ብሩንዲያውያን ፕሬዚዳንታንዊ ምርጫቸውን ትናንት ሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ያካሄዱት በተኩስና በፍንዳታ ታጅበው ነበር፡፡ አገሪቱን እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩት ፒዬሪ ንኩሪንዚዛ፣ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት የፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸውን ጨርሰዋል፡፡ ዳግም መወዳደር አይችሉም ተብሎ ካለፈው ሚያዝያ ጀምሮ በአገሪቱ ተቃውሞ የተቀሰቀሰባቸው ቢሆንም ፕሬዚዳንቱ ለሦስተኛ ጊዜ ከመወዳደር አልተቆጠቡም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ‹‹እ.ኤ.አ. በ2005 ለፕሬዚዳንትነት የተመረጥኩት በአገሪቱ ፓርላማ ነው፡፡ ሕዝቡ በምርጫ የሾመኝ በ2010 ነው፡፡ ስለሆነም ከ2010 ጀምሮ ለሁለት ጊዜ የመወዳደርና የመመረጥ መብት ሕገ መንግሥቱ ሰጥቶኛል፤›› የሚለው ነው፡፡ የፕሬዚዳንቱን መከራከሪያ የአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ቢቀበለውም ከሕዝቡ ተቃውሞ ከገጠማቸው ሰንብተዋል፡፡ የእሳቸው በምርጫ መወዳደርም ምርጫውን በውጥረት እንዲሞላ፣ የተኩስ ልውውጥና ፍንዳታ እንዲኖርና ዜጎችም እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡
በአገሪቱ ሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ምርጫው ከመጀመሩ አስቀድሞ በዋና ከተማዋ ቡጁምቡራ በነበረው የተኩስ ልውውጥ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል፡፡ መንግሥት በአገሪቱ ለተከሰተው አለመረጋጋት ተቃዋሚዎችን ሲወነጅል፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ሕገ መንግሥቱ ከሰጣቸው የጊዜ ገደብ በላይ በመወዳደራቸው ችግሩ ተከስቷል ብለዋል፡፡ ቢቢሲ የፕሬዚዳንቱን ጽሕፈት ቤት ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ምርጫን አስመልክቶ በብሩንዲ የተከሰተው አለመረጋጋት ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የፕሬዚዳንቱ ዋና የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ዊሊ ኒያማቲው፣ ‹‹ሰዎች ምርጫውን የሚያሸብሩት መራጮችን ለማወክ ነው፡፡ መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዲሄዱ አይፈልጉም፤›› ብለዋል፡፡
በብሩንዲ ምርጫን አስመልክቶ ውጥረት ቢፈጠርም፣ ተቃዋሚዎች የፕሬዚዳንቱ መወዳደር አግባብ አይደለም ቢሉም፣ ፕሬዚዳንቱን የሚተካ ብቁ ተቀናቃኝ እንደሌለ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ‹‹ሰባቱ የፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎች ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ የሚያሳድሩ አይደሉም፤›› ሲልም አትቷል፡፡ ብዙዎቹ ፓርቲዎችም ራሳቸውን ከምርጫ አግልለዋል፡፡
የፕሬዚዳንት ንኩሪንዚዛ ዋና ተቀናቃኝ አጋቶን ራዋሳ ፓርቲያቸው ኤፍኤንኤል (ፎርስስ ፓር ላ ሊብሬሽን ናሽናሌ) በመንግሥት ዕውቅና ሲያጣ፣ በግል ለመወዳደር ተመዝግበዋል፡፡ ሆኖም ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት፣ ስማቸው በምርጫ ወረቀቱ ላይ ቢኖርም በምርጫው ሒደት እንደማይሳተፉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፕሬዚዳንት ንኩሪንዚዛ በምርጫው እንዲያሸንፉና የተከፋፈለ ሕዝብ እንዲመሩም ዕድል ይፈጥራል፡፡
‹‹መንግሥት ራሱን አግልሏል፡፡ ምርጫውም ለይስሙላ ነው›› የሚሉት ደግሞ ሊዮንስ እንጊንደኩማና የተባሉት ሌላው የፕሬዚዳንቱ ተቀናቃኝ ናቸው፡፡ ‹‹መንግሥት ኃላፊነቱን ዘንግቷል፡፡ አገሪቱ ከማቆልቆል ወደባሰ አዘቅት እንዳትገባ ከማድረግ ይልቅ ሥራውን ረስቷል፤›› ሲሉም ጂን ሚናኒ የተባሉ ሌላ ተቃዋሚ የአገሪቱን መንግሥት ኮንነዋል፡፡
ለፕሬዚዳንቱ ቅርብ የሆኑ ባለሥልጣናት ግን ከተቃዋሚ የተለየ ምልከታ አላቸው፡፡ የ51 ዓመቱ የቀድሞ ሽምቅ ተዋጊና መምህር፣ የአሁኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ንኩሪንዚዛ፣ ‹‹የሕዝቡ መሪ፣ አገሪቷ ከነበረችበት ለአሥር ዓመታት የዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ አገሪቱን መልሶ የገነባ፣ አገር ለማስተዳደር የወሰነ ሰው ነው፤›› ብለዋል፡፡
አገሪቷ ከቤልጂየም ነፃ ከወጣች እ.ኤ.አ. ከ1962 ጀምሮ በየጊዜው የሚጋጩት አገሪቷ ካላት 10.5 ሚሊዮን ሕዝብ 85 በመቶውን የሚይዙት ሁቱ እንዲሁም ቀሪዎቹ የቱትሲ ጎሳ አባላት፣ ምርጫውን ተከትሎ ዳግም ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳይገቡ ተሰግቷል፡፡ የሁቱ ጎሳ ተወላጅ የሆኑት ፕሬዚዳንት ንኩሪንዚዛ፣ በቱትሲ የበላይነት የነበረውን የጦር ኃይል ለመዋጋት የሁቱ ነፃ አውጪ ቡድንን በመቀላቀልና በኋላም ከወቅቱ መንግሥት ጋር በመደራደርና ወደ ሰላም ስምምነት በመምጣት እ.ኤ.አ. በ2005 ነበረ በፓርላማው ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የተመረጡት፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. በ2015 ግንቦት ላይ የእሳቸውን ለሦስተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት እወዳደራለሁ ማለት ተከትሎ መፈንቅለ መንግሥትም ተሞክሮባቸዋል፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱ በመክሸፉ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሽምቅ ውጊያ ተጀምሯል፡፡
ከአሥር ዓመታት ለበለጠ ጊዜ በእርስ በርስ ጦርነት የከረመችው ብሩንዲ፣ እ.ኤ.አ. በ2005 ከሁቱ ነፃ አውጪ ቡድን ወገን የሆኑትን ፕሬዚዳንት በመምረጥ አገሪቷን ወደ ሰላም ጎዳና ማምጣት ተችሎ ነበር፡፡ ሆኖም የሰላም ጎዳናው በአሥር ዓመቱ ዳግም ፈተና ተጋርጦበታል፡፡ በዚህ ፈተና ውስጥ ሆነው 3.8 ሚሊዮን ብሩንዲያውያን ፕሬዚዳንት ለመመምረጥ የተመዘገቡ ሲሆን፣ ምርጫው ግን ሰላማዊ አልነበረም፡፡ በኅብረቱ አባል አገሮች ጉዳይ የሚመለከተው የአፍሪካ ኅብረትም፣ ወደ አገሪቱ የምርጫ ታዛቢዎችን አላከም፡፡ ይኼም ኅብረቱ ለአባል አገሩ የምርጫ ታዛቢ ያላከበት የመጀመርያው ጊዜ ተብሏል፡፡
የፕሬዚዳንቱን መወዳደር ዜና ተከትሎ በአገሪቱ በተቀሰቀሰ ግጭት ከ70 በላይ ዜጎች ተገድለዋል፡፡ ቀውሱ የባህር በር በሌላት ብሩንዲ ብቻ አያበቃም፣ ይስፋፋል የሚል ሥጋትም አለ፡፡ በብሩንዲና በአካባቢው ባሉት ጎረቤት አገሮች ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳና በተለይ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የውስጥ ግጭት በተነሳ ቁጥር ወደ ጎረቤት አገሮች መዛመቱም የተለመደ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ሁቱና ቱትሲ በጎረቤታሞቹ አገሮች ተበትነው መኖር ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡
በብሩንዲ ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ ተነፃፃሪ ሰላም ሰፍኖ ነበር፡፡ የማኅበረሰብ ደኅንነት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና የተቃዋሚ ሚዲያ ተጠብቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬ ግን ይህ ሥጋት ውስጥ ይገኛል፡፡ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረትም በአገሪቱ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ለአገሪቱ ይሰጡ ከነበረው ዕርዳታ የተወሰነውን አጥፈዋል፡፡ ለምርጫው ማካሄጃም ድጋፍ አላደረጉም፡፡
ብሩንዲያውያን አገሪቱ ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ሰላሟ ቢናወጥም፣ ምርጫውን በተኩስና በፍንዳታ ታጅበው አካሂደዋል፡፡ ይህ ምርጫ በብሩንዲ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የእርስ በርስ ጦርነት ይዞ ሊመጣ ይችላል የሚል ሥጋትም ተከስቷል፡፡ በብሩንዲ ምርጫ ሳቢያ እ.ኤ.አ. ከ1993 እስከ 2005 ድረስ የዘለቀው የእርስ በርስ ግጭት ዳግም ያገረሽ ይሆን?
ፕሬዚዳንት ንኩሪንዚዛ ካሸነፉ በአገሪቱ የእርስ በርስ ግጭት ዳግም ሊያገረሽ ይችላል የሚያስብሉ የተለያዩ ምክንያቶች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ በተለይ ከሦስት ወራት በፊት በአገሪቱ ተሞክሮ የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት፣ እንዲሁም የመፈንቅለ መንግሥቱ ሞካሪዎች ማምለጥ በአገሪቱ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ይሆናል፡፡ የተጀመሩ ግጭቶችም ይቀጥላሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን እስኪወርዱ ድረስም መፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎቹ ተኝተው አያድሩም፡፡
በአገሪቱ እ.ኤ.አ. በ1993 የእርስ በርስ ጦርነት ለመነሳቱ ዋናው ምክንያትም በወቅቱ ተደርጎ የነበረ ምርጫ ነው፡፡ ጦርነቱም በጎሳ የተከፈለ ነበር፡፡ አብላጫውን የአገሪቱን ዜጎች ቁጥር የሚይዙት የሁቱ አማፂያን አገሪቱን ሲመሩ ከነበሩትና አብዛኛውን የፖለቲካ መንበር ከተቆጠሩት ቱትሲዎች ጋር ነበር ለ13 ዓመታት ያህል የተዋጉት፡፡ ረዥም ዓመታት ከወሰደ ድርድር በኋላ በቁጥራቸው አነስተኛ ሆነው ሥልጣኑን ከተቆጣሩት ቱትሲዎች ጋር ስምምነት በመደረሱ፣ ሁቱዎች ሥልጣን እንዲጋሩ ተደርጓል፡፡ አገሪቱም ተነፃፃሪ ሰላም አግኝታ ከርማለች፡፡ ይህ ግን የሚዘልቅ አልሆነም፡፡ የፕሬዚዳንቱን በሥልጣን መቆየት የተቃወሙት የሁለቱም ጎሳ አባላት ቢሆኑም፣ የአገሪቱ ሚዲያዎች ግን የጥላቻ ንግግሮችን እያስተላለፉ ነው፡፡ ሕዝቡን አንድ የሚያደርግ ሳይሆን ለእልቂት የሚዳርግ ዘገባ እያተቱ ነው፡፡ ግጭቱንም የጎሳ አድርገውታል፡፡
ይህ በቀጣናው ምን ያስከትላል? ቀጣናው እ.ኤ.አ. ከ1998 ጀምሮ ከፍተኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል በማስተናገድ ይታወቃል፡፡ ሰላም አስከባሪ ኃይሉ ከ1998 ጀምሮ የእርስ በርስ ጦርነት ባሸማቀቃት ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የሰፈረ ቢሆንም፣ የቀጣናውን ችግር መፍታት አልቻለም፡፡ በቀጣናው ያሉ አገሮችም የችግሩ አመንጪ፣ ለመፍትሔም እንቅፋት ናቸው፡፡ አንዱ አገር የሌላውን አገር አማፂ በማስታጠቅ የቀጣናውን ሰላም አደፍርሰዋል፡፡ አንድ አማፂ ከመንግሥት ጋር ለመስማማት ሲወስን በሌላ በኩል ጠብ ይጫራል፡፡ ለዚህ ሁሉ መንስዔዎቹ በየአገሩ ያሉት መንግሥታት ናቸው፡፡ እርስ በርሳቸው አይተማመኑም፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እርስ በርሳቸው ሲወነጃጀሉ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡
የብሩንዲ መበጣበጥ ማለት ለጎረቤት አገሮች ሁሉ ሥጋት ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለውም 144,000 የብሩንዲ ዜጎች ወደ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ተሰደዋል፡፡ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በብሩንዲ ተቃዋሚዎችንና መንግሥትን ለማደራደር እየጣሩ ቢሆንም፣ ከጫፍ አልደረሱም፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1986 ጀምሮ ሥልጣን ላይ የሚገኙት ሙሴቪኒ፣ በአገራቸው ሕገ መንግሥት የተቀመጠውን የፕሬዚዳንት የሥልጣን ዘመን ከሰረዙ በኋላ፣ በብሩንዲያውያንም ዘንድ ተቀባይነት አጥተዋል፡፡ የድርድሩ ስኬታማነት ላይ ደግሞ የአሁኑ ምርጫም ጥላውን አጥልቷል፡፡ ይህ ምርጫ ከብሩንዲም አልፎ የጎረቤት አገሮችን ሰላም ያናጋል እየተባለም ነው፡፡ ብሩንዲ ሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ያካሄደችው ምርጫ እ.ኤ.አ. የ1993ቱ ታሪክ እንዲደገም ምክንያት ይሆን ይሆን? ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