Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሆቴሎችና የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ብሔራዊ ማኅበር ሊመሠረት ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን የሆቴሎችና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ብሔራዊ ማኅበር ለመመሥረት ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለጸ፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር እንደገለጹት፣ በተለይ በሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ የተሰማሩ በርካታ ባለሀብቶችና አሠሪዎች በመኖራቸው እንዲሁም ዘርፉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞችን የያዘ በመሆኑ በብሔራዊ ደረጃ በማኅበር እንዲደራጅ ማድረጉ ጠቃሚ ነው፡፡

የማኅበሩ መመሥረት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ያመለከቱት አቶ ታደለ፣ በተለይ ኢትዮጵያ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በከፍተኛ ደረጃ እያስተናገደች ከመሆኗም ባሻገር የዓለም አቀፋዊና አኅጉራዊ ስብሰባዎች ቁጥር እያደጉ በመምጣታቸው፣ በዚሁ ልክ የአገሪቱ ሆቴሎች አገልግሎት ብቃትና ጥራት እንዲያድግ ለማድረግ የብሔራዊ ማኅበሩ አስተዋጽኦ የላቀ ይሆናል፡፡

ዓለም አቀፋዊ ደረጃን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ደግሞ በዕውቀት ላይ የተመሠረተና የተፈጠረውን የገበያ ዕድል በጋራ በመሥራት የበለጠ ማሳደግ ግድ በመሆኑ፣ የአሠሪዎች ፌዴሬሽን የሆቴሎች ብሔራዊ ማኅበር እንዲመሠረት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ተመልክቷል፡፡

ማኅበሩ ዘርፉን ከማሳደግ ሌላ የሆቴል አሠሪዎችንም መብት ለማስከበር ጭምር የሚንቀሳቀስ እንደሚሆን የገለጹት አቶ ታደለ፣ ከዚሁ ጐን ለጐን የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ብሔራዊ ማኅበርም ለመመሥረት ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን የኢንተርፕራይዞቹን ብሔራዊ ማኅበር እንዲመሠረት የሻተው፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ እያደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴ ከግምት በማስገባት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጐችን የያዙት እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ኩባንያ ደረጃ እየተሸጋገሩ በመሆኑ፣ መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲባል ማኅበሩ እንደሚመሠረት ገልጸዋል፡፡ ወደፊትም በርካታ ሠራተኞችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ ዘርፉ ራሱን የቻለ ብሔራዊ ማኅበር ያስፈልገዋል ተብሏል፡፡ ለማኅበሩ መመሥረትም በሁሉም ክልሎች ያሉ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትን የሚወክሉ ማኅበራት ለብሔራዊ ማኅበር ምሥረታው እንዲዘጋጁ ተደርጓል፡፡

በዚህ ዘርፍ ብቻ ወደ ስምንት ሚሊዮን ዜጐች የታቀፉ ስለመሆኑም የአቶ ታደለ ገለጻ ያስረዳል፡፡ የሁለቱን ብሔራዊ ማኅበራት ምሥረታ ይፋ ለማድረግም ቅድመ ዝግጅቶች የተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ ይፋ ይሆናል ተብሏል፡፡

የአሠሪዎች ፌዴሬሽን እንቅስቃሴን በተመለከተ በተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያ፣ በአሠሪና ሠራተኞች መካከል ይታይ የነበረው አለመግባት በአሁኑ ወቅት እየተቀረፈ መምጣቱን የሚያመለክት ነው፡፡

እንደ አቶ ታደለ ገለጻ በተለይ በቅርቡ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ሠራተኞችን ለማደራጀት በጀመረው ዘመቻ አሠሪዎች የሠራተኞች ማኅበር እንዲመሠርቱ ፈቅደዋል፡፡

ይህ ለውጥ የመጣው የአሠሪዎች ፌዴሬሽን የሠራተኛ ማኅበር መመሥረት ጥቅም እንዳለው ግንዛቤ በመስጠቱ ጭምር እንደሆነ በመግለጽ፣ ከዚህ በፊት አሠሪዎች ማኅበር እንዳይመሠረት ያደርጋሉ የሚለው ትችት አሁን እየቀነሰ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ከ300 በላይ አሠሪዎች የሙያ ማኅበራት ተወካዮችና የመንግሥት ባለሥልጣናት የተገኙበትን ‹‹የአሠሪዎች ፎረም›› ሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል አካሂዷል፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሒ በተገኙበት የተካሄደው ሲምፖዚየም ላይ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግና አፈጻጸም በኢትዮጵያ፣ የታክስ አስተዳደርና የታዩ ዋና ዋና ችግሮችና መፍትሔዎች፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳደርና አፈጻጸም ሒደት በኢትዮጵያ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ የቀረበበትና ውይይት የተደረገበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ባካሄደው ሲምፖዚየም ላይ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ዓለሙ፣ የዓለም ሥራ ድርጅት የኢትዮጵያና ሶማሊያ ዳይሬክተር ጆርጅ ኦኩቱ ተገኝተው ነበር፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች