,000 ብር እንደሚያስፈልጋትም ገልጾላታል፡፡ በሽታ ከሥራ ያገዳት ትዕግሥት ለሕክምና የተጠየቀችው ገንዘብ በባለቤቷ አነስተኛ ደመወዝ የሚሸፈን አይደለም፡፡ ሥጋቷን የሚጋሩት አባቷ አቶ ክፍሌ ገብረማርያም የልጃቸውን ሕይወት ለማትረፍ ያላንኳኩት በር እንደሌለ ይናገራሉ፡፡

አቶ ክፍሌ በ1983 ዓ.ም. ከጦር ሠራዊት በጡረታ ከተገለሉ በኋላ በግለሰብ ቤት በሾፌርነት ይሠራሉ፡፡ የሚኖሩት በቀበሌ ቤት ውስጥ ሲሆን፣ ደመወዛቸውና አነስተኛ የጡረታ ገንዘባቸው ለትዕግሥት ሕክምና በቂ አይደለም፡፡ ለዓመታት ስትታከም በየወሩ የምትወስደውን መድኃኒት ለመግዛት ያወጡት ወጪ ቀላል አልነበረም፡፡

አሁን የበሽታዋ ደረጃ ስለተባባሰ የምትወስደው መድኃኒት መጠን ጨምሯል፡፡ የሚወጣው ገንዘብም እንዲሁ፡፡ ያለችበት ሁኔታ የመላ ቤተሰቡን ልብ እንደሰበረ የሚናገሩት አባቷ፣ ከምንም በላይ ልጆቻቸው እናታቸውን የማጣት ነገር ዘወትር ሲያሳቅቃቸው ማየት እንደሚከብድ በመግለጽ ነው፡፡ ‹‹ለ27 ዓመታት በበረሃ ሆኜ ያሳደግኳትን ልጄን ለማዳን አቅሜ የፈቀደውን ሳደርግ ቆይቻለሁ፤ አሁን ከአቅሜ በላይ ስለሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰጥቼዋለሁ፤›› ይላሉ፡፡

ወይዘሮ ማሜና አቶ ክፍሌ የልጆቻቸውን ሕይወት ለማዳን በሚሯሯጡበት ወቅት ነበር ከተዋናይ ሰለሞን ቦጋለ ጋር የተገናኙት፡፡ አልአዛርና ትዕግሥት ሕክምና እንዲያገኙ ለማስቻል ጥቂት የሙያ አጋሮቹን አስተባብሮ ገንዘብ እያሰባሰበ ነው፡፡ ከአገር ውስጥና ከውጪ አገር በተለያየ መንገድ ዕርዳታ እያሰባሰበ ሲሆን፣ በቅርቡ አሜሪካ አገር የተካሄደው የገቢ ማሰባሰብያ የጃዝ ኮንሰርት ይጠቀሳል፡፡ ሰለሞን በአፋጣኝ ሕክምና እንዲያኙ በሚል መኪናውን ለጨረታ ማቅረቡንም አስታውቋል፡፡ ጨረታው በቅርቡ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚገኝበት ይጠበቃል፡፡

አቶ ክፍሌ ዕርዳታ ለመጠየቅ ቤቱ ድረስ መሄዳቸውን ይናገራል፡፡ ስለ አልአዛር የሰማው ከተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ ነው፡፡ ገንዘብ ለማሰባሰብ ከአልአዛር ጋር ፎቶግራፍ ተነስተው ፌስቡክ ላይ እንዲለጥፉ ጠይቆት ተገናኝተዋል፡፡ የሁለቱ ታማሚዎች ጉዳይ እንዳሳዘነው የሚናገረው ሰለሞን፣ ሕዝቡ ያለውን እንዲለግስ ለማነሳሳት በተለያየ መንገድ እየቀሰቀሰ ነው፡፡ ‹‹ያለኝ ትልቅ ነገር መኪናዬ ነውና ከሰው ሕይወት አይበልጥም ብዬ ለዚህ ጉዳይ አውየዋለሁ፤›› ይላል፡፡

ዕርዳታው በሁለት ሰዎች መቆም እንደሌለበት ያምናል፡፡ ሌሎች ሰዎችም የሚረዱበት ማዕከል የማቋቋም ዕቅድ እንዳለው ይናገራል፡፡ ሰው በመረባረቡ እየተሰበሰበ ያለው ገንዘብ ተስፋ ሰጪ መሆኑን በመግለጽ፣ በዚህ ሁኔታ ሌሎችንም ለመርዳት የሚቻልበት ማዕከል ካለ ለአሠራር እንደሚያመች ይናገራል፡፡

በቅርቡ እንደ ትዕግሥት ዓይነት ሕመም ላለባቸው ቀዶ ጥገና የሚያደርጉ ባለሙያዎች ከውጪ እንደሚመጡ ይናገራል፡፡ በወቅቱ ሕክምናውን እንደምታገኝም ተስፋ ያደርጋል፡፡ ‹‹አልአዛር አሁን የሚገኝበት ደረጃ የከፋ ነው፤ ሕይወቱን ለመታደግ የሁላችንም ትብብር ያሻዋል፤›› ይላል፡፡

መነሻውን ሁለቱን ታማሚዎች ቢያደርግም ዘለቄታ ያለው ዕርዳታ ለማድረግ በተለይ በቅርቡ ያሉ የሙያ አጋሮቹ እንዲተባበሩ ይጠይቃል፡፡ አሁን አብረውት እየሠሩ ካሉ አርቲስቶች መካከል ግሩም ኤርሚያስ፣ ሳምሶን ታደሰ (ቤቢ)፣ ሰውመሆን ይስማውና ሲሳይ በቀለ ይጠቀሳሉ፡፡

ሰለሞን ‹‹ከተባበርን ትንሿ ሹክሹክታ ትሰማለች፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አንድ ከሆንን ብዙ ነገር መሥራት ይቻላል፡፡ በየጓዳው ያሉ ወገኖቻችንን መርዳት አለብን፤›› በማለት ለሙያ አጋሮቹ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...