Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ፍኖተ ካርታና አዲሱ ዕቅድ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍን በእጅጉ ያሳድጋል፤ ዘርፉ ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት ይመራበታል የተባለው ‹‹የእንስሳት ሀብት ፍኖተ ካርታ›› ከመስከረም 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር ተጠቆመ፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማሳደግ ከ7.6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጁ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን ለማካሄድ ታቅዷል፡፡

የአገሪቱ የእንስሳት ሀብት ዘርፍ በቀጣዩ 15 ዓመታት ይመራበታል የተባለው ይህ ፍኖተ ካርታ፣ ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር ተሳስሮ የተሠራ ስለመሆኑም የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ፍኖተ ካርታው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ተግባራዊ እንዲሆን ይሁንታ የተሰጠውም ነው ተብሏል፡፡ በዚሁ መሠረት ከመጪው መስከረም 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባ ታውቋል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ያሉ በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎችን አካትቶ የተሰናዳው ይህ ፍኖተ ካርታ የአገሪቱን የሥጋ፣ የእንስሳት፣ የመኖ፣ የዶሮ፣ የወተትና የመሳሰሉ ምርቶች በሚቀጥሉት 15 ዓመታት የት መድረስ እንዳለባቸው፣ በባህላዊ ወይም በተለምዶ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶችን፣ በአዳዲስ ኢንቨስትመንት መሠራት ያለባቸውና ከእነዚህም ሊገኙ ይገባል የተባለውን ምርት መጠንና ግብ የያዘ ነው፡፡ በየዓመቱም ሊከናወኑ ይገባቸዋል የተባሉ ክዋኔዎችን ጭምር የያዘው ይህ ፍኖተ ካርታ፣ በዘርፉ በ15 ዓመታት ውስጥ ሊደረስበት ይገባል የተባለውን ዕቅድ ለማስፈጸምም ምን መደረግ እንዳለበት የተለያዩ የማስፈጸሚያ ስልቶችን ጭምር ያስቀመጠ ነው፡፡

ፍኖተ ካርታው በተለይ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መፈጸም አለባቸው ያላቸውን በዝርዝር ይዟል፡፡ በዘርፉ በኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ልማት በተቀናጀ ሁኔታ እንዲራመድ ያስችላልም የሚል እምነት ይዞ የተነሳም ነው ተብሏል፡፡

ይህ የእንስሳት ሀብት ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀው በግብርና ሚኒስቴር የበላይ አስተባባሪነት ሲሆን፣ የኢንተርናሽናል ላይቭስቶክ ሪሰርች ኢንስቲትዩት (ILRI) የቴክኒክ ድጋፍ ያደረገበት ነው፡፡ ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ደግሞ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የተሰናዳ ሲሆን፣ በፍኖተ ካርታው ዝግጅት በእንስሳት ሀብት ዙሪያ የታወቁ ምሁራንና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች የተሳተፉበት እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገውን ፍኖተ ካርታ ተፈጻሚ ለማድረግም ራሱን የቻለ የእንስሳት ሀብት ሚኒስቴር እንደሚቋቋም የተገለጸና ይህም በመንግሥት የተደገፈ ስለመሆኑ የምንጮች መረጃ ያስረዳል፡፡ ይህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አዲሱን ፍኖተ ካርታ ተፈጻሚ በማድረግ ራዕዩንና ስትራቴጂውን አውጥቶ የሚንቀሳቀስ ይሆናል የሚል ውጥን አለ፡፡

ፍኖተ ካርታው ከተለያዩ ደረጃዎች የሚያስገኟቸው ጥቅሞች ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የእንስሳት ሀብት ስትራቴጂ መረጃን የሚሰጥ በመሆኑ በቀጣይ በዘርፉ እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚጠቁም ነው፡፡ ፍኖተ ካርታው በአገሪቱ ድህነትን በመቀነስና የኢኮኖሚ ፍጥነትን በማፋጠን ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረውም በሰነዱ ተመልክቷል፡፡ ፍኖተ ካርታው ሰፊ ዝርዝር ጉዳዮች ያሉት ሲሆን፣ የዚህ ፍኖተ ካርታ ተፈጻሚ መሆን የሚያስገኛቸው ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ከማመላከቱ ሌላ ፍኖተ ካርታው ባይተገበር የሚፈጥረውን ክፍተትም ይጠቁማል፡፡ በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ላይ ምንም ኢንቨስትመንት ሳይካሄድ እስከ እ.ኤ.አ. 2028 ድረስ ቢኬድ፣ 42 በመቶ የሥጋ ወይም (1,213 ቶን) የሥጋ አቅርቦት ችግር ይፈጠራል የሚለው ነጥብ አንዱ ነው፡፡ በላም ወተት ምርት ላይ ካልተሠራ ደግሞ 23 ከመቶ ወይም (1,958 ሚሊዮን ሊትር) ወተት እጥረት ሊፈጥር እንደሚችልም ይጠቁማል፡፡

ይህ ክፍተት ሊፈጠር የሚችለውም የሕዝብ ብዛት ዕድገትና የነፍስ ወከፍ ገቢ እየጨመረ ስለሚመጣ ፍጆታቸውም ስለሚጨምር ነው፡፡ እ.ኤ.አ. 2013 የተገኘው መረጃ እንደተጠቆመው፣ በኢትዮጵያ 11.4 ሚሊዮን በእንስሳት ርቢ የሚተዳደሩ አባወራዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 49 ከመቶ የሚሆኑት በድህነት ውስጥ የሚኖሩ በመሆናቸው ይህንን መለወጥ ተገቢ ስለመሆኑ ፍኖተ ካርታው ይጠቁማል፡፡ ለዚህም ለውጥ አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ክዋኔዎች በዕቅድ መልክ አስቀምጧል፡፡

በኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፉን በማሳደግ በተለይ በወተት፣ በሥጋና በመኖ አቅርቦት ዙሪያ የተደራጀ ፕሮግራም ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ በፍኖተ ካርታው ከተጠቀሱ ዋና ዋና ክዋኔዎች መካከል በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሊደረስበት ይገባል ብሎ ካስቀመጠው አኃዛዊ መረጃዎች ውስጥ የአገሪቱን የዶሮ ሥጋ ምርት በ2007 ዓ.ም. ካለበት 48.9 ሺሕ ቶን፣ በ2012 ዓ.ም. በ235 በመቶ በማሳደግ 164 ሺሕ ቶን ማድረስ አንዱ ነው፡፡

በ2007 ዓ.ም. 419 ሚሊዮን የእንቁላል ምርት እንደሚኖር ታሳቢ ያደገው ዕቅድ፣ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ (2012 ዓ.ም.) የእንቁላል ምርትን በ828 በመቶ በማሳደግ 3.7 ቢሊዮን እንቁላሎች መመረት ይኖርበታል ይላል፡፡

የላም ወተት ምርትንም በየዓመቱ በ93 በመቶ በማሳደግ በ2007 ዓ.ም. 167 ሚሊዮን ሊትር የነበረውን ምርት በ2012 ዓ.ም. 1.49 ቢሊዮን ሊትር ማድረስ ነው፡፡ በዕቅዱ መሠረት ከተሠራም የወተት አገራዊ የምርት ዕድገት (GDP) አስተዋጽኦ አሁን ካለበት 3.6 ቢሊዮን ብር በ2012 ዓ.ም. 9.6 ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ የሌሎቹንም ዘርፎች ዕድገትና ውጤት በተመሳሳይ ተንትኖ የያዘ ነው፡፡

የቁም እንስሳትም በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ በማርባት በዕቅዱ መጨረሻ መዳረስ አለበት ያለውን ግብ አሳይቷል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ዘርፍ ያለውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስፈልገው የኢንቨስትመንት መጠን 7.6 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ይህ የኢንቨስትመንት ወጪ ደግሞ በግል ዘርፉና በመንግሥት የሚሸፈን ነው፡፡ እንደ ዕቅዱ ከሆነ ከሚያስፈልገው ጠቅላላ ኢንቨስትመንት ውስጥ 54 ከመቶ ወይም 3.9 ቢሊዮን ብር በመንግሥት ይሸፈናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በግሉ ዘርፍ ደግሞ 46 ከመቶውን ወይም 3.3 ቢሊዮን ብር እንዲሸፈን ይፈለጋል፡፡

በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚካሄዱ ኢንቨስትመንቶች በሦስት ዘርፎች የተቀመጡ ሲሆን፣ የላም ወተት ሀብት 1.3 ቢሊዮን ብር፣ ለሥጋና ለወተት ሀብት ፕሮግራም 3.4 ቢሊዮን ብር፣ የዶሮ ሀብት ልማት ደግሞ 2.4 ቢሊዮን ብር ወጪ ይፈልጋሉ፡፡

በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን በወተት ልማት ዘርፍ ይደረስበታል የተባለውን ግብ ለማሳካት ሊሠሩ ይገባል ተብለው ከተቀመጡት ክዋኔዎች አንዱ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የወተት ማቀነባበሪያዎችን መገንባት የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ከአምስቱ ዓመት የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በማቋቋም በቀን አሥር ሺሕ ሊትር ወተት ለማምረት ይቻላልም ይላል፡፡

እነዚህ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በአገሪቱ አሥር የተለያዩ አካባቢዎች የሚገነቡ ሲሆን፣ ሁለቱ በአዲስ አበባ አካባቢ ናቸው፡፡ አሥሩ የወተት 100 ሺሕ ሊትር በቀን ውስጥ ማምረት የሚችሉ ይሆናሉ፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ሁለት የዱቄት ወተት ማምረቻ ፋብሪካዎች፣ እያንዳንዳቸው በቀን 400 ሺሕ ሊትር ወተት ማምረት የሚችሉ እንዲሁም አንድ ፋብሪካ ደግሞ በቀን አምስት ሺሕ ሊትር የሚያመርት ወተትን ለብዙ ጊዜ ቆይቶ ለመሸጥ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ያለው ፋብሪካ መገንባት ነው፡፡

ዕቅዱ አገሪቷን የእንስሳት ሀብት መጠን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተቀረፁ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ ከልማዳዊ ወደ ዘመናዊ የምርት ሒደት የሚያስገባ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ብሏል፡፡

በሌላ በኩል የእንስሳት የጤንነትና የአመጋገብ ሁኔታ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ በዚህም መሠረት አዳዲስ የእንስሳት ሕክምና ቴክኖሎጂዎች፣ የምርጥ ዘር ማስፋፊያና የመኖ አቅርቦትን የተካተተበት ነው፡፡

የመኖ አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ በፍኖተ ካርታው ውስጥ በዶሮ ሀብት ልማት ኢንዱስትሪ ጠቀሜታችን በምግብ   ራስን መቻል፣ ለሥጋ ፍጆታና የተመጣጠነ ምግብ ብሎም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረው ጠቀሜታ ሰፊ ነው፡፡

በፍኖተ ካርታው ከላይ የተቀመጡት ግቦች ሊሳካ የሚችሉት፣ የመኖ ችግር መቀረፍ ሲቻል፣ ውጤታማ የኤክስቴንሽን ዘዴ ተግባራዊ ሲሆንና የግሉ ዘርፍ በዶሮ ሀብት ልማት ዘርፍ በስፋት ተሳታፊ እንዲሆን በቂ ማበረታቻዎች ሲሰጥ ነው ይላል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የታክስ እፎይታ፣ የመሬት ሊዝ ዋጋ ድጎማ፣ ምርት ማቅረብና ይህንን ከሁሉም ቅደሚያ ሰጥቶ መሬት ማቅረብ ሲቻል መሆኑን አስምሮበታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የአገር ውስጥ ባለሀብትን የሚያበረታቱና ጥበቃ የሚሰጡ የንግድ ፖሊሲዎችን በዶሮ ሀብት ኢንዱስትሪ ማስፈን ይጠበቃል ይላል፡፡

የዚህ ዕቅድ መፈጸም ደግሞ በዶሮ ልማት ዘርፍ በ2007 ዓ.ም. ከጂዲፒው የነበረውን የ4.172 ቢሊዮን ብር ድርሻ በ2012 ዓ.ም. ወደ 15.6 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ያስችላል፡፡

ፍኖተ ካርታው የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ከተቻለ እየጨመረ የመጣውን የአገሪቱ ፍጆታ ከመሸፈን አልፎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ምርት እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች