Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የ36 ዓመት ፎቶዎች

ትኩስ ፅሁፎች

እነዚህ ፎቶዎች ከ36 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ አብዮት 4ኛ ዓመት መስከረም 2 ቀን 1971 ዓ.ም. ሲከበር የተነሡ ናቸው፡፡  አንሺውም ሽመልስ ደስታ ነው፡፡ በበዓሉ በክብር እንግድነት የተገኙት የኩባ ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ሩዝ ነበሩ፡፡ የአዲስ አበባና ያካባቢው ኅብረተሰብ ከ12 ሰዓት ዠምሮ ‹‹አብዮት አደባባይ›› የተገኘ ሲሆን በዕለቱ ንጋት ላይ አዲስ አበባ ይገባሉ የተባሉትን ፊደል ካስትሮን፣ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበር ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ለመቀበል ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ቢጠብቁ ቢጠብቁ በተባለው ሰዓት ባለመድረሳቸው ወደ አብዮት አደባባይ በመመለስ በዓሉን ማክበር ጀምረው ነበር፡፡ ገድለ አብዮቱንም አስመልክቶ ዲስኩራቸውን እያሰሙ ሳለ አንዱ አጋፋሪያቸው በጆሮዋቸው ፊደል ካስትሮን የያዘው ጢያራ አዲስ አበባ መድረሱን ሹክ ሲላቸው ንግግራቸውን አቋርጠው በመሔድ ይዘዋቸው ወደ አብዮት አደባባይ መመለሳቸው ይታወሳል፡፡ በቀይ ክፍት ማርቼዲስ ላይ ሁለቱ መሪዎች ባንድነት ከአደባባዩ ሲደርሱ ‹‹ቪቫ መንግሥቱ ቪቫ ካስትሮ›› እያለ ታዳሚው መቀበሉም አይዘነጋም፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ካሉት (መጀመርያ የመጡት መጋቢት 5 ቀን 1969 ዓ.ም. ነበር) ፊደል ካስትሮና መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር ተያይዞ የሚነገሩ ቀልዶችም አልጠፉም፡፡ ከፎክሎር ጋር አያይዘን ‹‹መንግሥቱሎር››፣ ‹‹ካስትሮሎር›› ብለንም ልናጠና እንችላለን፡፡ እስቲ ስለሁለቱ መሪዎች ከተባሉት ወይም ከተቀለዱት የሰማን፣ ያነበብን እስቲ እናሰማ፣ እናስነብብ፤ ላሁን ሁለቱን ልበል፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ቦሌ ሔደው ካስትሮን ሲቀበሉ እንዲህ አጋጠማቸው አሉ፡፡ ካስትሮ ከአውሮፕላን ወርደው ለሊቀመንበር መንግሥቱ ሰላምታ ሲያቀርቡ ‹‹ፊደል ካስትሮ ሩዝ እባላለሁ›› ሲሏቸው፣ እሳቸውም ባጸፋው ‹‹መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ኑግ›› እባላለሁ አሉ፡፡ ሌላው ወግ፣ ለ4ኛው አብዮት በዓል ሕዝቡ በነቂስ አብዮት አደባባይ እንዲወጣና ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮንም እንዲቀበል በአዲስ አበባ አንዱ ቀበሌ፣ መስከረም 1 ቀን 1971 ዓ.ም. ምሽት ላይ፣ በባትሪ በሚሠራ ማይክራፎን አንዱ ለፋፊ እንዲህ አለ፡፡ ‹‹የቀበሌያችን ነዋሪዎች የኩባው ‹ፊየል ታስሮ› ነገ አዲስ አበባ ይገባልና ከንጋቱ 12 ሰዓት ሰልፍ እንድትወጡ በጥብቅ እናስታውቃለን፡፡›› (ሔኖክ መደብር)

**************

ዝና ገናናነት

ከጆን ኪትስ 1795-1821/ስድ ትርጉም በከበደ ዳግማዊ

ዝና ገናናነት፤ እንደ ሰድ ኮረዳ፤ ትሽኮረመማለች፤ ዞር በሉ እያለች

እንደማንም ባርያ ለሚንበረከኩት ለሚሰግዱላት፤

ግን ላንድ ቀልበቢስ ወጣት እጇን ትሰጣለች፤

ረጋ ላለ ልብ ግን ደጅ ታስጠናለች፡፡

ጂፕሲ ነች አልኳችሁ፤ ሰው የማታናግር፣

አለሷ ለመኖር ካልተማሩ በቀር፣

ነጃሳ ከሃዲ፤ ምሥጢር በጆሮዋ ሹክ ያላሉባት፣

ያች ጉደኛ ጂፕሲ ኒሉስ የደቀላት፤

ይች የቀናተኛው የጶጢፋር አማች፤

እላንት አባቅኔዎች የፍቅር በሽተኞች!

ካላት አጸፌታ ንቀቷን በንቀት፣

እናንተም አርቲስቶች ፍቅር ያጠቃችሁ!

መቼም አትረቡም ወፈፌዎች ናችሁ!

ሰገዱላት በደምብ ተሰናበቷት፤

ያኔ፤ ከፈለገች፤ ትከተልሃለች እንዲያ ካሰኛት፡፡

******************

የጶጢፋር ሚስት ማለት ዮሴፍን ለማሳሳት ሞክራ ሳይሆንላት ሲቀር የከሰሰችውና ያሳሰረችው ሴትዮ ናት፡፡ ኒሉስ የተባለው ከንኡሰን የግሪኮች አማልክት አንዱ ሲሆን፣ የናይል አምላክ ይሉታል፡፡ ኒሉስ የኦሺያኑስና የቴቲስ የተባሉት አማልክት ልጅ ነው ይላሉ፡፡ ጂፕሲ የሚለው ስም ከኢጅብት የመነጨ ጎሳዎች ከማለት ጋር ቢመሳሰልም፤ በመሠረቱ ጂፖሲ የፈለሱት ከህንድ ነው፡፡ የጥንቆላ ተግባር ግብፅ ውስጥ ከጥንቱም የደረጀ ስለነበር፤ ጂፕሲ ዛሬም ቢሆን መጠንቆል እናውቃለን እያሉ በርካታ የዋሆችን ያስተናግዳሉ፡፡ ታሪካዊ ሃቁ ግን የሚጠቁመው የመነጩት ከህንድ ቢሆንም በይመስላል ብቻ ኤሮፓውያን ጂፕሲ በሚል መጠርያ ይሰይሟቸዋል፡፡

********************

‹‹ምስኪን ብችል ይህቺን ጨረቃ እመርቅልህ ነበር››

አንድ የዜን መምህር ከተራራ ሥር በሚገኝ ትንሽ ቤታቸው ውስጥ ለረዥም ዓመታት እጅግ በጣም ቀላል የሆነ ሕይወት በመምራት ይኖሩ ነበር፡፡
አንድ ምሽት ከቤታቸው ርቀው እግራቸውን እያፍታቱ ሳለ ሌባ እቤታቸው ገብቶ መበርበር ይጀምራል፡፡ ይሁንና በቤት ውስጥ አንዳች የሚሰረቅ ጠቃሚ ነገር ሳያገኝ ሲንጎዳጎድ ቆይቶ ባዶ እጁን ሊወጣ ወደበሩ ሲያመራ መምህሩ ተመልሰው ከቤት ይደርሳሉ፡፡

የዜኑ መምህር ሌባውን ከቤታቸው ሲወጣ ሲመለከቱ

ወዳጄ ሆይ ልትጎበኝ ከሩቅ ስፍራ እዚህ ድርስ ተጉዘህ መጥተህማ ባዶ እጅህን አትመለስም በማለት የለበሱትን ልብስ አውልቀው ከእጁ ላይ ያስቀምጡታል
በዚህ ጊዜ ሌባው ሀፍረትም ንዴትም እየተሰማው የዜኑ ልብስ ይዞ መሮጥ ይጀምራል፡፡

የዜኑ መምህር ሌባውን ተከትለው በመውጣት ከደጃፍ ተቀመጡና ዓይናቸውን ወደ ምሽት ጨረቃ በመላክ ‹‹ምስኪን ብችል ይህቺን ጨረቃ እመርቅልህ ነበር›› አሉ፡፡

ዜኖች ሲናገሩ በእጁ ባለው ነገር እንደማይደሰት ሰው አሳዛኝ ፍጡር የለም ይላሉ
ዛሬ ፋጣሪ የሰጠህ ማንኛውን ነገር ለሕይወትህ በቂ መሆኑን አምነህ ተቀበል ስግብግብነት ስስት እንዲሁም ምሬት ምንጫቸው በሕይወት ውስጥ በያዝነው ነገር አለመርካት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

የዜኑ መምህር ሮሽ ሌባውን የእሱ ንብረት ያልሆነውን በመስረቅ ሊፈጽመው ከነበረው ኃጢያት የዜኑ መምህር በመስጠት አዳኑት ሌባውም ባለመስረቁ ዜኑም ያላቸውን በማካፋል ሁለቱም በእኩል ደረጃ መልካም ሆኑ።

– ምንጭ ዜን ቡድሂዝም !! ከእንደ ወረደ ገጽ የተገኘ

*********

አለንጋና ምስር

…አንድ ቀን ማታ የቴሌቪዥን ኳስ ጨዋታ ካየሁ በኋላ የቤት ሥራዬን ለመሥራት መኝታ ቤት ስገባ ኢሌኒን ለማነጋገር ቁርጥ ሀሳብ አደረግሁ (እንደ ትልቅ ዓላማ)፡፡ ይሔ ሀሳብ በየት ቀዳዳ ጭንቅላቴ ውስጥ ገብቶ እንደሰፈረ ትዝ አይለኝም፡፡ አንዲት ሴት ላይ ተደብቆ በማፍጠጥ ምንም ሊገኝ እንደማይችል ስለተረዳሁ ይሆናል፡፡ የማቸስተር ዩናይትድ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ከመከላከል ይልቅ በማጥቃት ማሸነፋቸው ትምህርት ሰጥቶኝም ይሆናል፡፡ እሷን ከማዋራቴ በፊት ግን አንዳንድ ነገሮች መለማመድ ነበረብኝ፡፡ እንዴት እንደምናገር፣ ምን እንደምናገር፣ የት ቦታ እንደማናግራት…… እነዚህን ሁሉ መለማመድ ነበረብኝ፡፡ በተለይ ቄንጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ሺሕ ልብስ ለዋውጬ አላየችኝም፡፡ ፋሽን ቀያይሬ አላየችኝም፡፡ ስህተቴ በአፍ አለመቅረቤ ይሆናል፡፡ በአፍ፡፡ የሚያጥረኝ እሱ ነው፡፡ አፍ፡፡

ልምምዴ ግን የማልፈራቸው ሴቶች ላይ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ በመንገድ ሳልፍ ታክሲና አውቶብስ የሚጠብቁ ልጃገረዶች ላይ፡፡ ካፍቴሪያ ገብቼ ጁስ ስጠጣ ተያይዘው የሚገቡ ልጃገረዶች ካሉ እነሱን በመጥቀስ የሚያወርዱትን የስድብ ሆነ የትችት ናዳ መቀበል፡፡ ወይ በመልሱ ቁና ሙሉ ጥቅሻ፣ ጣሳ ሙሉ መሽኮርመም መቀበል፡፡ ከእነዚህም ትንንሽ ልምዶች ለኢሌኒ የሚሆነኝን ማቀነባበር፡፡

ታዲያ ቤቴ ውዬ ሳጠና፣ ሳነብ፣ ልብስ ሳጥብ ሬዲዮ ስሰማ የምውለው ሰው ከሰኞ እስከ ዓርብ ሲመሽ ወይም ቅዳሜና እሑድ ቀን ከተማ ውስጥ መዋል ጀመርኩ፡፡ ሲኒማ ኢትዮጵያ ሲኒማ ዓድዋ ሲኒማ አምፒር ቤቶቼ ሆኑ፡፡ አብሬ የምውላቸው ልጆች ፈጣን፣ ፒያሳንና አራት ኪሎን ያቃጠሉ ሆኑ፡፡

ሺሕ ሴቶች ጠቀስኩ፡፡ 250ዎቹ ዘጉኝ፡፡ 250ዎቹ ተሽኮረመሙ፡፡ 250ዎቹ መልሰው ጠቀሱኝ፡፡ 250ዎቹ ሰላም ይሉኝ ጀመር፡፡

ሰላምታ ከሚሰጡኝ ሁለት መቶ ሃምሳዎቹ መቶው ከአራዳ ልጆ ጋር በመዋሌ፣ መቶው መልኬ ደስ ስላላቸው፣ የቀሩት ደግሞ ደጋግመው ስላዩኝ ነው፡፡

መልኬ ደስ ካላቸው መቶዎቹ ሃምሳው አብረውኝ መሆን ሲፈልጉ ሃምሳው አድንቀውኝ ያለፉ ናቸው፡፡

አብረውኝ ከሚሆኑ ሃምሳዎቹ ሃያ አምስቱ እየተጫወቱ ሊያዩኝ የሚፈልጉ ሲሆኑ የቀሩት ልባቸው የከጀለ ናቸው፡፡

ከቀሩት ሃያ አምስቱ 12 ተኩሉን ስስማቸው 12ቱን ስተኛቸው የቀረችዋ ግማሽ ሴት ግን ጀርባዬ ላይ እንደ ቡግር ተተክላ ፊቴ ላይ እንደ ፂም በቅላ ሚስቴ ሆነች…… ስድስት ዓመት ሳትለየኝ፡፡

ከመሐል ኢሌንን ባልረሳትም ጠፋች፡፡

አለንጋና ምስር

 

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች