Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየጡረታ ማሻሻያ አዋጆች አፀዳደቅ ከተለመዱ አሠራሮች የወጣ አይደለም

የጡረታ ማሻሻያ አዋጆች አፀዳደቅ ከተለመዱ አሠራሮች የወጣ አይደለም

ቀን:

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት

የመንግሥትና የግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ አዋጆች መሻሻያ ቀርቦባቸው ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ምክር ቤቱ ባደረገው አንደኛ ልዩ ስብሰባ ማሻሻያዎቹ ፀድቀዋል፡፡ ይህን ሁኔታ በማመልከት ሪፖርተር ጋዜጣ በቅፅ 20፣ ቁጥር 1558 የረቡዕ ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕትሙ፣ ‹‹በሁለቱ የጡረታ አዋጆች ላይ የተካተተው ማሻሻያ ከፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ጋር ይጋጫል የሚል ክርክር አስነሳ›› የሚል ዜና በፊት ገጹ ይዞ ወጥቷል፡፡ ይህ ዜናው ሁለት ስህተቶችን ይዟል፡፡

አንደኛው ስህተት አልቆ የደቀቀ ጉዳይን እንዳልተቋጨ አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡ በሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር፣ ፕሮቪደንት ፈንድን የሚመለከቱ ማሻሻያዎች መቅረታቸውን አረጋግጠውና ባለድርሻ አካላትም በመንግሥት በኩል የተወሰደውን ዕርምጃ አመስግነው ከተለያዩ በኋላ፣ ጋዜጣው ምክር ቤቱ ፕሮቪደንት ፈንድን የመረጡ ሠራተኞችን ጥያቄ ‹‹ሳይቀበለው ቀርቷል›› በማለት ዳግም ሠራተኞች ወደ ሥጋት እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ይህም ብዙ ሰዎች ወደ ምክር ቤቱ በርካታ የስልክ ጥሪዎችን እንዲያደርጉ አስገድዶ ነበር፡፡ ሆኖም ጋዜጣው የሠራውን ስህተት አውቆ በራሱ ድረ ገጽ ይቅርታ በመጠየቅ የእርምት ዕርምጃ መውሰዱ ተገቢ ነው፡፡ በድረ ገጹ የተለቀቀው መረጃ በጋዜጣውም ሊደገም ይገባል፡፡ የእሑዱ ዕትም ምሥጋናና ዜና እንደ እርማት ማካካሻ ሊወሰድ አይገባም፡፡

ሁለተኛው ስህተት የክርክሩ አካል የነበሩ የምክር ቤቱ አባላት በመግባባት የቋጩትን ጉዳይ በሕግ ባለሙያዎች አስተያየት ሽፋን አዋጆቹ ለፕሬዚዳንት በሕገ መንግሥት የተሰጠውን ሥልጣን እንደሚቃረኑ አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረትም በዚህ ነጥብ ላይ ይሆናል፡፡

በምክር ቤቱ አወጣጥ ሒደት ውስጥ አንዱ በምክር ቤቱ የፀደቁ አዋጆች በፕሬዚዳንቱ እየተፈረሙ በነጋሪት ጋዜጣ እየታተሙ መውጣታቸው ነው፡፡ ይህም በሕጎች ለሚጠቀሙ ወገኖች እንደ ማስረጃ ሆኖ ያገለግላቸዋል፡፡ ይህ አንዱ የሕግ አወጣጥ ሒደት ነው፡፡ የአሁኑ አዋጆችም አካሄድም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

የማሻሻዎቹ አንቀጽ 3 በምክር ቤቱ እንደገና ሲሻሻሉ የአዋጆቹ የተፈጻሚነት ጊዜ ላይ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ስለረቂቁ አዋጆቹ የተፈጻሚነት ጊዜ ቀድሞ ሲደነገግ አዋጆቹ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምረው የፀኑ እንዲሆኑ ነው፡፡ የምክር ቤቱ ማሻሻያ ደግሞ አዋጆቹ የሚፀኑበትን ቀን ወደ ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ያመጣል፡፡ ስለዚህ ፕሬዚዳንቱ ሳይፈርሙና ፈርመውም በነጋሪት ጋዜጣ ሳይታተሙ አስቀድሞ የመፅናት ቀናቸውን መወሰን ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ ሥራ ነው በሚል፣ የሕግ ባለሙያዎች አስተያየት እንደሰጡ ነው ጋዜጣው የዘገበው፡፡

ዋናው መታየት ያለበት ጉዳይ ምክር ቤቱ የአዋጆቹን የተፈጻሚነት ጊዜ ወደ ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲያመጣ የፕሬዚዳንቱን በአዋጆቹ ላይ የመፈረም ሥልጣንን ያስቀራል ወይ የሚለው ጥያቄ መሆን ይገባል፡፡ ውሳኔው የፕሬዚዳንቱን የመፈረም ሥልጣን ፈጽሞ አያስቀርም፡፡

የፕሬዚዳንቱ ፊርማና የነጋሪት ጋዜጣ ኅትመት ከምክር ቤቱ ውሳኔ ጋር አብረው የሚሄዱ እንጂ፣ የምክር ቤቱን ውሳኔ የሚገድቡ አይደሉም፡፡ በፕሬዚዳንቱ የተፈረመውና በነጋሪት ጋዜጣ የወጣው አዋጅ ወደ አፈጻጸም ሲሻገር ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ይሆናል፡፡ አዋጁ የሚፀናበት ቀን የሕጉ አካል ስለሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 1 ሥር ያርፋል፡፡ ፊርማውና ኅትመቱ ምክር ቤቱ ሕግ ስለማውጣቱ ማስረጃ ይሆንለታል፡፡ ኤጀንሲው ውሳኔውን መተግበር የሚጀምረው አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በእጁ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ይህም የፕሬዚዳንቱን የመፈረም ሥልጣን ያከበረና በነጋሪት ጋዜጣ አዋጆች ታትመው መውጣት እንደሚገባቸው የተቀመጡ አሠራሮችን የሚያከብር አካሄድ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ኤጀንሲው ማስረጃውን በመያዝ ወደ ሥራው ይገባል፡፡

ጥያቄ ሊነሳ ከሆነ ኤጀንሲው አዋጁን መተግበር የጀመረው የፀደቀው አዋጅ ፕሬዚዳንቱ በሕገ መነግሥቱ በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሳይፈርሙና በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ሳይወጣ ቢሆን ኖሮ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ባለመደረጉ ከፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ጋር የሚጋጭ ነገር የለም፡፡

ምክር ቤቱ የሚያፀድቃቸው አዋጆች የተፈጻሚነት ጊዜ በምክር ቤቱ ፍላጎት ይወሰናል፡፡ አንዱን ሕግ ወደኋላ ሄዶ እንዲሠራ ሊወስን ይችላል፡፡ አንዱን ደግሞ ስብሰባ ከተቀመጠበትና ከወሰነበት ቀን ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል ሊወስን ይችላል፡፡ ሌላውን ደግሞ ከዓመትና ከዚያ በኋላ ተፈጻሚ እንዲሆንም ሊወስን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የሚገደበው በሕገ መንግሥቱና በሕግ መርሆዎች ክልከላ ካለ ብቻ ነው፡፡ የተነሳው ጉዳይ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደማይቃረን ታይቷል፡፡ ከሕግ መርሆዎች አንፃር የወንጀል ሕግ ብቻ ነው ወደኋላ ሄዶ የማይሠራው፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕግ ግን ጉዳዩ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወደኋላ ሄዶ እንዲሠራ ማድረግም ይቻላል፡፡ የጡረታ መዋጮ በሚያዘገዩ የግል ድርጅቶች ላይ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ቢተላለፍ ከሕግ መርሆ አኳያ ምክር ቤቱ የተላለፈው ነገር የለም፡፡ የምክር ቤቱ ያለፉ ልምዶችም ይህን ያሳያሉ፡፡

ከዚህ በፊት ከንግድ ባንክ ብድር የወሰዱ ሰዎች የብድር መመለሻ ጊዜው በይርጋ መታገዱን በማመልከት ከብድር መመለስ ነፃ የሆኑበትን የፍርድ ቤት ውሳኔ የሚያስቀር አዋጅ ምክር ቤቱ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ ይህ አዋጅ አሥርና ከዚያ በላይ ዓመታት ወደኋላ ሄዶ እንዲሠራ ነው ምክር ቤቱ የወሰነው፡፡ ታዲያ ይህ አዋጅ ለምን ከፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ጋር ሳይጋጭ ቀረ?

ምክር ቤቱ አሁንም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ውሳኔ ከሚያስተላልፍበት ቀን ጀምሮ ሕጉ እንዲፀና አድርጎ ማወጅ ይችላል፡፡ ይህም በፕሬዚዳንቱ ተፈርሞ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ የሚወጣ ይሆናል፡፡ ወደ ሥራ ለመግባት የቀረቡ የብድር ስምምነቶች በዚህ መልክ በምክር ቤቱ ሲፀድቁ ታይተዋል፡፡

ከእነዚህ ሌላ ከዓመታት በኋላ ተፈጻሚነታቸው እንዲጀምር የሚታወጁ አዋጆችም አሉ፡፡ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነትና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጆችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የዝግጅት ጊዜ ስለሚጠይቅ በነጋሪት ጋዜጣ ስለወጡ ብቻ ሕዝቡ ወዲያውኑ ብሔራዊ መታወቂያ እያገኘ አይደለም፡፡ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባም በአስገዳጅነት እየተካሄደ አይደለም፡፡ የመረጃ ነፃነት አዋጁም ወደ ሥራ የገባው በመጀመሪያው አዋጅ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ አልቆ በምክር ቤቱ ውሳኔ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ እየተመደበለት ወደ ትግበራ ሊገባ ችሏል፡፡ አሁን ምን ልዩ ነገር ተፈጥሮ ነው ሪፖርተር የምክር ቤቱ ውሳኔ ከፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ጋር እንደተጋጩ አድርጎ የሚያነሳው?

ከእነዚህ ሁኔታዎች አንፃር የአዋጆቹ አወጣጥ ሲታይ የሕገ መንግሥቱንም ሆነ የሕግ መርሆችን የሚጥስ አይደለም፡፡ የተለመደውን የሕግ አወጣጥ ሒደት የተከተለ ነው፡፡ ግን ጉዳዩ አንድ ጊዜ አነጋጋሪ ሆኖ በመውጣቱ ብቻ ሁኔታዎች በነበሩበት እንዲቀጥሉ የሚፈልጉ ወገኖች የሚፈጥሩት የውዥንብር ምልክት ዜና ከመሆን ባለፈ ሌላ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡

ምክር ቤቱ የግል ድርጅት ሠራተኞችን ጥያቄ ተቀብሏል፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ጋር የሚጋጭ ተግባርም አልፈጸመም፡፡ በተሰጠው ሥልጣን ከልል ሆኖ ተግባሩን አከናውኗል፡፡ አንባቢያን ይህንን እንዲረዱ እንፈልጋለን፡፡ ጋዜጣው ግን ምክር ቤቱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ለአንባቢያን የተሳሳተ መረጃ በተደጋጋሚ እያስተላለፈ ይገኛል፡፡

   ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...