Friday, June 9, 2023

ኢትዮጵያንና ኬንያን ያስተሳሰረው ከሶማሊያ የሚነሳው ሥጋት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ናይሮቢ በአፍሪካ ዓለም አቀፍ ትኩረት ከሚስቡ የቢዝነስና የቱሪዝም ማዕከል አንዷ ናት፡፡ የሰዎችም ሆነ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በከፍተኛ መጠን ይስተዋልባታል፡፡ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት ጎዳናዎች በተለያዩ የአፍሪካ መሪዎች፣ በታዋቂ የዓለማችን ሰዎችና እንዲሁም በቀድሞ የኬንያ መሪዎች ስም ተሰይመዋል፡፡

በመዲናዋ እጅግ ከፍተኛ የቢዝነስ እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው መካከል ግንባር ቀደሙ በቀድሞው ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ የተሰየመው ‹‹ኃይለ ሥላሴ አቬኑ›› ይባላል፡፡ ወደ ላይ ትንሽ ከፍ ብሎ በሚገኘው ወደ ናይሮቢ የገበያ ማዕከል የሚወስደው ደግሞ ለአፄ ምንሊክ ማስተዋሻነት የተሰየመ መንገድ ይገኛል፡፡

ከናይሮቢ ቤተ መንግሥት በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሲሆን፣ የሁለቱም አገሮች የቆየና ሥር የሰደደ ግንኙነት የሚያመላክት ይመስላል፡፡

የዘመናዊት ኬንያ አባት ተደርገው የሚቆጠሩት ዝነኛው ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬንያታ፣ በበዓለ ሲመታቸው የተለመደውን አሠራር በመጣስ የመጀመርያው ሊያገኙት የሚፈልጉት የአገር መሪ አፄ ኃይለ ሥላሴን አደረጉ፡፡ ቀደም ብለው ናይሮቢ የደረሱትን የሌሎች የአፍሪካ አገሮች መሪዎች እንዲቆዩ በማድረግ ፕሬዚዳንቱ ይህንን መወሰናቸውን ያስነበቡት፣ ከእዚህ ዝግጅት ጀርባ የነበሩት የፕሬዚዳንቱ ፕሮቶኮል ዱንካን እንዴናዋ ‹‹Walking in Kenyatta Struggle›› በሚለው መጽሐፋቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያና ኬንያ አልፎ አልፎ በድንበር አካባቢ ከሚከሰቱ መለስተኛ የአርብቶ አደሮች ግጭቶች በላይ ይኼ ነው የሚባል ጦርነት ውስጥ ገብተው አያውቁም፡፡ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋር ከተደረጉት የትብብር ስምምነቶች ይልቅ የኢትዮ ኬንያ ወታደራዊ ስምምነት ግንባር ቀደምትነቱን ይይዛል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1964 የተፈረመው ይኼው ስምምነት 60 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በየዓመቱ በሚካሄደው የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ እየተሻሻለ መምጣቱ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ይኼው ስምምነት የሁለቱም አገሮች የደኅንነትና የፀጥታ የጋራ ጥቅምን ለማስጠበቅ የተፈረመ ቢሆንም፣ መነሻው ግን በወቅቱ ሁለቱም አገሮች ከአንድ ጎረቤት አገር የተነሳባቸውን ሥጋት ለመከላከል እንደነበር፣ ዋንጆሂ ኩብኩሩ የተባለ ኬንያዊ የፖለቲካ ጸሐፊ ኒው አፍሪካን በተባለው ድረ ገጽ ባስነበበው ጽሑፍ ይተነትናል፡፡

ጸሐፊው እንደሚለው፣ አዲስ አበባና ናይሮቢ እንደ ኮላ አጣብቆ የያዛቸው ማግኔት ሁለቱም ከሶማሊያ ‹‹ግዛት መላሽ›› አጥባቂዎች የሚነሳባቸው ሥጋት ነው፡፡ የ‹‹ታላቋ ሶማሊያ›› አቀንቃኞች ጥንታዊቷን ሶማሊያ እንደገና ለመመሥረት የሰሜን ኬንያና የምሥራቅ ኢትዮጵያ (የኦጋዴን ግዛት) ማስመለስን የሚያስተጋቡ ሲሆን፣ ይኼው ሙከራ የሶማሊያ የቀድሞ መሪዎችን ከሁለቱም ጎረቤቶች ጋር ሲያላትማቸው የቆየ አስተሳሰብ ነው፡፡

በተቃራኒው ይኼው የቆየ አስተሳሰብ ለኬንያና ለኢትዮጵያ የጋራ ሥጋት በመፍጠሩ እንዲተባበሩ ዛሬም ድረስ እየረዳቸው ይመስላል፡፡

ሶማሊያ ሥጋትም ማግኔትም

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ አፄ ኃይለ ሥላሴ ‘ማኦማኦ’ ለተባለው የኬንያ ነፃ አውጪ ቡድን፣ ውስጥ ለውስጥ ድጋፍ ማድረጋቸው ይነገራል፡፡ ኬንያ ከቅኝ ገዥዋ ከእንግሊዝ ነፃ እንደወጣች ባሉት ተከታታይ አሥር ዓመታት ውስጥ፣ በኬንያ የሚገኙ የሶማሊያ ተወላጆች ከዋናዋ ሶማሊያ ጋር ለመቀላቀል በመፈለጋቸው ተደጋጋሚ አመፅ ሲቀሰቀሱ ነበር፡፡ አማፂዎቹ ድጋፍ የሚያገኙት ሞቃዲሾ ከነበረው የሶማሊያ መንግሥት ነበር፡፡ የፕሮፓጋንዳ ድጋፉም እንዲሁ ከሞቃዲሾ ነበር፡፡

ኢትዮጵያም በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ሆነ በደርግ አገዛዝ ሁለት ታላላቅ ጦርነቶች ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ያካሄደች ሲሆን፣ መነሻውም ይኼው የሶማሊያ ተወላጆች የሚገኙበትን የኦጋዴን ግዛት ለማስመለስ የተቀሰቀሰ ነበር፡፡ ጦርነቶቹ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ያስከተሉ መሆኑን ታሪካዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ተመሳሳይ ጥቃቶችንና ለመመከት በኢትዮጵያና በኬንያ ወታደራዊ ትብብር መደረጉም ይነገራል፡፡

በወቅቱ የሶማሊያ መሪ የነበሩት ፕሬዚዳንት ዛይድ ባሬ ኢትዮጵያን የወረሩት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲካሄድ የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀምና ከቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት በተደረገላቸው ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ነበር፡፡ በመጨረሻ ሳይሳካላቸው ቀርቶ ለውድቀታቸውም መንስዔ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያና በአሜሪካ የሚደገፉ የጦር አበጋዞች ባካሄዱት መፈንቅለ መንግሥት የሥልጣን ዕድሜያቸው አብቅቷል፡፡

የሶማሊያ የመንግሥት ብተና

የፕሬዚዳንት ዛይድ ባሬ መንግሥት ከተንኮታኮተ በኋላ ሶማሊያ ለሃያ ዓመታት ገደማ መንግሥት አልባ ሆና የቆየች ሲሆን፣ ለአሸባሪዎች የተመቸች መናኸርያም ሆና ነበር፡፡ ከዋናዋ ሶማሊያ የሚነሱ የኦጋዴንን ግዛት ነፃ እናወጣለን የሚሉ ቡድኖች በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ጥቃቶችን ፈጽመዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በአንድ በኩል ተቀባይነት ያለው ዓለም አቀፍ መንግሥት (ወዳጅ) በመትከል፣ በሌላ በኩል ከአካባቢው የሚሰነዘረውን የሽብርና የአመፅ ጥቃት በመከላከል ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል፡፡ በመጨረሻም በኢትዮጵያ፣ በጂቡቲና በኬንያ በተካሄዱ የሰላም ስምምነቶች ፌዴራላዊ የሽግግር መንግሥት (TFG) በሶማሊያ የተመሠረተ ቢሆንም፣ በሁለት እግሩ ከመቆሙ በፊት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡

በደቡብ ሶማሊያ አካባቢ የመሸገውና በደቡባዊ የአገሪቱን ግዛቶች ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ በቁጥጥሩ ሥር ማድረግ የቻለው እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት በመባል የሚታወቀው ኃይል ሲሆን፣ ደካማውን የሽግግር መንግሥትም ለመጣል ተቃርቦ ነበር፡፡

ይኸው በ1999 ዓ.ም. የታየው መሰባሰብ አንዳንዶች በሶማሊያ ጠንካራ መንግሥት ለመቋቋሙ እንደ መልካም አጋጣሚ አይተውት ነበር፡፡ ኅብረቱ ከጅምሩ ከአልቃይዳ ጋር ትስስር መፍጠሩንና የቆየው ይኼው ‹‹ግዛትን የማስመለስ›› አባዜ መቀስቀሱ ሁለት የውጭ ጠላቶች ጠርቷል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ተቀዛቅዞ የነበረው የኬንያና የኢትዮጵያ ወዳጅነትም ተቀስቅሶ ኅብረቱ ከኤርትራ ቀጥተኛ ድጋፍ እንደሚደረግለት ያወቀው የኢትዮጵያ መንግሥትም፣ በሽግግር መንግሥቱ ግብዣ በኢጋድ ሥር ወታደሮቹን ወደ አካባቢው አንቀሳቅሷል፡፡ በሳምንት ውስጥ ጦርነቱ ተጠናቆ በኢትዮጵያ ላይ ጅሃድ ያወጀው ኅብረትም ለመበታተን በቅቷል፡፡ ይኼው የውክልና ጦርነት መልክ ለነበረው የሶማሊያ ቀውስ ምክንያት የሆነው ‹‹እስላማዊ›› ቡድን ይበታተን እንጂ፣ ወጣቶቹ ተዋጊዎች በዚያው ተበታትነው አልቀሩም፡፡ አልሸባብ በሚል ስያሜ መጡ፡፡

‹‹ዘመቻ ጁባ ኮሪደር››

ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ አካባቢ የአልሸባብ ኃይሎች በአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ላይ በፈጸሙት ጥቃት በስምንት ዓመታት ውስጥ ያልታየ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ፣ በርከት ያሉ የኡጋንዳ ወታደሮች ለሞት ተዳርገዋል፡፡

አልሸባብ በአሚሶም ላይ ካደረሰው ጥቃት በኋላ የአሜሪካ መንግሥት በሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖች ባካሄደው መልሶ ማጥቃት ከ30 በላይ አባላቱን ከነአመራሩ አጥቷል፡፡ አልሸባብም እዚያም እዚህም እያለ የመልሶ ማጥቃት ዓይነት የሽብር ተግባር እየፈጸመ ነው፡፡ የአሚሶም፣ የኬንያ፣ የኢትዮጵያና የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች በጥምር ሰሞኑን ዘመቻ ከፍተውበታል፡፡

የኢትዮጵያና የኬንያ ጦር ኃይሎች አሚሶም ውስጥ ያሉ በመሆናቸው፣ በአሁኑ ወቅት የአልሸባብ የመጨረሻ ጠንካራ ይዞታ የሚባሉት ባይና ጌዶ ክልሎች (ደቡብ ሶማሊያ) ጨርሰው ለመጠራረግ ተነስተዋል፡፡

የአልሸባብ ሽምቅ ተዋጊዎች የመሸጉባቸው ዲንሶርና ባርዴር የሚባሉ አካባቢዎችን ለማጥቃት የሚካሄደው ዘመቻ ተጨማሪ ሠራዊት የጠየቀ በመሆኑ፣ በታንክና በከባድ መሣርያዎች የታጀበው የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ወደ አካባቢው መንቀሳቀሱ እየተነገረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም አረጋግጧል፡፡

‹‹ኦፕሬሽን ጁባ ኮሪደር›› የሚል ስያሜ በተሰጠው በዚህ ዘመቻ፣ ኬንያና ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስማቸው እየተነሳ ሲሆን፣ አልሸባብም ጥቃቱን ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳይቀይረው ተሰግቷል፡፡

