እነሆ ከሽሮ ሜዳ ወደ እንጦጦ ልንጓዝ ነው። “እዚህ ጋ ጠጋ! ጠጋ! ‘ማዘር’ እዚህ ተጠጉላቸው፤” ተለምዷዊ ቀጭን ትዕዛዝ ናት። ዛሬ ግን መብት አስከባሪ ገጥሞታል። “አልጠጋም! ለምድነው የምጠጋው? የከፈልኩህ ለአንድ መቀመጫዬ ብቻ መሰለህ?” ተጠጊ የተባለችው ወይዘሮው ብልጭ ብሎባታል። ከዓመት ዓመት ባርቆብን እንዴት ልንሆን ነው? “ምናለበት በሁለቱም መቀመጫችን ተዘፍዝፈን ወያላና መንግሥትን ከማማት እርስ በርስ ብንተባበር? አይ ሐበሻ። ተቀምጦ ሰማይ ቀዶ መስፋት ብቻ፤” ወያላው አጋዥ ለማግኘት አሳባሪ መንገዶችን በሙሉ በመጠቀም ላይ ነው። “ደግ አደረገ። እዚያ ያስለመዱህ ይጠጋጉልህ። ጊዜው የመጠጋጋት ነው ብለህ ከሆነ በጊዜ የማያምን ዜጋ አለ፤” ወይዘሮዋ እንደ እንዝርት ሾራለች። ሹረቷን ትክ ብሎ እያየ ያዞረው ደግሞ፣ “ምናለበት ብትጠጋና ብንቀሳቀስ? ና ብሎ ከመደህየት ተጨናንቆ ማደግ አይሻለም? ይገርማል!” ይላል አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት። ከኋላችን ሦስተኛው ረድፍ ላይ ደግሞ “ይኼ ነው። የት አባቱ እንዳትሰሚው፤” እያለ ኑሮ ጀምሮት መጠጥ የጨረሰው ጎስቋላ ጎልማሳ ያጉተመትማል።
አጠገቡ ‘ማች በማች’ የለበሰች ዝንጥ ያለች ወጣት ቦርሳዋን እንቅ አድርጋ ታቅፋ አልሰማሁም አላየሁም ጣቢያ ከፍታለች። መጨረሻ ወንበር አንድ አዛውንት፣ አንድ ጎልማሳና ዕድሜያቸው በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገመቱ ወጣቶች ጎን ለጎን ተሰይመዋል። ወያላው እልህ ይዞት አጠጋግቶ ሊያስቀምጣቸው የነበሩትን ተሳፋሪዎች አንዱን ጎማ ላይ አንዱን ከጋቢና ወንበር ጀርባ፣ ሌላውን ሞተር ላይ አደላድሎ አስቀምጦ “ሳበው!” ብሎ በሩን ከረቸመ። ወይዘሮዋ በድል አድራጊነት ስሜት ፈገግ ብላ፣ “እኛን የሰለቸን ከእናንተ ጀምሮ ጉድለታችንና ክፍተታችንን ምክንያት አድርጎ ሙሴያችሁ ነኝ ተቀበሉኝ፣ ተከተሉኝ፣ እመኑኝ የሚለን ሐሰተኛ ነብይ ብዛት ነው። ራሳችን ለራሳችን መብት ብንቆም ከመጀመሪያው መቼ በየአቅጣጫው ነጂ ይልክብን ነበር፤” ብላ በራሷ ዓለም ጠፋች። ነገሩ ከምኔው የነጂና ተነጂ አተካራ ውስጥ እንደገባ ፈጣሪ ይወቀው!
ጉዟችን ተጀምሯል። ሥራ አልጀምር ስላለው ባቡራችን ጨዋታ የጀመሩ አሉ። “እኔ መጀመሪያ ‘መቼስ በኑሯችን መቀለድ እንጂ መደሰት ስለማናውቅ እናጋንናለን’ ብዬ ትቼው ነበር ለካ እውነት ነው፤” እያለ ከአዛውንቱ አጠገብ የተቀመጠው ሞላ ያለ ተክለ ሰውነት ያለው ጎልማሳ ያወራል። “ምኑ ነው እውነት?” አዛውንቱ አፋቸውን ማንቀሳቀስ የደከማቸው ናቸው። “ባቡርና ተማሪ በአገራችን ተመርቆ ቶሎ ሥራ አይጀምርም ሲባል የሰማሁት ተረብ እውነት መሆን እያደረ ገርሞኛል፤” አለ ጎልማሳው። “ኤድያ! አትተወውም?” አዛውንቱ ነገሩን በአጭሩ ለመቅጨት ትግል የያዙ ይመስላሉ። “ምኑን ነው የምተወው?” ጎልማሳው መነዝነዙን ተያያዘው። “ባቡሩንም ሥራ አጡንም፣ መንገዱንም ታክሲውንም፣ ወሬውንም፣ መንግሥትንም ሁሉንም መተው ተለማመድ እንደ እኔ…” ብለው ምራቃቸውን እግራቸው ሥር ተፉ። ወያላው አበደ። “ምን ነካዎት ትልቅ ሰው አይደሉም እንዴ? እንዴት ሕዝብ መሀል ይተፋሉ?” ተንጫጫ ወያላው።
ሁላችንንም ተራ በተራ ሲያየን ቆይቶ፣ “አሁን እናንተ አይደለም ተሠልፋችሁ መዋል፣ ምንስ ብትሆኑ ይታዘንላችኋል?” እያለ ፊቱን ሲያዞር፣ “ምን ያበሳጨዋል ይኼ! ይኼው ዙሪያችንን የሌለ መመርያና ነቀፌታ፣ ሕግና ትዕዛዝ ያለጠፍክበት ቦታ የለም። አትትፉ የሚል ግን አለ? ንገረኛ! ከየትኛው ሕግ ነው ጠቅሰህ የምትከሰኝ? ማታ በዜና ተመርቆ ተከፈተ ተብሎ የታየን አስፋልት መንገድ፣ ጠዋት ለማኝ ሳይቀድመው ተነስቶ ፊኛውን የሚያስተነፈስ የዕድገት ምቀኛ ሳይታሰር እኔ ልታሰር ነው? ወይስ ስንቱ በዕድሜያችንና በህልማችን ተጫውቶ አላምጦ እየተፋን መኖራችን አናዳጅ ሆኖ ተገኝቶ ነው እንደ ቻይና አትትፉ የሚል ትዕዛዝ የወጣው?” ብለው አዛውንቱ ባሱ። ይኼን ጊዜ ጎን ለጎን የተቀመጡት ወጣቶች ቀበል አድርገው፣ “ወይ ኢቲዮ ቻይና! በስማችሁ ስንቱን እንስማ?” ሲሉ ሰማን!
ወያላው ሞተር ላይ ያስቀመጠው ተሳፋሪ ስልኩ ትጮሃለች። በስንት ስቃይ በስንት አሳር ካለችበት ታስሳ ወጣች። “ይኼ ሰውዬ ነዳጅና የከበሩ የተፈጥሮ ማዕድናት ላይ ቢሠራ ያው መጀመሪያ ራሱን ከዚያ ምናልባት ራርቶ አገሩን ሊጠቅም የሚችል ሰው ይመስላል፤” ይላል ከጎኔ የተቀመጠው። ባለ ስልኩ “ሃሎ!” የጆሯችን ታንቡር እስኪበሳ መጮህ ጀመረ። “ይሰማኛል። ቅድም እኮ ተቋረጠ። ምን ይታወቃል ሚሊዮን እያልኩ ሳወራ ቴሌ ትን ብሎት ይሆናላ! ሃሃሃ…” ገልመጥ ገልመጥ እያለ ያየናል። ቀጥሏል። “ስድስት ሚሊዮን እጄ ላይ አለ። ቀሪው እህል እጃችን ሲገባ በባንክ ትራንስፈር ይደረግልሃል ብለውኛል። አዎ ተፈራርመናል እንጂ፤” እያለ ስለሥራው ቀጠለ። ተሳፋሪዎች እያልጎመጎሙ ወሬ ጀመሩ።
“እህም ወይ ሚሊዮን እንዲህ ሳናስበው አፋችን ይግባ?” አለች ከወያላው የተናቆረችው ወይዘሮ። “እኛ ያፉችን ነገር መቼ ቸገረን። የሆዳችን እንጂ የሚያንገዋልለን። እንይዘዋለን ባዶ። መቶ ብር ብን ስትል አትራራ። አብሮ በልቶ ጠጥቶ የሚንሸራተተው ወዳጅ በዛ ብለን ሳንጨርስ በላባችን የምናመጣው ገንዘብ ረድኤተ ቢስ መሆን ባሰ፤” ትላለች አጠገቧ የተመቀጠች ደርባባ። ሦስተኛ ረድፍ ላይ ደግሞ ያ ጎስቋላ ጎልማሳ፣ “እኔ ግን እንደምንም ብዬ ፌስታል ነው ማምረት ያለብኝ። አይመስልሽም?” ከመነጽር እስከ አልቦ በ‘ማች’ ያበደችውን ተሳፋሪ አስጨነቃት። ዞር ብላ “አልገባኝም?” ከማለቷ፣ “በዚህ አያያዝ እንደ ዚምባቤ በዘንቢልና በፌስታል ገንዘብ ተሸክመን ጉልት መውጣታችን አይቀርማ! ዋናው ማደጋችን ነው፤” ሲላት እንሰማለን። ሰው ግን እንዴት አዙሮ ተኳሽ ሆኗል?!
ጉዟችን እንደቀጠለ ነው። ወያላችን አንድ ሚሊዮነር ሞተር ላይ አስቀምጦ እየተጓዘ መሆኑን ሲሰማ የባሰውን ተናደደ። “ወይ አይጠቀሙ ወይ አያስጠቅሙ ወይ አይጠጉ ወይ አያስጠጉ፤” ይላል። ነጋዴው ስልኩን እንደቀጠለ ነው። ጋቢና የተሰየሙት ተሳፋሪዎች ሳይቀሩ ወያላውን ሰምተውት ኖሮ፣ “እባክህ በተጠጋጋ ብቻ አይደለም። ዕድል ያስፈልጋል። ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ሲሄድ የሚታለፍ አለ። የማይታይ። እንደ እኔ ያለው ደግሞ አለላችሁ በትንኝ የሚጋለጥ። ሌብነትም እኮ ‘ታለንት’ ይጠይቃል፤” አለ አንደኛው። “በቃ እኛ ግን መጠቃቀም መጠጋጋት ስንባል የሚታየን ሌብነት ብቻ ነው? የሥራ ዕድል ማግኘት፣ በጎ በሆነ መንገድ መረዳዳት አይታየንም?” ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠችው አቋርጣ ገባች።
“ሆሆ መጀመሪያ ያለ ‘አይዲ’ የሚያስጠጋህ አለ እንዴ? የለም እኮ! እንደ እኛ ዓይነቱ ከምኑም የሌለበት ወይ ግንባር የለው ወይ የሚጋጨው ‘ቻፓ’ ዝርዝር ሳንቲሙን እያንቃጨለ ዕድሜው በታክሲ ሠልፍ ያልቃል። ምናልባት ከቀናህ ደህሞ አገርህ በሀብት ከ184 አገሮች 171ኛ ሆነች የሚል ዜና ቢመረቅልህ ነው። በማትሞቀው እሳት አገርህ ደረጃ ስትመደብ አንተም ቶሎ ብለህ ምድብህን ማስተካከል ነው፤” ከጎኔ የተሰየመው ይለፈልፍብኛል። ይኼን ሲል የሰማው ሌላ ጎልማሳ “ማስተካካል ካልቻልክስ? ምድቡ የሞት ምድብ ከሆነስ?” ብሎ መጣብን። “አሁን ይኼ ጥያቄ ነው? ልማታዊ ኑሮ ካቃተህ ልማታዊ ሞት መሞት ነዋ!” ብሎ የተሳፋሪውን ወሽመጥ በጠሰው። “ልማታዊ ኑሮን እያየነው ነው፣ ልማታዊ ሞት ደግሞ እንዴት ያለ ነው?” ሲሉ አዛውንቱ፣ “ለመንግሥት ሳያሳሙ፣ ቀባሪ ሳያስቸግሩ ‘ሳይለንት’ ሆኖ ማለፍ ማለት ነዋ። ሌላ ምን ይሆናል? ወይ ስም ሳያስነሱ መመንተፍ ወይ ተረስቶ ማለፍ ነው፤” ብትል ቆንጂት ተሳፋሪው ተገርሞ እየተገላመጠ አያት። ብሶት በታረዘና በተጠማ መሀል ብቻ ነው ያለው ግን ማን ይሆን?
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ታክሲያችን በጉዟችን መገባደጃ መክለፍለፍ ጀምራለች። “የምን ሩጫ ነው በአትሌቶች እንጂ በታክሲ ሾፌሮች እኮ የተሰበረ ‘ሪከርድ’ የለም ቀስ ብል አቦ!” ይላል ተሳፋሪው። ሾፌሩ መልሶ፣ “ያራገፈ እንጂ ሩጫውን የጨረሰ ታክሲ የለም እያለ፤” እንደ ፍጥርጥራችሁ ይለናል። በጎን ወያላው፣ ለ10 እና ለ20 ሳንቲም መልስ ምን ያጨቃጭቃችኋል?” ብሎ መልሱን ዓይን ባይን ካላስቀረሁ ይለናል። “በል አምጣ 10 ሳንቲም ይጎለኛል ሙላና ውሰደኝ ብልህ ታሳፍረኛለህ? እንደ ራስ ማየት ነው፤” ይላሉ አዛውንቱ። ወያላው ሳንቲም የለኝም ብሎ ድርቅ። ነገር ተባባሰ። ተሳፋሪው ተንጫጫ። “ምን ያድርግ ብላችሁ ነው ሕግ አክብሮ የሚያስከብር ብናጣ፣ ቁስላችን አመርቅዞ ‘ኢንፌክሽን’ ካልሆነ በቀር ዞር ብሎ የሚያየን እንደሌለ ቢያይ ነው፤” ሲል አንዱ፣ “እኮ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ብረት ማንሳትና ብረት መግፋት አለብን መብት ለማስከበር፤” ትላለች ደርባባዋ።
“ያዝ እንግዲህ! ወሬኛ ቢሸፍት ከፌስቡክ አይወጣም፤” እያለ አፍ ይካፈታል ወያላው። “እኮ በስተርጅና ከዚህ ሁሉ የደም ታሪክና የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ እንደገና መተነኳኮስ ተጀመረ?” ሲሉ አዛውንቱ ከጎናቸው የተሰየመው ጎልማሳ ቀበል አድርጎ፣ “ተናግሮ ሊያናግረን ነው። ኃላፊነት የጎደለውን የሰብዕና አምልኮ ናፋቂ ፉከራና ቀረርቶ በሰማን ቁጥር ደንፍተንማ አይሆንም፤” ይላል። “ኧረ ተወኝ በዕድገት፣ በመልካም አስተዳደር መሻሻል፣ በፍሕት ሥርዓት፣ በዲሞክራሲ እንጂ በጦርነትና በብጥብጥ ማንም ሪኮርድ ያስመዘገበ የለም በለው፤” ሲል ከወደ ጋቢና ወያላው “መጨረሻ!” ብሎ በሩን ከፈተው። ብር ዘርዝሮ ሳንቲም ይዞ እስኪመጣ ንቅንቅ ያለ የለም። እያንዳንዳችን ተራ በተራ መልሳችንን እየተቀበልን ስንበታተን ሌሎች የባሱብን ችግሮች ላይ ለምን ይህቺን ታህል ተሰባስበን መብት እንደማናስከብር ተገርመን እንተያይ ነበር። በዚህ መሀል ነበር አንዱ ወፈፍ ያደረገው የሚመስል፣ “… ገቡ አሉ፡፡ በእርግጥ ገብተዋል? እግራቸውን ነው ያስገቡት? ወይስ ቃል ነው የገቡት? መግባቱንስ ገቡ መውጪያውን አውቀውታል…” እያለ ሲለፈልፍ ከግርምታችን ወጥተን ሳቅ በሳቅ ሆንን፡፡ ወይ ጊዜ? እንሳቀው እንጂ ሌላ ምን ይባላል? መልካም ጉዞ!