በጥቃቱ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ እስካሁን ባይታወቅም፣ የአልሸባብ የወቅቱ መሪ የሆኑት አህመድ ድሪየ፣ ባለፈው ዓርብ የኢድ አል አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት አልሸባብ ጥቃቱን ከሶማሊያ ውጪ በኢትዮጵያና በኬንያ ለመፈጸም እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአልሸባብ መሪ ያስተላለፉት መልዕክት አልሸባብ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን በሊቢያ በጭካኔ ከፈጀው ከአይኤስ ጋር እንዳይጣመር ሥጋት ፈጥሯል፡፡       

አልሸባብ የጠራው ትብብር

የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ‹‹የጠፋውን ግዛት›› ለማስመለስ ፍላጎት የነበረው ቢሆንም፣ በቀጥታ የጅሃድ ጦርነት ያወጀው ግን በኢትዮጵያ ላይ ነበር፡፡ የኤርትራ እጅ እንደነበረበትም አይዘነጋም፡፡ አስመራ ላይ የተጠለሉት የቡድኑ መንፈሳዊ መሪም ከዚያ አካባቢ ሆነው አመራር መስጠት ቀጥለው ነበር፡፡ ቀስ በቀስም አልሸባብ የተባለው የወጣቶቹ ወታደራዊ ክንፍ መሰባሰብ ችሏል፡፡ ኢትዮጵያ ከአንዴም ሁለቴ ወደ ሶማሊያ በመዝለቅ ቡድኑን ብትመታም፣ ዋናውን ማኅበራዊና ድርጅታዊ መሠረት መንቀል አልተቻለም፡፡

ቡድኑ ከአራት ዓመት በፊት በኡጋንዳ ካምፓላ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ላይ ጥቂት ፈጽሞ ነበር፡፡ ትንሽ ቆይቶም በኬንያ ትልቁ የገበያ ማዕከል (ዌስት ጌት) ላይ ባደረሰው ጥቃት የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ በተደጋጋሚም በኬንያ ዜጎችን ፈጅቷል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ከአፍሪካ ኅብረትና ከተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ጋር በመተባበር በዋናነት ከብሩንዲ የተውጣጡ ስምንት ሺሕ ወታደሮችን ያቀፈ ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ቢያሰማራም፣ በቂ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በመጀመርያ በቡድኑ ጥቃት የደረሰባት ኬንያ ወደ አካባቢው ያንቀሳቀሰችው ሠራዊት በዚሁ ኃይል ሥር እንዲሆን ተደረገ፡፡ ቀስ በቀስም የኢትዮጵያ ጦር ኃይል በዚሁ ኮማንድ ሥር እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፣ አልሸባብ ግን የሽምቅ ውጊያውን አላቆመም፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ በሽግግር መንግሥቱ ባለሥልጣናትና በጥምር ኃይሉ ላይ አደጋ ሲያደርስ ይስተዋላል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአሚሶም፣ የኢትዮጵያ፣ የኬንያና የሶማሊያ ጥምር ጦር የከፈተው ዘመቻ ሦስት ቀጠናዎችን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ በእግረኛና በአየር የተጀመረው ይኼ የጋራ ዘመቻ በስኬት እየተካሄደ በርካታ አካባቢዎችን ከአልሸባብ እያስለቀቀ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ጸሐፊው ዋንጁሂ ኪብኩሩ እንደሚለው፣ የኢትዮጵያና የኬንያ ወዳጅነት ምንጭ ከሶማሊያ የሚነሳ ሥጋት ሲሆን፣ ዛሬም ከ60 ዓመታት በፊት የነበረውን ያህል ጠቃሚ ነው፡፡ በፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መካከል ያለው ወዳጅነት በፕሬዚዳንት ኬንያታና በአፄ ኃይለ ሥላሴ መካከል የነበረውን ግንኙነት ያህል የጠበቀ ነው ይላል የፖለቲካ ተንታኙ፡፡ ‹‹ባለ 60 ዓመቱ ስምምነት አሁንም ድረስ በአስፈላጊነቱ ቦታ ላይ ነው›› በማለት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -